የጥናት ርዕስ 47
ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የምናገኛቸው ትምህርቶች
“ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማሉ።”—2 ጢሞ. 3:16
መዝሙር 98 ቅዱሳን መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው
ማስተዋወቂያ *
1-2. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ለዘሌዋውያን መጽሐፍ ትኩረት ሊሰጡ የሚገባው ለምንድን ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ወዳጁ ለሆነው ለወጣቱ ጢሞቴዎስ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማሉ” ብሎታል። (2 ጢሞ. 3:16) ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል የዘሌዋውያን መጽሐፍ ይገኝበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለሆነው ስለዚህ መጽሐፍ ምን አመለካከት አለህ? አንዳንዶች ይህ መጽሐፍ፣ ለዘመናችን የማይሠሩ በርካታ ሕጎችን እንደያዘ ይሰማቸው ይሆናል፤ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን የዚህ ዓይነት አመለካከት የላቸውም።
2 የዘሌዋውያን መጽሐፍ የተጻፈው ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ቢሆንም ይሖዋ “ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” ሲል ይህ መጽሐፍ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። (ሮም 15:4) የዘሌዋውያን መጽሐፍ የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት ስለሚያስችለን ትኩረት ሰጥተን ልንመረምረው ይገባል። እንዲያውም በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው ከዚህ መጽሐፍ ብዙ ልንማራቸው የምንችላቸው ነገሮች አሉ። ከእነዚህ መካከል እስቲ አራቱን እንመልከት።
የይሖዋን ሞገስ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
3. በየዓመቱ በስርየት ቀን ላይ መሥዋዕቶች ይቀርቡ የነበረው ለምንድን ነው?
3 የመጀመሪያው ትምህርት፦ የምናቀርበው መሥዋዕት ተቀባይነት እንዲኖረው የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ያስፈልገናል። በየዓመቱ በስርየት ቀን ላይ የእስራኤል ብሔር አንድ ላይ የሚሰበሰብ ሲሆን የእንስሳት መሥዋዕቶች ይቀርቡ ነበር። እነዚህ መሥዋዕቶች፣ እስራኤላውያንን ከኃጢአት መንጻት እንደሚያስፈልጋቸው ያስታውሷቸው ነበር። ይሁንና በዚያ ቀን ሊቀ ካህናቱ የመሥዋዕቱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከመግባቱ በፊት ሊያከናውነው የሚገባ አንድ ሥራ አለ፤ ይህ ሥራ የብሔሩን ኃጢአት ከማስተሰረይም ይበልጥ ትልቅ ቦታ ይሰጠው ነበር።
4. በዘሌዋውያን 16:12, 13 ላይ እንደተገለጸው ሊቀ ካህናቱ በስርየት ቀን ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገባ ምን ያደርጋል? (ሽፋኑን ተመልከት።)
ዘሌዋውያን 16:12, 13ን አንብብ። በስርየት ቀን የሚከናወነውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፦ ሊቀ ካህናቱ ወደ ማደሪያው ድንኳን ይገባል። ሊቀ ካህናቱ በዚህ ዕለት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሦስት ጊዜ የሚገባ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገባው በዚህ ወቅት ነው። በአንድ እጁ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን፣ በሌላኛው እጁ ደግሞ ፍም የሞላበትን ከወርቅ የተሠራ ዕጣን ማጨሻ ይይዛል። የቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ ላይ ያለው መጋረጃ ጋ ሲደርስ ቆም ይላል። ከዚያም በጥልቅ አክብሮት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከገባ በኋላ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ይቆማል። በምሳሌያዊ ሁኔታ በይሖዋ አምላክ ፊት የቆመ ያህል ነው! ቀጥሎም ቅዱሱን ዕጣን በጥንቃቄ ፍሙ ላይ ይጨምረዋል፤ በዚህ ጊዜ ክፍሉ ደስ በሚል መዓዛ ይታወዳል። * በኋላ ላይ፣ ሊቀ ካህናቱ የኃጢአት መባውን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ተመልሶ ይገባል። ሊቀ ካህናቱ ዕጣኑን የሚያጨሰው የኃጢአት መባውን ደም ከማቅረቡ በፊት እንደሆነ ልብ በል።
45. በስርየት ቀን ዕጣን የሚጨስ መሆኑ ምን ያስተምረናል?
