በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓለም ላይ ከሰፈነው የራስ ወዳድነት መንፈስ ራቅ

በዓለም ላይ ከሰፈነው የራስ ወዳድነት መንፈስ ራቅ

በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ለየት ባለ መንገድ ሊያዙ ወይም ለየት ያለ መብት ሊሰጣቸው እንደሚገባ እንደሚሰማቸው አስተውለሃል? ምንም ያህል ነገር ቢሰጣቸው ተጨማሪ ነገር እንደሚገባቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለው የራስ ወዳድነትና የምስጋና ቢስነት ዝንባሌ በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩ ሰዎች መገለጫ ነው።—2 ጢሞ. 3:2

እርግጥ ነው፣ ራስ ወዳድነት አዲስ ነገር አይደለም። አዳምና ሔዋን ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር በራሳቸው ለመወሰን መርጠዋል፤ ይህም አስከፊ መዘዝ አስከትሏል። በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ደግሞ የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ዕጣን የማጠን መብት እንዳለው ተሰምቶት ነበር፤ ሆኖም ክፉኛ ተሳስቶ ነበር። (2 ዜና 26:18, 19) በተመሳሳይም ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የአብርሃም ዘሮች በመሆናቸው ብቻ አምላክ ለየት ያለ ሞገስ ሊያሳያቸው እንደሚገባ ይሰማቸው ነበር።—ማቴ. 3:9

የተከበብነው ራስ ወዳድና ትምክህተኛ በሆኑ ሰዎች ነው፤ በመሆኑም ይህ ዝንባሌያቸው ሊጋባብን ይችላል። (ገላ. 5:26) አንድ መብት ሊሰጠን ወይም ለየት ያለ አስተያየት ሊደረግልን እንደሚገባ ማሰብ እንጀምር ይሆናል። እንዲህ ካለው አስተሳሰብ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ይሖዋ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ማወቅ ይኖርብናል። በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመልከት።

ምን ልናገኝ እንደሚገባ የሚወስነው ይሖዋ ነው። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

  • በቤተሰብ ውስጥ ባል በሚስቱ ሊከበር፣ ሚስት ደግሞ በባሏ ልትወደድ ይገባል። (ኤፌ. 5:33) ባለትዳሮች የትዳር አጋራቸው ለእነሱ ብቻ የፍቅር ስሜት እንዲያሳይ መጠበቃቸው ተገቢ ነው። (1 ቆሮ. 7:3) ወላጆች ልጆቻቸው እንዲታዘዟቸው የመጠበቅ መብት አላቸው፤ ልጆች ደግሞ የወላጆቻቸውን ፍቅርና ድጋፍ ሊያገኙ ይገባል።—2 ቆሮ. 12:14፤ ኤፌ. 6:2

  • በጉባኤ ውስጥ በትጋት የሚሠሩ ሽማግሌዎች አክብሮት ይገባቸዋል። (1 ተሰ. 5:12) ይሁንና በወንድሞቻቸውና በእህቶቻቸው ላይ የመሠልጠን መብት የላቸውም።—1 ጴጥ. 5:2, 3

  • አምላክ ለሰብዓዊ መንግሥታት ከተገዢዎቻቸው ግብር የመጠየቅና አክብሮት የመቀበል መብት ሰጥቷቸዋል።—ሮም 13:1, 6, 7

ይሖዋ ስለሚወደን ከሚገባን በላይ አትረፍርፎ ይሰጠናል። ኃጢአተኞች ስለሆንን የሚገባን ሞት ብቻ ነበር። (ሮም 6:23) ሆኖም ይሖዋ ለእኛ ባለው ታማኝ ፍቅር ተነሳስቶ ብዙ በረከቶችን ይሰጠናል። (መዝ. 103:10, 11) የትኛውንም በረከትም ሆነ መብት የሚሰጠን ስለሚገባን ሳይሆን በጸጋው ነው።—ሮም 12:6-8፤ ኤፌ. 2:8

ከራስ ወዳድነትና ከትምክህተኝነት መንፈስ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

የዓለም ዝንባሌ እንዳይጋባብህ ተጠንቀቅ። ካልተጠነቀቅን፣ ሳይታወቀን ከሌሎች የበለጠ ነገር እንደሚገባን ማሰብ ልንጀምር እንችላለን። ኢየሱስ አንድ ዲናር ስለተከፈላቸው ሠራተኞች በሚገልጸው ምሳሌ ላይ እንዲህ ያለው አመለካከት በቀላሉ ሊያድርብን የሚችለው እንዴት እንደሆነ አሳይቷል። አንዳንዶቹ ሠራተኞች ከጠዋት አንስቶ ቀኑን ሙሉ በጠራራ ፀሐይ ሲሠሩ ውለዋል፤ ሌሎቹ ግን የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው። የመጀመሪያዎቹ ሠራተኞች ቀኑን ሙሉ ሲሠሩ በመዋላቸው ተጨማሪ ክፍያ እንደሚገባቸው ተሰምቷቸው ነበር። (ማቴ. 20:1-16) ኢየሱስ የምሳሌውን ትርጉም ሲያብራራ፣ ተከታዮቹ አምላክ በሚሰጣቸው ነገር መርካት እንዳለባቸው ተናግሯል።

ቀኑን ሙሉ ሲሠሩ የዋሉት ሰዎች ተጨማሪ ክፍያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተሰምቷቸው ነበር

ይገባኛል ከማለት ይልቅ አመስጋኝ ሁን። (1 ተሰ. 5:18) የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ተከተል፤ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከነበሩት ወንድሞች ቁሳዊ ድጋፍ የመጠየቅ መብት ቢኖረውም እንዲህ ከማድረግ ተቆጥቧል። (1 ቆሮ. 9:11-14) ለምናገኘው ለእያንዳንዱ በረከት አመስጋኝ መሆን እንዲሁም ይገባኛል የሚል መንፈስ ከማንጸባረቅ መቆጠብ ይኖርብናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ቁሳዊ ድጋፍ እንዲሰጠው አልጠየቀም

ትሕትና አዳብር። አንድ ሰው ለራሱ የተጋነነ አመለካከት ካዳበረ አሁን ካለው ነገር የበለጠ እንደሚገባው ማሰብ ሊጀምር ይችላል። እንዲህ ላለው መርዛማ አስተሳሰብ ማርከሻው ትሕትና ነው።

ነቢዩ ዳንኤል ትሑት መሆኑ በይሖዋ ዘንድ ውድ አድርጎታል

ነቢዩ ዳንኤል ትሕትና በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ከትልቅ ቤተሰብ የመጣ እንዲሁም ጥሩ ቁመና፣ ጥበብና ችሎታ ያለው ሰው ነበር። ይህም የተሰጠው ለየት ያለ መብት የሚገባው ነገር እንደሆነ እንዲያስብ ሊያደርገው ይችል ነበር። (ዳን. 1:3, 4, 19, 20) ይሁንና ዳንኤል እስከ መጨረሻው ትሑት ሆኖ ኖሯል፤ ይህ ባሕሪውም በይሖዋ ዘንድ ውድ አድርጎታል።—ዳን. 2:30፤ 10:11, 12

እንግዲያው በዓለም ላይ ከሰፈነው የራስ ወዳድነትና የትምክህተኝነት መንፈስ እንራቅ። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በጸጋው በሚሰጠን በእያንዳንዱ በረከት መደሰታችንን እንቀጥል።