ወጣቶች፣ እርካታ ያለው ሕይወት መምራት ትችላላችሁ
“የሕይወትን መንገድ አሳወቅከኝ።”—መዝ. 16:11
1, 2. የቶኒ ተሞክሮ እንደሚያሳየው አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ምን ዓይነት ለውጥ ሊያደርግ ይችላል?
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆነው ቶኒ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተቃርቦ ነበር። ያለአባት ያደገው ይህ ልጅ ለትምህርት ያን ያህል ፍላጎት አልነበረውም፤ ቅዳሜና እሁድን የሚያሳልፈው ፊልም በማየት ወይም ከጓደኞቹ ጋር በመዝናናት ነበር። ዓመፀኛ ወይም የዕፅ ሱሰኛ ባይሆንም በሕይወቱ ውስጥ ምንም ዓላማ አልነበረውም። በተጨማሪም አምላክ መኖሩን ይጠራጠር ነበር። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክር ከሆኑ አንድ ባልና ሚስት ጋር ተገናኘ። ለእነዚህ ባልና ሚስት በውስጡ ስላደሩበት ጥርጣሬዎች ነገራቸው፤ እንዲሁም የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠየቃቸው። እነሱም የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች እና ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የሚሉትን ሁለት ብሮሹሮች ሰጡት።
2 ባልና ሚስቱ በሚቀጥለው ጊዜ ተመልሰው ሲሄዱ የቶኒ አመለካከት ተቀይሮ ነበር። ብሮሹሮቹን ደጋግሞ ከማንበቡ የተነሳ ብሮሹሮቹ ተሻሽተውና ተጨማደው ነበር። ቶኒ ባልና ሚስቱን “አምላክ መኖር አለበት” አላቸው። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማ ሲሆን ቀስ በቀስ ለሕይወት ያለው አመለካከት እየተለወጠ ሄደ። በትምህርቱ መጥፎ ውጤት ያመጣ የነበረው ቶኒ በትምህርት ቤቱ ካሉት ጎበዝ ተማሪዎች መካከል አንዱ ሆነ። ሌላው ቀርቶ ርዕሰ መምህሩ እንኳ በጣም ተገርሞ “በአመለካከትህ ላይ ትልቅ ለውጥ አድርገሃል፤ የትምህርት ውጤትህም በጣም ተሻሽሏል” አለው። አክሎም “እንዲህ ያለ ለውጥ ያደረግከው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብረህ መሆን ከጀመርክ በኋላ ነው?” በማለት ጠየቀው። ቶኒም ‘አዎ’ ካለው በኋላ አጋጣሚውን ተጠቅሞ መሠከረለት። ቶኒ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚና መዝ. 68:5
የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። በተጨማሪም እንደ ይሖዋ ያለ አፍቃሪ አባት በማግኘቱ ደስተኛ ነው።—ይሖዋን ከታዘዛችሁ ስኬታማ ትሆናላችሁ
3. ይሖዋ ለወጣቶች ምን ምክር ሰጥቷቸዋል?
