የጥናት ርዕስ 19
ፍቅርና ፍትሕ—ክፋት በሞላበት ዓለም ውስጥ
“አንተ በክፋት የምትደሰት አምላክ አይደለህምና፤ ክፉ ሰው ከአንተ ጋር አይቀመጥም።”—መዝ. 5:4
መዝሙር 142 ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ
የትምህርቱ ዓላማ *
1-3. (ሀ) በመዝሙር 5:4-6 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ለክፋት ምን አመለካከት አለው? (ለ) ሕፃናትን ማስነወር ‘ከክርስቶስ ሕግ’ ጋር ይጋጫል የምንለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ አምላክ ማንኛውንም ዓይነት ክፋት ይጠላል። (መዝሙር 5:4-6ን አንብብ።) ሕፃናትን እንደማስነወር ያለውን ጭካኔ የሚንጸባረቅበትና እጅግ ዘግናኝ የሆነ ድርጊትማ ምንኛ ይጸየፈው ይሆን! እኛም የእሱ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ይህን ድርጊት አጥብቀን የምንጸየፈው ሲሆን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በምንም ዓይነት በቸልታ አናልፈውም።—ሮም 12:9፤ ዕብ. 12:15, 16
2 ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዘ ማንኛውም ድርጊት ‘ከክርስቶስ ሕግ’ ጋር ፈጽሞ ይጋጫል! (ገላ. 6:2) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በቃልም ይሁን ምሳሌ በመሆን ያስተማራቸውን ትምህርቶች በሙሉ የሚያካትተው የክርስቶስ ሕግ፣ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም ሌላ ፍትሕ እንዲሰፍን እንደሚያደርግ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ ሕግ ስለሚመሩ ልጆችን የሚይዙት የደህንነት ስሜት እንዲያድርባቸውና ከልብ እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው በሚያደርግ መንገድ ነው። በልጆች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት ግን ልጆች ስጋት እንዲያድርባቸውና እንደማይወደዱ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ፍትሕ የጎደለው ብሎም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት ነው።
3 የሚያሳዝነው፣ በልጆች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት ልክ እንደ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ ተስፋፍቷል፤ ይህ ጉዳይ እውነተኛ ክርስቲያኖችንም ነክቷል። ምክንያቱም “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች” ከቀን ወደ ቀን እየበዙ የሄዱ ሲሆን አንዳንዶቹ ወደ ክርስቲያን ጉባኤም ጭምር ሰርገው ሊገቡ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:13) ከዚህም በተጨማሪ፣ ይሖዋን እንደሚያገለግሉ የሚናገሩ አንዳንድ የጉባኤው አባላት ተገቢ ላልሆነ የፆታ ምኞት በመሸነፍ ልጆችን አስነውረዋል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በልጆች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት ከባድ ኃጢአት ነው የምንለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚያም ሽማግሌዎች በልጆች ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደመፈጸም ያሉ ከባድ ኃጢአቶችን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው እንዲሁም ወላጆች ልጆቻቸውን ከጥቃት መጠበቅ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። *
ከባድ ኃጢአት
4-5. ሕፃናትን ማስነወር፣ የጥቃቱ ሰለባ በሆኑት ልጆች ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
4 በልጆች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት፣ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ጉዳት ያስከትላል። ጥቃት የተፈጸመበትን ግለሰብ አልፎ ተርፎም ግለሰቡን የሚወዱትን ሁሉ፣ ለምሳሌ የቤተሰቡን አባላት እንዲሁም ክርስቲያን ወንድሞቹንና እህቶቹን ይጎዳል። በእርግጥም ሕፃናትን ማስነወር ከባድ ኃጢአት ነው።
