ቡና በሰውነትህ ውስጥ የሚገኘውን የኮሌስትሮል መጠን እያሳደገው ይሆን?
ቡና በሰውነትህ ውስጥ የሚገኘውን የኮሌስትሮል መጠን እያሳደገው ይሆን?
ብራዚል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ኔዘርላንድ፣ ቫክኒንገን በሚገኘው የእርሻ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች ያልተጣራ ቡና መጠጣት በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን የኮሌስትሮል መጠን ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
“ያልተጣራ” የሚለው ቃል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው። ለምን? በኔዘርላንድ የሳይንስ ምርምር ተቋም የሚታተመው ሪሰርች ሪፖርትስ የተባለ አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው በቡና ውስጥ ካፌስቶል የሚባል የኮሌስትሮል መጠንን ከፍ የሚያደርግ ንጥረ ነገር ይገኛል። የፈላ ውኃ በተፈጨ ቡና ላይ በሚጨመርበት ጊዜ ካፌስቶል ይወጣል። ልክ እንደ ቱርክ ቡና እስኪልም ድረስ የተፈጨ ቡና በተደጋጋሚ በውኃ ሲፈላ ወይም ደግሞ የወረቀት ማጥለያ ከመጠቀም ይልቅ ከብረት በተሠራ ማጥለያ ሲጠል ተመሳሳይ ነገር ይከሰታል። በወረቀት ማጥለያ ያላለፈ ቡና በውስጡ ካፌስቶል ይጠራቀምበታል።
አንድ ስኒ ያልተጣራ ቡና እስከ አራት ሚሊ ግራም የሚደርስ ካፌስቶል ሊይዝ የሚችል ሲሆን በሰውነት ውስጥ ያለውን የኮሌስትሮል መጠን 1 በመቶ ከፍ ሊያደርገው ይችላል። ኤስፕሬሶ ቡና በወረቀት ማጥለያ በኩል የሚያልፍ ባለመሆኑ በውስጡ ካፌስቶል አለው። ይሁን እንጂ የምትጠጣበት ስኒ አነስተኛ ከሆነ በኮሌስትሮል መጠን ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ይሄን ያህል ከፍተኛ አይሆንም። በአንድ ትንሽ ስኒ ውስጥ የሚገኘው የካፌስቶል መጠን ከአንድ ወይም ከሁለት ሚሊ ግራም የማይበልጥ በመሆኑ አነስተኛ ኤስፕሬሶ የሚይዘው የካፌስቶል መጠን አነስተኛ ይሆናል። ሆኖም ሪሰርች ሪፖርት በቀን ትንንሽ በሆኑ አምስት ስኒዎች ኤስፕሬሶ ቡና መጠጣት በሰውነት ውስጥ ያለውን የኮሌስትሮል መጠን 2 በመቶ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
እዚህ ላይ መግለጽ የተፈለገው ዋናው ነገር በወረቀት ማጥለያ የተዘጋጀ ቡና ከካፌስቶል ነፃ መሆኑን ነው።