የጥናት ርዕስ 5
“ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል”
‘በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል።’—2 ቆሮ. 5:14, 15
መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ
ማስተዋወቂያ a
1-2. (ሀ) ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ስናስብ ምን ሊሰማን ይችላል? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ናፍቆቱ በጣም ከባድ ይሆንብናል። መጀመሪያ አካባቢ የሞተበትን ሰሞን ስናስብ ውስጣችንን ያመናል፤ በተለይ አሟሟቱ ሥቃይ ከነበረው። እያደር ግን ሐዘኑ እየቀነሰ ይሄዳል። ግለሰቡ ያስተማረንን ነገር እናስታውሳለን፤ ምን ብሎ ወይም ምን አድርጎ ያበረታታን ወይም ያስቀን እንደነበረም ትዝ ይለናል። እነዚህ ትዝታዎች በኋላ ላይ ደስታ የሚያስገኙልን ነገር ይሆናሉ።
2 በተመሳሳይም ኢየሱስ ስለደረሰበት መከራና ስለ አሟሟቱ ስናስብ በጣም እናዝናለን። በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ቤዛው ስላለው ዋጋ ጊዜ ወስደን እንደምናስብ የታወቀ ነው። (1 ቆሮ. 11:24, 25) ያም ቢሆን በጥቅሉ ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ስለተናገራቸውና ስላከናወናቸው ነገሮች ማሰባችን ላቅ ያለ ደስታ ያስገኝልናል። በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገ እንዳለና ወደፊት ምን እንደሚያደርግልን ማሰባችንም በጣም ያበረታታናል። በእነዚህ ነገሮችና ለእኛ ባሳየን ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን አድናቆታችንን በተግባር እንድናሳይ ያነሳሳናል፤ ይህ ጉዳይ በዚህ ርዕስ ላይ በሰፊው ይብራራል።
አመስጋኝነት ኢየሱስን ለመከተል ያነሳሳናል
3. ለቤዛው አመስጋኝ እንድንሆን የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉን?
3 ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ሞት ስናስብ ልባችን በአመስጋኝነት ይሞላል። ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ለሰዎች አስተምሯል። እነዚህን የመንግሥቱን እውነቶች ትልቅ ቦታ እንሰጣቸዋለን። ቤዛው ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት አጋጣሚ ከፍቶልናል፤ ለዚህም አመስጋኞች ነን። በተጨማሪም በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ለዘላለም የመኖር እንዲሁም በሞት ያጧቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች ዳግም የማየት ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሮም 6:23) እነዚህ በረከቶች ይገባናል የምንላቸው አይደሉም፤ ምንም ብናደርግ አምላክና ክርስቶስ የዋሉልንን ውለታ መክፈልም አንችልም። (ሮም 5:8, 20, 21) ሆኖም የአመስጋኝነታችንን ጥልቀት ልናሳያቸው እንችላለን። እንዴት?
4. መግደላዊቷ ማርያም ኢየሱስ ላደረገላት ነገር አመስጋኝነቷን ያሳየችው እንዴት ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)
4 መግደላዊት ማርያም የተባለች አይሁዳዊት ሴት ያደረገችውን እንመልከት። ሰባት አጋንንት ስላደሩባት በጣም ትሠቃይ ነበር። ከዚህ ሁኔታ የምትገላገልበት ምንም መንገድ እንደሌለ ተሰምቷት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ኢየሱስ ከአጋንንት ቁጥጥር ነፃ ሲያወጣት ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆነች መገመት ይቻላል! አመስጋኝነቷ የኢየሱስ ተከታይ እንድትሆን እንዲሁም ጊዜዋን፣ ጉልበቷንና ንብረቷን ተጠቅማ እሱን እንድታገለግል አነሳስቷታል። (ሉቃስ 8:1-3) ማርያም ኢየሱስ በግሏ ላደረገላት ነገር ጥልቅ አድናቆት እንደነበራት ግልጽ ነው፤ በኋላ ላይ ከዚህም እጅግ የላቀ ነገር እንደሚያደርግ ግን በወቅቱ አልተገነዘበች ይሆናል። “[በእሱ] የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው” ሲል ሕይወቱን ለሰው ልጆች ይሰጣል። (ዮሐ. 3:16) ማርያም ለኢየሱስ ታማኝ በመሆን አድናቆቷን አሳይታለች። ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በነበረበት ወቅት ማርያም በቦታው ተገኝታለች። በዚህ መንገድ እሱን እንደምትደግፍ አሳይታለች፣ ሌሎቹንም አጽናንታለች። (ዮሐ. 19:25) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ማርያምና ሌሎች ሁለት ሴቶች ቅመሞች ይዘው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር። (ማር. 16:1, 2) ማርያም ላሳየችው ታማኝነት በእጅጉ ተክሳለች። ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ስታገኝና ስታነጋግር ምን ያህል ተደስታ ይሆን! ይህ አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት ያላገኙት መብት ነው።—ዮሐ. 20:11-18
5. ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉልን ነገር አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 እኛም ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ንብረታችንን ተጠቅመን የመንግሥቱን ሥራ በመደገፍ ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉልን ነገር አመስጋኝነታችንን ማሳየት እንችላለን። ለምሳሌ ለንጹሕ አምልኮ የሚሆኑ ሕንፃዎችን በመገንባቱና በመንከባከቡ ሥራ ለማገዝ ራሳችንን ማቅረብ እንችላለን።
ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለን ፍቅር ሌሎችን እንድንወድ ያነሳሳናል
6. ቤዛው በግለሰብ ደረጃ የተሰጠን ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
6 ይሖዋና ኢየሱስ ምን ያህል እንደሚወዱን ስናስብ እኛም በምላሹ እነሱን ለመውደድ እንነሳሳለን። (1 ዮሐ. 4:10, 19) ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን እንደሞተ መገንዘባችን ደግሞ ይበልጥ እንድንወዳቸው ያደርገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ እውነታ ያለውን አድናቆት ገልጿል፤ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘የአምላክ ልጅ ወዶኛል፤ ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ ብሏል። (ገላ. 2:20) ይሖዋ ቤዛውን መሠረት በማድረግ ወዳጁ እንድትሆን ወደ ራሱ ስቦሃል። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ አንድ መልካም ነገር እንዳየብህና ወዳጁ እንድትሆን ሲል ከሁሉ የላቀውን ዋጋ እንደከፈለ ስታስብ ልብህ በጥልቅ አይነካም? ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለህ ፍቅርስ አይጨምርም? እንግዲያው ‘ይህ ፍቅር ምን እንዳደርግ ግድ ይለኛል?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።
7. በሥዕሉ ላይ እንደሚታየው ሁላችንም ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15፤ 6:1, 2)
7 ለአምላክና ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ለሌሎች ፍቅር እንድናሳይ ያነሳሳናል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን እና 6:1, 2 አንብብ።) ፍቅራችንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል ነው። ላገኘነው ሰው ሁሉ እንሰብካለን። ሰዎች ዘራቸው፣ ብሔራቸው፣ የኑሮ ደረጃቸው ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ምንም ሆነ ምን ማንንም ሳንመርጥ ሁሉንም ሰው እናናግራለን። በዚህ መንገድ የይሖዋ ፈቃድ እንዲፈጸም እናደርጋለን፤ “የእሱ ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።”—1 ጢሞ. 2:4
8. ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
8 ለአምላክና ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ማሳየት ነው። (1 ዮሐ. 4:21) በግለሰብ ደረጃ ትኩረት እንሰጣቸዋለን፤ ችግር ሲያጋጥማቸው ደግሞ እናግዛቸዋለን። የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ እናጽናናቸዋለን፤ ሲታመሙ እንጠይቃቸዋለን እንዲሁም ተስፋ ሲቆርጡ እናበረታታቸዋለን። (2 ቆሮ. 1:3-7፤ 1 ተሰ. 5:11, 14) “ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል” እንዳለው ስለምናውቅ ሁሌም እንጸልይላቸዋለን።—ያዕ. 5:16
9. ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር እንዳለን ለማሳየት ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን?
