‘ብዙ ፍሬ ማፍራታችንን’ መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
“ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብታሳዩ በዚህ አባቴ ይከበራል።”—ዮሐ. 15:8
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ብሏቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) የስብከቱን ሥራ ለማከናወን ምክንያት የሚሆኑንን ነገሮች በአእምሯችን መያዛችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ሐ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ ለሐዋርያቱ ብዙ ሐሳቦችን ያካፈላቸው ሲሆን ለእነሱ ያለውን ጥልቅ ፍቅርም አረጋግጦላቸዋል። በተጨማሪም ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ስለ አንድ የወይን ተክል የሚገልጽ ምሳሌ ነግሯቸዋል። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ተጠቅሞ፣ ደቀ መዛሙርቱን ‘ብዙ ፍሬ ማፍራታቸውን’ እንዲቀጥሉ ማለትም የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩ ሥራ እንዲጸኑ አበረታቷቸዋል። *—ዮሐ. 15:8
2 ይሁንና ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን ይህን ማድረግ ያለባቸው ለምን እንደሆነም ጭምር ነው። የስብከቱን ሥራ ለማከናወን ምክንያት የሚሆኗቸውን ነገሮች ገልጾላቸዋል። እነዚህን ምክንያቶች መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በስብከቱ ሥራ ያለማሰለስ መካፈል ያለብን ለምን እንደሆነ ምንጊዜም በአእምሯችን መያዛችን ‘ለብሔራት ሁሉ ምሥክርነት’ በመስጠቱ ሥራ እንድንጸና ያነሳሳናል። (ማቴ. 24:13, 14) እንግዲያው ለመስበክ የሚያነሳሱንን አራት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት። በተጨማሪም በጽናት ፍሬ እንድናፈራ የሚረዱንን ከይሖዋ ያገኘናቸውን አራት ስጦታዎች እንመረምራለን።
ይሖዋን እናስከብራለን
3. (ሀ) በዮሐንስ 15:8 ላይ ለመስበክ የሚያነሳሳን ምን ምክንያት ተጠቅሷል? (ለ) በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት የወይን ፍሬዎች ምን ያመለክታሉ? ይህስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
3 በስብከቱ ሥራ የምንካፈልበት ዋነኛ ምክንያት ይሖዋ እንዲከበርና ስሙ እንዲቀደስ ለማድረግ ስለምንፈልግ ነው። (ዮሐንስ 15:1, 8ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ አባቱን የወይን ተክል ከሚንከባከብ አትክልተኛ ጋር አመሳስሎታል። እሱ ራሱ የወይኑን ተክል ወይም ግንድ፣ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ተከታዮቹን እንደሚያመለክቱ ተናግሯል። (ዮሐ. 15:5) ስለሆነም በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው የወይን ፍሬ፣ የክርስቶስ ተከታዮች የሚያፈሩትን ፍሬ ይኸውም የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ ማመልከቱ ተገቢ ነው። ኢየሱስ ሐዋርያቱን “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብታሳዩ በዚህ አባቴ ይከበራል” ብሏቸዋል። ጥሩ የወይን ፍሬ የሚያፈሩ የወይን ተክሎች አትክልተኛውን እንደሚያስከብሩ ሁሉ እኛም የመንግሥቱን መልእክት አቅማችን በፈቀደ መጠን ስናውጅ ለይሖዋ ክብር እናመጣለን።—ማቴ. 25:20-23
4. (ሀ) የአምላክ ስም እንዲቀደስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ስም እንዲቀደስ የማድረግ መብት በማግኘትህ ምን ይሰማሃል?