5 ጥቃት በደረሰበት ግለሰብ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት። * በሌሎች ላይ ጉዳትና ሥቃይ የሚያስከትል ነገር ማድረግ ኃጢአት ነው። በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው፣ በአንድ ልጅ ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚፈጽም ሰው ልጁን በብዙ መንገዶች ይጎዳዋል። በሚያምነው ሰው እንዲህ ያለ ድርጊት የተፈጸመበት ልጅ፣ ሰዎችን ለማመን ሊቸገርና ስጋት ሊያድርበት ይችላል። ልጆች እንዲህ ካለው የጭካኔ ድርጊት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፤ እንዲህ ያለው ድርጊት ሰለባ የሆኑ ልጆች ደግሞ ማጽናኛና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።—1 ተሰ. 5:14
6-7. ሕፃናትን ማስነወር በጉባኤውም ሆነ በሰብዓዊ ባለሥልጣናት ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
6 በጉባኤው ላይ የሚፈጸም ኃጢአት። አንድ የጉባኤው አባል ሕፃናትን ቢያስነውር በጉባኤው ላይ ነቀፋ ያመጣል። (ማቴ. 5:16፤ 1 ጴጥ. 2:12) ‘ለእምነት ብርቱ ተጋድሎ’ እያደረጉ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታማኝ ክርስቲያኖች በዚህ ግለሰብ ምክንያት መነቀፋቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነው! (ይሁዳ 3) እንዲህ ያሉ አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈጽመው ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ የማይሆኑ እንዲሁም የጉባኤውን መልካም ስም የሚያጎድፉ ሰዎችን በጭራሽ አንታገሥም።
7 በሰብዓዊ ባለሥልጣናት ላይ የሚፈጸም ኃጢአት። ክርስቲያኖች “ለበላይ ባለሥልጣናት” መገዛት ይጠበቅባቸዋል። (ሮም 13:1) ለምንኖርበት አገር ሕጎች ተገቢውን አክብሮት በማሳየት ለባለሥልጣናት እንድንገዛ የተሰጠንን ትእዛዝ እንፈጽማለን። የመንግሥትን ሕግ በመጣስ ወንጀል የሚሠራ፣ ለምሳሌ ሕፃናትን የሚያስነውር አንድ የጉባኤው አባል በሰብዓዊ ባለሥልጣናት ላይ ኃጢአት ይፈጽማል። (ከሐዋርያት ሥራ 25:8 ጋር አወዳድር።) ሽማግሌዎች የመንግሥትን ሕጎች የማስፈጸም ሥልጣን ባይኖራቸውም ሕፃናትን ያስነወረ ክርስቲያን ድርጊቱ ከሚያስከትልበት ሕጋዊ ቅጣት እንዲያመልጥ ከለላ አያደርጉም። (ሮም 13:4) ኃጢአት የሠራው ግለሰብ የዘራውን ሊያጭድ ይገባል።—ገላ. 6:7
8. ይሖዋ አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ የሚፈጽመውን ኃጢአት እንዴት ይመለከተዋል?
8 በአምላክ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት። (መዝ. 51:4) ሕፃናትን ማስነወር ከምንም በላይ በአምላክ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው። አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ ኃጢአት ሲሠራ በይሖዋም ላይ ኃጢአት እንደሠራ ይቆጠራል። አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው አንድ ሕግ ይህን ሐቅ ያስገነዝበናል። ሕጉ ባልንጀራውን የሚያታልል ሰው “በይሖዋ ላይ ታማኝነት የማጉደል ተግባር [እንደሚፈጽም]” ይናገራል። (ዘሌ. 6:2-4) በመሆኑም ሕፃናትን የሚያስነውር አንድ የጉባኤው አባል፣ ጥቃት የተፈጸመበትን ልጅ ስለሚያታልል በይሖዋ ላይ ታማኝነት የማጉደል ተግባር ይፈጽማል። ልጁ እምነት በሚጥልበት ሰው እንዲህ ያለ በደል ስለተፈጸመበት ከዚያ በኋላ የመረጋጋት ስሜት አይሰማውም። በተጨማሪም በልጆች ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚፈጽም ክርስቲያን በይሖዋ ስም ላይ ከፍተኛ ነቀፋ ያስከትላል። በእርግጥም ሕፃናትን ማስነወር፣ በአምላክ ላይ የሚፈጸም ከባድ ኃጢአት ስለሆነ ሊወገዝ ይገባል።
9. ባለፉት ዓመታት የይሖዋ ድርጅት ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች ሲያወጣ ቆይቷል? ለምንስ?
