የጥናት ርዕስ 22
መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?
በተሳካ ሁኔታ መጠናናት የሚቻለው እንዴት ነው?
“ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው . . . የተሰወረ የልብ ሰው [ነው]።”—1 ጴጥ. 3:4
ዓላማ
አንድ ወንድና አንዲት ሴት በተሳካ ሁኔታ መጠናናት የሚችሉት እንዴት ነው? በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖችስ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
1-2. አንዳንዶች ስለ መጠናናት ምን ይሰማቸዋል?
መጠናናት አስደሳች ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ወቅት እየተጠናናችሁ ከሆነ አስደሳች እንዲሆንላችሁ እንደምትፈልጉ ምንም ጥያቄ የለውም። ደግሞም በርካታ ጥንዶች በመጠናናት የሚያሳልፉት ጊዜ አስደሳች ሆኖላቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የምትኖር ጽዮን a የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከተደሰትኩባቸው ጊዜያት አንዱ ከባለቤቴ ጋር በመጠናናት ያሳለፍነው ጊዜ ነው። ቁም ነገር ያዘሉ ውይይቶችን እናደርግ ነበር፤ እንስቅም ነበር። የምወደውና የሚወደኝ ሰው በማግኘቴ በጣም ተደስቼ ነበር።”
2 ሆኖም በኔዘርላንድስ የሚኖር አሌሾ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከባለቤቴ ጋር እንጠናና በነበረበት ወቅት አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል። ሆኖም ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመውናል።” በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በመጠናናት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችንና በተሳካ ሁኔታ ለመጠናናት የሚረዱ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመለከታለን። በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶችን መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
የመጠናናት ዓላማ
3. የመጠናናት ዓላማ ምንድን ነው? (ምሳሌ 20:25)
3 መጠናናት አስደሳች ሊሆን ቢችልም በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እርምጃ ነው፤ ምክንያቱም ወደ ትዳር ሊመራ ይችላል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሠርጋቸው ቀን፣ በሕይወት እስካሉ ድረስ እርስ በርስ ለመዋደድና ለመከባበር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ይገባሉ። ማንኛውንም ቃል ኪዳን ከመግባታችን በፊት ስለ ጉዳዩ በጥንቃቄ ልናስብበት ይገባል። (ምሳሌ 20:25ን አንብብ።) ከጋብቻ ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት መጠናናታቸው በደንብ ለመተዋወቅና ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳቸዋል። አንዳንዶቹ ለመጋባት ይወስኑ ይሆናል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለመለያየት ይወስናሉ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለመለያየት ቢወስኑ መጠናናቱ አልተሳካም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጠናናቱ ዓላማውን አከናውኗል፤ ጥሩ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ረድቷቸዋል።