4 የስብከቱ ሥራችን የአምላክ ስም እንዲቀደስ የሚያደርገው እንዴት ነው? እርግጥ የአምላክ ስም ይበልጥ ቅዱስ እንዲሆን ማድረግ አንችልም። ምክንያቱም የአምላክ ስም፣ ፍጹም በሆነ መልኩ ቅዱስ ነው። ሆኖም ነቢዩ ኢሳይያስ “ቅዱስ አድርጋችሁ ልትመለከቱ የሚገባው የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ነው” ብሎ እንደተናገረ ልብ እንበል። (ኢሳ. 8:13) የአምላክ ስም እንዲቀደስ ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል፣ ስሙን ከሌሎች ስሞች ሁሉ የተለየ አድርገን መመልከትን እንዲሁም ሌሎች ቅዱስ አድርገው እንዲመለከቱት መርዳትን መጥቀስ ይቻላል። (ማቴ. 6:9) ለምሳሌ ያህል፣ አስደናቂ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት እንዲሁም የሰው ልጆች በገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ለማድረግ ስላለው ዓላማ እውነቱን ስናውጅ፣ ሰይጣን በአምላክ ስም ላይ የሰነዘረው ነቀፋ ውሸት መሆኑን እናጋልጣለን። (ዘፍ. 3:1-5) ከዚህም ሌላ ይሖዋ “ግርማ፣ ክብርና ኃይል” ሊቀበል እንደሚገባው በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ስናሳውቅ የአምላክ ስም እንዲቀደስ እናደርጋለን። (ራእይ 4:11) ለ16 ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለው ሩነ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ አጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ የመመሥከር አጋጣሚ ስላገኘሁ አመስጋኝ ነኝ። እንዲህ ዓይነት መብት እንዳገኘሁ ማወቄ መስበኬን እንድቀጥል ያነሳሳኛል።”
ለይሖዋ እና ለልጁ ያለን ፍቅር
5. (ሀ) በዮሐንስ 15:9, 10 ላይ ለመስበክ የሚያነሳሳን የትኛው ምክንያት ተጠቅሷል? (ለ) ኢየሱስ የጽናትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
5 ዮሐንስ 15:9, 10ን አንብብ። የመንግሥቱን መልእክት እንድንሰብክ የሚያነሳሳን አንዱ ወሳኝ ምክንያት ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለን ፍቅር ነው። (ማር. 12:30፤ ዮሐ. 14:15) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “በፍቅሬ ኑሩ” ብሏቸዋል። እንዲህ ያላቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለዓመታት የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ሆኖ መኖር ጽናት ይጠይቃል። ኢየሱስ ከዮሐንስ 15:4-10 ባሉት ጥቂት ቁጥሮች ላይ ‘መኖር’ የሚለውን ቃል በተለያየ አገባቡ ደጋግሞ በመጠቀም የጽናትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል።
6. በክርስቶስ ፍቅር መኖር እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
6 በክርስቶስ ፍቅር መኖርና እሱን ማስደሰት እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ትእዛዛቱን በመጠበቅ ነው። በቀላል አነጋገር ኢየሱስ ‘ታዘዙኝ’ እያለን ነው። ደግሞም ኢየሱስ እንድናደርግ የጠየቀን እሱ ራሱ ያደረገውን ነገር ነው፤ “እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ [እኖራለሁ]” ብሏል። (ዮሐ. 15:10) ኢየሱስ ግሩም አርዓያ ትቶልናል።—ዮሐ. 13:15
7. በታዛዥነትና በፍቅር መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
7 ኢየሱስ “እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው” በማለት ቀደም ሲል ለሐዋርያቱ የተናገረው ሐሳብ ታዛዥነትና ፍቅር ያላቸውን ግንኙነት ዮሐ. 14:21) በተጨማሪም ኢየሱስ ሄደን እንድንሰብክ የሰጠንን ተልእኮ ስንፈጽም ለአምላክም ፍቅር እንዳለን እናሳያለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የሰጣቸው ትእዛዛት ምንጭ ይሖዋ ነው። (ማቴ. 17:5፤ ዮሐ. 8:28) ለይሖዋና ለኢየሱስ ፍቅር ስናሳይ ደግሞ እነሱም በምላሹ በፍቅራቸው እንድንኖር ያደርጉናል።
በግልጽ ያሳያል። (ሰዎችን ለማስጠንቀቅ
8, 9. (ሀ) ለመስበክ የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) በሕዝቅኤል 3:18, 19 እና 18:23 ላይ ይሖዋ የተናገረው ሐሳብ መስበካችንን እንድንቀጥል የሚገፋፋን ለምንድን ነው?
