እውነትን አስተምሩ
“ይሖዋ ሆይ፣ . . . የቃልህ ፍሬ ነገር እውነት ነው።”—መዝ. 119:159, 160
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የሰጠው ለየትኛው ሥራ ነው? ለምንስ? (ለ) “ከአምላክ ጋር አብረን [ስንሠራ]” ስኬታማ ለመሆን ምን ይረዳናል?
ኢየሱስ ክርስቶስ አናጺና አስተማሪ ነበር። (ማር. 6:3፤ ዮሐ. 13:13) በሁለቱም ሙያዎች በጣም የተካነ ነበር። አናጺ እንደመሆኑ መጠን፣ ለሥራው የሚያስፈልጉትን መሣሪያዎች ተጠቅሞ እንጨትን ጠቃሚ ወደሆኑ ዕቃዎች መለወጥ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተምሮ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የምሥራቹ አስተማሪ እንደመሆኑ መጠን፣ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያለውን ጥልቅ እውቀት ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቅሞ ተራ የሆኑ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ማስተዋል እንዲችሉ ይረዳ ነበር። (ማቴ. 7:28፤ ሉቃስ 24:32, 45) ኢየሱስ 30 ዓመት ሲሞላው የአናጺነት መሣሪያዎቹን ትቶ ትኩረቱን ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው የማስተማሩ ሥራ ላይ አደረገ። አምላክ እሱን ወደ ምድር ከላከበት ምክንያቶች መካከል አንዱ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲያውጅ መሆኑን ተናግሯል። (ማቴ. 20:28፤ ሉቃስ 3:23፤ 4:43) ኢየሱስ አገልግሎቱ በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ እንዲይዝ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም በዚህ ሥራ አብረውት እንዲካፈሉ ይፈልግ ነበር።—ማቴ. 9:35-38
2 አብዛኞቻችን አናጺዎች አይደለንም፤ ሆኖም ሁላችንም የምሥራቹ አገልጋዮች ነን። ይህ ሥራ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ አምላክ ራሱ በሥራው ይካፈላል፤ እኛም “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።” (1 ቆሮ. 3:9፤ 2 ቆሮ. 6:4) “[የይሖዋ ቃል] ፍሬ ነገር እውነት” እንደሆነ እናውቃለን። (መዝ. 119:159, 160) በመሆኑም በአገልግሎት ስንካፈል “የእውነትን ቃል በአግባቡ [መጠቀማችን]” በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። (2 ጢሞቴዎስ 2:15ን አንብብ።) ከዚህ አንጻር ዋነኛ መሣሪያችን የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን ለሰዎች ስለ ይሖዋ፣ ስለ ኢየሱስና ስለ አምላክ መንግሥት እውነቱን የማስተማር ችሎታችንን እያሻሻልን መሄድ እንፈልጋለን። የይሖዋ ድርጅት በአገልግሎታችን ስኬታማ እንድንሆን የሚረዱንን ጠቃሚ መሣሪያዎች አዘጋጅቶልናል፤ ከእነዚህ መሣሪያዎች ጋር በደንብ ልንተዋወቅ ይገባል። መሣሪያዎቹ “የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን” ተብለው ይጠራሉ።
3. የስብከቱ ሥራ ከማብቃቱ በፊት ባለን አጭር ጊዜ ውስጥ በዋነኝነት ትኩረት ማድረግ ያለብን በምን ላይ ነው? ሥራ 13:48 በዚህ ረገድ የሚረዳን እንዴት ነው?
3 እነዚህ መሣሪያዎች “የስብከት መሣሪያዎቻችን” ሳይሆን “የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን” የተባሉት ለምንድን ነው? “መስበክ” አንድን መልእክት ማወጅ ማለት ነው፤ “ማስተማር” ግን መልእክቱ ወደ ግለሰቡ ልብና አእምሮ ዘልቆ እንዲገባ በማድረግ ግለሰቡን ለተግባር ማነሳሳትንም ይጨምራል። የስብከቱ ሥራ ከማብቃቱ በፊት ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ በዋነኝነት ትኩረት ማድረግ ያለብን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማስጀመርና ለሰዎች እውነትን በማስተማር ላይ መሆን ይኖርበታል። በሌላ አባባል “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ [ያላቸውን]” ሰዎች ለመፈለግ ልባዊ ጥረት ማድረግና አማኞች እንዲሆኑ መርዳት ይኖርብናል።—የሐዋርያት ሥራ 13:44-48ን አንብብ።
4. “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” እነማን እንደሆኑ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህን ሰዎች ማግኘት የምንችለውስ እንዴት ነው?