4. ከመጠናናት ጋር በተያያዘ ትክክለኛው አመለካከት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
4 ከመጠናናት ጋር በተያያዘ ትክክለኛውን አመለካከት መያዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ያላገቡ ሰዎች ትክክለኛው አመለካከት ካላቸው ለማግባት ከማያስቡት ሰው ጋር መጠናናት አይጀምሩም። ይሁንና ትክክለኛው አመለካከት ሊኖራቸው የሚገባው ያላገቡ ክርስቲያኖች ብቻ አይደሉም። ሁላችንም ከመጠናናት ጋር በተያያዘ ትክክለኛው አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ አንዳንዶች፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት እየተጠናኑ ከሆነ የግድ መጋባት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ይህ አመለካከት ባላገቡ ክርስቲያኖች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ሜሊሳ የተባለች ያላገባች እህት እንዲህ ብላለች፦ “እየተጠናኑ ያሉ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ጫና ይደርስባቸዋል። በዚህም የተነሳ እየተጠናኑ ያሉ አንዳንድ ጥንዶች እንደማይጣጣሙ ቢገባቸውም ግንኙነታቸውን ከማቋረጥ ወደኋላ ይላሉ። ሌሎች ያላገቡ ክርስቲያኖች ደግሞ ከናካቴው ከመጠናናት ወደኋላ ይላሉ። ምክንያቱም ጫናው በጣም ከባድ ነው።”
በደንብ ተዋወቁ
5-6. እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶች አንዳቸው ስለ ሌላው የትኞቹን ነገሮች ማወቅ ይኖርባቸዋል? (1 ጴጥሮስ 3:4)
5 እየተጠናናችሁ ከሆነ ለመጋባት ወይም ላለመጋባት ለመወሰን ምን ሊረዳችሁ ይችላል? በደንብ ተዋወቁ። መጠናናት ከመጀመራችሁ በፊትም ስለ ግለሰቡ አንዳንድ ነገሮችን እንደምታውቁ ምንም ጥያቄ የለውም። አሁን ግን ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ለማወቅ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝታችኋል። (1 ጴጥሮስ 3:4ን አንብብ።) ይህም ለማግባት ስለምታስቡት ሰው መንፈሳዊነት፣ ባሕርይና አስተሳሰብ በደንብ ማወቅን ይጨምራል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን መመለስ መቻል ይኖርባችኋል፦ ‘ግለሰቡ ጥሩ የትዳር አጋር ይሆነኛል?’ (ምሳሌ 31:26, 27, 30፤ ኤፌ. 5:33፤ 1 ጢሞ. 5:8) ‘አንዳችን የሌላውን ስሜታዊ ፍላጎት ማሟላት እንችላለን? አንዳችን የሌላውን ድክመት ችለን መኖር እንችላለን?’ b (ሮም 3:23) ይበልጥ እየተዋወቃችሁ ስትሄዱ የሚከተለውን ነጥብ አስታውሱ፦ እርስ በርስ የምትጣጣሙ መሆናችሁ በዋነኝነት የተመካው ምን ያህል ትመሳሰላላችሁ በሚለው ላይ ሳይሆን ልዩነታችሁን ምን ያህል አቻችላችሁ መኖር ትችላላችሁ በሚለው ላይ ነው።
6 በምትጠናኑበት ወቅት ስለ ግለሰቡ ሌላስ ምን ማወቅ ይኖርባችኋል? በስሜት በጣም ከመቀራረባችሁ በፊት ግቦቻችሁን ጨምሮ ስለ አንዳንድ አስፈላጊ ጉዳዮች መወያየታችሁ ጠቃሚ ነው። ይሁንና የጤንነት ሁኔታን፣ የገንዘብ ችግርን ወይም በማንነታችሁ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ መጥፎ ትዝታዎችን ጨምሮ ስለ አንዳንድ የግል ጉዳዮችስ ምን ማለት ይቻላል? መጠናናት እንደጀመራችሁ ስለ ሁሉም ርዕሰ ጉዳዮች መነጋገር አለባችሁ ማለት አይደለም። (ከዮሐንስ 16:12 ጋር አወዳድር።) አንዳንድ ጥያቄዎችን ለመመለስ የትውውቃችሁ ደረጃ እንደማይፈቅድ ከተሰማችሁ ለግለሰቡ በግልጽ ንገሩት። ይሁንና እየተጠናናችሁ ያላችሁት ሰው ሚዛናዊ የሆነ ውሳኔ ማድረግ እንዲችል ይዋል ይደር እንጂ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ማወቅ ያስፈልገዋል። ስለዚህ የሆነ ወቅት ላይ ስለ እነዚህ ጉዳዮች መነጋገር ይኖርባችኋል።
7. እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶች ይበልጥ መተዋወቅ የሚችሉት እንዴት ነው? (“ በርቀት መጠናናት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
7 የግለሰቡን ውስጣዊ ማንነት ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ከሚቻልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ በግልጽና በሐቀኝነት መነጋገር፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንዲሁም በጥሞና ማዳመጥ ነው። (ምሳሌ 20:5፤ ያዕ. 1:19) ለዚህም ሲባል ለማውራት በሚያመቹ እንቅስቃሴዎች መካፈላችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አብራችሁ መብላት፣ ሰዋራ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ በእግር መንሸራሸር ወይም አብራችሁ ማገልገል ትችላላችሁ። ከጓደኞቻችሁና ከቤተሰቦቻችሁ ጋር አብራችሁ ጊዜ ማሳለፋችሁም እርስ በርስ ለመተዋወቅ ሊረዳችሁ ይችላል። ከዚህም ሌላ፣ ግለሰቡ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሁም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ሲሆን ምን ዓይነት ምግባር እንደሚያሳይ ለማወቅ በሚያስችሏችሁ እንቅስቃሴዎች ተካፈሉ። በኔዘርላንድስ የሚኖረው አሽዊን ምን እንዳደረገ እንመልከት። ከአሊሻ ጋር ይጠናኑ በነበረበት ወቅት ምን ያደርጉ እንደነበር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ይበልጥ ለመተዋወቅ በሚረዱን እንቅስቃሴዎች ለመካፈል እንሞክር ነበር። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግ ከፍተኛ ጥረት አይጠይቅም። አብረን ምግብ እናበስላለን ወይም ሌሎች ሥራዎችን እንሠራለን። እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች ስንካፈል አንዳችን የሌላውን ጠንካራና ደካማ ጎን ማየት ችለናል።”
8. የሚጠናኑ ጥንዶች አብረው ማጥናታቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
8 ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች አብራችሁ በማጥናትም ይበልጥ መተዋወቅ ትችላላችሁ። ከተጋባችሁ፣ አምላክ የትዳራችሁ ዋነኛ ክፍል እንዲሆን ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ መመደብ ይጠበቅባችኋል። (መክ. 4:12) ታዲያ ከአሁኑ ማለትም እየተጠናናችሁ ባላችሁበት ወቅት አብራችሁ ለማጥናት ለምን ጊዜ አትመድቡም? እርግጥ ነው፣ እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶች ገና ቤተሰብ አልሆኑም፤ ወንድምም ቢሆን ገና የእህት ራስ አልሆነም። ያም ቢሆን አዘውትራችሁ አብራችሁ ማጥናታችሁ አንዳችሁ ስለ ሌላው መንፈሳዊነት ለማወቅ ይረዳችኋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ማክስ እና ላይሳ እንዲህ ማድረጋቸው ሌላ ጥቅምም እንዳለው ተገንዝበዋል። ማክስ እንዲህ ብሏል፦ “መጠናናት እንደጀመርን አካባቢ ስለ ፍቅር ግንኙነት፣ ስለ ትዳርና ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚገልጹ ጽሑፎችን እናጠና ነበር። እነዚህ ጽሑፎች በራሳችን ቢሆን ኖሮ ላናነሳቸው በምንችላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንድንወያይ መንገድ ከፍተውልናል።”
ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ሌሎች ነገሮች
9. በመጠናናት ላይ ያሉ ጥንዶች እየተጠናኑ መሆኑን ከመናገር ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል?