9 ባለፉት ዓመታት የይሖዋ ድርጅት በልጆች ላይ የሚፈጸመውን ፆታዊ ጥቃት በተመለከተ በርካታ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል። ለምሳሌ፣ ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች ከደረሰባቸው ስሜታዊ ቁስል ማገገም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ፣ ሌሎች እነሱን መርዳትና ማበረታታት የሚችሉት እንዴት እንደሆነና ወላጆች ልጆቻቸውን ከዚህ ጥቃት መጠበቅ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚያብራሩ ርዕሶች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ወጥተዋል። ሽማግሌዎች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ኃጢአቶችን ስለሚይዙበት መንገድ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ሰፊ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። ወደፊትም ቢሆን ድርጅቱ እንዲህ ያሉ ኃጢአቶች የሚያዙበትን መንገድ እየገመገመ ማስተካከያ ማድረጉን ይቀጥላል። ለምን? ጉባኤዎች ጉዳዩን የሚይዙበት መንገድ ከክርስቶስ ሕግ ጋር የሚስማማ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።
ከባድ ኃጢአት ሲፈጸም ሽማግሌዎች ምን ያደርጋሉ?
10-12. (ሀ) ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት እንደተፈጸመ የሚገልጽ ሪፖርት ሲደርሳቸው ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል? የትኞቹን ነገሮችስ ግምት ውስጥ ያስገባሉ? (ለ) በያዕቆብ 5:14, 15 መሠረት ሽማግሌዎች ምን ለማድረግ ይጥራሉ?
10 ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት እንደተፈጸመ የሚገልጽ ሪፖርት ሲደርሳቸው፣ መንጋውን በፍቅር እንዲይዙ እንዲሁም በአምላክ ዓይን ትክክልና ፍትሐዊ የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ የሚያዝዘውን የክርስቶስን ሕግ ያስታውሳሉ። በመሆኑም በርካታ ነገሮችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። ሽማግሌዎችን በዋነኝነት የሚያሳስባቸው የአምላክ ስም ቅድስና ነው። (ዘሌ. 22:31, 32፤ ማቴ. 6:9) በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ደህንነት በእጅጉ የሚያሳስባቸው ከመሆኑም ሌላ በተፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የተጎዱትን መርዳት ይፈልጋሉ።
11 ከዚህም ሌላ፣ ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ የጉባኤው አባል ከሆነና ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ከሆነ ሽማግሌዎች ግለሰቡ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ማደስ እንዲችል ለመርዳት ይጥራሉ። (ያዕቆብ 5:14, 15ን አንብብ።) በመጥፎ ምኞት ተሸንፎ ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ታሟል። በሌላ አነጋገር ከይሖዋ ጋር የነበረው ጤናማ ግንኙነት ተበላሽቷል። * ሽማግሌዎች መንፈሳዊ ሐኪሞች ናቸው ሊባል ይችላል። ‘የታመመው ሰው [በዚህ አገባቡ፣ ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ] ፈውስ እንዲያገኝ’ ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች የሚሰጡት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲያድስ ይረዳዋል፤ ሆኖም ይህ ሊሆን የሚችለው ግለሰቡ ከልቡ ንስሐ ከገባ ብቻ ነው።—ሥራ 3:19፤ 2 ቆሮ. 2:5-10
12 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ሽማግሌዎች ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። አምላክ በአደራ ለሰጣቸው መንጋ ከልብ ያስባሉ። (1 ጴጥ. 5:1-3) ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው በጉባኤው ውስጥ ያለስጋት እንዲኖሩ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ሕፃናትን ማስነወርን ጨምሮ ከባድ ኃጢአት እንደተፈጸመ የሚገልጽ ሪፖርት ሲደርሳቸው ፈጣን እርምጃ ይወስዳሉ። እስቲ በአንቀጽ 13፣ 15 እና 17 ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች እንመርምር።