5 በስርየት ቀን ዕጣን የሚጨስ መሆኑ ምን ያስተምረናል? መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የሚያቀርቡት ጸሎት እንደ ዕጣን እንደሆነ ይገልጻል። (መዝ. 141:2፤ ራእይ 5:8) ሊቀ ካህናቱ፣ ዕጣኑን ይዞ ወደ ይሖዋ ፊት የሚገባው በታላቅ አክብሮት እንደሆነ እናስታውስ። እኛም በተመሳሳይ በጸሎት ወደ ይሖዋ የምንቀርበው በጥልቅ አክብሮት ሊሆን ይገባል። የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ፣ አንድ ልጅ አባቱን የሚቀርበውን ያህል ወደ እሱ እንድንቀርብና በጸሎት እንድናነጋግረው ስለፈቀደልን በጣም አመስጋኝ ነን። (ያዕ. 4:8) ይሖዋ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ይመለከተናል! (መዝ. 25:14) ይህን መብት በጣም ከፍ አድርገን ስለምንመለከተው ፈጽሞ እሱን ማሳዘን አንፈልግም።
6. ሊቀ ካህናቱ መሥዋዕቶቹን ከማቅረቡ በፊት ዕጣን ማጨሱ ምን ያስተምረናል?
6 ሊቀ ካህናቱ መሥዋዕቶቹን ከማቅረቡ በፊት ዕጣኑን ማጨስ እንደነበረበት እናስታውስ። ይህን ማድረጉ፣ መሥዋዕቱን ከማቅረቡ በፊት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ያስችለዋል። ከዚህ ምን እንማራለን? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ከማቅረቡ በፊት ሊያከናውነው የሚገባ በጣም አስፈላጊ ነገር ነበር፤ ይህም ለሰው ልጆች መዳን ከማስገኘት ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ታዲያ ሊያከናውነው የሚገባው ነገር ምን ነበር? በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት በሙሉ ንጹሕ አቋሙን መጠበቅና በታማኝነት መመላለስ ነበረበት፤ የሚያቀርበው መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘው እንዲህ ካደረገ ነው። ኢየሱስ ይህን በማድረግ፣ ሕይወታችንን ልንመራበት የሚገባው ትክክለኛው አካሄድ የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል እንደሆነ አሳይቷል። ኢየሱስ፣ የአባቱ ሉዓላዊነት ማለትም አገዛዙ ትክክለኛና ፍትሐዊ መሆኑን አረጋግጧል።
7. ኢየሱስ በምድር ላይ ሕይወቱን የመራበት መንገድ አባቱን ያስደሰተው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት ሁሉ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ፍጹም በሆነ መንገድ ታዟል። ምንም ዓይነት ፈተና ወይም መከራ ቢደርስበትም ሌላው ቀርቶ ተሠቃይቶ እንደሚሞት ቢያውቅም እንኳ የአባቱን አገዛዝ ከመደገፍ ወደኋላ አላለም። (ፊልጵ. 2:8) ኢየሱስ ፈተና ሲያጋጥመው “በከፍተኛ ለቅሶና እንባ” ጸልዮአል። (ዕብ. 5:7) አጥብቆ መጸለዩ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ በታዛዥነት ለመጽናት ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮለታል። ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት በይሖዋ ፊት ጥሩ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ነበር። ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት የይሖዋን ልብ በጣም ደስ ያሰኘ ከመሆኑም ሌላ አባቱ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል።
8. በአኗኗራችን የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
8 እኛም ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖርና በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን ሕጎች በታማኝነት ለመታዘዝ የቻልነውን ሁሉ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ይሖዋን ማስደሰት ስለምንፈልግ፣ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የእሱን እርዳታ ለማግኘት አጥብቀን እንጸልያለን። እነዚህን ነገሮች በማድረግ፣ የይሖዋን አገዛዝ እንደምንደግፍ ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ የሚያወግዘውን ነገር የምናደርግ ከሆነ ጸሎታችን ተሰሚነት እንደማይኖረው እናውቃለን። በሌላ በኩል ደግሞ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ የምንኖር ከሆነ የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት በይሖዋ ፊት ጥሩ መዓዛ እንዳለው ዕጣን እንደሚሆን መተማመን እንችላለን። እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችንና በታማኝነት መታዘዛችን የሰማዩን አባታችንን እንደሚያስደስተው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ምሳሌ 27:11
ይሖዋን የምናገለግለው በአመስጋኝነትና በፍቅር ተነሳስተን ነው
9. እስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕቶች ያቀርቡ የነበረው ለምንድን ነው?
