“በእውነትህ እሄዳለሁ”
“ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረኝ። በእውነትህ እሄዳለሁ።”—መዝ. 86:11
1-3. (ሀ) ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? በምሳሌ አስረዳ። (በመግቢያው ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
በበርካታ አገሮች አንድን የተገዛ ዕቃ መመለስ የተለመደ ነገር ነው። ግምታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአንዳንድ አገሮች ገዢዎች ወደ መደብር ሄደው ከገዟቸው ዕቃዎች መካከል ዘጠኝ በመቶ የሚያህሉትን ይመልሳሉ። በኢንተርኔት አማካኝነት ከገዟቸው ዕቃዎች መካከል ደግሞ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑትን ይመልሳሉ። ሰዎች የገዙትን ዕቃ የሚመልሱት ዕቃውን እንደጠበቁት ሆኖ ስላላገኙት፣ ጉድለት ስላለበት ወይም ስላልወደዱት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ዕቃው እንዲቀየርላቸው ወይም ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው ይጠይቃሉ።
2 የገዛነውን ዕቃ በመመለስ ገንዘባችንን መቀበል እንችል ይሆናል። ከእውነት ጋር በተያያዘ ግን እንዲህ ማድረግ አንፈልግም። ‘የገዛነውን’ እውነት ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርነውን “ትክክለኛ እውቀት” ለመመለስ ወይም ‘ለመሸጥ’ ፈጽሞ ፈቃደኞች አይደለንም። (ምሳሌ 23:23ን አንብብ፤ 1 ጢሞ. 2:4) ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው እውነትን ለመግዛት ስንል ጊዜያችንን መሥዋዕት አድርገናል። በተጨማሪም ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝልንን ሥራና ከሌሎች ጋር የነበረንን ጥሩ ግንኙነት መሥዋዕት ማድረግ እንዲሁም አስተሳሰባችንንና ምግባራችንን መለወጥ አልፎ ተርፎም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕሎችንና ልማዶችን መተው አስፈልጎናል። ሆኖም የከፈልነው ዋጋ ካገኘነው በረከት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
3 ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለን አመለካከት ኢየሱስ በተናገረው አጭር ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሰው ካለው አመለካከት ጋር ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ ስለ ማቴ. 13:45, 46) በተመሳሳይም ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን እውነት ጨምሮ ከአምላክ ቃል ላይ የተማርናቸው ውድ እውነቶች በሙሉ ለእኛ በጣም ከፍተኛ ዋጋ አላቸው፤ በመሆኑም እነዚህን እውነቶች ለማግኘት ስንል ወዲያውኑ አስፈላጊውን መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች ሆነናል። እውነትን ከፍ አድርገን መመልከታችንን እስከቀጠልን ድረስ ፈጽሞ ‘አንሸጠውም።’ የሚያሳዝነው ግን ከአምላክ ሕዝቦች መካከል አንዳንዶቹ እውነት ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳለው የዘነጉ ከመሆኑም በላይ እውነትን ሸጠውታል። እኛ ግን እንዲህ ያለ ነገር ማድረግ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው! እውነትን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተውና ፈጽሞ ልንሸጠው እንደማንፈልግ ለማሳየት ‘በእውነት ውስጥ ተመላለሱ’ የሚለውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። (3 ዮሐንስ 2-4ን አንብብ።) በእውነት መመላለስ ማለት በሕይወታችን ውስጥ ለእውነት ቅድሚያ መስጠትና ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ማለት ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን፦ አንዳንዶች እውነትን ‘የሸጡት’ ለምን እና እንዴት ነው? እንዲህ ያለውን አሳዛኝ ስህተት ከመሥራት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? ‘በእውነት ውስጥ ለመመላለስ’ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
አምላክ መንግሥት የሚገልጸው እውነት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ለማሳየት ጥሩ ዕንቁ ሲፈልግ ቆይቶ መጨረሻ ላይ ያገኘን አንድ ተጓዥ ነጋዴ ምሳሌ ሰጥቷል። ነጋዴው ያገኘው ዕንቁ በጣም ከፍተኛ ዋጋ ያለው ከመሆኑ የተነሳ ንብረቱን ሁሉ “ወዲያውኑ በመሸጥ” ዕንቁውን ገዝቶታል። (አንዳንዶች እውነትን ‘የሸጡት’ ለምን እና እንዴት ነው?
4. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እውነትን ‘የሸጡት’ ለምንድን ነው?