3 የቶኒ ተሞክሮ፣ ይሖዋ በመካከላችን ላላችሁት ወጣቶች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳያል። አምላክ እውነተኛ ስኬትና እርካታ እንድታገኙ ይፈልጋል። በመሆኑም “በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ” የሚል ምክር ሰጥቷችኋል። (መክ. 12:1) ሆኖም በዛሬው ጊዜ ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ተፈታታኝ ነው። ፈጽሞ የማይቻል ነገር ግን አይደለም። በአምላክ እርዳታ ወጣት እያላችሁ ብቻ ሳይሆን ሕይወታችሁን በሙሉ ስኬታማ መሆን ትችላላችሁ። የዚህን እውነተኝነት ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር መቆጣጠር የቻሉት እንዲሁም ዳዊት ግዙፉን ጎልያድን ድል ማድረግ የቻለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።
4, 5. እስራኤላውያን ከነአንን ድል ካደረጉበት መንገድና ዳዊት ጎልያድን ካሸነፈበት መንገድ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ሥዕሎች ተመልከት።)
4 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲቃረቡ አምላክ የውጊያ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ወይም ለጦርነት እንዲሠለጥኑ አላዘዛቸውም። (ዘዳ. 28:1, 2) ከዚህ ይልቅ ትእዛዛቱን መጠበቅና በእሱ መታመን እንደሚያስፈልጋቸው ነግሯቸዋል። (ኢያሱ 1:7-9) ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ይህ ሞኝነት ይመስል ነበር። ሆኖም ምክሩ ከሁሉ የተሻለ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሕዝቦቹ በከነአናውያን ላይ ተከታታይ ድል እንዲጎናጸፉ ረድቷቸዋል። (ኢያሱ 24:11-13) አዎ፣ አምላክን መታዘዝ እምነት የሚጠይቅ ነገር ቢሆንም እንዲህ ያለው እምነት ምንጊዜም ለስኬት ያበቃል። ይህ እውነታ መቼም ቢሆን አይለወጥም። በጥንት ጊዜ ይሠራ እንደነበር ሁሉ ዛሬም ይሠራል።
5 ኃያል ተዋጊ የነበረው ጎልያድ ቁመቱ 2.9 ሜትር ሲሆን የተሟላ የጦር ትጥቅ ነበረው። (1 ሳሙ. 17:4-7) ዳዊት ግን ከወንጭፍና በአምላኩ በይሖዋ ላይ ካለው እምነት በቀር ምንም ነገር አልነበረውም። እምነት የሌላቸው ሰዎች ዳዊትን እንደ ሞኝ ቆጥረውት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ምንኛ ተሳስተዋል! ሞኝ የነበረው ጎልያድ ነው።—1 ሳሙ. 17:48-51
6. ከዚህ ቀጥሎ የትኞቹን ነገሮች እንመለከታለን?
6 ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ በሕይወታችን ደስተኛና ስኬታማ እንድንሆን የሚረዱንን አራት ነገሮች ተመልክተናል። እነሱም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማሟላት፣ አምላክን ከሚወዱ ጋር ጓደኝነት መመሥረት፣ ጠቃሚ ግቦችን ማውጣትና አምላክ የሰጠንን ነፃነት ከፍ አድርጎ መመልከት ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ፣ በመዝሙር 16 ላይ የሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶች እነዚህን አራት ነገሮች ለማድረግ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
መንፈሳዊ ፍላጎታችሁን አሟሉ
7. (ሀ) መንፈሳዊ ሰው የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው? (ለ) የዳዊት “ድርሻ” ምን ነበር? ይህስ ምን እንዲሰማው አድርጓል?
7 መንፈሳዊ ሰው በአምላክ ላይ እምነት ያለው ከመሆኑም ሌላ ነገሮችን የሚመለከተው በአምላክ ዓይን ነው። የአምላክን አመራር ለማግኘትና በማንኛውም ሁኔታ ሥር እሱን ለመታዘዝ ጥረት ያደርጋል። (1 ቆሮ. 2:12, 13) ዳዊት በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። “ይሖዋ ድርሻዬ፣ ዕጣ ፋንታዬና ጽዋዬ ነው” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 16:5) የዳዊት “ድርሻ” መጠጊያው ከሆነው ከይሖዋ ጋር የመሠረተውን ጥሩ ዝምድና ያካትታል። (መዝ. 16:1) ዳዊት ከአምላክ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና መመሥረቱ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል? “ሁለንተናዬ ደስ ይለዋል” በማለት ጽፏል። አዎ፣ ለዳዊት ከምንም በላይ ደስታ የሚሰጠው ነገር ከአምላክ ጋር የመሠረተው የቀረበ ዝምድና ነበር።—መዝሙር 16:9, 11ን አንብብ።
8. እውነተኛ እርካታ ያለው ሕይወት ለመምራት አስተዋጽኦ የሚያደርጉት አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
8 ሥጋዊ ደስታን በማሳደድና ቁሳዊ ሀብትን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች ዳዊት የነበረው ዓይነት ደስታ ሊኖራቸው አይችልም። (1 ጢሞ. 6:9, 10) በካናዳ የሚኖር አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እውነተኛ እርካታ የሚያመጣልን በሕይወታችን ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን ማግኘታችን ሳይሆን የመልካም ስጦታ ሁሉ ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ መስጠታችን ነው።” (ያዕ. 1:17) ወጣቶች፣ በይሖዋ ላይ እምነት ማዳበራችሁ እንዲሁም እሱን ማገልገላችሁ ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራትና እርካታ ለማግኘት ይረዳችኋል። ታዲያ በይሖዋ ላይ ያላችሁን እምነት ማሳደግ የምትችሉት እንዴት ነው? ከእሱ ጋር ጊዜ በማሳለፍ ማለትም ቃሉን በማንበብ፣ የፍጥረት ሥራዎቹን በመመልከትና ለእናንተ ያሳየውን ፍቅር ጨምሮ በተለያዩ ባሕርያቱ ላይ በማሰላሰል ነው።—ሮም 1:20፤ 5:8
9. ልክ እንደ ዳዊት የአምላክ ቃል እንዲቀርጻችሁ መፍቀድ የምትችሉት እንዴት ነው?
