የጥናት ርዕስ 39
ክርስቲያን ሴቶችን ደግፏቸው
“ምሥራቹን የሚያውጁ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት ናቸው።”—መዝ. 68:11
መዝሙር 137 ታማኝ ሴቶች፣ ክርስቲያን እህቶች
ማስተዋወቂያ *
1. እህቶች በየትኞቹ መንገዶች ድርጅቱን ይደግፋሉ? ብዙዎቹ እህቶች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎችስ ያጋጥሟቸዋል? (ሽፋኑን ተመልከት።)
በጉባኤ ውስጥ በትጋት የሚያገለግሉ እጅግ ብዙ እህቶች ስላሉን ምንኛ አመስጋኞች ነን! እነዚህ እህቶች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይሳተፋሉ እንዲሁም በአገልግሎት ይካፈላሉ። አንዳንዶች የስብሰባ አዳራሹን በመንከባከቡ ሥራ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፤ እንዲሁም ለእምነት አጋሮቻቸው በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ያሳያሉ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ እህቶች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። አንዳንዶቹ በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ይንከባከባሉ። ሌሎች ደግሞ የቤተሰብ ተቃውሞ ይደርስባቸዋል። ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ብዙ የሚደክሙ ነጠላ እናቶችም አሉ።
2. ለእህቶች ድጋፍ ስለ መስጠት መወያየት ያስፈለገን ለምንድን ነው?
2 ለእህቶች ድጋፍ ስለ መስጠት መወያየት ያስፈለገን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ይህ ዓለም ለሴቶች የሚገባቸውን ክብር አይሰጣቸውም። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን እንድንደግፋቸው ያበረታታናል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ፌበንን እንዲቀበሏትና ‘የምትፈልገውን እርዳታ ሁሉ እንዲያደርጉላት’ በሮም ጉባኤ ለነበሩ ክርስቲያኖች ጽፎላቸው ነበር። (ሮም 16:1, 2) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚመለከተው የፈሪሳውያን ቡድን አባል ነበር። ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ግን የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሴቶችን በአክብሮትና በደግነት መያዝ ጀመረ።—1 ቆሮ. 11:1
3. ኢየሱስ ሴቶችን ይይዝ የነበረው እንዴት ነው? የአምላክን ፈቃድ ለሚያደርጉ ሴቶች ምን አመለካከት ነበረው?
3 ኢየሱስ ሁሉንም ሴቶች በአክብሮት ይይዝ ነበር። (ዮሐ. 4:27) በወቅቱ የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ለሴቶች የነበራቸው ዓይነት አመለካከት አልነበረውም። እንዲያውም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ “ኢየሱስ ሴቶችን የሚያቃልል ወይም ዝቅ የሚያደርግ ነገር ፈጽሞ ተናግሮ አያውቅም” ይላል። ኢየሱስ በተለይ ደግሞ የአባቱን ፈቃድ ለሚያደርጉ ሴቶች ልዩ አክብሮት ነበረው። እንደ እህቶቹ አድርጎ ይመለከታቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ የመንፈሳዊ ቤተሰቡ አባላት አድርጎ ከሚቆጥራቸው ወንዶች ጋር አብሮ ጠቅሷቸዋል።—ማቴ. 12:50
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
4 ኢየሱስ መንፈሳዊ እህቶቹን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነበር። ያደንቃቸውና ጥብቅና ይቆምላቸው ነበር። እኛም ለእህቶች አሳቢነት በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ውድ እህቶቻችንን አስቧቸው
5. አንዳንድ እህቶች ከሌሎች ጋር ተገናኝተው ጥሩ ጊዜ እንዳያሳልፉ እንቅፋት የሚሆንባቸው ምን ሊሆን ይችላል?