4 “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” እነማን እንደሆኑ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማወቅ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ያደርጉ እንደነበረው ምሥክርነት መስጠት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “በምትገቡበት ማንኛውም ከተማ ወይም መንደር መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው ፈልጉ” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። (ማቴ. 10:11) ቅን ልቦና የሌላቸው፣ ኩሩ ወይም መንፈሳዊ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ለምሥራቹ በጎ ምላሽ እንዲሰጡ አንጠብቅም። የምንፈልገው ሐቀኛ፣ ትሑትና መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ሰዎችን ነው። ይህን ፍለጋ ኢየሱስ የአናጺነት ሥራውን ሲያከናውን አድርጎት ሊሆን ከሚችለው ነገር ጋር ልናመሳስለው እንችላለን፤ በመጀመሪያ የቤት ዕቃ፣ በር፣ ቀንበር ወይም ሌሎች ነገሮችን ለመሥራት ተስማሚ የሆነውን የእንጨት ዓይነት ይፈልጋል። ከዚያ በኋላ መሣሪያዎቹንና የእንጨት ሥራ ችሎታውን ተጠቅሞ የፈለገውን ዕቃ ይሠራል። እኛም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ስንጥር ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አለብን።—ማቴ. 28:19, 20
5. “በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን” ውስጥ የተካተተውን እያንዳንዱን መሣሪያ በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብናል? በምሳሌ አስረዳ። (በመግቢያው ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ተመልከት።)
5 አንድ ባለሙያ የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ሁሉ የየራሳቸው አገልግሎት አላቸው። ኢየሱስ ተጠቅሞባቸው ሊሆን የሚችሉትን የአናጺ መሣሪያዎች እንደ ምሳሌ እንመልከት። * እንጨት ለመለካትና ምልክት ለማድረግ፣ ለመቁረጥ፣ ለመቦርቦርና ቅርጽ ለመስጠት፣ ውኃ ልክ ለመጠበቅና ቁርጥራጮቹን ለማያያዝ የተለያዩ መሣሪያዎችን መጠቀም ያስፈልገው ነበር። በተመሳሳይም “በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን” ውስጥ የተካተተው እያንዳንዱ መሣሪያ የራሱ አገልግሎት አለው። እስቲ እነዚህን አስፈላጊ መሣሪያዎች እንዴት መጠቀም እንደምንችል አንድ በአንድ እንመልከት።
ሰዎች ስለ እኛ እንዲያውቁ ለመርዳት የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች
6, 7. (ሀ) የአድራሻ ካርዶችን እየተጠቀምክባቸው ያለኸው እንዴት ነው? (ለ) የጉባኤ ስብሰባ መጋበዣ ምን ሁለት ዓላማዎች አሉት?
6 የአድራሻ ካርዶች። እነዚህ ካርዶች ሰዎች ስለ እኛ እንዲያውቁና ድረ ገጻችንን እንዲጎበኙ ለመርዳት የምንጠቀምባቸው በመጠን አነስተኛ ሆኖም ውጤታማ መሣሪያዎች ናቸው። በድረ ገጻችን አማካኝነት ሰዎች ስለ እኛ ይበልጥ ማወቅ አልፎ ተርፎም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ። እስከዛሬ ድረስ ከ400,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በjw.org አማካኝነት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ጥያቄ ያቀርባሉ! የዕለት ተዕለት ጉዳያችሁን በምታከናውኑበት ወቅት ለምታገኟቸው ሰዎች መመሥከር እንድትችሉ የተወሰኑ የአድራሻ ካርዶችን መያዛችሁ ጠቃሚ ነው።
7 መጋበዣዎች። በተለምዶ የጉባኤ ስብሰባ መጋበዣ ብለን የምንጠራው መጋበዣ ወረቀት ሁለት ዓላማዎች አሉት። መጋበዣው “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ ተጋብዘዋል” ይላል። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን “በስብሰባዎቻችን ላይ በመገኘት” “ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ጋር በግል በመወያየት” መማር እንደሚቻል ይገልጻል። በመሆኑም ይህ መሣሪያ ሌሎች ስለ እኛ እንዲያውቁ ከመርዳት ባለፈ “መንፈሳዊ ነገሮችን ማቴ. 5:3) እርግጥ ነው፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ፈለጉም አልፈለጉ በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ይችላሉ። ይህም የምናስተምረው ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል።