4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ለኢየሱስ ትምህርቶች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር፤ በኋላ ላይ ግን በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን አልቀጠሉም። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስ እጅግ ብዙ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከመገበ በኋላ ሰዎቹ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተከትለውት ሄዱ። ከዚያም ኢየሱስ “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም” በማለት የሚያስደነግጥ ነገር ተናገረ። ሰዎቹ ኢየሱስ ጉዳዩን እንዲያብራራላቸው ከመጠየቅ ይልቅ በተናገረው ነገር ተሰናከሉ፤ እንዲያውም “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” በማለት ተናገሩ። በውጤቱም “ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ትተውት ወደነበረው ነገር ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እሱን መከተላቸውን አቆሙ።”—ዮሐ. 6:53-66
5, 6. (ሀ) በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ሰዎች ከእውነት ጎዳና የራቁት ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው ቀስ በቀስ ከእውነት ሊወሰድ የሚችለው እንዴት ነው?
5 የሚያሳዝነው በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እውነትን አጥብቀው ሳይዙ ቀርተዋል። አንዳንዶቹ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በምንረዳበት መንገድ ላይ በተደረገው ማስተካከያ አሊያም ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ምክንያት ተሰናክለዋል። ሌሎቹ ደግሞ እውነትን የተዉት በተሰጣቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ቅር ስለተሰኙ ወይም በእነሱና በእምነት አጋራቸው መካከል አለመግባባት ስለተፈጠረ ነው። ከከሃዲዎች ወይም የምናምንባቸውን ነገሮች ከሚያጣምሙ ተቃዋሚዎች ጎን በመቆማቸው ምክንያት ከእውነት መንገድ የወጡ ክርስቲያኖችም አሉ። በዚህ መንገድ ሆን ብለው ከይሖዋና ከጉባኤው ‘ርቀዋል።’ (ዕብ. 3:12-14) እነዚህ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት ጠብቀው ቢቀጥሉ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! ኢየሱስ ሐዋርያቱን፣ እነሱም መሄድ ይፈልጉ እንደሆነ ሲጠይቃቸው ጴጥሮስ ወዲያውኑ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት መልሷል።—ዮሐ. 6:67-69
6 ሌሎች ደግሞ ከእውነት ጎዳና የሚወጡት ቀስ በቀስ ምናልባትም ሳይታወቃቸው ነው። የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ ቀስ በቀስ ከወደቡ እየራቀ ከሚሄድ ጀልባ ጋር ይመሳሰላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ሂደት ‘ቀስ በቀስ መወሰድ’ በማለት ይገልጸዋል። (ዕብ. 2:1) ቀስ በቀስ ከእውነት የሚወሰድ ሰው ከእውነት ከሚርቅ ሰው በተለየ መልኩ ይህን የሚያደርገው ሆን ብሎ አይደለም። ይሁንና እንዲህ ያለው ሰው ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና እንዲዳከም ውሎ አድሮም እንዲጠፋ ሊፈቅድ ይችላል። ታዲያ ይህ አስከፊ ሁኔታ እንዳይደርስብን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?
እውነትን እንዳንሸጥ ምን ሊረዳን ይችላል?
7. እውነትን ላለመሸጥ የሚረዳን የመጀመሪያው እርምጃ ምንድን ነው?
7 በእውነት ጎዳና ለመሄድ ይሖዋ የተናገራቸውን ነገሮች በሙሉ መቀበልና መታዘዝ አለብን። በሕይወታችን ውስጥ ለእውነት ቅድሚያውን መስጠትና አኗኗራችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ማስማማት ይኖርብናል። ንጉሥ ዳዊት “በእውነትህ እሄዳለሁ” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (መዝ. 86:11) ዳዊት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። እኛም በአምላክ እውነት መሄዳችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። አለዚያ ለእውነት ስንል በከፈልነው ዋጋ መቆጨት ልንጀምር አልፎ ተርፎም ከከፈልነው ነገር ላይ የተወሰነውን መልሰን ለመውሰድ ልንፈተን እንችላለን። በመሆኑም መላውን የእውነት ቃል አጥብቀን መያዛችን አስፈላጊ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መካከል የፈለግነውን ተቀብለን ያልፈለግነውን መተው እንደማንችል እንገነዘባለን። ምክንያቱም ይሖዋ ‘በእውነት ሁሉ’ እንድንሄድ ይጠብቅብናል። (ዮሐ. 16:13) እስቲ ለእውነት ስንል መሥዋዕት ያደረግናቸውን አምስት ነገሮች በድጋሚ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ከከፈልነው ነገር ላይ የተወሰነውን እንኳ መልሰን ላለመውሰድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።—ማቴ. 6:19
8. አንድ ክርስቲያን ጊዜውን በጥበብ አለመጠቀሙ ቀስ በቀስ ከእውነት እንዲወሰድ ሊያደርገው የሚችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
