የጥናት ርዕስ 23
“ስምህ ይቀደስ”
“ይሖዋ ሆይ፣ ስምህ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—መዝ. 135:13
መዝሙር 10 ይሖዋ አምላካችንን አወድሱ!
ማስተዋወቂያ *
1-2. የይሖዋ ምሥክሮች ለየትኞቹ ጉዳዮች ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ?
ሁላችንንም የሚመለከቱ በጣም ወሳኝ ጉዳዮች አሉ፤ እነሱም የአምላክ ሉዓላዊነት መረጋገጥ እና የስሙ መቀደስ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ስለ እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች መወያየት ያስደስተናል። ሆኖም የአምላክ ሉዓላዊነት መረጋገጥ እና የስሙ መቀደስ እርስ በርስ የማይዛመዱ ጉዳዮች ናቸው? እንደዚያ ማለት አይደለም።
2 የአምላክ ስም ከነቀፋ ነፃ መሆን እንደሚያስፈልገው ሁላችንም ተገንዝበናል። የይሖዋ ሉዓላዊነት ማለትም አገዛዙ፣ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ መረጋገጥ እንዳለበትም ተምረናል። ሁለቱም ጉዳዮች በጣም አስፈላጊና ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው።
3. ይሖዋ የሚለው ስም ምን ያጠቃልላል?
3 የይሖዋ ስም፣ የእሱን አገዛዝ ጨምሮ ከአምላካችን ጋር የተያያዙ ነገሮችን በሙሉ የሚያጠቃልል ነው። በመሆኑም የይሖዋ ስም ከተሰነዘረበት ነቀፋ ሁሉ ነፃ መሆን እንዳለበት ስንናገር አገዛዙ ከሁሉ የተሻለ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበትም መግለጻችን ነው። የይሖዋ ስም፣ ሉዓላዊ አምላክ በመሆን ከሚገዛበት መንገድ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።—“ ከአምላክ ስም መቀደስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
4. መዝሙር 135:13 የአምላክን ስም በተመለከተ ምን ይላል? በዚህ ርዕስ ላይ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?
4 ይሖዋ የሚለው ስም በዓይነቱ ልዩ ነው። (መዝሙር 135:13ን አንብብ።) የአምላክ ስም ይህን ያህል ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው? ይህ ስም በመጀመሪያ ነቀፋ የተሰነዘረበት እንዴት ነው? አምላክ ስሙን የሚቀድሰው እንዴት ነው? እኛስ ለስሙ ጥብቅና መቆም የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመልከት።
ስም ትልቅ ቦታ አለው
5. ስለ አምላክ ስም መቀደስ ስናስብ ምን ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል?
5 “ስምህ ይቀደስ።” (ማቴ. 6:9) ኢየሱስ በጸሎታችን ላይ ቅድሚያ ልንሰጠው እንደሚገባ የጠቀሰው ይህን ሐሳብ ነው። ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? አንድን ነገር መቀደስ ሲባል ቅዱስና ንጹሕ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። ሆኖም አንዳንዶች ‘የይሖዋ ስም ቀድሞውንስ ቢሆን ቅዱስና ንጹሕ አይደለም እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ያነሱ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት፣ ስም ምን ነገሮችን እንደሚያካትት መመርመር ያስፈልገናል።
6. ስም ትልቅ ቦታ ያለው ለምንድን ነው?
6 ስም፣ በወረቀት ላይ ከሚሰፍረው ቃል ወይም ከስሙ አጠራር ያለፈ ነገርን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይመረጣል” እንደሚል ልብ በል። (ምሳሌ 22:1፤ መክ. 7:1) ስም ይህን ያህል ትልቅ ቦታ ያለው ለምንድን ነው? ሰዎች ስለ ስሙ ባለቤት ያላቸውን አመለካከትም ስለሚያካትት ነው። በመሆኑም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር፣ አንድ ስም የሚጻፍበት ወይም የሚጠራበት መንገድ ሳይሆን ስሙ ሲነሳ በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚመጣው ነገር ነው።
7. ሰዎች የአምላክን ስም እያጠፉ ያሉት እንዴት ነው?
7 ሰዎች ስለ ይሖዋ ውሸት ሲናገሩ ስሙን እያጠፉ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በአምላክ ስም ላይ ጥቃት የተሰነዘረው በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ አካባቢ ነው። ከዚህ ታሪክ ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት።
የአምላክ ስም በመጀመሪያ ነቀፋ የተሰነዘረበት እንዴት ነው?