5 ወንድሞችም ሆንን እህቶች ሁላችንም ከሌሎች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንፈልጋለን። አንዳንድ ጊዜ ግን እህቶች አብሯቸው ጊዜ የሚያሳልፍ ጓደኛ ማግኘት ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። ለምን? እስቲ አንዳንዶች የሰጧቸውን ሐሳቦች እንመልከት። ጆርዳን * የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ስላላገባሁ በጉባኤ ውስጥ ቦታ እንደሌለኝ ብዙውን ጊዜ ይሰማኛል፤ በጉባኤ ውስጥ ካሉት ጋር የሚያግባባኝ ነገር እንደሌለ አስባለሁ።” አገልግሎቷን ለማስፋት ወደ ሌላ አካባቢ የሄደች ክርስቲን የተባለች የዘወትር አቅኚ “ወደ ሌላ ጉባኤ ስትዛወሩ ብቸኝነት ሊሰማችሁ ይችላል” ብላለች። በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖር ክርስቲያን፣ ከሥጋ ቤተሰቡም ሆነ ከመንፈሳዊ ቤተሰቡ እንደተገለለ ይሰማው ይሆናል። በአቅም ገደብ ምክንያት ከቤት መውጣት የማይችሉ ወይም የታመሙ የቤተሰባቸውን አባላት የሚንከባከቡ ክርስቲያኖች ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል። አኔት “እናቴን የመንከባከቡ ኃላፊነት በዋነኝነት የእኔ ስለነበር ከሌሎች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ የሚቀርቡልኝን ግብዣዎች መቀበል አልችልም ነበር” ብላለች።
6. በሉቃስ 10:38-42 ላይ እንደተጠቀሰው ኢየሱስ ማርያምንና ማርታን የረዳቸው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ ከመንፈሳዊ እህቶቹ ጋር ጊዜ ያሳልፍ ነበር፤ እውነተኛ ወዳጅም ሆኖላቸዋል። ከማርያምና ከማርታ ጋር የነበረውን ወዳጅነት እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ሁለቱም ነጠላ የነበሩ ይመስላል። (ሉቃስ 10:38-42ን አንብብ።) ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ነፃነት ተሰምቷቸው እንዲቀርቡት አድርጓቸው መሆን አለበት። ማርያም አንድ ደቀ መዝሙር እንደሚያደርገው ሳትፈራ እግሩ ሥር ተቀምጣለች። * ማርታም ብትሆን ማርያም ስላላገዘቻት በተበሳጨችበት ወቅት፣ ስሜቷን ለኢየሱስ በነፃነት ነግራዋለች። በዚህ ግብዣ ላይ ኢየሱስ ሁለቱንም ሴቶች በመንፈሳዊ ለመርዳት አጋጣሚውን ተጠቅሞበታል። በተጨማሪም እነዚህን ሴቶችም ሆነ ወንድማቸውን አልዓዛርን በሌሎች አጋጣሚዎችም ሄዶ በመጠየቅ እንደሚያስብላቸው አሳይቷል። (ዮሐ. 12:1-3) አልዓዛር በጠና በታመመበት ወቅት ማርያምና ማርታ የኢየሱስን እርዳታ ለመጠየቅ ያልተሳቀቁት ለዚህ ነው።—ዮሐ. 11:3, 5
7. እህቶችን ማበረታታት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
7 አንዳንድ እህቶች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር መገናኘት የሚችሉበት ዋነኛ አጋጣሚ የጉባኤ ስብሰባ ነው። በመሆኑም በእነዚህ አጋጣሚዎች እህቶቻችንን ሞቅ አድርገን መቀበል፣ እነሱን ማጫወት እንዲሁም እንደምናስብላቸው ማሳየት እንፈልጋለን። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጆርዳን እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች፣ ስብሰባ ላይ የሰጠሁትን ሐሳብ አንስተው ሲያመሰግኑኝ፣ አብሬያቸው አገልግሎት እንድወጣ ሲጋብዙኝ ወይም በሌሎች መንገዶች እንደሚያስቡልኝ ሲያሳዩኝ በጣም እበረታታለሁ።” እህቶቻችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከታቸው ልናሳያቸው ይገባል። ኪያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ስብሰባ ብቀር ወንድሞችና እህቶች ደህና መሆኔን ለማወቅ የጽሑፍ መልእክት እንደሚልኩልኝ አውቃለሁ። ይህም እንደሚያስቡልኝ እንዲሰማኝ ያደርጋል።”
