እውነተኛ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
እውነተኛ ወዳጆች የሚረዱን እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ ከወዳጆቹ ጋር በመጓዙ ብዙ ጥቅም አግኝቷል። (ቆላ. 4:7-11) ጳውሎስ ሮም ውስጥ ታስሮ ሳለ ወዳጆቹ በራሱ ማከናወን ያልቻላቸውን ነገሮች በማከናወን አግዘውታል። ለምሳሌ አፍሮዲጡ በፊልጵስዩስ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የላኳቸውን አስፈላጊ ቁሳቁሶች ለጳውሎስ አድርሶለታል። (ፊልጵ. 4:18) ቲኪቆስ፣ ጳውሎስ የጻፋቸውን ደብዳቤዎች ወደተለያዩ ጉባኤዎች ወስዷል። (ቆላ. 4:7) ጳውሎስ በቁም እስር እንዲሁም በወህኒ ከሰዎች ተገልሎ በነበረበት ጊዜ አገልግሎቱን ማከናወን የቻለው የወዳጆቹ ድጋፍ ስላልተለየው ነው። አንተስ እውነተኛ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
በዘመናችንም እውነተኛ ወዳጅ መሆን ያለውን ጥቅም የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎች አሉ። ስፔን ውስጥ በዘወትር አቅኚነት የምታገለግለው ኤሊሳቤት ጥሩ ወዳጅ በማግኘቷ የተጠቀመችው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እናቷ በማይድን የካንሰር በሽታ በተያዘችበት ወቅት የኤሊሳቤት ጓደኛ የሆነች እህት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በርካታ የሚያበረታቱ የጽሑፍ መልእክቶች ትልክላት ነበር። ኤሊሳቤት እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ መልእክቶች በእያንዳንዱ ቀን የሚያጋጥመኝን ፈተና ብቸኝነት ሳይሰማኝ ለመወጣት ኃይል ሰጥተውኛል።”—ምሳሌ 18:24
የእምነት ባልንጀሮቻችን የጉባኤ እንቅስቃሴዎችን እንዲያከናውኑ በመደገፍ ከእነሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት ማጠናከር እንችላለን። ለምሳሌ አንድን አረጋዊ ወንድም ወይም እህት ወደ ጉባኤ ስብሰባ አሊያም ወደ አገልግሎት በመኪና ልትወስድ ትችላለህ? እንዲህ ማድረግህ እርስ በርስ የምትበረታቱበት አጋጣሚ ይፈጥርላችኋል። (ሮም 1:12) አንዳንድ ክርስቲያኖች ግን ከቤት መውጣት አይችሉም። ታዲያ ለእነሱ እውነተኛ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
ከቤት መውጣት ለማይችሉ እውነተኛ ወዳጅ ሁን
አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን በጤና ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በአካል መገኘት አይችሉም። ዴቪድን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዴቪድ ሊምፎማ የተባለ የካንሰር በሽታ እንዳለበት ታወቀ። ከስድስት ወር በላይ የኬሞቴራፒ ሕክምና ይወስድ ነበር። ሕክምናው እስኪጠናቀቅ ድረስ ዴቪድና ባለቤቱ ሊዲያ በስብሰባዎች ላይ የሚገኙት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ነበር።
በጉባኤያቸው ያሉ ወዳጆቻቸው ምን ድጋፍ አደረጉላቸው? ስብሰባ ካለቀ በኋላ ምንጊዜም በስብሰባ አዳራሹ ያሉ
አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ዴቪድንና ሊዲያን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ለማነጋገር ጥረት ያደርጉ ነበር። በተጨማሪም ዴቪድና ሊዲያ ሐሳብ ሲሰጡ ከስብሰባው በኋላ የእምነት ባልንጀሮቻቸው አበረታች የጽሑፍ መልእክት ይልኩላቸው ነበር። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ዴቪድና ሊዲያ የሚሰማቸው የብቸኝነት ስሜት ቀንሶላቸዋል።ከቤት መውጣት ከማይችሉ የእምነት ባልንጀሮችህ ጋር አብረህ ማገልገል ትችል ይሆን? ጥቂት ማስተካከያዎች ብቻ በማድረግ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንን እንዳልረሳናቸው ማሳየት እንችላለን። (ምሳሌ 3:27) በደብዳቤ ወይም በስልክ አብረሃቸው ለማገልገል ለምን ቀጠሮ አትይዝም? ከቤት መውጣት የማይችሉ አስፋፊዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችሉ ይሆናል። ዴቪድ እና ሊዲያ ጉባኤያቸው እንዲህ ያለ ዝግጅት በማድረጉ በጣም ተደስተዋል። ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “ከአገልግሎት ጓደኞቻችን ጋር በስምሪት ስብሰባው ላይ ጥቂት ውይይት አድርገን አብረን መጸለያችን ከፍተኛ ጉልበት ሰጥቶናል።” በተጨማሪም ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነና እንዲህ ማድረግ የወንድሞችህን ደህንነት አደጋ ላይ የማይጥል ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን ከቤት መውጣት ወደማይችሉ አስፋፊዎች ቤት ወስደህ አልፎ አልፎ ጥናት ልትጋብዛቸው ትችል ይሆን?