8 ጊዜ። ቀስ በቀስ ከእውነት እንዳንወሰድ ጊዜያችንን በጥበብ መጠቀም አለብን። ጠንቃቆች ካልሆንን በመዝናናት፣ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ እንቅስቃሴ በመካፈል፣ ኢንተርኔት በመቃኘት ወይም ቴሌቪዥን በመመልከት ከልክ ያለፈ ጊዜ ማሳለፍ ልንጀምር እንችላለን። እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም ቀደም ሲል ለግል ጥናትና ለሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እናውል የነበረውን ጊዜ ሊሻሙብን ይችላሉ። ኤማ * የተባለች እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ኤማ ከልጅነቷ ጀምሮ ፈረሶችን በጣም ትወድ ነበር። ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ፈረስ ትጋልብ ነበር። በኋላ ላይ ግን ፈረስ በመጋለብ ከልክ ያለፈ ጊዜ በማሳለፏ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማት ጀመር። በመሆኑም ለመዝናኛ በምታውለው ጊዜ ላይ ማስተካከያ አደረገች። በተጨማሪም ቀደም ሲል የፈረስ ግልቢያ ትርኢት ታሳይ የነበረችው የኮሪ ዌልስ ተሞክሮ በጣም አበረታታት። * በአሁኑ ጊዜ ኤማ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል እንዲሁም እንደ እሷ ይሖዋን ከሚያገለግሉ የቤተሰቧ አባላትና ጓደኞቿ ጋር አብራ ለመሆን የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት በመቻሏ ደስተኛ ነች። ከይሖዋ ጋር ይበልጥ እንደተቀራረበች የሚሰማት ከመሆኑም ሌላ ጊዜዋን በጥበብ እየተጠቀመችበት እንደሆነ በማወቋ ውስጣዊ ሰላም አግኝታለች።
9. አንዳንዶች ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ መስጠታቸው መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ እንዲሉ ያደረጋቸው እንዴት ነው?
9 ቁሳዊ ነገሮች። በእውነት ውስጥ መመላለሳችንን መቀጠል ከፈለግን ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ይኖርብናል። እውነትን ስንማር ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም እንዳለብን ተገንዝበናል። በእውነት ጎዳና ለመሄድ ስንል ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነናል። ከጊዜ በኋላ ግን ሌሎች ሰዎች ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ሲገዙ ወይም በገንዘባቸው አንዳንድ ነገሮችን ሲያደርጉ ስንመለከት ብዙ ነገር እንደቀረብን ይሰማን ይሆናል። በመሆኑም ባሉን መሠረታዊ ነገሮች ረክተን ከመኖር ይልቅ ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ስንል መንፈሳዊ ነገሮችን ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ ልንጀምር እንችላለን። እንዲህ ያለው አካሄድ የዴማስን ሁኔታ ያስታውሰናል። ዴማስ “በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት” መውደዱ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር የማገልገል መብቱን ትቶ እንዲሄድ አድርጎታል። (2 ጢሞ. 4:10) ዴማስ ጳውሎስን ትቶ የሄደው ለምንድን ነው? ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችን ስለወደደ ይሆን? አሊያም ከጳውሎስ ጋር ለማገልገል ሲል መሥዋዕት መክፈሉን ለመቀጠል ፈቃደኛ ስላልሆነ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ዴማስ ካጋጠመው ሁኔታ የምናገኘው ትምህርት አለ። እኛም ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር ዳግመኛ እንዳይቀጣጠልና ለእውነት ያለንን ፍቅር እንዳያጠፋብን መጠንቀቅ ይኖርብናል።
10. በእውነት ጎዳና መመላለሳችንን ለመቀጠል የትኛውን ተጽዕኖ መቋቋም ይኖርብናል?
10 ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት። በእውነት ውስጥ መመላለሳችንን ለመቀጠል ሌሎች በሚያሳድሩብን ተጽዕኖ እንዳንሸነፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል። በእውነት ጎዳና መጓዝ ስንጀምር የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ጓደኞቻችንና የቤተሰባችን አባላት ጋር ያለን ግንኙነት ተቀይሯል። አንዳንዶቹ ለምናምንባቸው ነገሮች አክብሮት ቢያሳዩም ሌሎቹ ግን ተቃዋሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 4:4) ከቤተሰባችን አባላት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ጥረት ማድረግና እነሱን በደግነት መያዝ ቢኖርብንም እነሱን ለማስደሰት ስንል አቋማችንን እንዳናላላ መጠንቀቅ ይኖርብናል። እርግጥ ከእነሱ ጋር ተስማምተን ለመኖር ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ሆኖም በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ በተሰጠው ግልጽ ማስጠንቀቂያ መሠረት የቅርብ ወዳጅነት የምንመሠርተው ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ብቻ ነው።
11. አምላክ ከማይደሰትበት አስተሳሰብና ምግባር ለመራቅ ምን ይረዳናል?