8 መስበካችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን ሌላም ምክንያት አለ። የምንሰብከው ለሰዎች ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኖኅ “ሰባኪ” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ጴጥሮስ 2:5ን አንብብ።) ኖኅ የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት ያከናወነው የስብከት ሥራ ሰዎችን ስለሚመጣው ጥፋት ማስጠንቀቅን የሚያካትት መሆን አለበት። እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ያስቻለን ምንድን ነው? ኢየሱስ ምን እንዳለ ልብ እንበል፦ “ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።” (ማቴ. 24:38, 39) ሰዎቹ ለሚሰብከው መልእክት ግድየለሽ ቢሆኑም ኖኅ የተሰጠውን የማስጠንቀቂያ መልእክት በታማኝነት አውጇል።
9 ዛሬም ለሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች የምንሰብከው፣ አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ የማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ ስለምንፈልግ ነው። እኛም እንደ ይሖዋ፣ ሰዎች መልእክቱን ተቀብለው ‘በሕይወት እንዲኖሩ’ ከልብ እንፈልጋለን። (ሕዝ. 18:23) በሌላ በኩል ደግሞ ከቤት ወደ ቤትም ይሁን በአደባባይ በመስበክ፣ የአምላክ መንግሥት እንደሚመጣና ይህን ክፉ ዓለም እንደሚያጠፋ ለሰዎች ሁሉ ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን።—ሕዝ. 3:18, 19፤ ዳን. 2:44፤ ራእይ 14:6, 7
ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር
10. (ሀ) በማቴዎስ 22:39 ላይ ለመስበክ የሚያነሳሳን የትኛው ምክንያት ተጠቅሷል? (ለ) ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ አንድን የእስር ቤት ጠባቂ እንዴት እንደረዱት ግለጽ።
10 በስብከቱ ሥራችን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን ሌላው አስፈላጊ ምክንያት ደግሞ ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር ነው። (ማቴ. 22:39) እንዲህ ያለው ፍቅር፣ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ ሲቀየር ለምሥራቹ ያላቸው አመለካከትም ሊቀየር እንደሚችል በመገንዘብ በዚህ ሥራ እንድንጸና ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኛው ሲላስ ያጋጠማቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በፊልጵስዩስ ከተማ እያገለገሉ ሳሉ ተቃዋሚዎች እስር ቤት አስገቧቸው። ከዚያም እኩለ ሌሊት ገደማ ከባድ የምድር ነውጥ በድንገት የተከሰተ ሲሆን የእስር ቤቱ በሮችም ተከፈቱ። የእስር ቤቱ ጠባቂ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ። ሆኖም ጳውሎስ ድምፁን ከፍ አድርጎ “በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርግ!” በማለት ተናገረ። በዚህ ጊዜ፣ በጭንቀት የተዋጠው የእስር ቤት ጠባቂ “ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀ። እነሱም ‘በጌታ ኢየሱስ እመን፤ ትድናለህ’ አሉት።—ሥራ 16:25-34
11, 12. (ሀ) ስለ እስር ቤቱ ጠባቂ የሚናገረው ዘገባ ከአገልግሎታችን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (ለ) መስበካችንን መቀጠል የምንፈልገው ለምንድን ነው?
11 ስለ እስር ቤቱ ጠባቂ የሚናገረው ዘገባ ከስብከቱ ሥራችን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? የእስር ቤቱ ጠባቂ አመለካከቱን ቀይሮ ጳውሎስና ሲላስ እንዲረዱት
የጠየቀው የምድር ነውጡ ከተከሰተ በኋላ መሆኑን ልብ እንበል። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ ያልነበሩ አንዳንድ ሰዎች፣ ሕይወታቸውን የሚያናውጥ ነገር ሲገጥማቸው አመለካከታቸውን ይቀይሩና እርዳታ ይሹ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በክልላችን ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ለብዙ ዓመታት ከቆዩበት ሥራቸው በድንገት በመፈናቀላቸው ተደናግጠው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ትዳራቸው በመፍረሱ ምክንያት ቅስማቸው ተሰብሮ ይሆናል። ከባድ የጤና እክል እንዳለባቸው በማወቃቸው ግራ የተጋቡ አሊያም የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው በሐዘን የተደቆሱ ሰዎችም ይኖራሉ። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች የተነሳ በጭንቀት የተዋጡ አንዳንድ ሰዎች ስለ ሕይወት ዓላማ ጥያቄ ማንሳት ሊጀምሩ ይችላሉ፤ እነዚህ ሰዎች ከዚያ በፊት ይህ ጉዳይ አሳስቧቸው አያውቅ ይሆናል። አሁን ግን ‘ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብለው እስከመጠየቅ ሊደርሱ ይችላሉ። እንዲህ ያሉት ሰዎች ከእኛ ጋር ሲገናኙ፣ የምንነግራቸውን ተስፋ ያዘለ መልእክት ለማዳመጥ በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ።12 በስብከቱ ሥራችን በታማኝነት መቀጠላችን ሰዎች ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ በሚሆኑበት ጊዜ ማጽናኛ ለመስጠት ያስችለናል። (ኢሳ. 61:1) ለ38 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆየችው ሻርሎት “በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ግራ ተጋብተዋል። ምሥራቹን ለመስማት አጋጣሚ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል” ብላለች። ለ34 ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለችው ኤቮር ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች በጭንቀት ተውጠዋል። በመሆኑም ልረዳቸው እጓጓለሁ። ይህም ለመስበክ ያነሳሳኛል።” በእርግጥም ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር በአገልግሎታችን ለመቀጠል የሚያነሳሳ ትልቅ ምክንያት ነው!
