በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?

“ሰማያትና ምድር በተፈጠሩበት ጊዜ፣ . . . የተከናወነው ነገር ይህ ነው።” (ዘፍጥረት 2:4) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፕላኔታችን አጀማመር የሚገልጸውን ታሪክ የሚደመድመው በእነዚህ ቃላት ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር በሳይንስ ከተረጋገጡ እውነታዎች ጋር ይስማማል? እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

በመጀመሪያ፦ ሰማያትና ምድር ተፈጠሩ

ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ አለው?

ዘፍጥረት 1:1 “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል።

እስከ 1950ዎቹ ዓመታት ድረስ በርካታ ታዋቂ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንደሌለው ያምኑ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ጽንፈ ዓለም በእርግጥም መጀመሪያ እንዳለው አምነዋል።

ምድር መጀመሪያ ላይ ምን ትመስል ነበር?

ዘፍጥረት 1:2, 9 እንደሚገልጸው ምድር መጀመሪያ ላይ “ቅርጽ አልባና ባድማ” እንዲሁም በውኃ የተሸፈነች ነበረች።

ይህ መግለጫ ዘመናዊ ሳይንስ ከደረሰበት ነገር ጋር ይስማማል። ፓትሪክ ሺ የተባሉት የባዮሎጂ ባለሙያ ምድራችን መጀመሪያ ላይ ስለነበራት ሁኔታ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ኦክስጅን የሌለውና ለመተንፈስ የማይሆን ከባቢ አየር ነበራት። . . . በጥቅሉ ሲታይ የምድራችን መልክ ሳይንስ ፊክሽን (ሳይንሳዊ ልብ ወለድ) ላይ የሚታየውን ይመስል ነበር።” አስትሮኖሚ መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “አዳዲስ የምርምር ውጤቶች እንደሚያሳዩት የጥንቷ ምድር የውኃ ዓለም ነበረች፤ የብስ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር።”

ከባቢ አየር በጊዜ ሂደት የተቀየረው እንዴት ነው?

ዘፍጥረት 1:3-5 ብርሃን ወደ ከባቢ አየር እንደደረሰ ይናገራል፤ ሆኖም መጀመሪያ ላይ፣ ምድር ላይ ሆኖ የብርሃኑን ምንጭ መለየት አይቻልም ነበር። ከምድር ሆኖ ፀሐይን እና ጨረቃን በግልጽ ማየት የተቻለው የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ነበር።—ዘፍጥረት 1:14-18

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በምድር ላይ ያለው ሕይወት ሁሉ የተፈጠረው የ24-ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ አይናገርም

የስሚዝሶኒያን የአካባቢ ምርምር ማዕከል እንደሚገልጸው መጀመሪያ ላይ ከባቢ አየሩን አልፎ ወደ ምድር መድረስ የሚችለው ደብዛዛ ብርሃን ብቻ ነበር። ማዕከሉ ያወጣው ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “የሜቴን ቅንጣቶች እንደ ጉም ምድርን ጥቅጥቅ አድርገው ሸፍነዋት ነበር።” ውሎ አድሮ ግን “ይህ የሜቴን ጉም እየጠራ ሄደና ሰማያዊ ሰማይ ታየ።”

ሕይወት ያላቸው ነገሮች ምድር ላይ የታዩት በየትኛው ቅደም ተከተል ነው?

ዘፍጥረት 1:20-27 ዓሦች፣ ወፎች፣ የየብስ እንስሳት፣ በመጨረሻም ሰዎች እንደተፈጠሩ ይናገራል። ሳይንቲስቶች የመጀመሪያው አጥቢ እንስሳ የታየው የመጀመሪያው ዓሣ ከታየ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ ያምናሉ፤ የሰው ልጆች ምድር ላይ የታዩት ደግሞ ከዚያ በጣም ቆይቶ እንደሆነ ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በጊዜ ሂደት ለውጥ አያደርጉም ብሎ አይናገርም

መጽሐፍ ቅዱስ ምን አይልም?

አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ዘመናዊ ሳይንስ ከደረሰባቸው ነገሮች ጋር እንደማይስማማ ይናገራሉ። ይሁንና ይህ አስተሳሰብ በአብዛኛው የሚመነጨው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የጽንፈ ዓለም ወይም የምድር ዕድሜ 6,000 ዓመት ብቻ እንደሆነ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ምድርም ሆነች ጽንፈ ዓለም “በመጀመሪያ” እንደተፈጠሩ ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 1:1) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነው መቼ እንደሆነ በቀጥታ አይናገርም።

መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ያለው ሕይወት ሁሉ የተፈጠረው የ24-ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ “ቀን” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት የተለያየ ርዝማኔ ያለውን ጊዜ ለማመልከት ነው። ለምሳሌ ፕላኔታችንና ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተፈጠሩበትን ጊዜ (በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ የተገለጹትን ስድስት የፍጥረት “ቀናት” ማለት ነው) “ይሖዋ a አምላክ ምድርንና ሰማይን [የሠራበት] ቀን” ብሎ ይጠራዋል። (ዘፍጥረት 2:4) በመሆኑም አምላክ ምድርን ለመኖሪያነት ያመቻቸባቸውና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረባቸው ስድስት የፍጥረት “ቀናት” እያንዳንዳቸው በጣም ረጅም ጊዜን የሚያመለክቱ ሊሆኑ ይችላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በጊዜ ሂደት ለውጥ አያደርጉም ብሎ አይናገርም። የዘፍጥረት መጽሐፍ እንስሳት “እንደየወገናቸው” እንደተፈጠሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:24, 25) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው “ወገን” የሚለው ቃል ሳይንሳዊ ትርጉም ያለው ቃል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰፋ ያለ ምድብን የሚያመለክት ቃል ይመስላል። በመሆኑም አንድ “ወገን” በውስጡ ብዙ ዝርያዎችን ሊያካትት ይችላል። ይህ ቃል በአንድ ወገን ውስጥ የዝርያ ለውጥ ሊካሄድ የሚችልበት ክፍተት ይሰጣል፤ ከዚህ አንጻር የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ዝርያዎች በጊዜ ሂደት ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚለው ሐሳብ ጋር አይጋጭም።

ታዲያ ምን ይመስልሃል?

ቀደም ብለን እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጽንፈ ዓለም አጀማመር፣ ምድር መጀመሪያ ላይ ስለነበረችበት ሁኔታ እንዲሁም ሕይወት ያላቸው ነገሮች ምድር ላይ ስለታዩበት ቅደም ተከተል የያዘው ሐሳብ ቀላልና ትክክለኛ ነው። ታዲያ ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ነገሮች የፈጠረ አካል እንዳለ የሚናገረው ሐሳብስ ትክክል ሊሆን አይችልም? ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወት የተገኘው ከሰው በላይ በሆነ ኃይል ጣልቃ ገብነት ነው የሚለው ሐሳብ በጥቅሉ ሲታይ ዘመናዊ ሳይንስ ከደረሰበት ጋር የሚጋጭ አይደለም።” b

a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።

b ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው የሚል አቋም አያራምድም።