8. አዳምና ሔዋን ምን ያውቁ ነበር? የትኞቹ ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?
8 አዳምና ሔዋን የይሖዋን ስም እንዲሁም ከስሙ ባለቤት ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ያውቁ ነበር። ይሖዋ ፈጣሪያቸውና ሕይወት ሰጪያቸው እንደሆነ እንዲሁም ውብ የሆነች ገነት እና ፍጹም የትዳር ጓደኛ የሰጣቸው እሱ እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ዘፍ. 1:26-28፤ 2:18) ይሁንና ፍጹም የሆነ አእምሯቸውን ተጠቅመው ይሖዋ ባደረገላቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላቸውን ይቀጥሉ ይሆን? የስሙ ባለቤት ለሆነው አካል ያላቸው ፍቅርና አድናቆት እያደገ እንዲሄድስ ጥረት ያደርጉ ይሆን? የአምላክ ጠላት ፈተና ሲያቀርብላቸው የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ግልጽ ሆኗል።
9. በዘፍጥረት 2:16, 17 እንዲሁም 3:1-5 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምን ብሏቸዋል? ሰይጣን እውነቱን አዛብቶ ያቀረበውስ እንዴት ነው?
9 ዘፍጥረት 2:16, 17ን እንዲሁም 3:1-5ን አንብብ። ሰይጣን በእባብ በመጠቀም ሔዋንን “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?” ሲል ጠየቃት። ይህ፣ ስውር የሆነ ውሸት ያዘለ መርዛማ ጥያቄ ነው። አምላክ የተናገረው ከአንዱ ዛፍ በቀር ከማንኛውም ዛፍ መብላት እንደሚችሉ ነው። አዳምና ሔዋን ከምግብ ጋር በተያያዘ ብዙ ምርጫ ነበራቸው። (ዘፍ. 2:9) አዎ፣ ይሖዋ በጣም ለጋስ አምላክ ነው። ይሁንና አምላክ የአንደኛውን ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ አዳምንና ሔዋንን ከልክሏቸው ነበር። ስለዚህ ሰይጣን ጥያቄውን ያቀረበው እውነቱን በሚያዛባ መንገድ ነበር። ሰይጣን፣ አምላክ ለጋስ እንዳልሆነ ለመግለጽ ሞክሯል። ሔዋን ‘አምላክ ያስቀረብን ነገር ይኖር ይሆን እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮባት ሊሆን ይችላል።
10. ሰይጣን የአምላክን ስም በቀጥታ ያጎደፈው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ነበረው?
10 ሰይጣን ጥያቄውን ባቀረበበት ወቅትም እንኳ ሔዋን ገዢዋ አድርጋ የምትመለከተው ይሖዋን ነበር። አምላክ የሰጣቸውን ግልጽ መመሪያ ለሰይጣን ደገመችለት። ዛፉን መንካትም እንኳ እንደማይፈቀድላቸው አክላ ተናገረች። ሔዋን አለመታዘዝ ሞት እንደሚያስከትል አምላክ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ በሚገባ ታውቅ ነበር። ሰይጣን ግን “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም” አላት። (ዘፍ. 3:2-4) ሰይጣን ይህን ሲል፣ በተዘዋዋሪ መንገድ ለመናገር መሞከሩን ትቶ የአምላክን ስም የሚያጎድፍ ነገር በቀጥታ መናገሩ ነበር፤ ሰይጣን፣ ይሖዋ ውሸታም እንደሆነ የገለጸ ያህል ነው። ሰይጣን በዚህ መንገድ፣ ዲያብሎስ ወይም ስም አጥፊ ሆነ። ሔዋንም ተታለለች፤ ሰይጣንን አመነችው። (1 ጢሞ. 2:14) ሔዋን ከይሖዋ ይልቅ በሰይጣን ላይ እምነት ጣለች። ይህም ከሁሉ የከፋ ውሳኔ ወደ ማድረግ መራት። የይሖዋን ትእዛዝ ለመጣስ ወሰነች። ከዚያም ይሖዋ እንዳትበላ የከለከላትን ፍሬ በላች። በኋላም ፍሬውን ለአዳም ሰጠችው።—ዘፍ. 3:6
11. የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምን ማድረግ ይችሉ ነበር? ሆኖም ምን ሳያደርጉ ቀሩ?