ለመጽናት የሚረዱን ስጦታዎች
13, 14. (ሀ) በዮሐንስ 15:11 ላይ የትኛው ስጦታ ተጠቅሷል? (ለ) ኢየሱስ ያገኘውን ደስታ እኛም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ሐ) ደስታ በአገልግሎታችን የሚረዳን እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት፣ በጽናት ፍሬ ለማፍራት የሚረዱ የተለያዩ ስጦታዎችንም ለሐዋርያቱ ነግሯቸዋል። እነዚህ ስጦታዎች ምንድን ናቸው? የሚጠቅሙንስ እንዴት ነው?
14 ደስታ። ኢየሱስ እንድንሰብክ የሰጠን ትእዛዝ ከባድ ሸክም ነው? በጭራሽ። ኢየሱስ ስለ ወይን ተክሉ የሚገልጸውን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ የመንግሥቱን መልእክት ስንሰብክ ደስታ እንደምናገኝ ገልጿል። (ዮሐንስ 15:11ን አንብብ።) እንዲያውም ኢየሱስ፣ እሱ ያገኘውን ደስታ እኛም እንደምናገኝ አረጋግጦልናል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኢየሱስ ራሱን ከወይን ተክል፣ ደቀ መዛሙርቱን ደግሞ ከወይኑ ተክል ቅርንጫፎች ጋር አመሳስሏቸዋል። ቅርንጫፎቹ ውኃና ሌሎች አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የሚያገኙት ከወይኑ ተክል ጋር ተጣብቀው እስከቀጠሉ ድረስ ነው። በተመሳሳይ እኛም የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ በመከተል ከእሱ ጋር ተጣብቀን እስከኖርን ድረስ ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ በማድረግ ያገኘውን ዓይነት ደስታ ማጣጣም እንችላለን። (ዮሐ. 4:34፤ 17:13፤ 1 ጴጥ. 2:21) ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለችው ሃኔ “በስብከቱ ሥራ ከተካፈልኩ በኋላ ሁልጊዜ የሚሰማኝ ደስታ በይሖዋ አገልግሎት እንድቀጥል ይገፋፋኛል” ብላለች። በእርግጥም አገልግሎቱ የሚያስገኝልን ጥልቅ ደስታ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ክልሎች ውስጥ እንኳ መስበካችንን እንድንቀጥል ብርታት ይሰጠናል።—ማቴ. 5:10-12
15. (ሀ) ዮሐንስ 14:27 ስለ የትኛው ስጦታ ይናገራል? (ለ) የኢየሱስ ሰላም፣ ፍሬ ማፍራታችንን ለመቀጠል የሚረዳን እንዴት ነው?
15 ሰላም። (ዮሐንስ 14:27ን አንብብ።) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ ለሐዋርያቱ “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። የኢየሱስ ሰላም፣ ፍሬ ለማፍራት የሚረዳን እንዴት ነው? በስብከቱ ሥራ ስንጸና፣ ይሖዋ እና ኢየሱስ እንደሚደሰቱብን ማወቅ የሚያስገኘውን ውስጣዊ ሰላም ማጣጣም እንችላለን። (መዝ. 149:4፤ ሮም 5:3, 4፤ ቆላ. 3:15) ለ45 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተካፈለው ኡልፍ “የስብከቱ ሥራ ቢያደክመኝም እውነተኛ እርካታ እንዳገኝና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድመራ ያደርገኛል” ብሏል። በእርግጥም ዘላቂ ሰላም ማግኘት በመቻላችን አመስጋኞች ነን!
16. (ሀ) በዮሐንስ 15:15 ላይ የትኛው ስጦታ ተጠቅሷል? (ለ) ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ጠብቀው ማቆየት የሚችሉት እንዴት ነው?