13-14. ሽማግሌዎች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ክሶች ለሕግ አካላት ሪፖርት እንዲደረጉ የሚጠይቁ ሰብዓዊ ሕጎችን ይታዘዛሉ? አብራራ።
13 ሽማግሌዎች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ክሶች ለሕግ አካላት ሪፖርት እንዲደረጉ የሚጠይቁ ሰብዓዊ ሕጎችን ይታዘዛሉ? አዎ። አንዳንድ አገሮች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ክሶች ለሕግ አካላት ሪፖርት እንዲደረጉ የሚጠይቁ ሕጎች አሏቸው፤ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉ ሕጎችን ይታዘዛሉ። (ሮም 13:1) እነዚህ ሕጎች ከአምላክ ሕግ ጋር አይጋጩም። (ሥራ 5:28, 29) በመሆኑም ሽማግሌዎች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዘ ክስ ሲደርሳቸው ወዲያውኑ እነዚህን ሕጎች መፈጸም የሚችሉበትን መንገድ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ።
14 ሽማግሌዎች ጥቃቱ ለተፈጸመባቸው ግለሰቦች፣ ለወላጆቻቸው እንዲሁም ስለ ጉዳዩ ለሚያውቁ ሌሎች ሰዎች
ክሱን ለሕግ አካላት የማሳወቅ ነፃነት እንዳላቸው ሊነግሯቸው ይገባል። ይሁንና ክሱ የቀረበበት ሰው የጉባኤው አባል ቢሆንና ጉዳዩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ቢታወቅስ? ክሱን ያቀረበው ግለሰብ በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ እንዳመጣ ሊሰማው ይገባል? በፍጹም። በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ ያመጣው ፆታዊ ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ ነው።15-16. (ሀ) በ1 ጢሞቴዎስ 5:19 ላይ በተገለጸው መሠረት ሽማግሌዎች የፍርድ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? (ለ) ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ያለ አንድ ሰው ሕፃናትን እንዳስነወረ የሚገልጽ ክስ ሲደርሳቸው ምን ያደርጋሉ?
15 የጉባኤ ሽማግሌዎች አንድን ጉዳይ በተመለከተ የፍርድ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ላቅ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ የፍትሕ መሥፈርት እንዲህ እንዲደረግ ስለሚጠይቅ ነው። ግለሰቡ ኃጢአቱን ካልተናዘዘ ሽማግሌዎች ክስ መመሥረትና የፍርድ ኮሚቴ ማቋቋም እንዲችሉ ሁለት ምሥክሮች ያስፈልጋሉ። (ዘዳ. 19:15፤ ማቴ. 18:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:19ን አንብብ።) ይህ ሲባል ታዲያ ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ክሶችን ለሕግ አካላት ሪፖርት እንዲያደርጉ የግድ ሁለት ምሥክሮች ያስፈልጋሉ ማለት ነው? በፍጹም። ይህ መሥፈርት፣ የወንጀል ክሶችን ሪፖርት ከማድረግ ጋር በተያያዘ አይሠራም።
16 ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ያለ አንድ ሰው ሕፃናትን እንዳስነወረ የሚገልጽ ክስ ሲደርሳቸው ጉዳዩ ለሕግ አካላት ሪፖርት እንዲደረግ የሚያዙትን ሕጎች ለመፈጸም ይጥራሉ፤ ከዚያም ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመው ክሱን ለመመርመር ይሞክራሉ። ክሱ የቀረበበት ግለሰብ ድርጊቱን እንዳልፈጸመ ከተናገረ ሽማግሌዎች ምሥክሮች የሚሰጡትን ቃል ይመረምራሉ። ክሱ ቢያንስ በሁለት ሰዎች ማለትም ክሱን ባቀረበው ሰውና ተከሳሹ በዚህ ልጅ ላይ ወይም በሌላ ልጅ ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደፈጸመ ሊመሠክር በሚችል ሌላ ሰው ከተረጋገጠ የፍርድ ኮሚቴ ይቋቋማል። * ሁለተኛ ምሥክር አልተገኘም ማለት ክሱን ያቀረበው ሰው ዋሽቷል ማለት አይደለም። አንድ ክስ በሁለት ምሥክሮች ባይረጋገጥ እንኳ ሽማግሌዎች በሌሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ከባድ ኃጢአት ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል ይገነዘባሉ። በመሆኑም ለተጎዱት ሰዎች ቀጣይ የሆነ ድጋፍ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ሕፃናትን አስነውሯል ተብሎ የተከሰሰው ሰው በጉባኤው ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ሽማግሌዎች በቅርበት ይከታተሉታል።—ሥራ 20:28
