በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለልጆቻችሁ ምን ዓይነት ምሳሌ እየተዋችሁ ነው?

ለወላጆች

8፦ ምሳሌ መሆን

8፦ ምሳሌ መሆን

ምን ማለት ነው?

የሚናገሩትን ነገር በሥራ ላይ የሚያውሉ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ልታናግረው የማትፈልገው ሰው ቤትህ በሚመጣበት ጊዜ “የለም በሉት” ስትል ልጅህ የሚሰማህ ከሆነ ሌላ ጊዜ ልጅህ እውነቱን እንዲነግርህ መጠበቅ አትችልም።

“ወላጆች የሚናገሩትን ነገር በተግባር ሳያውሉ ልጆቻቸው እነሱ የተናገሩትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መጠበቅ የለባቸውም። ልጆች ልክ እንደ ስፖንጅ ስለሆኑ የምንናገረውንና የምናደርገውን ነገር ሁሉ በቀላሉ የመያዝ ችሎታ አላቸው። የምንናገረውና የምናደርገው ነገር የማይጣጣም ከሆነ ይህን መገንዘባቸው አይቀርም።”—ዴቪድ

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንተ ‘አትስረቅ’ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ?”—ሮም 2:21

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በልጆችም ሆነ በወጣቶች ላይ እኩዮቻቸውን ጨምሮ ሌላ ማንኛውም ሰው የወላጆችን ያህል ተጽዕኖ ማሳደር አይችልም። ይህ ማለት ወላጆች የሚያስተምሩትን ነገር ተግባራዊ በማድረግ ምሳሌ ከሆኑ፣ ልጆቻቸውን በትክክለኛው መንገድ በመምራት ረገድ ከማንም የበለጠ ሚና መጫወት ይችላሉ።

“ለልጃችን አንድን ነገር አሥር ጊዜ ከነገርነው በኋላ ‘ይሄ ልጅ አይሰማም እንዴ?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል፤ ሆኖም የተናገርነውን ሳናደርግ የቀረንበት አንድ አጋጣሚ ቢኖር ይህን አላደረጋችሁም ከማለት ወደኋላ አይልም። ልጆች እኛ አያስተውሉትም ብለን የምናስበውን ነገር ጨምሮ የምናደርገውን ነገር ሁሉ በትኩረት ይከታተላሉ።”—ኒኮል

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ግብዝነት የሌለበት ነው።”—ያዕቆብ 3:17

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ራሳችሁን መርምሩ። የምትመለከቱት ምን ዓይነት መዝናኛ ነው? የትዳር ጓደኛችሁንና ልጆቻችሁን የምትይዙት እንዴት ነው? ጓደኞቻችሁ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? ለሌሎች ታስባላችሁ? በሌላ አባባል፣ ልጆቻችሁ እንዲሆኑ የምትፈልጉት ዓይነት ሰው ናችሁ?

“እኔና ባለቤቴ እኛ ተግባራዊ የማናደርገውን መሥፈርት ልጆቻችን እንዲከተሉ አንጠብቅባቸውም።”—ክሪስቲን

ስህተት ስትሠሩ ይቅርታ ጠይቁ። ልጆቻችሁ ፍጹም እንዳልሆናችሁ ያውቃሉ። ስህተት ስትሠሩ የትዳር ጓደኛችሁንም ሆነ ልጆቻችሁን “ይቅርታ አጥፍቻለሁ” ማለታችሁ ሐቀኛና ትሑት መሆን ያለውን ጥቅም ልጆቻችሁ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።

“ልጆቻችን ጥፋታችንን አምነን እንደምንቀበል ስንናገርና ለሠራነው ጥፋት ይቅርታ ስንጠይቅ መስማታቸው ጠቃሚ ነው። እንዲህ የማናደርግ ከሆነ እነሱም ጥፋታቸውን መሸፋፈንን ይማራሉ።”—ሮቢን

“ወላጆች እንደመሆናችን መጠን በልጆቻችን ላይ ከማንም የበለጠ ተጽዕኖ ማሳደር የምንችለው እኛ ነን። ይህን ማድረግ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ደግሞ ምሳሌ በመሆን ነው፤ ምክንያቱም የምናደርገውን ነገር ምንጊዜም ይመለከታሉ። እኛ የምንተወው ምሳሌ ሁልጊዜ ትምህርት እንደሚገኝበት መጽሐፍ ነው።”—ዌንደል