9 አንዳንድ ጊዜ አምላክ ለእኛ ያለውን አባታዊ ፍቅር የሚያሳየው በሚሰጠን እርማት በኩል ነው። ዳዊት እንዲህ ያለውን ደግነት የተንጸባረቀበት ምክር በፈቃደኝነት ተቀብሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ምክር የሰጠኝን ይሖዋን አወድሳለሁ። በሌሊትም እንኳ በውስጤ ያለው ሐሳብ ያርመኛል።” (መዝ. 16:7) ዳዊት በአምላክ ማሳሰቢያዎች ላይ ያሰላስል ነበር፤ በተጨማሪም የአምላክን አስተሳሰብ ለማዳበርና በእሱ አስተሳሰብ ለመቀረጽ ጥረት ያደርግ ነበር። እናንተም እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ለአምላክ ያላችሁ ፍቅርና እሱን ለመታዘዝ ያላችሁ ፍላጎት ይጨምራል። ከዚህም በላይ መንፈሳዊ ጉልምስናና ብስለት ይኖራችኋል። ክሪስቲን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ምርምር ሳደርግና ባነበብኩት ነገር ላይ ሳሰላስል ይሖዋ ያን ሐሳብ ያጻፈው ለእኔ ብሎ እንደሆነ ይሰማኛል!”
10. ኢሳይያስ 26:3 ላይ እንደተገለጸው መንፈሳዊ አመለካከት መያዝ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?
10 መንፈሳዊ አመለካከት መያዛችሁ የምንኖርበትን ዓለምና ወደፊት የሚጠብቁትን ነገሮች በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት እይታ እንዲኖራችሁ ያስችላችኋል፤ ይህም የላቀ እውቀትና ማስተዋል ያላችሁ ሰዎች እንድትሆኑ ይረዳችኋል። አምላክ እንዲህ ያለ እውቀትና ማስተዋል የሚሰጣችሁ ለምንድን ነው? በሕይወታችሁ ውስጥ ተገቢ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ እንድትሰጡ፣ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች እንድታደርጉና የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድትጠባበቁ ስለሚፈልግ ነው። (ኢሳይያስ 26:3ን አንብብ።) በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ጆሹዋ የተባለ ወንድም “ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት ለነገሮች ተገቢውን አመለካከት ለመያዝ ይረዳል” በማለት ተናግሯል። በእርግጥም እንዲህ ያለው ሕይወት እውነተኛ እርካታ ያስገኛል!
እውነተኛ ጓደኞችን አፍሩ
11. ዳዊት እንደተናገረው እውነተኛ ጓደኞችን ለማግኘት ቁልፉ ምንድን ነው?
11 መዝሙር 16:3ን አንብብ። ዳዊት እውነተኛ ጓደኞችን ለማግኘት ቁልፉ ምን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር መሆን ‘እጅግ ደስ ያሰኘው’ ነበር። “ቅዱሳን” ተብለው የተገለጹት እነዚህ ሰዎች በሥነ ምግባር ንጹሕና ነቀፋ የሌለባቸው ናቸው። አንድ ሌላ መዝሙራዊም ስለ ጓደኛ ምርጫ ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው። “አንተን ለሚፈሩ ሁሉ፣ መመሪያዎችህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 119:63) ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው እናንተም ይሖዋን ከሚፈሩና ከሚታዘዙ አገልጋዮቹ መካከል በርካታ ጥሩ ጓደኞችን ማግኘት ትችላላችሁ። እነዚህ ሰዎች በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግልጽ ነው።
12. በዳዊትና በዮናታን መካከል ለነበረው ጓደኝነት መሠረት የሆነው ነገር ምንድን ነው?