17-18. የፍርድ ኮሚቴውን ሚና አብራራ።
17 የፍርድ ኮሚቴው ሚና ምንድን ነው? “ፍርድ” የሚለው ቃል ሽማግሌዎች ሕፃናትን ያስነወረው ግለሰብ ለፈጸመው ወንጀል በሕግ አካላት መቀጣት ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ የመፍረድ ወይም የመበየን ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚጠቁም አይደለም። ሽማግሌዎች የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎችን በማስፈጸሙ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም፤ ከወንጀል ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለሕግ አካላት ይተዋሉ። (ሮም 13:2-4፤ ቲቶ 3:1) የሽማግሌዎች ኃላፊነት፣ ግለሰቡ የጉባኤው አባል ሆኖ ይቀጥል ወይስ አይቀጥል የሚለውን ጉዳይ መፍረድ ወይም መወሰን ነው።
18 ሽማግሌዎች በፍርድ ኮሚቴ ውስጥ ሲያገለግሉ ኃላፊነታቸው ከመንፈሳዊ ወይም ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመው፣ ፆታዊ ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ ንስሐ መግባት አለመግባቱን ለመወሰን ጥረት ያደርጋሉ። ግለሰቡ ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ካልሆነ ከጉባኤ ይወገዳል፤ ከዚያም ለጉባኤው ማስታወቂያ ይነገራል። (1 ቆሮ. 5:11-13) ንስሐ ከገባ ግን የጉባኤው አባል ሆኖ ሊቀጥል ይችላል። ሆኖም ሽማግሌዎች ወደፊት በጉባኤ ውስጥ ምንም ዓይነት መብት ወይም ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ ላይሆን እንደሚችል ይነግሩታል። ሽማግሌዎች የልጆችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ትናንሽ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በግል ጠርተው ግለሰቡ ከልጆቻቸው ጋር ያለውን ግንኙነት በጥንቃቄ እንዲከታተሉ ሊያሳስቧቸው ይችላሉ። ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉ እርምጃዎችን ሲወስዱ በተፈጸመው ኃጢአት የተጎዱትን ሰዎች ማንነት ላለማሳወቅ መጠንቀቅ አለባቸው።
ልጆቻችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
19-22. ወላጆች ልጆቻቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይችላሉ? (ሽፋኑን ተመልከት።)
19 ልጆችን ከጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው እነማን ናቸው? ወላጆች ናቸው። * ልጆቻችሁ ይሖዋ በአደራ የሰጣችሁ ስጦታ ወይም “ውርሻ” ናቸው። (መዝ. 127:3) ይህን አደራ መጠበቅ የእናንተ ኃላፊነት ነው። ታዲያ ልጆቻችሁን ከጥቃት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
20 በመጀመሪያ፣ ስለ ፆታዊ ጥቃት በቂ እውቀት ይኑራችሁ። ልጆችን ስለሚያስነውሩ ሰዎችና እነዚህ ሰዎች ስለሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ለጥቃት የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በንቃት ተከታተሉ። (ምሳሌ 22:3፤ 24:3) አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለ ጥቃት የሚፈጽሙት፣ ልጆቹ የሚያውቋቸውና የሚያምኗቸው ሰዎች እንደሆኑ አስታውሱ።
21 ሁለተኛ፣ ከልጆቻችሁ ጋር በነፃነት የመነጋገር ልማድ ይኑራችሁ። (ዘዳ. 6:6, 7) ይህም ጥሩ አድማጭ መሆንን ይጨምራል። (ያዕ. 1:19) አብዛኛውን ጊዜ ልጆች፣ ፆታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው መናገር ሊፈሩ እንደሚችሉ አስታውሱ። ይህን ጉዳይ ቢናገሩ ማንም ሰው እንደማያምናቸው ሊያስቡ ይችላሉ፤ አሊያም ደግሞ ጥቃት የፈጸመባቸው ግለሰብ ለማንም እንዳይናገሩ አስፈራርቷቸው ሊሆን ይችላል። ልጃችሁ የሆነ ችግር እንደደረሰበት ከጠረጠራችሁ ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ጥያቄዎች በመጠየቅና የሚሰጠውን መልስ በትዕግሥት በማዳመጥ ያጋጠመውን ነገር እንዲናገር አበረታቱት።