11 ሔዋን ለሰይጣን ምን ምላሽ መስጠት ይገባት እንደነበር እስቲ እናስብ። ሔዋን እንዲህ ብላ ልትመልስለት ትችል ነበር፦ “አንተ ማን እንደሆንክ አላውቅም፤ አባቴን ይሖዋን ግን አውቀዋለሁ፣ እወደዋለሁ ደግሞም አምነዋለሁ። ለእኔና ለአዳም ሁሉንም ነገር የሰጠን ይሖዋ ነው። እንዴት ደፍረህ ስሙን ታጠፋለህ? ከፊቴ ዞር በል!” የምትወደው ልጁ እንዲህ ያለ ምላሽ በመስጠት ታማኝነቷን ብታሳይ ኖሮ ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ነበር! (ምሳሌ 27:11) ሔዋን ግን ለይሖዋ እንዲህ ያለ ታማኝ ፍቅር አልነበራትም፤ አዳምም ቢሆን ይህ ባሕርይ አልነበረውም። አዳምና ሔዋን ለአባታቸው እንዲህ ዓይነት ፍቅር ስላላዳበሩ ለእሱ ስም ጥብቅና መቆም አልቻሉም።
12. ሰይጣን በሔዋን አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ የዘራው እንዴት ነው? አዳምና ሔዋን ምን ሳያደርጉ ቀርተዋል?
12 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሰይጣን መጀመሪያ ያደረገው ነገር በሔዋን አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ መዝራት ነው። ይሖዋ ተብሎ የሚጠራው አምላክ፣ ጥሩ አባት መሆኑን እንድትጠራጠር አደረጋት። አዳምና ሔዋንም ለይሖዋ ስም ጥብቅና ሳይቆሙ ቀሩ። ሰይጣን በአባታቸው ላይ እንዲያምፁ ያቀረበላቸውን ሐሳብ በቀላሉ ተቀበሉ። ሰይጣን በዛሬው ጊዜም እንዲህ ዓይነት ዘዴዎችን
ይጠቀማል። በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ይሰነዝራል። ሰዎች የሰይጣንን ውሸት ማመናቸው በይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ላይ እንዲያምፁ ያደርጋቸዋል።ይሖዋ ስሙን ይቀድሳል
13. ሕዝቅኤል 36:23 የመጽሐፍ ቅዱስን ዋነኛ ጭብጥ የሚያጎላው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ በስሙ ላይ የተሰነዘረውን እንዲህ ያለ ነቀፋ በዝምታ ያልፈዋል? በጭራሽ! መላው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወሳው ይሖዋ፣ በኤደን ገነት ውስጥ ከተሰነዘረበት ነቀፋ ስሙን ለማንጻት ስለወሰዳቸው እርምጃዎች ነው። (ዘፍ. 3:15) እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስን ዋነኛ ጭብጥ በዚህ መንገድ ጠቅለል አድርገን መግለጽ እንችላለን፦ ይሖዋ በልጁ በሚመራው መንግሥት አማካኝነት ስሙን ያስቀድሳል እንዲሁም በምድር ላይ ጽድቅና ሰላም እንደገና እንዲሰፍን ያደርጋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው መረጃ ይሖዋ ስሙን የሚቀድሰው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል።—ሕዝቅኤል 36:23ን አንብብ።
14. ይሖዋ በኤደን ለተነሳው ዓመፅ የሰጠው ምላሽ ስሙን ያስቀደሰው እንዴት ነው?
14 ይሖዋ ዓላማውን እንዳያሳካ ለማድረግ ሰይጣን የቻለውን ያህል ሲጥር ቆይቷል። ሆኖም በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ስለወሰዳቸው እርምጃዎች የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ እንደ ይሖዋ ያለ አምላክ እንደሌለ ያረጋግጣል። እርግጥ ነው፣ ሰይጣንም ሆነ ከእሱ ጎራ የተሰለፉት ሁሉ በይሖዋ ላይ ማመፃቸው አምላካችንን በእጅጉ አሳዝኖታል። (መዝ. 78:40) ሆኖም ለተሰነዘረበት ነቀፋ ምላሽ የሰጠው ጥበብ፣ ትዕግሥትና ፍትሕ በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ከዚህም ሌላ ገደብ የለሽ ኃይሉን በብዙ መንገዶች አሳይቷል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ ፍቅሩን የሚያሳዩ ናቸው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ስሙን ለመቀደስ የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰዱን አላቆመም።
15. ሰይጣን በዛሬው ጊዜ የአምላክን ስም እያጠፋ ያለው እንዴት ነው? ይህስ ምን አስከትሏል?