11 አምላክ የማይደሰትበት አስተሳሰብና ምግባር። በእውነት ጎዳና ላይ የሚጓዙ ሁሉ ቅዱስ መሆን አለባቸው። (ኢሳ. 35:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:14-16ን አንብብ።) ሁላችንም ወደ እውነት ቤት ስንመጣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ለመስማማት ስንል ማስተካከያዎች ማድረግ አስፈልጎናል። አንዳንዶች ትላልቅ ለውጦች ማድረግ አስፈልጓቸዋል። ያደረግነው ለውጥ ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ አሁን ያለንን ንጹሕና ቅዱስ አቋም በዓለም ውስጥ ባለው በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ሕይወት መለወጥ አንፈልግም። የሥነ ምግባር አቋማችንን እንድናበላሽ በሚደርስብን ተጽዕኖ እንዳንሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ እኛን ቅዱስ ለማድረግ ሲል በከፈለው ከፍተኛ ዋጋ ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል፤ ይሖዋ ለእኛ ሲል ውድ የሆነውን የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ከፍሎልናል። (1 ጴጥ. 1:18, 19) በይሖዋ ፊት ያለንን ንጹሕ አቋም ይዘን ለመቀጠል የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል።
12, 13. (ሀ) በዓላትን በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት መያዛችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?
12 ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕሎችና ልማዶች። የቤተሰባችን አባላት፣ የሥራ ባልደረቦቻችንና አብረውን የሚማሩ ልጆች በሚያከብሯቸው በዓላት ላይ እንድንካፈል ተጽዕኖ ያደርጉብን ይሆናል። ይሖዋን በማያስከብሩ ባሕሎችና በዓላት ላይ እንድንካፈል የሚደርስብንን ተጽዕኖ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ እንዲህ ላሉት ልማዶች ያለውን አመለካከት ማስታወሳችን ይረዳናል። ታዋቂ የሆኑ ክብረ በዓላትን አመጣጥ አስመልክቶ በጽሑፎቻችን ላይ የወጡ ሐሳቦችን መከለስ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ በዓላት ላይ የማንካፈልባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ማስታወሳችን “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት” ባለው መንገድ እየተጓዝን እንዳለ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ኤፌ. 5:10) በይሖዋና እውነት በሆነው ቃሉ ላይ እምነት ማሳደራችን ‘ሰውን በመፍራት ወጥመድ’ እንዳንያዝ ይጠብቀናል።—ምሳሌ 29:25
13 በእውነት ጎዳና ላይ የምናደርገው ጉዞ ቀጣይ የሆነ ሂደት ነው፤ ለዘላለም በዚህ ጎዳና ላይ መጓዛችንን መቀጠል እንፈልጋለን። ታዲያ በእውነት ጎዳና ላይ ለመሄድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ ሦስት መንገዶችን እንመልከት።
በእውነት ጎዳና ላይ ለመሄድ ያደረጋችሁትን ቁርጥ ውሳኔ አጠናክሩ
14. (ሀ) እውነትን መግዛታችንን መቀጠላችን እውነትን ፈጽሞ ላለመሸጥ ያደረግነውን ውሳኔ የሚያጠናክርልን እንዴት ነው? (ለ) ጥበብ፣ ተግሣጽና ማስተዋል አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
14 በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ውድ እውነቶች አጥኑ እንዲሁም ባጠናችሁት ነገር ላይ አሰላስሉ። አዎ፣ እነዚህን ውድ እውነቶች የምትመገቡበት ቋሚ ጊዜ በመመደብ እውነትን ግዙ። ምሳሌ 23:23 እውነትን ከመግዛት በተጨማሪ “ጥበብን፣ ተግሣጽንና ማስተዋልን” መግዛት እንዳለብን ይናገራል። እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም። ያወቅነውን እውነት በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ማስተዋል ካለን ይሖዋ ባስተማረን ትምህርቶች መካከል ያለውን ተያያዥነት እንገነዘባለን። ጥበብ የተማርነውን ነገር በሥራ ላይ እንድናውል ያነሳሳናል። አንዳንድ ጊዜ እውነት በየትኛው አቅጣጫ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን በመጠቆም ይገሥጸናል። እንግዲያው እንዲህ ላለው መመሪያ ምንጊዜም አዎንታዊ ምላሽ እንስጥ። ምክንያቱም ተግሣጽ ከብር የበለጠ ዋጋ አለው።—ምሳሌ 8:10
እንዲህ ማድረጋችሁ ለእውነት ያላችሁን አድናቆት ለማሳደግና እውነትን ፈጽሞ ላለመሸጥ ያደረጋችሁትን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር ይረዳችኋል።15. የእውነት ቀበቶ ጥበቃ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?
