መልሱን ማወቅህ ለውጥ የሚያመጣው ለምንድን ነው?
የፈጣሪ መኖር ለውጥ የሚያመጣው ለምንድን ነው? ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ የቀረበልህ ማስረጃ ካሳመነህ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈውም እሱ መሆኑን የሚያሳየውን ማስረጃ መመርመር ትፈልግ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ሐሳብ ከተማመንክ ደግሞ የሚከተሉትን ጥቅሞች ታገኛለህ።
በሕይወትህ ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለህ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “[አምላክ] ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችሁን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል።”—የሐዋርያት ሥራ 14:17
ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ከተፈጥሮ የምትደሰትባቸው ነገሮች ሁሉ ከፈጣሪ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው። እነዚህን ስጦታዎች የሰጠህ ፈጣሪ ምን ያህል እንደሚወድህ ስታውቅ ለስጦታዎቹ ያለህ አድናቆት ይጨምራል።
ለዕለት ተዕለት ሕይወትህ የሚጠቅም አስተማማኝ መመሪያ ታገኛለህ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ጽድቅ፣ ፍትሕና ትክክል የሆነውን ነገር ይኸውም የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ ትረዳለህ።”—ምሳሌ 2:9
ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? አምላክ ፈጣሪህ ስለሆነ ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልግህን ነገር ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርህ ለአሁኑ ሕይወትህ የሚጠቅምህ ትምህርት ለማግኘት ይረዳሃል።
ለጥያቄዎችህ መልስ ታገኛለህ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ስለ አምላክ እውቀት ትቀስማለህ።”—ምሳሌ 2:5
ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ፈጣሪ እንዳለ ማወቅህ እንደሚከተሉት ላሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይረዳሃል፦ የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው? ስንሞት ምን እንሆናለን? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጥሃል።
ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ ይኖርሃል
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “‘ለእናንተ የማስበውን ሐሳብ በሚገባ አውቀዋለሁና’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ለእናንተ የማስበው ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን እንዲሁም የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን ነው።’”—ኤርምያስ 29:11
ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? አምላክ ወደፊት ክፋትን፣ መከራን ሌላው ቀርቶ ሞትን እንኳ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። አምላክ በገባው ቃል ላይ ስትተማመን ይህ ብሩህ ተስፋ ዛሬ የሚያጋጥሙህን ችግሮች በድፍረት ለመወጣት ያስችልሃል።