9 እየተጠናናችሁ እንዳለ ለማን መንገር ይኖርባችኋል? ይህን ተነጋግራችሁ መወሰን ያለባችሁ እናንተ ናችሁ። መጀመሪያ አካባቢ ለጥቂት ሰዎች ብቻ ለመናገር ትወስኑ ይሆናል። (ምሳሌ 17:27) እንዲህ ማድረጋችሁ ከአላስፈላጊ ጫናና ጥያቄ ሊጠብቃችሁ ይችላል። ይሁንና ለማንም ካልተናገራችሁ ሌሎች እንዳያውቁ በሚል ፍርሃት ገለልተኛ ቦታ ላይ ለመገናኘት ልትፈተኑ ትችላላችሁ። ይህ ደግሞ ለአደጋ ሊያጋልጣችሁ ይችላል። ስለዚህ ቢያንስ ጥሩ ምክርና ተግባራዊ እርዳታ ሊሰጧችሁ ለሚችሉ ሰዎች መንገራችሁ ጥበብ ይሆናል። (ምሳሌ 15:22) ለምሳሌ ለአንዳንድ የቤተሰባችሁ አባላት፣ የጎለመሱ ጓደኞቻችሁ ወይም የጉባኤ ሽማግሌዎች መናገር ትችላላችሁ።
10. በመጠናናት ላይ ያሉ ጥንዶች ግንኙነታቸው ክብር ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ምሳሌ 22:3)
10 ክብር ባለው መንገድ መጠናናት የምትችሉት እንዴት ነው? ይበልጥ እየተዋደዳችሁ ስትሄዱ በመካከላችሁ ያለው መሳሳብ ይጨምራል። ታዲያ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችሁን ለመጠበቅ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? (1 ቆሮ. 6:18) ሥነ ምግባር የጎደለው ጭውውት ከማድረግ፣ ብቻችሁን አብራችሁ ከመሆን እንዲሁም ከልክ በላይ ከመጠጣት ተቆጠቡ። (ኤፌ. 5:3) እነዚህ ነገሮች የፆታ ስሜትን ሊቀሰቅሱ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ያላችሁን ቁርጠኝነት ሊያዳክሙት ይችላሉ። ግንኙነታችሁ ክብር ያለው እንዲሆን የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንደምትችሉ ለምን አዘውትራችሁ አትወያዩም? (ምሳሌ 22:3ን አንብብ።) በኢትዮጵያ የሚኖሩትን ዳዊትንና አልማዝን ምን እንደረዳቸው እንመልከት። እንዲህ ብለዋል፦ “ጊዜ የምናሳልፈው ብዙ ሰዎች ባሉበት አካባቢ ወይም ከሌሎች ጓደኞቻችን ጋር ነበር። መኪና ውስጥ ወይም ቤት ውስጥ በፍጹም ብቻችንን አንሆንም። ይህም ከፈታኝ ሁኔታዎች እንድንርቅ ረድቶናል።”
11. በመጠናናት ላይ ያሉ ጥንዶች ከፍቅር መግለጫዎች ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል?
11 የፍቅር መግለጫዎችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ግንኙነታችሁ እየተጠናከረ ሲመጣ አንዳንድ የፍቅር መግለጫዎችን ማሳየታችሁ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ይሁንና የፆታ ስሜታችሁ እያየለ ከመጣ ከግለሰቡ ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ ሊከብዳችሁ ይችላል። (መኃ. 1:2፤ 2:6) ከዚህም ሌላ የፍቅር መግለጫዎች በቀላሉ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑና ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ወደመፈጸም ሊመሩ ይችላሉ። (ምሳሌ 6:27) ስለዚህ መጠናናት ከጀመራችሁበት ጊዜ አንስቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መልኩ የትኞቹን ገደቦች እንደምታበጁ ተወያዩ። c (1 ተሰ. 4:3-7) እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘በምንኖርበት አካባቢ ያሉ ሰዎች አንዳችን ለሌላው የምናሳየውን የፍቅር መግለጫ እንዴት ይመለከቱታል? እነዚህ ድርጊቶች የፆታ ስሜት እንዲቀሰቀስብን ሊያደርጉ ይችሉ ይሆን?’
12. እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮችና አለመግባባቶች ጋር በተያያዘ ምን መገንዘብ ይኖርባቸዋል?