15 ሰይጣን በዛሬው ጊዜም የይሖዋን ስም እያጠፋ ነው። አምላክ ኃያል፣ ፍትሐዊ፣ ጥበበኛና አፍቃሪ መሆኑን እንዲጠራጠሩ በማድረግ ሰዎችን ያታልላቸዋል። ለምሳሌ ሰይጣን፣ ይሖዋ ፈጣሪ እንዳልሆነ ሰዎችን ለማሳመን ይጥራል። በአምላክ መኖር የሚያምኑ ሰዎችን ደግሞ አምላክም ሆነ መሥፈርቶቹ ከልክ በላይ
ጥብቅና ምክንያታዊነት የጎደላቸው እንደሆኑ ለማሳመን ይሞክራል። ይባስ ብሎም፣ ይሖዋ ሰዎችን በገሃነመ እሳት የሚያቃጥል ጨካኝና ርኅራኄ የሌለው አምላክ እንደሆነ ሰይጣን ያስተምራል። ሰዎች እንዲህ ያለውን ውሸት ማመናቸው ቀጣዩን እርምጃ ወደ መውሰድ ይኸውም በይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ላይ ወደ ማመፅ ይመራቸዋል። ሰይጣን ሙሉ በሙሉ ድል እስኪደረግ ድረስ የስም ማጥፋት ዘመቻውን ይገፋበታል፤ አንተንም በአምላክ ላይ እንድታምፅ ለማድረግ መሞከሩ አይቀርም። ታዲያ ይሳካለት ይሆን?ወሳኝ በሆነው ጉዳይ ላይ ያለህ ሚና
16. አዳምና ሔዋን ሳያደርጉ የቀሩትን የትኛውን ነገር የማድረግ አጋጣሚ አለህ?
16 ይሖዋ፣ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ስሙን በመቀደስ ረገድ ድርሻ እንዲኖራቸው ፈቅዷል። በመሆኑም አንተም፣ አዳምና ሔዋን ሳያደርጉ የቀሩትን ነገር የማድረግ አጋጣሚ አለህ። የምንኖረው የይሖዋን ስም የሚያጠፉና የሚሳደቡ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ቢሆንም ከይሖዋ ጎን በመቆም እውነቱን መናገር ትችላለህ፤ ይሖዋ ቅዱስ፣ ጻድቅ፣ ጥሩና አፍቃሪ አምላክ መሆኑን መናገር ትችላለህ። (ኢሳ. 29:23) በተጨማሪም የይሖዋን አገዛዝ መደገፍ ትችላለህ። በጽድቅ ላይ የተመሠረተው እንዲሁም ለፍጥረታት ሁሉ ሰላምና ደስታ የሚያስገኘው የይሖዋ አገዛዝ ብቻ እንደሆነ መግለጽ ትችላለህ።—መዝ. 37:9, 37፤ 146:5, 6, 10
17. ኢየሱስ የአባቱን ስም ያሳወቀው እንዴት ነው?
17 ለይሖዋ ስም ጥብቅና ስንቆም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እየተከተልን ነው። (ዮሐ. 17:26) ኢየሱስ የአባቱን ስም ያሳወቀው፣ በስሙ በመጠቀም ብቻ ሳይሆን ሰዎች ስለ አባቱ ትክክለኛ ማንነት እንዲያውቁ በማድረግም ነው። ለምሳሌ ይሖዋን ጨካኝ፣ ከፍጥረታቱ ብዙ የሚጠብቅ፣ የማይቀረብና ምሕረት የለሽ አምላክ አድርገው የሚያቀርቡትን ፈሪሳውያን አውግዟቸዋል። አባቱ ምክንያታዊ፣ ትዕግሥተኛ፣ አፍቃሪና ይቅር ባይ አምላክ መሆኑን እንዲያስተውሉ ሰዎችን ረድቷል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ በማንጸባረቅ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ አድርጓል።—ዮሐ. 14:9
18. ስለ ይሖዋ የሚነገሩትን ውሸቶች ማጋለጥ የምንችለው እንዴት ነው?