12 መዝሙራዊው ዳዊት ጓደኝነት የመሠረተው ከእኩዮቹ ጋር ብቻ አልነበረም። ‘ክብር ከተላበሱት አገልጋዮች’ መካከል የዳዊት የቅርብ ወዳጅ የነበረው ማን እንደሆነ ታስታውሳላችሁ? ዮናታን ነው። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት በጣም ጠንካራ የሆኑ ወዳጅነቶች መካከል አንዱ በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረው ወዳጅነት ነው። ይሁንና ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ገደማ ይበልጠው እንደነበር ታውቃላችሁ? ታዲያ ለጓደኝነታቸው መሠረት የሆነው ነገር ምንድን ነው? በአምላክ ላይ ያላቸው እምነት፣ እርስ በርስ የነበራቸው አክብሮትና የአምላክን ጠላቶች በተፋለሙበት ወቅት አንዳቸው የሌላውን ድፍረት መመልከታቸው ነው።—1 ሳሙ. 13:3፤ 14:13፤ 17:48-50፤ 18:1
13. ከተለያዩ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መመሥረት የምትችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጡ።
13 እናንተም ልክ እንደ ዳዊትና ዮናታን ይሖዋን ከሚወዱና በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት በመመሥረት ‘እጅግ ደስ መሰኘት’ ትችላላችሁ። ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ያገለገለችው ኪራ እንዲህ ብላለች፦ “ከእኔ የተለየ አስተዳደግና ባሕል ካላቸው በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መመሥረት ችያለሁ።” እናንተም በዚህ መልኩ ፍቅራችሁን የምታሰፉ ከሆነ የአምላክ ቃልና ቅዱስ
መንፈሱ በአምላክ ሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲሰፍን የማድረግ ኃይል እንዳላቸው በግልጽ መመልከት ትችላላችሁ።ጠቃሚ ግቦችን አውጡ
14. (ሀ) በሕይወታችሁ ውስጥ ጠቃሚ ግቦችን ለማውጣት የሚረዳችሁ ምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ወጣቶች መንፈሳዊ ግብ ማውጣትን በተመለከተ ምን አስተያየት ሰጥተዋል?
14 መዝሙር 16:8ን አንብብ። ዳዊት በአምላክ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመራ ነበር። እናንተም በሕይወታችሁ ውስጥ ለይሖዋ አገልግሎት ምንጊዜም ቅድሚያ የምትሰጡ ከሆነና የእሱን ፈቃድ ግምት ውስጥ ያስገቡ ግቦችን የምታወጡ ከሆነ እውነተኛ እርካታ ማግኘት ትችላላችሁ። ስቲቨን የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣሬ፣ እዚያ ግብ ላይ መድረሴና ያደረግኳቸውን ማሻሻያዎች መለስ ብዬ ማሰቤ እርካታ ያስገኝልኛል።” በአሁኑ ጊዜ በሌላ አገር እያገለገለ ያለ አንድ ጀርመናዊ ወጣት ደግሞ “ካረጀሁ በኋላ ሕይወቴን መለስ ብዬ ስመለከት፣ ያደረግኩት ነገር ሁሉ በራሴ ዙሪያ ያጠነጠነ እንደነበር እንዲሰማኝ አልፈልግም” በማለት ተናግሯል። እናንተም ተመሳሳይ አመለካከት እንደሚኖራችሁ ተስፋ እናደርጋለን። እንግዲያው ተሰጥኦዋችሁን አምላክን ለማክበርና ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ተጠቀሙበት። (ገላ. 6:10) መንፈሳዊ ግቦች አውጡ፤ በተጨማሪም ግቦቻችሁ ላይ ለመድረስ እንዲረዳችሁ ይሖዋን በጸሎት ጠይቁት። ይሖዋ እንዲህ ላሉ ጸሎቶች መልስ መስጠት ያስደስተዋል።—1 ዮሐ. 3:22፤ 5:14, 15
15. በግለሰብ ደረጃ ምን ዓይነት ግብ ልታወጡ ትችላላችሁ? (“ ሊደረስባቸው የሚችሉ አንዳንድ ግቦች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
15 ምን ዓይነት ግቦችን ልታወጡ ትችላላችሁ? ለምሳሌ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በራሳችሁ አባባል ሐሳብ ለመስጠት፣ አቅኚ ሆናችሁ ለማገልገል፣ ቤቴል ለመግባት ወይም አዲስ ቋንቋ ተምራችሁ የውጭ አገር ቋንቋ በሚነገርበት ክልል ውስጥ ለማገልገል ግብ ልታወጡ ትችላላችሁ። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ ባራክ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በየቀኑ ከእንቅልፌ ስነሳ ሙሉ ኃይሌን ለይሖዋ እየሰጠሁት እንዳለ ይሰማኛል፤ እንዲህ ያለ ስሜት እንዲሰማኝ የሚያደርግ ሌላ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም።”
አምላክ የሰጣችሁን ነፃነት ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ
16. ዳዊት ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ምን አመለካከት ነበረው? ለምንስ?
