ንድፍ አውጪ አለው?
የፖሊያ ቤሪ ደማቅ ሰማያዊ ቀለም
በብዙ የአፍሪካ አገሮች የሚገኘው ፖሊያ ኮንዴንሳታ የተባለ ሳይንሳዊ ስያሜ የተሰጠው ተክል የሚያፈራው ፍሬ በየትኛውም ተክል ላይ የማይታይ ደማቅ ሰማያዊ ቀለም አለው። ይሁን እንጂ ፍሬው በውስጡ ሰማያዊ ቀለም እንዲኖረው የሚያደርግ ንጥረ ነገር የለውም። ታዲያ ይህን የመሰለ አስደናቂ ቀለም ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በፍሬው ቆዳ ላይ የሚገኙት የሴል ግድግዳዎች እንደ ክብሪት እንጨት በሥርዓት የተደረደሩ ጥቃቅን ክሮች አሏቸው። እነዚህ ክሮች የተነባበሩ ሲሆኑ እያንዳንዱ ንብርብር ከሥሩ ከሚገኘው ንብርብር በትንሹ የተዛነፈ በመሆኑ ንብርብሮቹ የቀለበት ቅርጽ ይፈጥራሉ። ክሮቹ ራሳቸው ሰማያዊ አይደሉም። ቀለሙ እንዲፈጠር የሚያደርገው ክሮቹ የተነባበሩበት መንገድ ነው። በመሆኑም ፍሬው ደማቅ አንጸባራቂ ቀለም እንዲኖረው ያደረገው የተሠራበት ንድፍ እንጂ በውስጡ ያለው ንጥረ ነገር አይደለም። አብዛኞቹ ሴሎች ሰማያዊ ሆነው ይታያሉ። ይሁን እንጂ የንብርብሮቹ መጠን ስለሚለያይ አንዳንዶቹ ከተለያየ አቅጣጫ ሲታዩ አረንጓዴ፣ ሮዝ ወይም ቢጫ ቀለም ይኖራቸዋል። ከዚህም በላይ በቅርበት ሲታዩ ቀለሞቹ በኮምፒውተር ስክሪን ላይ እንዳሉ ቀለማት ነጠብጣብ ናቸው እንጂ አንድ ወጥ አይደሉም።
የፖሊያ ቤሪ ፍሬዎች ቀለም እንዲኖራቸው የሚያደርግ ንጥረ ነገር የሌላቸው በመሆኑ ከተክሉ ላይ ከወደቁም በኋላ ቢሆን ቀለማቸው እንዳለ ይቆያል። እንዲያውም ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የተሰበሰቡ የፖሊያ ቤሪ ፍሬዎች አሁን የተለቀሙ ፍሬዎችን ያህል ደማቅ ቀለም አላቸው! እነዚህ ፍሬዎች በውስጣቸው ዘር እንጂ የሚበላ ነገር የሌላቸው ቢሆኑም በአካባቢው የሚገኙ ወፎችን የሚስብ ውበት እንዳላቸው ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
ሳይንቲስቶች የፖሊያ ቤሪ ቀለም የማይወይቡ ቀለሞችንም ሆነ ተመሳስለው ሊሠሩ የማይችሉ ወረቀቶችን ለመሥራት እንደ መነሻ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ያምናሉ።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የፖሊያ ቤሪ ደማቅ ሰማያዊ ቀለም በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?