8. ኢየሱስን መምሰል የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
8 እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ከእህቶች ጋር አብረን የምናሳልፈው ጊዜ መመደብ እንችላለን። ቀለል ያለ ምግብ ሠርተን ልንጋብዛቸው ወይም አብረውን እንዲዝናኑ ሮም 1:11, 12) ሽማግሌዎች የኢየሱስን ዓይነት አመለካከት መያዛቸው አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ነጠላነት ለአንዳንዶች ተፈታታኝ እንደሚሆን ያውቅ ነበር፤ ሆኖም ዘላቂ ደስታ ለማግኘት ቁልፉ ማግባት ወይም ልጆች መውለድ እንዳልሆነ ግልጽ አድርጓል። (ሉቃስ 11:27, 28) ዘላቂ ደስታ ማግኘት የሚቻለው የይሖዋን አገልግሎት በማስቀደም ነው።—ማቴ. 19:12
ልንጠይቃቸው እንችል ይሆናል። ይህን ስናደርግ ጭውውታችን የሚያንጽ እንዲሆን ጥረት እናድርግ። (9. ሽማግሌዎች እህቶችን ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?
9 በተለይ ሽማግሌዎች ክርስቲያን ሴቶችን እንደ መንፈሳዊ እህቶቻቸውና እናቶቻቸው አድርገው መያዝ ይኖርባቸዋል። (1 ጢሞ. 5:1, 2) ሽማግሌዎች ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ ከእህቶች ጋር ለመጨዋወት ጊዜ መመደብ ያስፈልጋቸዋል። ክርስቲን እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሽማግሌ ሥራ እንደሚበዛብኝ ስላስተዋለ ስለ ፕሮግራሜ ጠየቀኝ። አሳቢነት ስላሳየኝ ደስ ብሎኛል።” ሽማግሌዎች ከመንፈሳዊ እህቶቻቸው ጋር ለማውራት ዘወትር ጊዜ የሚመድቡ ከሆነ እንደሚያስቡላቸው ያሳያሉ። * ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አኔት ከሽማግሌዎች ጋር አዘውትሮ መነጋገር ያለውን ጥቅም ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ይበልጥ ለመተዋወቅ አስችሎናል። በመሆኑም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ የእነሱን እርዳታ መጠየቅ አይከብደኝም።”
እህቶችን አድንቋቸው
10. እህቶቻችንን ለማበረታታት ምን ማድረግ እንችላለን?
10 ወንዶችም ሆንን ሴቶች ሁላችንም፣ ሌሎች ሰዎች ችሎታችንን ሲያደንቁልን ወይም ላከናወንነው ሥራ ሲያመሰግኑን እንበረታታለን። በሌላ በኩል ግን ተሰጥኦዋችንንም ሆነ የምናከናውነውን ሥራ ልብ የሚለው እንደሌለ ሲሰማን ተስፋ እንቆርጣለን። አቢጋኤል የተባለች ያላገባች አቅኚ ማንም ትኩረት እንደማይሰጣት የሚሰማት ጊዜ እንዳለ ተናግራለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች እኔን የሚያውቁኝ የእገሊት እህት ወይም የእገሌ ልጅ በመሆኔ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ማንም እንደማያስተውለኝ ይሰማኛል።” በሌላ በኩል ግን ፓም የተባለች እህት የተናገረችውን እንመልከት። ፓም ነጠላ ሆና በሚስዮናዊነት ለብዙ ዓመታት አገልግላለች። ከጊዜ በኋላ ወላጆቿን ለመንከባከብ ስትል ወደ ትውልድ አገሯ ተመለሰች። አሁን በ70ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሲሆን አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው። ፓም “ሌሎች እንደሚያደንቁኝ የሚነግሩኝ መሆኑ በጣም ጠቅሞኛል” ብላለች።