15 በሁለተኛ ደረጃ፣ በየዕለቱ ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጠቁ። (ኤፌ. 6:14) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ወታደር የሚታጠቀው ቀበቶ ወገቡን ለመደገፍና ሆድ ዕቃውን ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳዋል። ሆኖም ቀበቶው ጥበቃ እንዲያስገኝ ከተፈለገ ጥብቅ ተደርጎ መታሰር አለበት። ላላ ተደርጎ የታሰረ ቀበቶ ለወታደሩ ያን ያህል ድጋፍ ሊሰጥ አይችልም። መንፈሳዊው የእውነት ቀበቶስ ጥበቃ የሚያስገኝልን እንዴት ነው? እውነትን ልክ እንደ ቀበቶ ጥብቅ አድርገን ከታጠቅነው ከተሳሳተ አስተሳሰብ የሚጠብቀን ከመሆኑም ሌላ ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ይረዳናል። ፈተና ወይም ስደት ሲያጋጥመን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ትክክለኛ እርምጃ ለመውሰድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። አንድ ወታደር ቀበቶውን ሳይታጠቅ ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ ፈጽሞ እንደማያስብ ሁሉ እኛም የእውነትን ቀበቶ ፈጽሞ ላለማላላት ወይም ላለማውለቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ተስማምተን በመኖር፣ የታጠቅነው የእውነት ቀበቶ ምንጊዜም ጥብቅ እንዲሆን የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። አንድ ወታደር የሚታጠቀው ቀበቶ የሚሰጠው ሌላ ጥቅም ደግሞ ሰይፍ ለመያዝ የሚያገለግል መሆኑ ነው። ይህም በእውነት ጎዳና መጓዛችንን ለመቀጠል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር የሚረዳንን ቀጣይ እርምጃ ይጠቁመናል።
16. እውነትን ለሌሎች ማስተማር በእውነት ጎዳና ለመጓዝ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር የሚረዳን እንዴት ነው?
16 በሦስተኛ ደረጃ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች በማስተማሩ ሥራ የተቻላችሁን ያህል ተሳትፎ አድርጉ። እንዲህ ማድረጋችሁ መንፈሳዊውን ሰይፍ ማለትም “የአምላክን ቃል” አጥብቆ ለመያዝ ይረዳችኋል። (ኤፌ. 6:17) ሁላችንም “የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም” የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (2 ጢሞ. 2:15) መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን ሌሎች እውነትን እንዲገዙና የሐሰት ትምህርቶችን እንዲተዉ ስንረዳ እውነት በራሳችን ልብና አእምሮ ውስጥ ይቀረጻል። ይህም በእውነት ጎዳና ለመጓዝ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር ይረዳናል።
17. እውነት ለአንተ ውድ የሆነው ለምንድን ነው?
17 እውነት ከይሖዋ ያገኘነው ውድ ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀ ቦታ የምንሰጠውን ነገር ለማግኘት ማለትም በሰማይ ካለው አባታችን ጋር የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት አስችሎናል። ይሖዋ እስካሁን ብዙ ነገር ያስተማረን ቢሆንም ወደፊት ከሚያስተምረን ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም! ገና ለዘላለም ተጨማሪ እውነቶችን እንደሚያስተምረን ቃል ገብቶልናል። እንግዲያው እውነትን እንደ ውድ ዕንቁ እንመልከተው። ‘እውነትን መግዛታችንን’ ለመቀጠልና ‘ፈጽሞ ላለመሸጥ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ልክ እንደ ዳዊት “በእውነትህ እሄዳለሁ” በማለት ለይሖዋ የገባነውን ቃል እንፈጽማለን።—መዝ. 86:11
^ አን.8 ስሟ ተቀይሯል።
^ አን.8 ቪዲዮው JW ብሮድካስቲንግ ላይ ቃለ መጠይቅ እና ተሞክሮ > እውነት ሕይወትን ይለውጣል በሚለው ሥር በእንግሊዝኛ ይገኛል።