9 ሁለተኛው ትምህርት፦ ይሖዋን የምናገለግለው አመስጋኝነታችንን መግለጽ ስለምንፈልግ ነው። በጥንት ዘመን በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራቸው የኅብረት መባዎች ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያስተምሩን ነገር አለ። * የዘሌዋውያን መጽሐፍ እንደሚያሳየው አንድ እስራኤላዊ “አመስጋኝነቱን ለመግለጽ” የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ይችል ነበር። (ዘሌ. 7:11-13, 16-18) ግለሰቡ ይህን መባ የሚያቀርበው ስለሚጠበቅበት ሳይሆን በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። ስለዚህ የኅብረት መሥዋዕት፣ አንድ ሰው ለአምላኩ ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ በፈቃደኝነት የሚያቀርበው መባ ነው። መባውን የሚያቀርበው ሰው፣ ቤተሰቡ እንዲሁም ካህናቱ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን እንስሳ ሥጋ ይበሉ ነበር። ሆኖም የእንስሳው የተወሰኑ ክፍሎች ለይሖዋ ብቻ መቅረብ ነበረባቸው። እነዚህ የትኞቹ ክፍሎች ናቸው?
10. በዘሌዋውያን 3:6, 12, 14-16 ላይ የተገለጹት የኅብረት መሥዋዕቶች ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ስለተነሳሳበት ምክንያት ምን ያስተምሩናል?
10 ሦስተኛው ትምህርት፦ ይሖዋን ስለምንወደው ምርጣችንን እንሰጠዋለን። ይሖዋ ስቡን ከእንስሳው የሰውነት ክፍሎች ሁሉ ምርጡ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረው ነበር። በተጨማሪም ኩላሊቶቹን ጨምሮ አንዳንድ የሰውነቱ ክፍሎች ልዩ ቦታ እንደሚሰጣቸው ገልጾ ነበር። (ዘሌዋውያን 3:6, 12, 14-16ን አንብብ።) በመሆኑም አንድ እስራኤላዊ እነዚህን የእንስሳው ክፍሎችና ስቡን መሥዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ ይሖዋ በጣም ይደሰት ነበር። እንዲህ ያለውን መባ የሚያቀርብ እስራኤላዊ ለአምላክ ምርጡን የመስጠት ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል። በተመሳሳይም ኢየሱስ ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ እሱን በሙሉ ነፍሱ በማገልገል በፈቃደኝነት ለይሖዋ ምርጡን ሰጥቷል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተው ነበር፤ ለአምላክ ሕጎችም ጥልቅ ፍቅር ነበረው። (መዝ. 40:8) ይሖዋ፣ ኢየሱስ በፈቃደኝነት እንደሚያገለግለው ሲመለከት ምንኛ ተደስቶ ይሆን!
11. ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት በጥንት ዘመን ከነበሩት የኅብረት መሥዋዕቶች ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ይህስ የሚያጽናናን ለምንድን ነው?
11 በጥንት ዘመን ይቀርቡ እንደነበሩት የኅብረት መሥዋዕቶች ሁሉ እኛም በፈቃደኝነት ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት ለእሱ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ነው። ለይሖዋ የምንሰጠው ምርጣችንን ሲሆን ይህን የምናደርገውም ከልባችን ስለምንወደው ነው። ይሖዋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አገልጋዮቹ ለእሱና ለመሥፈርቶቹ ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ተነሳስተው እንደሚያገለግሉት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን! ይሖዋ የምናደርገውን ነገር ብቻ ሳይሆን አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሳንበትን ምክንያት ጭምር እንደሚመለከትና ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ማወቃችን ያጽናናናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዕድሜ የገፋህ ክርስቲያን ከሆንክ እንደ ቀድሞህ የምትፈልገውን ያህል ማገልገል አትችል ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚመለከተው እያደረግክ ያለኸውን ነገር ብቻ እንዳልሆነ አስታውስ። በይሖዋ አገልግሎት የምታደርገው ተሳትፎ ከቁጥር የማይገባ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል፤ ይሁንና ይሖዋ እሱን አቅምህ በፈቀደ መጠን ለማገልገል ያነሳሳህ ለእሱ ያለህ ፍቅር መሆኑን ይመለከታል። ይሖዋ ለእሱ ምርጥህን በመስጠትህ ይደሰታል።
12. ይሖዋ የኅብረት መሥዋዕቶችን የሚመለከትበት መንገድ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?