11. ኢየሱስ፣ አገልግሎቱን ሲያከናውን አብረውት ይጓዙ የነበሩትን ሴቶች እንደሚያደንቃቸው ያሳየው እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ ‘በንብረታቸው ያገለግሉት’ የነበሩ ታማኝ ሴቶች የሚያደርጉለትን እርዳታ ያደንቅ ነበር። (ሉቃስ 8:1-3) እሱን የማገልገል መብት እንዲያገኙ ከመፍቀዱም ሌላ ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን አካፍሏቸዋል። ለምሳሌ፣ እንደሚሞትና ከሞት እንደሚነሳ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 24:5-8) ለሐዋርያቱ እንዳደረገው ሁሉ እነዚህን ሴቶችም ወደፊት ለሚጠብቃቸው ፈተና አዘጋጅቷቸዋል። (ማር. 9:30-32፤ 10:32-34) ኢየሱስን ያገለግሉ ከነበሩት ከእነዚህ ሴቶች አንዳንዶቹ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በነበረበት ወቅት ከጎኑ አለመለየታቸው ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት ሐዋርያቱ ጥለውት ሸሽተው ነበር።—ማቴ. 26:56፤ ማር. 15:40, 41
12. ኢየሱስ ለሴቶች ምን ሥራ ሰጥቷቸዋል?
12 ኢየሱስ ለሴቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሥራ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ፣ የኢየሱስ ትንሣኤ የመጀመሪያዎቹ ምሥክሮች አምላክን የሚፈሩ ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ፣ ከሞት መነሳቱን ለሐዋርያቱ እንዲነግሩ እነዚህን ሴቶች ልኳቸዋል። (ማቴ. 28:5, 9, 10) በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰበት ወቅት በቦታው ሴቶች ተገኝተው ሊሆን ይችላል። ከሆነ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት እነዚህ እህቶች በሌሎች ቋንቋዎች የመናገር ተአምራዊ ችሎታ ተሰጥቷቸው እንዲሁም “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ለሰዎች የመመሥከር አጋጣሚ አግኝተው መሆን አለበት።—ሥራ 1:14፤ 2:2-4, 11
13. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ሴቶች በየትኞቹ ሥራዎች ይካፈላሉ? ለሚያከናውኑት ሥራ ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
13 እህቶቻችን በይሖዋ አገልግሎት ለሚያከናውኑት ሥራ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። እህቶች ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች መካከል ሕንፃዎችን መገንባትና መንከባከብ፣ በሌላ ቋንቋ የሚመሩ ቡድኖችን መደገፍ እንዲሁም በቤቴል በፈቃደኝነት ማገልገል ይገኙበታል። በአደጋ ጊዜ እርዳታ በመስጠቱና ጽሑፎቻችንን በመተርጎሙ ሥራ እገዛ የሚያበረክቱ ሲሆን አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ሆነው ያገለግላሉ። እንደ ወንድሞች ሁሉ እህቶችም በአቅኚዎች ትምህርት ቤት፣ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት እንዲሁም በጊልያድ ትምህርት ቤት ይማራሉ። በተጨማሪም ሚስቶች፣ ባሎቻቸው በጉባኤ ውስጥም ሆነ በድርጅቱ ውስጥ ያለባቸውን ከባድ ኃላፊነት እንዲወጡ ይረዳሉ። እነዚህ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ሚስቶቻቸው ባይረዷቸው ኖሮ ‘ስጦታ’ ሆነው በተሟላ ሁኔታ ማገልገል ይከብዳቸው ነበር። (ኤፌ. 4:8) ታዲያ እነዚህን እህቶች ሥራቸውን ሲያከናውኑ መደገፍ የምትችልባቸው መንገዶች ይኖሩ ይሆን?