የተጠሙ” ሰዎች ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ይጋብዛል። (8. ሰዎች ቢያንስ አንድ ጊዜ በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
8 ሰዎች ቢያንስ አንድ ጊዜ በስብሰባዎቻችን ላይ እንዲገኙ መጋበዛችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በሚገኝባቸው ስብሰባዎቻችንና በመንፈሳዊ ድርቅ በተመታችው ታላቂቱ ባቢሎን መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ማስተዋል የሚችሉት በስብሰባዎቻችን ላይ ሲገኙ ነው። (ኢሳ. 65:13) በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሬይ እና ሊንዳ የተባሉ አንድ ባልና ሚስት ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ይህን አስተውለዋል። እነዚህ ባልና ሚስት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እንዳለባቸው ወሰኑ። በአምላክ መኖር የሚያምኑ ሲሆን መንፈሳዊ ፍላጎትም ነበራቸው፤ በመሆኑም በከተማቸው ውስጥ ያሉትን ቤተ ክርስቲያናት በሙሉ አንድ በአንድ ለማየት አሰቡ። በአካባቢያቸው በርካታ ቤተ ክርስቲያናትና የሃይማኖት ቡድኖች ነበሩ። ባልና ሚስቱ፣ አባል የሚሆኑበት ቤተ ክርስቲያን ማሟላት ያለበትን ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠው ነበር። አንደኛው ‘በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ላይ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት አለብን’ የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‘የቤተ ክርስቲያኑ አባላት አምላክን ከሚወክሉ ሰዎች የሚጠበቅ አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል’ የሚል ነው። ከዓመታት በኋላ፣ በከተማቸው ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ቤተ ክርስቲያን ያዳረሱ ሲሆን ባዩት ነገር በጣም ተስፋ ቆረጡ። አንዳች ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ከመሆኑም ሌላ የቤተ ክርስቲያናቱ አባላት አለባበስ ፈጽሞ ለአምላክ ክብር እንደማያመጣ አስተዋሉ። ሊጎበኟቸው ካሰቧቸው ቤተ ክርስቲያናት መካከል የመጨረሻውን ጎብኝተው ሲወጡ ሊንዳ ወደ ሥራዋ ሄደች፤ ሬይ ደግሞ ወደ ቤት ጉዞ ጀመረ። መኪናውን እየነዳ ሲሄድ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ተመለከተና ‘እነዚህን ሰዎች ለምን ገብቼ አላያቸውም?’ ብሎ አሰበ። ወደ ውስጥ ሲገባ ያየው ነገር እስከዚያ ጊዜ ድረስ ካየው ፈጽሞ የተለየ ነበር! ሁሉም አፍቃሪና የሚቀረቡ ከመሆናቸውም ሌላ ሥርዓታማ አለባበስ ነበራቸው። ሬይ የፊተኛው ወንበር ላይ የተቀመጠ ሲሆን ትምህርቱን በጣም ወደደው! የሬይ ሁኔታ ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቶ “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” ብሎ እንደተናገረ የገለጸውን ሐሳብ ያስታውሰናል። (1 ቆሮ. 14:23-25) ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሬይ እሁድ እሁድ በሚደረገው ስብሰባ ላይ አዘውትሮ መገኘት የጀመረ ሲሆን በኋላም በሳምንቱ መካከል በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረ። ሊንዳም በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች። እነዚህ ባልና ሚስት በ70ዎቹ ዕድሜ ላይ የነበሩ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማሙ፤ ከዚያም ተጠመቁ።
ውይይት ለመጀመር የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች
9, 10. (ሀ) ትራክቶች ለአጠቃቀም ቀላል ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የተባለውን ትራክት መጠቀም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
9 ትራክቶች። ውይይት ለመጀመር አመቺ የሆኑና ለአጠቃቀም ቀላል የሆኑ ስምንት ትራክቶች አሉን። እነዚህ ትራክቶች መውጣት ከጀመሩበት ከ2013 አንስቶ አምስት ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ቅጂዎች ታትመዋል! ደስ የሚለው ደግሞ እነዚህ ትራክቶች የተዘጋጁበት መንገድ ተመሳሳይ ስለሆነ የአንዱን አጠቃቀም አወቅን ማለት የሌሎቹንም አጠቃቀም እናውቃለን ማለት ነው። ታዲያ ትራክቶችን ተጠቅመን ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር የምንችለው እንዴት ነው?