16 መዝሙር 16:2, 4ን አንብብ። ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው በአምላክ የጽድቅ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት እውነተኛ ነፃነት ያስገኝልናል፤ እነዚህ መመሪያዎች መልካም የሆነውን እንድንወድና ክፉ የሆነውን እንድንጠላ ያሠለጥኑናል። (አሞጽ 5:15) መዝሙራዊው ዳዊት ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “ለእኔ የጥሩ ነገሮች ምንጭ አንተ ነህ” ብሏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጥሩነት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የላቀ ሥነ ምግባርንና በጎነትን ለማመልከትም ይሠራበታል። ይሖዋ የሚያደርገው ማንኛውም ነገር ጥሩነት የሚንጸባረቅበት ከመሆኑም ሌላ ያሉንን ጥሩ ነገሮች ሁሉ ያገኘነው ከእሱ ነው። ዳዊት አምላኩን ለመምሰል ማለትም የእሱን ጥሩነት ለማንጸባረቅ ጥረት ያደርግ ነበር። በተጨማሪም በአምላክ ዓይን መጥፎ ለሆኑ ነገሮች ጥላቻ አዳብሯል። ይህም የሰው ልጆችን የሚያዋርደውንና ለይሖዋ የሚገባው ክብር እንዳይሰጠው የሚያደርገውን ጣዖት አምልኮን መጸየፍን ይጨምራል።—ኢሳ. 2:8, 9፤ ራእይ 4:11
17, 18. (ሀ) ዳዊት በሐሰት አምልኮ መካፈል የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ምን አስተውሏል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ‘ሐዘናቸውን እያበዙ’ ያሉት እንዴት ነው?
17 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሐሰት አምልኮ አብዛኛውን ጊዜ ልቅ የሆነ የፆታ ብልግናን ያካተተ ነበር። (ሆሴዕ 4:13, 14) በርካታ ሰዎች ኃጢአተኛ ለሆነው ሥጋቸው ማራኪ በሆነው እንዲህ ባለው አምልኮ መካፈል ያስደስታቸው ነበር። ሆኖም ይህ ዘላቂ ደስታ አላስገኘላቸውም። እንዲያውም ውጤቱ ፍጹም ተቃራኒ ነበር! ዳዊት “ሌሎች አማልክትን የሚከተሉ ሐዘናቸውን ያበዛሉ” በማለት ተናግሯል። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ልጆችም በእነሱ ምክንያት ለአሰቃቂ መከራ ተዳርገዋል። (ኢሳ. 57:5) ይሖዋ እንዲህ ያለውን የጭካኔ ድርጊት ይጸየፋል! (ኤር. 7:31) እናንተ በዚያ ዘመን ብትኖሩ ኖሮ በይሖዋ ላይ እምነት ያላቸውና እሱን የሚታዘዙ ወላጆች ስላሏችሁ በጣም አመስጋኝ እንደምትሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
18 በዘመናችንም ቢሆን አብዛኞቹ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች የፆታ ብልግናን አልፎ ተርፎም ግብረ ሰዶማዊነትን በቸልታ ያልፋሉ። ሆኖም ሰዎች ሥነ ምግባራዊ ነፃነት ብለው የሚያስቡት አካሄድ ያስከተለው ውጤት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው። (1 ቆሮ. 6:18, 19) እንዲህ ያለ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች ‘ሐዘናቸውን እያበዙ’ እንዳሉ እናንተም ሳታስተውሉ አትቀሩም። እንግዲያው ወጣቶች፣ በሰማይ ያለው አባታችሁ የሚላችሁን