12 እስራኤላውያን ከሚያቀርቧቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ምን እንማራለን? ምርጥ የሆኑት የእንስሳው ክፍሎች በእሳት ሲቃጠሉና ጭሱ ወደ ላይ ሲወጣ ይሖዋ ይደሰት ነበር። ዛሬም ቢሆን ይሖዋ በፈቃደኝነት ተነሳስተህ በሙሉ ነፍስህ በምታቀርበው አገልግሎት እንደሚደሰት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ቆላ. 3:23) ይሖዋ በአንተ ሲደሰት ይታይህ! ትንሽም ይሁን ትልቅ በፍቅር ተነሳስተህ የምታቀርበውን አገልግሎት ለዘላለም የሚያስታውሰው ከመሆኑም ሌላ ምንጊዜም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ማቴ. 6:20፤ ዕብ. 6:10
ይሖዋ ድርጅቱን ይባርካል
13. በዘሌዋውያን 9:23, 24 መሠረት ይሖዋ የክህነት ሥርዓቱን እንደተቀበለው ያሳየው እንዴት ነው?
13 አራተኛው ትምህርት፦ ይሖዋ የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል እየባረከ ነው። በ1512 ዓ.ዓ. በሲና ተራራ ግርጌ ላይ የማደሪያው ድንኳን በተተከለበት ወቅት ምን እንደተከናወነ እንመልከት። (ዘፀ. 40:17) አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲሾሙ ሥርዓቱን የመራው ሙሴ ነበር። መላው የእስራኤል ብሔር፣ ካህናቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የእንስሳት መሥዋዕት ሲያቀርቡ ለመመልከት ተሰብስቦ ነበር። (ዘሌ. 9:1-5) ይሖዋ አዲስ የተቋቋመውን የክህነት ሥርዓት እንደተቀበለው ያሳየው እንዴት ነው? አሮንና ሙሴ ሕዝቡን ሲባርኩ ይሖዋ በመሠዊያው ላይ የቀረውን ነገር በሙሉ እሳት እንዲበላው አደረገ።—ዘሌዋውያን 9:23, 24ን አንብብ።
14. ይሖዋ የአሮንን የክህነት ሥርዓት መደገፉ የእኛን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?
14 ሊቀ ካህናቱ በተሾመበት ወቅት ይሖዋ ያደረገው አስደናቂ ነገር ምን ትርጉም አለው? በዚህ መንገድ ይሖዋ የአሮንን የክህነት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው አሳይቷል። እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ካህናቱን እንደሚደግፍ የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ መመልከታቸው እነሱም ይህን ዝግጅት ሊደግፉ እንደሚገባ አስገንዝቧቸው መሆን አለበት። ታዲያ ይህ ትኩረታችንን ሊስብ የሚገባ ነገር ነው? አዎ! በእስራኤል የነበረው የክህነት ሥርዓት ከዚያ ለላቀ ክህነት ጥላ ነበር። ታላቁ ሊቀ ካህናት ክርስቶስ፣ በሰማይ ከእሱ ጋር የሚያገለግሉ 144,000 ነገሥታትና ካህናት አሉት።—ዕብ. 4:14፤ 8:3-5፤ 10:1
15-16. ይሖዋ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ እየደገፈው እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
15 በ1919 ኢየሱስ የተወሰኑ ቅቡዓን ወንድሞችን “ታማኝና ልባም ባሪያ” አድርጎ ሾማቸው። ይህ ባሪያ የስብከቱን ሥራ የሚመራ ከመሆኑም ሌላ ለክርስቶስ ተከታዮች “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን” ይሰጣቸዋል። (ማቴ. 24:45) ለመሆኑ አምላክ ታማኝና ልባም ባሪያን እንደሚደግፈው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ አለ?