10 ለምሳሌ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የሚለውን ትራክት ለመጠቀም አሰብክ እንበል። ፊተኛው ገጽ ላይ ያለውን ጥያቄ ለግለሰቡ አሳየውና “‘የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?’ ብለህ አስበህ ታውቃለህ?” በማለት ጠይቀው። ከዚያም “አንተ ምን ትላለህ?” ካልከው በኋላ ከሦስቱ መልሶች የትኛውን እንደሚመርጥ ጠይቀው። የሰጠው መልስ ትክክል ወይም ስህተት መሆኑን ሳትናገር ከትራክቱ ውስጠኛ ገጽ ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?” በሚለው ሥር የተጠቀሱትን ዳንኤል 2:44ን እና ኢሳይያስ 9:6ን አንብብለት። ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ ውይይቱን መቀጠል ትችላለህ። በመጨረሻም ከትራክቱ የኋላ ገጽ ላይ “ምን ይመስልሃል?” በሚለው ሥር የሚገኘውን “በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምን ዓይነት ሕይወት ይኖረናል?” የሚለውን ለተመላልሶ መጠየቅ የተዘጋጀ ጥያቄ ጠይቀው። ይህም ከግለሰቡ ጋር በቀጣዩ ጊዜ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል መሠረት ለመጣል ይረዳሃል። በቀጣዩ ጊዜ ስትገናኙ ጥናት ለማስጀመር ከምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል አንዱ የሆነውን ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለውን ብሮሹር ትምህርት 7 ልታሳየው ትችላለህ።
የሰዎችን ፍላጎት ለመቀስቀስ የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች
11. መጽሔቶቻችን የሚዘጋጁበት ዓላማ ምንድን ነው? ሆኖም ስለ እነዚህ መጽሔቶች ምን ማወቅ ይኖርብናል?
11 መጽሔቶች። በዓለማችን ላይ ካሉት መጽሔቶች መካከል በስፋት በመታተምና በመተርጎም ረገድ የመጀመሪያውን ደረጃ የያዙት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ናቸው! መጽሔቶቹ በዓለም ዙሪያ ስለሚሰራጩ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚኖሩ ሰዎችን ትኩረት የሚስብ ርዕስ ይዘው እንዲወጡ ይደረጋል። እነዚህ መጽሔቶች ሰዎች በሕይወት ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር የማወቅ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመርዳት የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች ናቸው። ሆኖም የትኛውን መጽሔት ለማን እንደምናበረክት ለማወቅ መጽሔቶቹ የተዘጋጁት የትኞቹን አንባቢዎች ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል።
12. (ሀ) ንቁ! የተዘጋጀው እነማንን ታሳቢ በማድረግ ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? (ለ) በቅርቡ ይህን መሣሪያ ስትጠቀም ምን ጥሩ ውጤት አግኝተሃል?
12 ንቁ! የሚዘጋጀው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት እውቀት ያላቸውን ወይም ምንም እውቀት የሌላቸውን ሰዎች ታሳቢ በማድረግ ነው። እነዚህ ሰዎች የክርስትና ትምህርቶችን አያውቁ፣ በሃይማኖታዊ ድርጅቶች ላይ ጥርጣሬ ይኖራቸው ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን የሚጠቅም ሐሳብ እንደሌለው ይሰማቸው ይሆናል። የንቁ! ዋነኛ ዓላማ አንባቢዎቹ በአምላክ መኖር እንዲያምኑ የሚያደርግ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ነው። (ሮም 1:20፤ ዕብ. 11:6) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ቃል” እንደሆነ እንዲያምኑ መርዳት ነው። (1 ተሰ. 2:13) በ2018 የወጡት ሦስት ንቁ! መጽሔቶች የሽፋን ርዕስ “ደስታ የሚያስገኝ መንገድ፣” “ቤተሰብ ስኬታማ እንዲሆን የሚረዱ 12 ወሳኝ ነገሮች” እና “ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ” የሚል ነው።
13. (ሀ) ለሕዝብ የሚሰራጨው የመጠበቂያ ግንብ እትም የተዘጋጀው እነማንን ታሳቢ በማድረግ ነው? (ለ) በቅርቡ ይህን መሣሪያ ስትጠቀም ምን ጥሩ ውጤት አግኝተሃል?