12 ችግሮችንና አለመግባባቶችን መፍታት የምትችሉት እንዴት ነው? አልፎ አልፎ አለመግባባት የሚያጋጥማችሁ ከሆነስ? የምትጣጣሙ ሰዎች አይደላችሁም ማለት ነው? ላይሆን ይችላል፤ ሁሉም ጥንዶች አለመግባባት ያጋጥማቸዋል። ጠንካራ ትዳር ልዩነቶቻቸውን ለማሸነፍ ተባብረው መሥራት የሚችሉ ሁለት ሰዎች ጥምረት ነው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ችግሮቻችሁን የምትፈቱበት መንገድ የሰመረ ትዳር መመሥረት የምትችሉ መሆን አለመሆኑን ሊጠቁም ይችላል። እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘በእርጋታና በአክብሮት መወያየት እንችላለን? ድክመቶቻችንን አምነን ለመቀበልና ማሻሻያ ለማድረግ ፈቃደኞች ነን? እሺ ለማለት፣ ይቅርታ ለመጠየቅና ይቅር ለማለት ፈጣኖች ነን?’ (ኤፌ. 4:31, 32) ይሁንና በምትጠናኑበት ወቅት ሁልጊዜ የምትጣሉ ወይም የምትጨቃጨቁ ከሆነ ከተጋባችሁ በኋላ ሁኔታው ይሻሻላል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ አይደለም። ግለሰቡ ለእናንተ እንደማይሆናችሁ ከተገነዘባችሁ ግንኙነታችሁን ማቆሙ ለሁለታችሁም የተሻለ ነው። d
13. አንድ ወንድና አንዲት ሴት ምን ያህል ጊዜ እየተጠናኑ መቆየት እንዳለባቸው ለመወሰን የትኞቹን ነገሮች ከግምት ማስገባት ይኖርባቸዋል?
13 ለምን ያህል ጊዜ እየተጠናናችሁ ልትቆዩ ይገባል? የችኮላ ውሳኔ ማድረግ ብዙውን ጊዜ አስከፊ መዘዝ ያስከትላል። (ምሳሌ 21:5) ስለዚህ በደንብ እስክትተዋወቁ ድረስ እየተጠናናችሁ ልትቆዩ ይገባል። ሆኖም የምትጠናኑበትን ጊዜ ሳያስፈልግ ማራዘም አይኖርባችሁም። መጽሐፍ ቅዱስም “የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል” ይላል። (ምሳሌ 13:12) ከዚህም ሌላ፣ የምትጠናኑበት ጊዜ እየረዘመ ሲሄድ የፆታ ፈተናን መቋቋም ይበልጥ ሊከብዳችሁ ይችላል። (1 ቆሮ. 7:9) ‘በመጠናናት ያሳለፍነው ጊዜ ምን ያህል ነው’ በሚለው ላይ ከማተኮር ይልቅ እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ውሳኔ ከማድረጌ በፊት ስለ ግለሰቡ ላውቅ የሚገባኝ ሌላ ነገር አለ?’
ሌሎች በመጠናናት ላይ ያሉ ጥንዶችን መደገፍ የሚችሉት እንዴት ነው?
14. ሌሎች እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶችን መርዳት የሚችሉት በየትኞቹ ተግባራዊ መንገዶች ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 በመጠናናት ላይ ያሉ ጥንዶችን የምናውቅ ከሆነ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? አብረውን እንዲመገቡ፣ በቤተሰብ አምልኳችን ላይ እንዲገኙ ወይም አብረውን እንዲዝናኑ ልንጋብዛቸው እንችላለን። (ሮም 12:13) እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ይበልጥ ለመተዋወቅ ሊረዷቸው ይችላሉ። ብቻቸውን እንዳይሆኑ አብረናቸው ልንሆን፣ በመኪና ልንወስዳቸው ወይም በነፃነት የሚያወሩበት ቦታ ልናመቻችላቸው እንችላለን። (ገላ. 6:10) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አሊሻ፣ ወንድሞች እሷንና አሽዊንን የረዷቸው እንዴት እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ወንድሞች አብረን ጊዜ ማሳለፍ የምንችልበት ገለልተኛ ያልሆነ ቦታ ካስፈለገን ቤታቸው መምጣት እንደምንችል ሲነግሩን በጣም ተደሰትን።” የሚጠናኑ ጥንዶች ብቻቸውን እንዳይሆኑ አብረሃቸው እንድትሆን ከጠየቁህ አክብረው ስለጋበዙህ ልትደሰት ይገባል። ሙሉ በሙሉ ብቻቸውን እንዳትተዋቸው ተጠንቀቅ፤ ሆኖም ለብቻቸው ማውራት ሊፈልጉ ስለሚችሉ አጋጣሚውን ስጣቸው።—ፊልጵ. 2:4
15. ሌሎች እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶችን መርዳት የሚችሉበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? (ምሳሌ 12:18)