16 ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም፣ የታማኝና ልባም ባሪያን ሥራ ተፈታታኝ እንዲያውም ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር የማይቻል እንዲሆን ለማድረግ ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም። ሁለት የዓለም ጦርነቶች ከመካሄዳቸውና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከመከሰቱም ሌላ የአምላክ ሕዝቦች የማያባራ ስደት እንዲሁም ማቴ. 24:14) በእርግጥም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ድርጅቱን እየመራና አትረፍርፎ እየባረከ ነው።
ግፍ ደርሶባቸዋል፤ እነዚህ ሁሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ታማኝና ልባም ባሪያ በምድር ላይ ላሉት የክርስቶስ ተከታዮች መንፈሳዊ ምግብ ማቅረቡን አላቋረጠም። በዛሬው ጊዜ ከ900 በሚበልጡ ቋንቋዎች ያለምንም ክፍያ የምናገኘውን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እስቲ አስበው! ይህም ታማኙ ባሪያ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ነው። የይሖዋ በረከት የሚታይበትን ሌላ አቅጣጫ ይኸውም የስብከቱን ሥራም ለማሰብ ሞክር። ምሥራቹ “በመላው ምድር” ላይ እየተሰበከ እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው። (17. ይሖዋ የሚጠቀምበትን ድርጅት እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
17 እንግዲያው ‘በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ የመታቀፍ መብት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ይሖዋ በሙሴና በአሮን ዘመን ከሰማይ ያወረደውን እሳት ያህል አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ሰጥቶናል። በእርግጥም አመስጋኝ እንድንሆን የሚያነሳሱ ብዙ ምክንያቶች አሉን። (1 ተሰ. 5:18) ታዲያ ይሖዋ የሚጠቀምበትን ድርጅት እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ የምናገኛቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ነው። በተጨማሪም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ አቅማችን የፈቀደውን ያህል በመካፈል ድርጅቱን እንደምንደግፍ ማሳየት እንችላለን።—1 ቆሮ. 15:58
18. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
18 ከዘሌዋውያን መጽሐፍ ያገኘናቸውን ትምህርቶች በተግባር ለማዋል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይሖዋ የምናቀርበውን መሥዋዕት እንዲቀበለው በእሱ ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ጥረት እናድርግ። ይሖዋን በአመስጋኝነት ስሜት ተነሳስተን እናገልግለው። ለይሖዋ ባለን ልባዊ ፍቅር ተነሳስተን ለእሱ ምርጣችንን መስጠታችንን እንቀጥል። እንዲሁም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እየባረከው ያለውን ድርጅት በሙሉ ልባችን እንደግፍ። እነዚህን ነገሮች ስናደርግ ይሖዋ የእሱ ምሥክሮች እንድንሆን የሰጠንን መብት ከፍ አድርገን እንደምንመለከት እናሳያለን!
መዝሙር 96 የአምላክ መጽሐፍ ውድ ሀብት ነው
^ አን.5 የዘሌዋውያን መጽሐፍ ይሖዋ ለጥንት እስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕጎች ይዟል። ክርስቲያኖች እነዚህን ሕጎች እንድናከብር ባይጠበቅብንም ከእነሱ የምናገኘው ጥቅም አለ። ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የምናገኛቸውን ጠቃሚ ትምህርቶች በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
^ አን.4 በማደሪያው ድንኳን ውስጥ የሚጨሰው ዕጣን ቅዱስ ተደርጎ ይታይ ነበር፤ በጥንቷ እስራኤል እንዲህ ዓይነቱ ዕጣን ጥቅም ላይ የሚውለው ለይሖዋ አምልኮ ብቻ ነበር። (ዘፀ. 30:34-38) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ዕጣን ያጨሱ እንደነበር የሚገልጽ ዘገባ አናገኝም።
^ አን.9 የኅብረት መባዎችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 526ን እንዲሁም የጥር 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 19 አንቀጽ 11ን ተመልከት።
^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ በስርየት ቀን የእስራኤል ሊቀ ካህናት ዕጣንና ፍም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባል፤ ከዚያም ዕጣኑን ፍሙ ላይ ሲጨምረው ክፍሉ ደስ በሚል መዓዛ ይታወዳል። በኋላ ላይ ደግሞ የኃጢአት መባውን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ተመልሶ ይገባል።
^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ እስራኤላዊና ቤተሰቡ ለይሖዋ አመስጋኝነታቸውን ለመግለጽ ስለፈለጉ ለኅብረት መሥዋዕት የሚሆን በግ ለካህኑ ሲሰጡ።
^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅና ተከታዮቹም እንዲሁ እንዲያደርጉ በማስተማር ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል።
^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት በዕድሜ የገፉ እህት የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም በደብዳቤ በመመሥከር ለይሖዋ ምርጣቸውን ይሰጣሉ።
^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ፣ የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም የካቲት 2019 በጀርመንኛ መውጣቱን ሲገልጽ። በዛሬው ጊዜ በጀርመን የሚገኙ አስፋፊዎች እንደ እነዚህ እህቶች አዲሱን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በአገልግሎታቸው ላይ በደስታ ይጠቀሙበታል።