13 ለሕዝብ የሚሰራጨው መጠበቂያ ግንብ ለአምላክም ሆነ ለቃሉ በተወሰነ መጠን አክብሮት ላላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን ያብራራል። እነዚህ ሰዎች የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ቢኖራቸውም ስለ ትምህርቶቹ ትክክለኛ ግንዛቤ የላቸውም። (ሮም 10:2፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4) በ2018 የወጡት ሦስት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች “መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዘመንም ጠቃሚ ነው?” “የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣል?” እና “አምላክ ለአንተ ያስብልሃል?” ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።
ሰዎችን ለተግባር ለማነሳሳት የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች
14. (ሀ) በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የተካተቱት አራት ቪዲዮዎች ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) እነዚህን ቪዲዮዎች በመጠቀም ምን ጥሩ ውጤት አግኝተሃል?
14 ቪዲዮዎች። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አናጺዎች የሚጠቀሙት የእጅ መሣሪያዎችን ብቻ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ አናጺዎች ግን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ እንደ መጋዝ፣ መቦርቦሪያ፣ ማለስለሻና ምስማር መምቻ ያሉ መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ። እኛም ታትመው ከሚወጡ ጽሑፎች በተጨማሪ በአገልግሎት ለምናገኛቸው ሰዎች የምናሳያቸው ግሩም ቪዲዮዎች ተዘጋጅተውልናል፤ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የተካተቱ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው እንዴት ነው? በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? እና ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ማወቅ ትፈልጋለህ? የሚል ርዕስ አላቸው። ከሁለት ደቂቃ ያነሰ ርዝማኔ ያላቸውን ቪዲዮዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ስንመሠክር ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ረዘም ያሉትን ደግሞ ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ ወይም ሰፋ ያለ ጊዜ ያላቸውን ሰዎች ስናነጋግር እንጠቀምባቸዋለን። እነዚህ ግሩም መሣሪያዎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑና በስብሰባዎቻችን ላይ እንዲገኙ ለማነሳሳት ይረዱናል።
15. ሰዎች ቪዲዮዎቻችንን በራሳቸው ቋንቋ መመልከታቸው ምን ውጤት እንዳለው የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ጥቀስ።
15 ቪዲዮዎቻችን ያላቸውን ጥቅም የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ እንመልከት። አንዲት እህት ከማይክሮኔዥያ ተዛውራ የመጣች የያፕኛ ተናጋሪ የሆነች ሴት ስታገኝ መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ በቋንቋዋ አሳየቻት። ቪዲዮው ሲጀምር ሴትየዋ እንዲህ አለች፦ “ይሄማ የራሴ ቋንቋ ነው። በጣም ይገርማል! ሰውየው እኔ የነበርኩበት ደሴት ሰው እንደሆነ አነጋገሩ ያስታውቃል። የሚናገረው የእኔን ቋንቋ ነው!” ከዚያም ከjw.org ላይ በቋንቋዋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን በሙሉ እንደምታነብና ቪዲዮዎችን እንደምትመለከት ተናገረች። (ከሥራ 2:8, 11 ጋር አወዳድር።) ሌላ ተሞክሮም እንመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት በሌላ አገር ለሚኖረው የወንድሟ ልጅ በራሱ ቋንቋ የተዘጋጀውን የዚህኑ ቪዲዮ ሊንክ ላከችለት። ቪዲዮውን ከተመለከተው በኋላ እንዲህ በማለት ጻፈላት፦ “በተለይ መላው ዓለም በክፉው ኃይል ሥር እንደሆነ የሚናገረው ክፍል ትኩረቴን ስቦታል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥያቄ አቅርቤያለሁ።” ይህ ግለሰብ የሚኖረው የስብከቱ ሥራችን በታገደበት አገር ነው።
እውነትን ለማስተማር የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች
16. የሚከተሉትን ብሮሹሮች ዓላማ ግለጽ፦ (ሀ) አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ። (ለ) ከአምላክ የተላከ ምሥራች! (ሐ) በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