ከቤት መውጣት ከማይችሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አብረን ጊዜ ስናሳልፍና ማራኪ ባሕርያቸውን ስናስተውል ወደ እነሱ ይበልጥ እንቀርባለን። ለምሳሌ እንዲህ ካሉ አስፋፊዎች ጋር አብረህ በምታገለግልበት ወቅት የሰዎችን ልብ ለመንካት የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ ሲጠቀሙበት ስታይ ይበልጥ ታደንቃቸዋለህ። የእምነት ባልንጀሮችህ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ ስትረዳቸው ብዙ ወዳጆችን ታፈራለህ።—2 ቆሮ. 6:13
ጳውሎስ ወዳጁ ቲቶ ከእሱ ጋር በመሆኑ ተበረታቷል። (2 ቆሮ. 7:5-7) ይህ ዘገባ የሚያበረታቱ ቃላትን በመናገር ብቻ ሳይሆን ከወንድሞቻችን ጋር አብረን በመሆንና እነሱን ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ በማድረግ ልናጽናናቸው እንደምንችል ያሳያል።—1 ዮሐ. 3:18
በስደት ወቅት እውነተኛ ወዳጅ ሁን
በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እርስ በርስ በመደጋገፍ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። የሰርጌንና የባለቤቱን የታቲያናን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ፖሊሶች ቤታቸውን ከፈተሹ በኋላ ለምርመራ ወሰዷቸው። መጀመሪያ ላይ ተለቃ ወደ ቤቷ የተመለሰችው ታቲያና ነበረች። ሰርጌ እንዲህ ብሏል፦ “ልክ ቤት ስትደርስ አንዲት ደፋር እህት ቤታችን ከች አለች። ሌሎች ብዙ ወንድሞችና እህቶችም ቤታችንን በማስተካከል አግዘውናል።”
አክሎም ሰርጌ እንዲህ ብሏል፦ “ምሳሌ 17:17 ላይ የሚገኘውን ‘እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው’ የሚለውን ጥቅስ ከድሮም ጀምሮ እወደዋለሁ። ብቻዬን ልቋቋም በማልችለው በዚህ የስደት ጊዜ ደግሞ ይህ ጥቅስ ይበልጥ ሕያው ሆኖልኛል። ይሖዋ ያለአንዳች ፍርሃት ከጎኔ የሚቆሙና ሁኔታዎች ከባድ በሚሆኑበት ጊዜ እጃቸውን ሊዘረጉልኝ የሚችሉ ወዳጆች ሰጥቶኛል።” a
ወደፊት የሚያጋጥሙን ሁኔታዎች እየከበዱ ስለሚሄዱ የሚደግፉን ወዳጆች ያስፈልጉናል። በታላቁ መከራ ወቅት ደግሞ እንዲህ ያሉ ወዳጆች ይበልጥ ያስፈልጉናል። ስለዚህ ከአሁኑ እውነተኛ ወዳጅ ለመሆን የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናድርግ።—1 ጴጥ. 4:7, 8
a “ይሖዋ ያለአንዳች ፍርሃት ከጎኔ የሚቆሙ ወዳጆች ሰጥቶኛል” የሚለውን ርዕስ jw.org ላይ ተመልከት።