18 እኛም እንደ ኢየሱስ ስለ ይሖዋ የምናውቀውን ነገር ለሌሎች መናገር ይኸውም ይሖዋ በጣም አፍቃሪና ደግ አምላክ እንደሆነ ሰዎችን ማስተማር እንችላለን። ይህን ስናደርግ ስለ ይሖዋ የሚነገሩትን ውሸቶች እናጋልጣለን። ሰዎች የይሖዋን ስም ቅዱስ አድርገው እንዲመለከቱት በመርዳት ስሙን እንቀድሳለን። በተጨማሪም ኤፌ. 5:1, 2) በአነጋገራችንም ሆነ በድርጊታችን የይሖዋን ባሕርያት የምናንጸባርቅ ከሆነ ሰዎች፣ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ መመልከት ይችላሉ፤ በዚህ መንገድ ስሙ እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እናበረክታለን። ሰዎች ስለ አምላክ ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያስተካክሉ ስንረዳ ስሙ ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን ወይም ትክክለኛነቱ እንዲረጋገጥ እናደርጋለን። * በተጨማሪም ፍጹማን ያልሆኑ የሰው ልጆች ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ እናረጋግጣለን።—ኢዮብ 27:5
ይሖዋን መምሰል እንችላለን። ፍጹማን ባንሆንም እንኳ እንዲህ ማድረግ እንችላለን። (19. በኢሳይያስ 63:7 መሠረት ሰዎችን የምናስተምርበት ዋነኛ ዓላማ ምን ሊሆን ይገባል?
19 የይሖዋ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችልበትን ሌላም መንገድ እንመልከት። ለሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ስናስተምር ብዙ ጊዜ ጎላ አድርገን የምንገልጸው የአምላክን ሉዓላዊነት ይኸውም ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን የመግዛት መብት ያለው መሆኑን ነው፤ ደግሞም ይህ እውነት ነው። ሰዎችን ስለ አምላክ ሕግጋት ማስተማራችን አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ዓላማችን ሰዎች አባታችንን ይሖዋን እንዲወዱትና ለእሱ ታማኝ እንዲሆኑ መርዳት ነው። ለዚህ ሲባል የይሖዋን ተወዳጅ ባሕርያት ጎላ አድርገን መግለጽ ያስፈልገናል፤ ይሖዋ በሚለው ስም የሚጠራውን አምላክ ማንነት እንዲያውቁ መርዳት ይኖርብናል። (ኢሳይያስ 63:7ን አንብብ።) በዚህ መንገድ ስናስተምር ሰዎች፣ ይሖዋን እንዲወዱትና ለእሱ ባላቸው ታማኝነት ተነሳስተው እሱን እንዲታዘዙት መርዳት እንችላለን።
20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
20 ታዲያ ምግባራችንና የምናስተምረው ነገር የይሖዋን ስም የሚያስከብር እንዲሁም ሌሎች ወደ እሱ እንዲሳቡ የሚያደርግ እንዲሆን ምን ማድረግ እንችላለን? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።
መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው
^ አን.5 የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታትን ሁሉ የሚመለከት ምን ወሳኝ ጉዳይ ተነስቷል? ይህ ጉዳይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው? በዚህ ጉዳይ ውስጥ የእኛ ሚና ምንድን ነው? የእነዚህንና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ጥያቄዎችን መልስ ማወቃችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር ይረዳናል።
^ አን.18 የይሖዋ ስም ትክክለኛነት መረጋገጥ እንደማያስፈልገው በጽሑፎቻችን ላይ የተገለጸባቸው ጊዜያት አሉ፤ ለዚህ ምክንያት ሆኖ የቀረበው፣ ይሖዋ በዚህ ስም የመጠራት መብት ያለው ስለ መሆኑ ጥያቄ አለመነሳቱ ነው። ሆኖም በ2017 በተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ግንዛቤያችንን የሚያስተካክል ሐሳብ ቀርቦ ነበር። የስብሰባው ሊቀ መንበር እንዲህ ብሏል፦ “በአጭር አነጋገር የይሖዋ ስም ትክክለኛነት እንዲረጋገጥ መጸለያችን ስህተት አይደለም። ምክንያቱም ይሖዋ ያተረፈው ስም ከነቀፋ ነፃ መውጣት አለበት።”—የጥር 2018 ብሮድካስቲንግን jw.org® ላይ ተመልከት፤ ላይብረሪ > JW ብሮድካስቲንግ በሚለው ሥር ይገኛል።