16 ብሮሹሮች። የማንበብ ችሎታቸው ውስን ለሆነ ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በቋንቋቸው ለሌላቸው ሰዎች እውነትን ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው? ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀ መሣሪያ አለን፤ ይህም አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የሚለው ብሮሹር ነው። * ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለው ብሮሹር ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ ግሩም መሣሪያ ነው። ለምናነጋግረው ሰው በብሮሹሩ የኋላ ገጽ ላይ ያሉትን 14 ርዕሶች ካሳየነው በኋላ ይበልጥ ትኩረቱን የሚስበው የትኛው እንደሆነ ልንጠይቀው እንችላለን። ከዚያም በመረጠው ርዕስ ጥናት ልናስጀምረው እንችላለን። ተመላልሶ መጠየቆችህን ጥናት ለማስጀመር ይህን ዘዴ ተጠቅመህበት ታውቃለህ? በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የተካተተው ሦስተኛው ብሮሹር በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የሚለው ነው። ይህ ብሮሹር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ከድርጅቱ ጋር ለማስተዋወቅ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ይህን ብሮሹር በእያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራም ላይ መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ የመጋቢት 2017ን ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ ተመልከት።
17. (ሀ) ለማስጠናት የምንጠቀምባቸው መጻሕፍት እያንዳንዳቸው ምን ዓላማ አላቸው? (ለ) እድገት አድርገው የሚጠመቁ ሁሉ ምን ይጠበቅባቸዋል? ለምንስ?
17 መጻሕፍት። በብሮሹር ተጠቅመን ጥናት ካስጀመርን በኋላ በማንኛውም ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? ወደተባለው መጽሐፍ መሸጋገር እንችላለን። ይህ መሣሪያ ግለሰቡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ያለውን መሠረታዊ እውቀት ማስፋት እንዲችል ይረዳዋል። ይህን መጽሐፍ ከጨረስን በኋላ ግለሰቡ መንፈሳዊ እድገት እያደረገ ከሆነ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ የተባለውን መጽሐፍ ማስጠናታችንን መቀጠል እንችላለን። ይህ መሣሪያ ደግሞ ተማሪው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲገነዘብ ይረዳዋል። አዲሶች ቢጠመቁ እንኳ ሁለቱንም መጻሕፍት አጥንተው እስኪጨርሱ ድረስ ጥናታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አስታውሱ። ይህም በእውነት ውስጥ ጠንካራ መሠረት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።—ቆላስይስ 2:6, 7ን አንብብ።
18. (ሀ) አንደኛ ጢሞቴዎስ 4:16 እውነትን የምናስተምር እንደመሆናችን መጠን ምን እንድናደርግ ያበረታታናል? ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል? (ለ) የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችንን ስንጠቀም ግባችን ምን መሆን ይኖርበታል?
18 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ሰዎችን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው “የእውነት መልእክት ይኸውም [ምሥራቹ]” በአደራ ተሰጥቶናል። (ቆላ. 1:5፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16ን አንብብ።) ይህን ኃላፊነታችንን ለመወጣት እንዲረዳን ደግሞ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ አካትቶ የያዘ የማስተማሪያ መሣሪያ ተዘጋጅቶልናል። (“ የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን” የሚለውን ተመልከት።) እነዚህን መሣሪያዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተቻለንን ሁሉ እናድርግ። እያንዳንዱ አስፋፊ በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የተካተተውን የትኛውን ጽሑፍ በየትኛው ጊዜ ፍላጎት ላሳየ ሰው ማስተዋወቅ እንዳለበት መወሰን ይችላል። ሆኖም ዓላማችን ጽሑፎችን ማሰራጨት ብቻ እንዳልሆነ መዘንጋት አይኖርብንም፤ በተጨማሪም ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ ለማይሰጡ ሰዎች ጽሑፎቻችንን መስጠት አንፈልግም። ግባችን ሐቀኛ፣ ትሑትና መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ማለትም “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው።—ሥራ 13:48፤ ማቴ. 28:19, 20
^ አን.5 በነሐሴ 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አናጺው” የሚለውን ርዕስና “የአናጺው ዕቃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
^ አን.16 ግለሰቡ ጨርሶ ማንበብ የማይችል ከሆነ ጥቂት ጽሑፎችን ብቻ የያዘውን አምላክን ስማ የተባለውን ብሮሹር ይዞ እንዲከታተል ልታደርግ ትችላለህ።