22 ሦስተኛ፣ ልጆቻችሁን አስተምሩ። ፆታን በተመለከተ ዕድሜያቸውን ያገናዘበ ትምህርት ስጧቸው። አንድ ሰው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሊነካቸው ቢሞክር ምን ማለት ወይም ማድረግ እንዳለባቸው አስተምሯቸው። ልጆቻችሁን ከጥቃት መጠበቅ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ የይሖዋ ድርጅት ያወጣቸውን መረጃዎች ተጠቀሙ።—“ ራሳችሁንና ልጆቻችሁን አስተምሩ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
23. በልጆች ላይ ስለሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት ምን አመለካከት አለን? በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
23 እኛ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሕፃናትን ማስነወርን እንደ ከባድ ኃጢአትና እንደ ጭካኔ ድርጊት እንመለከተዋለን። ጉባኤዎቻችን በክርስቶስ ሕግ ስለሚመሩ፣ እንዲህ ያለ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች ኃጢአታቸው ከሚያስከትልባቸው መዘዝ እንዲያመልጡ ከለላ አያደርጉም። በሌላ በኩል ደግሞ ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። ለመሆኑ እነዚህን ሰዎች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? በቀጣዩ ርዕስ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን።
መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች
^ አን.5 ይህ ርዕስ ልጆችን ከፆታዊ ጥቃት መጠበቅ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። ሽማግሌዎች ጉባኤውን፣ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ከዚህ ጥቃት መጠበቅ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
^ አን.3 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ አንድ ልጅ ፆታዊ ጥቃት ተፈጸመበት የሚባለው አንድ አዋቂ የፆታ ፍላጎቱን ለማርካት መጠቀሚያ ሲያደርገው ነው። ይህም የፆታ ግንኙነት መፈጸምን፣ በአፍ ወይም በፊንጢጣ የፆታ ግንኙነት ማድረግን እንዲሁም የልጆችን ብልት፣ ጡት ወይም መቀመጫ ማሻሸትን ወይም ሌሎች የብልግና ድርጊቶች መፈጸምን ሊያካትት ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ጥቃት ሰለባ የሚሆኑት ሴቶች ቢሆኑም ወንዶችም ፆታዊ ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ልጆችን የሚያስነውሩት ወንዶች ቢሆኑም ሴቶችም እንዲህ ያለውን ድርጊት ሊፈጽሙ ይችላሉ።
^ አን.5 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በዚህና በቀጣዩ ርዕስ ላይ፣ ጥቃት የደረሰበት ግለሰብ የሚለው አገላለጽ በልጅነቱ ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመበትን ሰው ያመለክታል። ይህን አገላለጽ የምንጠቀመው፣ ልጁ ምንም ጥፋት እንደሌለበት እንዲያውም ተጎጂ እንደሆነና መጠቀሚያ እንደተደረገ ግልጽ ለማድረግ ነው።
^ አን.11 መንፈሳዊ ሕመም፣ ከባድ ኃጢአት ለመፈጸም ሰበብ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም። ኃጢአት የፈጸመው ሰው፣ ላደረገው የተሳሳተ ምርጫና ለፈጸመው መጥፎ ድርጊት ሙሉ ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ከመሆን አያመልጥም።—ሮም 14:12
^ አን.16 ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመበት ልጅ፣ ጥቃቱን ፈጽሟል ተብሎ የተከሰሰው ግለሰብ በተገኘበት ቃሉን እንዲሰጥ ፈጽሞ አይጠበቅበትም። ወላጁ ወይም ለልጁ ቅርብ የሆነ ሌላ ሰው የተፈጠረውን ነገር ለሽማግሌዎች ሊናገር ይችላል። ይህም ልጁ ተጨማሪ ስሜታዊ ጉዳት እንዳይደርስበት ይረዳል።
^ አን.19 ወላጆችን አስመልክቶ የቀረበው ሐሳብ፣ ለሕጋዊ አሳዳጊዎች ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰን ልጅ የመንከባከብ ኃላፊነት ለተጣለባቸው ሌሎች ሰዎችም ይሠራል።