ሕይወት ያላቸው ነገሮች ምን ይነግሩናል?
በዙሪያችን ያሉ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ያድጋሉ፣ ይንቀሳቀሳሉ እንዲሁም ይራባሉ። ፕላኔታችንን ልዩ ውበት ያጎናጽፏታል። በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆች፣ ሕይወት ስላላቸው ነገሮች ያላቸው እውቀት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጨምሯል። ታዲያ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ስለ ሕይወት አመጣጥ ምን ይነግሩናል? እስቲ እውነታውን እንመርምር።
ሕይወት ያላቸው ነገሮች የታሰበበት ንድፍ ያላቸው ይመስላሉ። ሴሎች ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተገነቡባቸው መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። ሴሎች ትንሽ ፋብሪካ ናቸው ሊባል ይችላል፤ ሕይወት እንዲቀጥልና እንዲራባ የሚያስፈልጉ እጅግ ውስብስብ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሥራዎችን ያከናውናሉ። እንዲህ ያለው የተራቀቀ ውስብስብነት በሁሉም ዓይነት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ላይ ይታያል። እርሾ ውስጥ ያለውን ይስት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይስት ባለአንድ ሴል ሕይወት ያለው ነገር ነው። ከሰው ልጆች ሴል ጋር ሲወዳደር የእርሾ ሴል ያልተወሳሰበ ሊመስል ይችላል። ግን በሚገርም ሁኔታ ውስብስብ ነው። የይስት ሴሎች ዲ ኤን ኤ ያለውና በሚገባ የተደራጀ ኒውክሊየስ አላቸው፤ ለሕልውናቸው አስፈላጊ የሆኑ ሂደቶችን የሚያከናውኑ በዓይን የማይታዩ “ማሽኖች” አሏቸው ሊባል ይችላል። እነዚህ ማሽኖች ሞለኪውሎቹን በመልክ በመልክ ይለዩዋቸዋል፣ ያጓጉዟቸዋል እንዲሁም ጥቅም ወዳለው ነገር ይቀይሯቸዋል። የይስት ሴል ምግብ ሲያልቅበት የሴሉ እንቅስቃሴ እንዲቀንስ የሚያደርግ አንድ ውስብስብ የሆነ የኬሚካል ሂደት ይጀምራል። በመሆኑም ይስቱ እንቅስቃሴውን ቢቀንስም በሕይወት ይቆያል። ኩሽናችን ውስጥ ያለው እርሾ፣ ሊጥ ውስጥ ሲገባ እንደገና የሚያንሰራራው በዚህ ሂደት የተነሳ ነው።
ሳይንቲስቶች የሰው ሴሎችን በተሻለ መንገድ ለመረዳት ሲሉ በይስት ሴሎች ላይ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ያም ቢሆን ብዙ የማያውቁት ነገር አለ። የቻልመርስ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮስ ኪንግ እንዲህ ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል፦ “እንደ ይስት ያለን ቀላል ነገር እንኳ ለመረዳት የሚያስፈልጉትን ሳይንሳዊ ሙከራዎች ለማድረግ በቂ የባዮሎጂ ባለሙያዎች የሉንም።”
አንተ ምን ትላለህ? ትንሽ የሚባለው የይስት ሴል እንኳ በአስገራሚ ሁኔታ ውስብስብ መሆኑ ንድፍ እንዳለው የሚጠቁም አይደለም? እንዲህ ያለው ንድፍ፣ ያለንድፍ አውጪ ሊገኝ ይችላል?
ሕይወት ሊገኝ የሚችለው ሕይወት ካለው ነገር ብቻ ነው። ዲ ኤን ኤ የተሠራው ኒክሊዮታይድ ከተባሉ ሞለኪውሎች ነው። በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ሴል 3.2 ቢሊዮን ኒክሊዮታይዶች አሉት። እነዚህ ሞለኪውሎች በትክክለኛው መንገድ ካልተዋቀሩ፣ ሴሉ ኤንዛይሞችን እና ፕሮቲኖችን ማምረት አይችልም።
በጣም ቀላል የሚባለው የኒክሊዮታይድ ገመድ እንኳ ትክክለኛውን አቀማመጥ በራሱ የማግኘት ዕድሉ ከ10150 አንድ ብቻ ነው (ይህ አኃዝ ከ1 በኋላ 150 ዜሮዎች ማለት ነው)። እንዲህ ያለው ክስተት ጨርሶ ሊሆን የማይችል ነው ሊባል ይችላል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ‘ሕይወት የተገኘው ሕይወት ከሌለው ነገር ነው’ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በየትኛውም ሳይንሳዊ ሙከራ አልተረጋገጠም።
የሰው ልጆች ሕይወት ካላቸው ነገሮች ሁሉ ይለያሉ። እኛ የሰው ልጆች ሌሎች ሕይወት ያላቸው ነገሮች የሌሏቸው፣ ሕይወትን ለማጣጣም የሚያስችሉ ብዙ ችሎታዎች አሉን። ላቅ ያለ የፈጠራ ችሎታ፣ ማኅበራዊ ክህሎትና ስሜት አለን። ቀምሰን፣ አሽትተን፣ ሰምተን እንዲሁም የተለያዩ ቀለማትን እና ነገሮችን አይተን መደሰት እንችላለን። ስለ ወደፊቱ ጊዜ እናቅዳለን እንዲሁም የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ ጥረት እናደርጋለን።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? እነዚህን ችሎታዎች ያዳበርናቸው በሕይወት ለመኖርና ለመራባት የግድ ስለሚያስፈልጉን ነው? ወይስ ሕይወት፣ አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ ስጦታ ነው?