16 የኢየሱስ ወዳጅ መሆን። ኢየሱስ የሐዋርያቱ “ደስታ የተሟላ እንዲሆን” ያለውን ምኞት ከገለጸ በኋላ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የማሳየትን አስፈላጊነት ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 15:11-13) ቀጥሎም “ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ” ብሏቸዋል። የኢየሱስ ወዳጅ መሆን እንዴት ያለ ትልቅ ስጦታ ነው! ይሁንና ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር ያላቸው ወዳጅነት እንዲቀጥል ምን ማድረግ ነበረባቸው? ‘ሄደው ፍሬ ማፍራታቸውን’ እንዲቀጥሉ ተነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:14-16ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ ከሁለት ዓመት በፊት ሐዋርያቱን “በምትሄዱበት ጊዜም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ” በማለት አዟቸው ነበር። (ማቴ. 10:7) ከመሞቱ በፊት ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ በጀመሩት ሥራ እንዲጸኑ ያበረታታቸው ለዚህ ነው። (ማቴ. 24:13፤ ማር. 3:14) የኢየሱስን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ተፈታታኝ ቢሆንባቸውም የተሰጣቸውን ተልእኮ መወጣትና ከእሱ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ጠብቀው ማቆየት ይችላሉ። እንዴት? ይህን ለማድረግ የሚረዳቸው ሌላ ስጦታ አለ።
17, 18. (ሀ) በዮሐንስ 15:16 ላይ የትኛው ስጦታ ተጠቅሷል? (ለ) ይህ ስጦታ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት የረዳቸው እንዴት ነው? (ሐ) በዛሬው ጊዜ የሚያበረታቱን የትኞቹ ስጦታዎች ናቸው?
17 ለጸሎታችን ምላሽ ማግኘት። ኢየሱስ “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ [ይሰጣችኋል]” ብሏል። (ዮሐ. 15:16) ኢየሱስ የገባው ቃል ሐዋርያቱን በጣም አበረታቷቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም! * ሐዋርያቱ በወቅቱ ባይገነዘቡትም መሪያቸው የሚሞትበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር፤ ያም ቢሆን እርዳታ የሚያገኙበት ዝግጅት ተደርጎላቸዋል። የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውንም እርዳታ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ጸሎት፣ ይሖዋ እንደሚሰማ መተማመን ይችሉ ነበር። ደግሞም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ያቀረቡትን ጸሎት ይሖዋ እንደመለሰላቸው ተመልክተዋል።—ሥራ 4:29, 31
18 ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በጽናት ፍሬ ስናፈራ የኢየሱስ ወዳጆች የመሆን መብት እናገኛለን። በተጨማሪም የመንግሥቱን ምሥራች ስንሰብክ የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች ለመወጣት እንዲረዳን የምናቀርበውን ጸሎት ይሖዋ እንደሚመልስልን መተማመን እንችላለን። (ፊልጵ. 4:13) ለጸሎታችን ምላሽ ማግኘትና ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት መመሥረት በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ከይሖዋ ያገኘናቸው እነዚህ ስጦታዎች ፍሬ ማፍራታችንን እንድንቀጥል ያበረታቱናል።—ያዕ. 1:17
19. (ሀ) በስብከቱ ሥራ መካፈላችንን የምንቀጥለው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ የሰጠንን ሥራ እስከ ፍጻሜው ለማድረስ ምን ይረዳናል?
19 በስብከቱ ሥራ መካፈላችንን የምንቀጥለው ይሖዋ እንዲከበርና ስሙ እንዲቀደስ ለማድረግ፣ ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር ለማሳየት፣ ለሰዎች በቂ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት እንዲሁም ለባልንጀራችን ፍቅር ለማሳየት ስለምንፈልግ እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ ተመልክተናል። በተጨማሪም ይሖዋ የሰጠን ስጦታዎች ይኸውም ደስታ፣ ሰላም፣ የኢየሱስ ወዳጅ የመሆን መብት እንዲሁም ለጸሎታችን የምናገኘው ምላሽ አምላክ የሰጠንን ሥራ እስከ ፍጻሜው ለማድረስ ብርታት ይሰጡናል። ይሖዋ ‘ብዙ ፍሬ ማፍራታችንን’ ለመቀጠል የምናደርገውን ልባዊ ጥረት ሲመለከት እጅግ እንደሚደሰት አንጠራጠርም!