የሕክምና አቅኚዎች
የሕክምና አቅኚዎች
ዩፔይ በተባለች ትንሽ መንደር ውስጥ የሚኖር ዦዜ የተባለ አንድ የ61 ዓመት ቤልጅየማዊ ጉበቱ በቀዶ ሕክምና ወጥቶ በሌላ ጉበት መተካት እንዳለበት ይነገረዋል። “በሕይወቴ እንደዚያ ቀን ደንግጬ አላውቅም” ሲል ተናግሯል። ከአራት አሥርተ ዓመታት በፊት ጉበትን በቀዶ ሕክምና መተካት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። በ1970ዎቹ ዓመታት እንኳ ከሞት የሚተርፉት 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ጉበትን በቀዶ ሕክምና የመተካቱ ተግባር የተለመደ ከመሆኑም በላይ በአብዛኛው ስኬታማ ነው።
አሁንም ቢሆን ግን ትልቅ እንቅፋት አለ። ጉበት በቀዶ ሕክምና ሲተካ አብዛኛውን ጊዜ ብዙ ደም ስለሚፈስስ ዶክተሮች በአብዛኛው በቀዶ ሕክምናው ወቅት ለታካሚው ደም ይሰጡታል። ዦዜ በሃይማኖታዊ እምነቱ የተነሳ ደም መውሰድ አልፈለገም። ይሁን እንጂ ጉበቱ በቀዶ ሕክምና በሌላ ጉበት እንዲተካለት ፈልጓል። ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነው? አንዳንዶች እንደዚያ ይሰማቸዋል። ሆኖም ዋናው ቀዶ ሐኪም እሱና የሥራ አጋሮቹ ያለ ደም ቀዶ ሕክምናውን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን የሚችሉበት ሰፊ አጋጣሚ እንዳለ ተሰማው። ያደረጉትም ይህንኑ ነበር! ዦዜ ቀዶ ሕክምናውን ባደረገ በ25 ቀን ውስጥ ወደ ቤት ተመልሶ ከሚስቱና ከሴት ልጁ ጋር ተቀላቀለ። *
ታይም መጽሔት “የሕክምናው ዓለም ጀግኖች” ሲል የጠራቸው ሰዎች ሙያ ምስጋና ይግባውና ያለ ደም የሚካሄደው ሕክምና ዛሬ ከምንጊዜውም በበለጠ ተስፋፍቷል። ይሁን እንጂ ይህ ሕክምና ይህን ያህል ተፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ደም በደም ሥር በመስጠት የሚካሄደው ሕክምና ያሳለፈውን በውጣ ውረድ የተሞላ ታሪክ መለስ ብለን እንመርምር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 የይሖዋ ምሥክሮች አባላካልን ለመተካት የሚካሄድ ቀዶ ሕክምና ለግለሰቡ ሕሊና የተተወ የግል ውሳኔ ነው የሚል አቋም አላቸው።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮችን ያለ ደም ለማከም ፈቃደኛ መሆናቸውን ያሳወቁ ከ 90, 000 በላይ የሚሆኑ ዶክተሮች አሉ