9 ሰላም ፈጣሪ ለመሆን ጥረት በማድረግም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን። ይሖዋን በይቅር ባይነቱ ለመምሰል ጥረት እናደርጋለን። ይሖዋ ለኃጢአታችን ሲል ልጁ እንዲሞት ከፈቀደ እኛስ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሲበድሉን ይቅር ልንላቸው አይገባም? በአንደኛው የኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ክፉ ባሪያ መሆን አንፈልግም። ጌታው ያን ሁሉ ዕዳ ቢተውለትም እሱ ግን በጣም ትንሽ ዕዳ ያለበትን እንደ እሱ ያለ ባሪያ ሊምረው አልፈለገም። (ማቴ. 18:23-35) በጉባኤ ካለ አንድ ሰው ጋር አለመግባባት አጋጥሞህ ከነበረ ከመታሰቢያው በዓል በፊት ሰላም ለመፍጠር ለምን ቅድሚያውን አትወስድም? (ማቴ. 5:23, 24) እንዲህ ማድረግህ ይሖዋና ኢየሱስን ከልብህ እንደምትወዳቸው ያሳያል።
10-11. ሽማግሌዎች ለይሖዋና ለኢየሱስ ፍቅር እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 5:1, 2)
10 ሽማግሌዎች ይሖዋንና ኢየሱስን እንደሚወዱ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የሚችሉበት አንዱ ወሳኝ መንገድ የኢየሱስን በጎች መንከባከብ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:1, 2ን አንብብ።) ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን በግልጽ ነግሮታል። ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ከካደው በኋላ ለጌታው ፍቅር እንዳለው ማሳየት የሚችልበት አጋጣሚ ለማግኘት ጓጉቶ መሆን አለበት። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ጴጥሮስን “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ትወደኛለህ?” ብሎ ጠየቀው። በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ለጌታው ያለውን ፍቅር ለማሳየት ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስም ጴጥሮስን “ግልገሎቼን ጠብቅ” አለው። (ዮሐ. 21:15-17) ደግሞም ጴጥሮስ በቀሪ ሕይወቱ ሁሉ የጌታውን በጎች በመንከባከብ ለኢየሱስ ያለውን ፍቅር አሳይቷል።
11 እናንት ሽማግሌዎች፣ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ለተናገረው ሐሳብ ትኩረት እንደምትሰጡ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው? በእረኝነቱ ሥራ አዘውትራችሁ በመካፈልና የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ለመርዳት ልዩ ጥረት በማድረግ ይሖዋንና ኢየሱስን ምን ያህል እንደምትወዷቸው ማሳየት ትችላላችሁ። (ሕዝ. 34:11, 12) በመታሰቢያው በዓል ላይ ለሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችና አዲሶች ትኩረት መስጠታችሁም አስፈላጊ ነው፤ እነሱም ነገ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ስለሚችሉ እንግድነት እንዳይሰማቸው ጥረት አድርጉ።
ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ደፋር እንድንሆን ያነሳሳናል
12. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት የተናገራቸውን ቃላት ማሰባችን ድፍረት የሚሰጠን ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 16:32, 33)
12 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐንስ 16:32, 33ን አንብብ።) ኢየሱስ ጠላቶቹን በድፍረት እንዲጋፈጥና እስከ ሞት ታማኝ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? በይሖዋ መታመኑ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹም ተመሳሳይ ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ስለሚያውቅ ይሖዋ እንዲጠብቃቸው ለምኗል። (ዮሐ. 17:11) ይህ ድፍረት የሚሰጠን ለምንድን ነው? ይሖዋ ከየትኛውም ጠላታችን በላይ ኃያል እንደሆነ ስለምናውቅ ነው። (1 ዮሐ. 4:4) ከይሖዋ እይታ የሚያመልጥ ነገር የለም። በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ፍርሃታችንን ማሸነፍና ደፋሮች መሆን እንደምንችል እርግጠኞች ነን።
13. የአርማትያሱ ዮሴፍ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው?
13 የአርማትያሱ ዮሴፍን ምሳሌ እንመልከት። በአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ውስጥ የተከበረ ሰው ነበር። የአይሁድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሆነው የሳንሄድሪን አባልም ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ዮሴፍ ደፋር አልነበረም። “ዮሴፍ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። ሆኖም አይሁዳውያንን ይፈራ ስለነበር ይህን ለማንም አልተናገረም” በማለት ዮሐንስ ተናግሯል። (ዮሐ. 19:38) ዮሴፍ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ቢኖረውም በኢየሱስ ማመኑን ከሌሎች ደብቆ ነበር። ይህን ያደረገው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን የተከበረ ቦታ እንዳያጣ ፈርቶ መሆን አለበት። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ዮሴፍ ‘ደፍሮ ወደ ጲላጦስ እንደገባና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው እንደጠየቀ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ማር. 15:42, 43) በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የኢየሱስ ተከታይ እንደሆነ በይፋ ታወቀ።
14. የሰው ፍርሃትን ለማሸነፍ ምን ማድረግ ትችላለህ?
