የአንባቢያን ጥያቄዎች
የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች በግል ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ማውጣት የማይፈቀደው ለምንድን ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን እና ሌሎች የሕትመት ውጤቶችን ለሰዎች የምንሰጠው በነፃ ስለሆነ አንዳንዶች ድረ ገጻችን ላይ የወጡ ነገሮችን ወስደው በራሳቸው ድረ ገጽ ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ማውጣት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ የድረ ገጾቻችንን የአጠቃቀም ውል * የሚጥስ ከመሆኑም በላይ ከባድ ችግሮች አስከትሏል። በአጠቃቀም ውሉ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ማንም ሰው “ከዚህ ድረ ገጽ ላይ የተወሰዱ ሥዕሎችን፣ የኤሌክትሮኒክ ጽሑፎችን፣ የንግድ ምልክቶችን፣ ሙዚቃዎችን፣ ፎቶዎችን፣ ቪዲዮዎችን ወይም ሐሳቦችን ኢንተርኔት (ፋይሎችንና ቪድዮዎችን ማጋራት የሚቻልባቸውን ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ጨምሮ ማንኛውም ድረ ገጽ) ላይ ፖስት ማድረግ” አይፈቀድለትም። እንዲህ ዓይነት ገደቦች ያስፈለጉት ለምንድን ነው?
በድረ ገጻችን ላይ የሚወጡት ነገሮች በሙሉ በቅጂ መብት ባለቤትነት ሕግ የተጠበቁ ናቸው። ተቃዋሚዎች ጽሑፎቻችንን በድረ ገጾቻቸው ላይ በማውጣት የይሖዋ ምሥክሮችንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ለማታለል ይሞክራሉ። የእነዚህ ድረ ገጾች ዓላማ በአንባቢያን አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ መዝራት ነው። (መዝ. 26:4፤ ምሳሌ 22:5) ሌሎች ደግሞ በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡ ነገሮችን ወይም የjw.org አርማችንን በማስታወቂያዎቻቸው፣ ለሽያጭ በቀረቡ ምርቶቻቸውና በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አፕሊኬሽኖች ላይ ተጠቅመዋል። እኛም የቅጂ መብታችንን እና የንግድ ምልክታችንን በሕግ ማስመዝገባችን አንዳንዶች ድረ ገጻችን ላይ የሚወጡ ነገሮችንና አርማችንን አላግባብ እንዳይጠቀሙ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለመከላከል ያስችለናል። (ምሳሌ 27:12) ይሁንና ሌሎች ሰዎች ሌላው ቀርቶ ወንድሞቻችንም እንኳ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት የምናዘጋጀውን ነገር በድረ ገጾቻቸው ላይ እንዲያወጡ ወይም በjw.org የንግድ ምልክት ተጠቅመው ሸቀጦቻቸውን እንዲሸጡ የምንፈቅድላቸው ከሆነ ተቃዋሚዎችና የንግድ ድርጅቶች ድረ ገጻችንን አላግባብ እንዳይጠቀሙ ለማገድ ብንፈልግ ፍርድ ቤቶች ጥያቄያችንን ላይቀበሉት ይችላሉ።
ጽሑፎቻችንን ከjw.org ካልሆነ በቀር ከሌላ ድረ ገጽ ላይ ማውረድ አደገኛ ነው። ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያቀርብ ኃላፊነት የሰጠው ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ ብቻ ነው። (ማቴ. 24:45) ይህ “ባሪያ” ደግሞ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀመው www.dan124.com፣ tv.dan124.com እና wol.dan124.com የተባሉትን ሕጋዊ ድረ ገጾች ብቻ ነው። እንዲሁም ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ጋር በተያያዘ የምንጠቀምባቸው ሕጋዊ አፕሊኬሽኖች ሦስት ብቻ ሲሆኑ እነሱም JW Language®፣ JW Library®፣ እና JW Library Sign Language® ናቸው። እነዚህ ድረ ገጾችና አፕሊኬሽኖች ከማስታወቂያዎች ነፃ እንደሆኑና በሰይጣን ዓለም እንዳልተበከሉ መተማመን እንችላለን። ከላይ ከተጠቀሱት ድረ ገጾችና አፕሊኬሽኖች ውጭ በሌሎች ድረ ገጾች ላይ የሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ግን ለውጥ እንዳልተደረገበት ወይም እንዳልተበከለ ዋስትና መስጠት አይቻልም።—መዝ. 18:26፤ 19:8
ከዚህም ሌላ፣ አስተያየት ማስፈር በሚቻልባቸው ድረ ገጾች ላይ የሕትመት ውጤቶቻችንን ማውጣት፣ ከሃዲዎችና ሌሎች ተቺዎች የይሖዋ ድርጅትን በተመለከተ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲዘሩ አጋጣሚውን ይከፍትላቸዋል። አንዳንድ ወንድሞች በኢንተርኔት በሚካሄዱ ክርክሮች ውስጥ ሳያስቡት የገቡ ሲሆን ይህም በይሖዋ ስም ላይ ተጨማሪ ነቀፋ አስከትሏል። ደግሞም እንዲህ ባሉት መድረኮች መካፈል “ቀና አመለካከት የሌላቸውን በገርነት [ለማረም]” የሚያስችል ተገቢ አካሄድ አይደለም። (2 ጢሞ. 2:23-25፤ 1 ጢሞ. 6:3-5) በተጨማሪም በድርጅታችን፣ በበላይ አካል እንዲሁም በበላይ አካል አባላት ስም የሐሰት የማኅበራዊ ድረ ገጽ አካውንቶች እንደተከፈቱ ተስተውሏል። ይሁን እንጂ የትኛውም የበላይ አካል አባል የግሉ ድረ ገጽ የለውም፤ በማንኛውም ማኅበራዊ ድረ ገጽም አይጠቀምም።
ሰዎች jw.orgን እንዲጠቀሙ ማበረታታት ‘ምሥራቹን’ ለማስፋፋት ይረዳል። (ማቴ. 24:14) የይሖዋ ድርጅት ለአገልግሎት እንዲረዱን ያዘጋጀልን ድረ ገጾችና አፕሊኬሽኖች ሁልጊዜ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል። ሁሉም ሰው ከእነዚህ ዝግጅቶች እንዲጠቀም እንፈልጋለን። በመሆኑም የአጠቃቀም ውሉ ላይ እንደተገለጸው በjw.org ድረ ገጽ ላይ የሚገኙ ጽሑፎችን፣ ቪዲዮዎችን ወይም የኦዲዮ ፕሮግራሞችን አውርደህ ወይም ሊንኩን ወስደህ ለሌሎች በኢ-ሜይል መላክ ትችላለህ። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሕጋዊ ድረ ገጾቻችንን እንዲጠቀሙ ስናበረታታቸው ብቸኛው የእውነተኛ መንፈሳዊ ምግብ ምንጭ ይኸውም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያቀርበውን ምግብ እንዲያገኙ እንረዳቸዋለን።