የታሪክ መስኮት
ዴሲዴርዩስ ኢራስመስ
ዴሲዴርዩስ ኢራስመስ (1469-1536 ገደማ) በዘመኑ ከነበሩት የአውሮፓ ምሁራን መካከል በእውቀቱ ተወዳዳሪ እንደሌለው ይነገርለት ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን ፈሪ እንዲሁም መናፍቅ ተብሎ ስሙ ጠፍቷል። በጦፈ ሃይማኖታዊ ክርክር ውስጥ በተካፈለበት ወቅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የለውጥ አራማጆቹን ስህተት በድፍረት አጋልጧል። በዛሬው ጊዜ ግን፣ በአውሮፓ የነበረውን ሃይማኖታዊ ገጽታ ለመቀየር ቁልፍ ሚና የተጫወተ ሰው እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ይህን ያደረገው እንዴት ነው?
ያደረገው ምርምርና የሚያምንባቸው ነገሮች
ኢራስመስ ጥሩ የግሪክኛና የላቲን እውቀት ስለነበረው እንደ ላቲን ቩልጌት ያሉ የላቲን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብለው ከሚጠሩት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ የግሪክኛ ቅጂዎች ጋር ማነጻጸር ችሏል። መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያምን ነበር። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዘመኑ ተራው ሕዝብ ይጠቀምባቸው ወደነበሩ ቋንቋዎች መተርጎም እንዳለበት አበክሮ ገልጿል።
ኢራስመስ፣ ክርስትና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን የመከተል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን መላ ሕይወትን የሚነካ መሆን እንዳለበት ስለሚያምን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ እንደሚያስፈልጋት ይናገር ነበር። በመሆኑም የለውጥ አራማጆች በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ማመፅና የሮም ቤተ ክርስቲያን ለውጥ እንዲያደርግ መጠየቅ በጀመሩ ጊዜ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢራስመስን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ጀመረች።
ኢራስመስ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የለውጥ አራማጆቹን ስህተት በድፍረት አጋልጧል
ኢራስመስ ባዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ ቀሳውስት ስለሚፈጽሙት ጭቆና፣ ስለሚመሩት የቅንጦት ሕይወት እንዲሁም ጦርነትን የሚደግፉ ጳጳሳት ስላላቸው የሥልጣን ጥመኝነት በአሽሙር መልክ ጽፏል። የኃጢአት ኑዛዜን፣ የቅዱሳን አምልኮን፣ ጾምን፣ መንፈሳዊ ጉዞን እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶችን ተጠቅመው አማኞችን ይበዘብዙ የነበሩትን ምግባረ ብልሹ ቀሳውስት ተቃውሟል። በተጨማሪም ለኃጢአት ይቅርታ ሲሉ ገንዘብ ማስከፈልን እንዲሁም ቀሳውስት እንዳያገቡ መከልከልን የመሳሰሉት የቤተ ክርስቲያን ልማዶች ስህተት እንደሆኑ ተናግሯል።
የግሪክኛ አዲስ ኪዳን
በ1516 ኢራስመስ በግሪክኛ ያዘጋጀውን አዲስ ኪዳን የመጀመሪያ እትም አወጣ፤ ይህ ሥራ የመጀመሪያው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት እትም ነው። ከኢራስመስ ሥራዎች መካከል ከማብራሪያ ጽሑፍ ጋር የተዘጋጀውና ራሱ የተረጎመው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የላቲን ትርጉም ይገኝበታል፤ ይህ ትርጉም ከቩልጌት የተለየ ነው። ውሎ አድሮ፣ ባዘጋጀው እትም ላይ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን የመጨረሻ ሥራው ከላቲን ቩልጌት ጋር ሰፊ ልዩነት ነበረው።
ከልዩነቶቹ አንዱ በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ይገኛል። ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለውን የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ለመደገፍ ሲባል ኮማ ዮሃኒየም ተብሎ የሚጠራው የሐሰት ሐሳብ በቩልጌት ውስጥ ተጨምሮ ነበር። እንዲህ ይላል፦ “በሰማይ . . . አብ፣ ቃልና መንፈስ ቅዱስ፤ እነዚህ ሦስቱ አንድ ናቸው።” ሆኖም ኢራስመስ ባመሣከራቸው ጥንታዊ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ ይህን ሐሳብ ስላላገኘ ካዘጋጃቸው የመጀመሪያ ሁለት የአዲስ ኪዳን እትሞች ላይ ይህን ሐሳብ የያዘውን ክፍል አውጥቶታል። በኋላ ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ባሳደረችበት ግፊት ምክንያት በሦስተኛ እትሙ ላይ ይህን ክፍል አካተተው።
ኢራስመስ ያዘጋጃቸው የተሻሻሉ የግሪክኛ አዲስ ኪዳን እትሞች በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ቋንቋዎች ይበልጥ ጥራት ያላቸው ትርጉሞች እንዲዘጋጁ በር ከፍተዋል። የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማርቲን ሉተር ወደ ጀርመንኛ፣ ዊልያም ቲንደል ወደ እንግሊዝኛ፣ አንቶኒዮ ብሩቾሊ ወደ ጣሊያንኛ እንዲሁም ፍራንዚስኮ ዴ ኤንዚናስ ወደ ስፓንኛ የተረጎሙት የኢራስመስን እትሞች መሠረት በማድረግ ነው።
ኢራስመስ የኖረው ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ነውጥ በነበረበት ዘመን ነው፤ የፕሮቴስታንት የተሃድሶ አራማጆች እሱ ያዘጋጀውን የግሪክኛ አዲስ ኪዳን በጣም ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ አግኝተውታል። የተሃድሶ ንቅናቄው እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ ኢራስመስ እንደ ተሃድሶ አራማጅ ይቆጠር ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ በተካሄዱት ሃይማኖታዊ ክርክሮች የትኛውንም ወገን ለመደገፍ ፈቃደኛ አልነበረም። የሚገርመው ከ100 ዓመታት ገደማ በፊት የኖሩት ዴቪድ ሻፍ የተባሉ ምሁር፣ “[ኢራስመስ] የሞተው የትኛውንም የሃይማኖት ቡድን ሳይደግፍ ነው። ካቶሊኮቹ ከእኛ ወገን ነው ሊሉ አልቻሉም፤ ፕሮቴስታንቶችም ቢሆኑ እንደዚያ አላሉም” ብለው ጽፈዋል።