14 አንተስ እንደ ዮሴፍ የሰው ፍርሃት አሽመድምዶህ ያውቃል? በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታህ የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ለመናገር የምትሸማቀቅበት ጊዜ አለ? ‘ሌሎች ምን ይሉኛል?’ የሚለው ፍርሃት አስፋፊ ለመሆን ወይም ለመጠመቅ እርምጃ እንዳትወስድ እንቅፋት ሆኖብሃል? እንዲህ ያሉት ስሜቶች ትክክል እንደሆነ የምታውቀውን ነገር ከማድረግ እንዲያግዱህ አትፍቀድ። ወደ ይሖዋ አጥብቀህ ጸልይ። የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስፈልግህን ድፍረት እንዲሰጥህ ጠይቀው። ይሖዋ ጸሎትህን እንዴት እየመለሰልህ እንዳለ ስታይ ብርታትና ድፍረት ታገኛለህ።—ኢሳ. 41:10, 13
ደስታ ይሖዋን ያለማሰለስ እንድናገለግል ያነሳሳናል
15. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከተገለጠላቸው በኋላ ያገኙት ደስታ ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል? (ሉቃስ 24:52, 53)
15 ኢየሱስ ሲሞት ደቀ መዛሙርቱ በጣም አዝነው ነበር። እስቲ ራስህን በእነሱ ቦታ አድርገህ ለማሰብ ሞክር። የሚወዱትን ወዳጃቸውን ብቻ አይደለም የተነጠቁት፤ ተስፋቸው እንደ ጉም በንኖ እንደጠፋም ተሰምቷቸው መሆን አለበት። (ሉቃስ 24:17-21) ሆኖም ኢየሱስ ተገለጠላቸውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ጋር በተያያዘ ያለውን ድርሻ ጊዜ ወስዶ አብራራላቸው። በተጨማሪም አንድ አስፈላጊ ሥራ ሰጣቸው። (ሉቃስ 24:26, 27, 45-48) ኢየሱስ ከ40 ቀናት በኋላ ወደ ሰማይ ባረገበት ወቅት የደቀ መዛሙርቱ ሐዘን ወደ ደስታ ተቀይሮ ነበር። ጌታቸው ሕያው እንደሆነና አዲሱን ተልእኳቸውን እንዲወጡ እንደሚረዳቸው ማወቃቸው ደስተኛ አድርጓቸዋል። ይህ ደስታ ደግሞ ይሖዋን ያለማሰለስ እንዲያወድሱ አነሳስቷቸዋል።—ሉቃስ 24:52, 53ን አንብብ፤ ሥራ 5:42
16. የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
16 የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ይሖዋን በደስታ በማገልገል ነው። ይህን ለማድረግ በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። ለምሳሌ ብዙዎች በአገልግሎት ለመካፈል፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንዲሁም በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ ሲሉ የሥራ ፕሮግራማቸውን አስተካክለዋል። አንዳንዶች ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ሥራዎችን ለማከናወን ወይም አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ሲሉ መሠረታዊ ተደርገው የሚታዩ ቁሳዊ ንብረቶችን ለመተው ፈቃደኛ ሆነዋል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋን ያለማሰለስ ማገልገል ጽናት ይጠይቃል፤ ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ለመንግሥቱ ቅድሚያ ከሰጠን አትረፍርፎ እንደሚባርከን ይሖዋ ቃል ገብቶልናል።—ምሳሌ 10:22፤ ማቴ. 6:32, 33
17. በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ምን ለማድረግ አስባችኋል? (ሥዕሉን ተመልከት።)
17 ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 4 የሚከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ ለመገኘት እንጓጓለን። በእርግጥ በኢየሱስ ሕይወትና ሞት እንዲሁም እሱና ይሖዋ ባሳዩን ፍቅር ላይ ለማሰላሰል እስከዚያ ቀን ድረስ መጠበቅ አያስፈልገንም። በመታሰቢያው በዓል ሰሞን በሙሉ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ ፈልጉ። ለምሳሌ አዲስ ዓለም ትርጉም ተጨማሪ መረጃ ለ12 ላይ “ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት የመጨረሻ ሳምንት” የሚል ሰንጠረዥ አለ፤ በዚህ ሰንጠረዥ ላይ የሚገኙትን ክንውኖች ለማንበብና በዚያ ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መድቡ። ይህን ስታደርጉ አመስጋኝነታችሁን፣ ፍቅራችሁን፣ ድፍረታችሁንና ደስታችሁን የሚጨምሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለማስተዋል ሞክሩ። ከዚያም ልባዊ አድናቆታችሁን ማሳየት የምትችሉባቸውን ተግባራዊ መንገዶች ፈልጉ። ኢየሱስ በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያው በዓል ሰሞን እሱን ለማሰብ የምታደርጉትን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኞች ሁኑ።—ራእይ 2:19
መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”
a በመታሰቢያው በዓል ሰሞን በኢየሱስ ሕይወትና ሞት እንዲሁም እሱና አባቱ ባሳዩን ፍቅር ላይ እንድናሰላስል ማበረታቻ ይሰጠናል። እንዲህ ማድረጋችን ለተግባር ያነሳሳናል። ይህ ርዕስ ለቤዛው ያለንን አድናቆት እንዲሁም ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ያብራራል። ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንድንወድ፣ ድፍረት እንድናሳይ እንዲሁም በደስታ እንድናገለግል የሚያነሳሳን ምን እንደሆነም እናያለን።