14. በመዝሙር 68:11 ላይ ከተገለጸው ሐሳብ አንጻር ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎች ምን ይገነዘባሉ?
14 ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎች፣ እህቶች ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያቀፈ “ታላቅ ሠራዊት” እንደሆኑና ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ብዙውን ጊዜ የተዋጣላቸው እንደሆኑ ይገነዘባሉ። (መዝሙር 68:11ን አንብብ።) በመሆኑም ሽማግሌዎች ከእነዚህ እህቶች ተሞክሮ ለመማር ጥረት ያደርጋሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አቢጋኤል፣ በክልሏ ውስጥ ሰዎችን ለማነጋገር ውጤታማ ሆነው ያገኘቻቸውን ዘዴዎች ወንድሞች ሲጠይቋት እንደምትበረታታ ገልጻለች። “እንዲህ ማድረጋቸው በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የማበረክተው ድርሻ እንዳለኝ እንዲሰማኝ ያደርጋል” ብላለች። በተጨማሪም ታማኝ የሆኑና በመንፈሳዊ የጎለመሱ እህቶች፣ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የገጠሟቸውን በዕድሜ ከእነሱ የሚያንሱ እህቶች በመርዳት ረገድ ውጤታማ እንደሆኑ ሽማግሌዎች ይገነዘባሉ። (ቲቶ 2:3-5) በእርግጥም እህቶቻችን አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል!
ለእህቶች ጥብቅና ቁሙ
15. እህቶች ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው የሚያስፈልጋቸው መቼ ሊሆን ይችላል?
15 እህቶች በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው ያስፈልጋቸው ይሆናል። (ኢሳ. 1:17) ለምሳሌ ያህል፣ መበለት የሆነች ወይም ከባሏ የተፋታች አንዲት እህት ስለ እሷ ሆኖ የሚናገርላት እንዲሁም ባሏ ያከናውናቸው የነበሩ አንዳንድ ሥራዎችን ስታከናውን የሚያግዛት ሰው ሊያስፈልጋት ይችላል። በዕድሜ የገፉ አንዲት እህት የሕክምና ባለሙያዎችን ሲያነጋግሩ የሚያግዛቸው ሰው ያስፈልጋቸው ይሆናል። አሊያም ደግሞ በሌሎች ቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ላይ የምትካፈል አቅኚ እህት የሌሎች አቅኚዎችን ያህል አዘውትራ አገልግሎት ባለመውጣቷ አንዳንዶች ቢተቿት የሚሟገትላት ሰው ያስፈልጋታል። ታዲያ እንዲህ ያለ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን እህቶቻችንን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ የኢየሱስን ምሳሌ እንደገና እንመልከት።
16. በማርቆስ 14:3-9 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ለማርያም ጥብቅና የቆመው እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ፣ መንፈሳዊ እህቶቹን ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዷቸው ወዲያውኑ ጥብቅና ይቆምላቸው ነበር። ለምሳሌ፣ ማርታ ማርያምን በወቀሰቻት ወቅት ለማርያም ጥብቅና ቆሞላታል። (ሉቃስ 10:38-42) በሌላ ጊዜም አንዳንዶች ማርያም የወሰደችው እርምጃ ስህተት እንደሆነ በማሰብ በወቀሷት ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ ለማርያም ተሟግቶላታል። (ማርቆስ 14:3-9ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ ማርያም ያንን እርምጃ እንድትወስድ ያነሳሳት ምን እንደሆነ ተረድቶ ስለነበር “ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች። . . . እሷ የምትችለውን አድርጋለች” በማለት አመስግኗታል። እንዲያውም “በመላው ዓለም ምሥራቹ በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ” ማርያም ያደረገችው መልካም ተግባር እንደሚነገርላት ትንቢት ተናግሯል፤ አሁን በዚህ ርዕስ ላይ እያደረግን ያለነውም ይህንኑ ነው። ኢየሱስ ይህች ሴት በፍቅር ተነሳስታ ያከናወነችውን ተግባር፣ የስብከቱ ሥራ በዓለም ዙሪያ ከሚከናወንበት ስፋት ጋር አያይዞ መጥቀሱ ትኩረት የሚስብ ነው። ሌሎች በተሳሳተ መንገድ የተረዷት ማርያም፣ ኢየሱስ በተናገረው ነገር ምንኛ ተበረታትታ ይሆን!