15 እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶችን መርዳት የምንችልበት ሌላው መንገድ በአንደበት አጠቃቀማችን ነው። አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን መቆጣጠር ሊያስፈልገን ይችላል። (ምሳሌ 12:18ን አንብብ።) ለምሳሌ አንድ ወንድምና አንዲት እህት መጠናናት እንደጀመሩ ለሌሎች ለመናገር እንጓጓ ይሆናል፤ ያም ቢሆን ወሬውን ራሳቸው መናገር ሊፈልጉ ይችላሉ። እየተጠናኑ ስላሉ ጥንዶች ሐሜት ማውራት ወይም ከግል ጉዳዮቻቸው ጋር በተያያዘ እነሱን መተቸት አይኖርብንም። (ምሳሌ 20:19፤ ሮም 14:10፤ 1 ተሰ. 4:11) ከዚህም ሌላ ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ወይም ሐሳቦችን በመሰንዘር ጫና ልናሳድርባቸው አይገባም። ኤሊዝ የተባለች እህትና ባለቤቷ እንዲህ ብለዋል፦ “እኛ ገና ስለ ሠርግ ሳናወራ ሌሎች ለሠርጋችን ምን ዓይነት ዕቅድ እንዳወጣን ሲጠይቁን እንሸማቀቅ ነበር።”
16. እየተጠናኑ የነበሩ ጥንዶች ግንኙነታቸውን ቢያቋርጡ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 እየተጠናኑ የነበሩ ጥንዶች ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ቢወስኑስ? ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ጥረት ከማድረግ ወይም ወገን ከመያዝ መቆጠብ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 4:15) ሌያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንዶች ከአንድ ወንድም ጋር መጠናናት ያቆምኩበትን ምክንያት በተመለከተ ግምታዊ ሐሳብ ሲሰነዝሩ እንደነበረ ሰማሁ። ይህም ስሜቴን በጣም ጎዳው።” ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለመለያየት ወስነዋል ማለት መጠናናቱ አልተሳካም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ብዙውን ጊዜ መጠናናቱ ዓላማውን እንዳከናወነ የሚጠቁም ነው፤ ምክንያቱም ጥንዶቹን ጥሩ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ረድቷቸዋል። ያም ቢሆን ይህ ውሳኔ የስሜት ቁስል ሊያስከትልባቸውና ብቸኝነት እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ እነሱን መደገፍ የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ እንችላለን።—ምሳሌ 17:17
17. እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶች ምን ማድረጋቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል?
17 እስካሁን እንደተመለከትነው መጠናናት ተፈታታኝ ነገሮች ሊኖሩት ይችላሉ፤ ሆኖም አስደሳች ሊሆን ይችላል። ጄሲካ እንዲህ ብላለች፦ “እውነቱን ለመናገር መጠናናት ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ሆኖም ለመጠናናት ያዋልነው ጊዜና ጉልበት ሙሉ በሙሉ የሚክስ ነው።” በአሁኑ ወቅት እየተጠናናችሁ ከሆነ በደንብ ለመተዋወቅ ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ በተሳካ ሁኔታ መጠናናት ይኸውም ሁለታችሁም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ላይ መድረስ ትችላላችሁ።
መዝሙር 49 የይሖዋን ልብ ማስደሰት
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b ሊታሰብባቸው የሚገቡ ሌሎች ጥያቄዎችን ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 ገጽ 39-40ን ተመልከት።
c የሌላን ሰው የፆታ ብልት ማሻሸት ከፆታ ብልግና ዓይነቶች አንዱ ሲሆን በኮሚቴ መታየት አለበት። ጡት ማሻሸት እንዲሁም የብልግና መልእክቶችን በጽሑፍ መልእክት መላላክ ወይም የብልግና ይዘት ያለው ወሬ በስልክ ማውራትም እንደ ሁኔታው በኮሚቴ ሊታይ ይችላል።
d ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በነሐሴ 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።