ስሙ። እሱን መታዘዛችሁ ራሳችሁን የሚጠቅማችሁ እንዴት እንደሆነ በሚገባ አስቡ። መጥፎ ድርጊት መፈጸም የሚያስከትለውን መዘዝ ለማጤን ሞክሩ፤ ደግሞም መጥፎ ድርጊት መፈጸም የሚያስገኘው ጊዜያዊ ደስታ ድርጊቱ ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም። (ገላ. 6:8) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆሹዋ “ነፃነታችንን በፈለግነው መንገድ መጠቀም እንችላለን፤ ነፃነታችንን አላግባብ መጠቀማችን ግን እርካታ አያስገኝልንም” ብሏል።
19, 20. በይሖዋ የሚታመኑና እሱን የሚታዘዙ ወጣቶች ምን በረከቶች ያገኛሉ?
19 ኢየሱስ ተከታዮቹን “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 8:31, 32) ኢየሱስ የጠቀሰው ነፃነት ከሐሰት ሃይማኖት፣ ከመንፈሳዊ ድንቁርናና ከአጉል እምነት ነፃ መውጣትን ይጨምራል። ከዚህም በላይ ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ይሖዋ ወደፊት የሚሰጠንን “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ያካትታል። (ሮም 8:21) በዛሬው ጊዜም እንኳ ‘የክርስቶስን ቃል’ ወይም ትምህርቶች ‘ጠብቀን በመኖር’ ይህን ነፃነት ማጣጣም እንችላለን። በዚህ መንገድ፣ በትምህርት ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግም ጭምር ‘እውነትን ማወቅ’ እንችላለን።
20 እናንት ወጣቶች፣ አምላክ የሰጣችሁን ነፃነት ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ። ይህን ነፃነት ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ በመጠቀም ለወደፊቱ ጊዜ ጥሩ መሠረት ጣሉ። አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ወጣት ሳላችሁ ነፃነታችሁን በጥበብ መጠቀማችሁ ወደፊት ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ስታደርጉ ለምሳሌ ተስማሚ ሥራ ስትፈልጉ አሊያም ‘ትዳር ልመሥርት ወይስ ለተወሰነ ጊዜ ሳላገባ ልቆይ?’ የሚለውን ጉዳይ ስትወስኑ ይጠቅማችኋል።”
21. “እውነተኛ [ወደሆነው] ሕይወት” በሚመራው ጎዳና ላይ መጓዛችሁን መቀጠል የምትችሉት እንዴት ነው?
21 በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ ስኬታማ የሚባለው ሕይወት እንኳ አጭር ከመሆኑም በላይ አስተማማኝ አይደለም። ነገ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም። (ያዕ. 4:13, 14) ስለዚህ “እውነተኛ [ወደሆነው] ሕይወት” ማለትም ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው ጎዳና ላይ መጓዛችንን መቀጠላችን ጥበብ ነው። (1 ጢሞ. 6:19) አምላክ በዚህ ጎዳና ላይ እንድንሄድ እንደማያስገድደን የታወቀ ነው። ምርጫውን ማድረግ ያለብን እኛው ራሳችን ነን። እንግዲያው ወጣቶች፣ ይሖዋን ‘ድርሻችሁ’ አድርጉ። እሱ የሰጣችሁን “መልካም ነገሮች” ከፍ አድጋችሁ ተመልከቱ። (መዝ. 103:5) እንዲሁም ይሖዋ ‘ለዘላለም ብዙ ደስታ’ እንደሚሰጣችሁ እምነት ይኑራችሁ።—መዝ. 16:11