17. ለአንዲት እህት ጥብቅና መቆም እንዲያስፈልገን የሚያደርግ ሁኔታ ጥቀስ።
17 መንፈሳዊ እህቶችህ ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው በሚያስፈልጋቸው ወቅት ትሟገትላቸዋለህ? አንድ ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። የማያምን ባል ያላት አንዲት እህት አለች እንበል፤ ይህች እህት ብዙውን ጊዜ ጉባኤ የምትደርሰው አርፍዳ እንደሆነና ስብሰባው እንዳለቀም ወደ ቤቷ እንደምትሄድ አንዳንድ አስፋፊዎች አስተውለዋል። ልጆቿን ወደ ስብሰባ የምታመጣቸውም ከስንት አንዴ እንደሆነ ተመልክተዋል። በመሆኑም ከባሏ ጋር በተያያዘ ቆራጥ አቋም ልትወስድ እንደሚገባት በመግለጽ ይነቅፏታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እህታችን አቅሟ የሚፈቅደውን ሁሉ እያደረገች ነው። ጊዜዋን የምትጠቀምበት መንገድ ሙሉ በሙሉ በእሷ ቁጥጥር ሥር አይደለም፤ ከልጆቿ ጋር በተያያዘም የመጨረሻውን ውሳኔ ማድረግ አትችልም። ታዲያ ይህች እህት ስትነቀፍ ብትሰማ እሷን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ? እህትን እንደምታደንቃት ብትገልጽላት እንዲሁም እያደረገች ያለችውን መልካም ነገር ለሌሎች ብትጠቅስ የሚሰነዘርባትን ነቀፋ ማስቆም ትችል ይሆናል።
18. እህቶቻችንን በየትኞቹ ሌሎች መንገዶች መርዳት እንችላለን?
18 እህቶቻችንን በሚያስፈልጓቸው ነገሮች በመርዳት 1 ዮሐ. 3:18) የታመሙ እናቷን ትንከባከብ የነበረችው አኔት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ወዳጆቼ መጥተው ይተኩኝ አሊያም ምግብ ያመጡልኝ ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው እንደምወደድና በጉባኤው ውስጥ ቦታ እንዳለኝ እንዲሰማኝ አድርጓል።” ጆርዳንም የሌሎችን እርዳታ አግኝታለች። አንድ ወንድም መኪናዋን እንዴት እንደምትጠግን አንዳንድ ሐሳቦች አካፈላት። “ወንድሞቼና እህቶቼ ስለ ደህንነቴ እንደሚጨነቁ ማወቄ በጣም ያስደስተኛል” በማለት ተናግራለች።
ምን ያህል እንደምናስብላቸው ማሳየት እንችላለን። (19. ሽማግሌዎች እህቶችን በየትኞቹ ተጨማሪ መንገዶች መርዳት ይችላሉ?
19 ሽማግሌዎችም እህቶች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ትኩረት ይሰጣሉ። ይሖዋ እነዚህ እህቶች በእንክብካቤ እንዲያዙ እንደሚፈልግ ያውቃሉ። (ያዕ. 1:27) በመሆኑም ደንቦችን ከማውጣት ይልቅ በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ለየት ያለ ደግነት በማሳየት እንደ ኢየሱስ ምክንያታዊ ለመሆን ይጥራሉ። (ማቴ. 15:22-28) ቅድሚያውን ወስደው እርዳታ የሚሰጡ ሽማግሌዎች፣ እህቶች እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ። ኪያ የተባለችው እህት የቡድን የበላይ ተመልካች፣ ቤት ልትቀይር እንደሆነ ሲሰማ እገዛ እንድታገኝ ወዲያውኑ ዝግጅት አደረገ። ኪያ እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ብዙ ውጥረት ቀንሶልኛል። ሽማግሌዎች የሚያበረታታ ሐሳብ በመናገርና የሚያስፈልገኝን እርዳታ በመስጠት በጉባኤው ውስጥ እንደምፈለግና ችግሮች ሲያጋጥሙኝ ብቻዬን እንደማልሆን አሳይተውኛል።”
ሁሉም ክርስቲያን እህቶቻችን የእኛ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል
20-21. ሁሉንም ክርስቲያን እህቶቻችንን እንደምንወዳቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
20 በዛሬው ጊዜ በጉባኤዎቻችን ውስጥ ድጋፋችን የሚገባቸው ታታሪ የሆኑ በርካታ ክርስቲያን ሴቶች አሉ። ከኢየሱስ ምሳሌ እንደተማርነው ከእነዚህ እህቶች ጋር ጊዜ በማሳለፍና እነሱን የበለጠ ለማወቅ ጥረት በማድረግ ልንደግፋቸው እንችላለን። በአምላክ አገልግሎት ለሚያከናውኑት ነገር አድናቆታችንን መግለጽ እንችላለን። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም ጥብቅና ልንቆምላቸው ይገባል።
21 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መደምደሚያ ላይ ዘጠኝ ክርስቲያን ሴቶችን ለይቶ ጠቅሷል። (ሮም 16:1, 3, 6, 12, 13, 15) እነዚህ ሴቶች የጳውሎስን ሰላምታና ምስጋና ሲሰሙ እንደተበረታቱ ጥያቄ የለውም። እኛም እንዲሁ በጉባኤያችን ያሉ እህቶችን በሙሉ እንደግፋቸው። በዚህ መንገድ፣ የምንወዳቸው የመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባላት እንደሆኑ እንዲሰማቸው እናደርጋለን።
መዝሙር 136 ከይሖዋ የምናገኘው “ሙሉ ወሮታ”
^ አን.5 ክርስቲያን ሴቶች ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ይህ ርዕስ፣ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል መንፈሳዊ እህቶቻችንን መደገፍ የምንችልበትን መንገድ ያብራራል። ኢየሱስ ከሴቶች ጋር ጊዜ በማሳለፍ፣ እነሱን በማድነቅ እንዲሁም ለእነሱ ጥብቅና በመቆም ከተወው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።
^ አን.5 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.6 አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ደቀ መዛሙርት በአስተማሪዎቻቸው እግር ሥር ይቀመጡ ነበር። እነዚህ ሰዎች በቁም ነገር ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አስተማሪ ለመሆን ነበር፤ ይህ ደግሞ ለሴቶች የሚፈቀድ ነገር አልነበረም። . . . ማርያም በባሕሉ ከሴቶች የሚጠበቀውን ድርሻ . . . ከመወጣት ይልቅ ኢየሱስ እግር ሥር መቀመጧና ከእሱ ለመማር የነበራት ጉጉት አብዛኞቹን አይሁዳውያን ወንዶች የሚያስደነግጥ ነበር።”
^ አን.9 ሽማግሌዎች እህቶችን በሚረዱበት ጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ለምሳሌ አንድ ሽማግሌ አንዲት እህትን ለመጠየቅ ብቻውን መሄድ የለበትም።
^ አን.65 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ሁለት እህቶችን የመኪናቸውን ጎማ በመቀየር ሲያግዛቸው፣ ሌላ ወንድም በዕድሜ የገፉ እህትን ሲጠይቅ እንዲሁም አንድ ሌላ ወንድም ከሚስቱ ጋር ወደ አንዲት እህት ቤት ሄዶ ከእሷና ከልጇ ጋር የቤተሰብ አምልኮ ሲያደርጉ። በዚህ መንገድ፣ ኢየሱስ ለታማኝ ሴቶች አሳቢነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ ተከትለዋል።