የተስፋ መቁረጥን ስሜት መቋቋም የሚቻልበት መንገድ
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የተስፋ መቁረጥን ስሜት መቋቋም የሚቻልበት መንገድ
የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢያንስ በተወሰነ መጠን በሁሉም ሰዎች ዘንድ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ያደረባቸው የትካዜ ስሜት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በሕይወት ከመኖር ይልቅ መሞት የሚሻል መስሎ ይታያቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ጭምር ተስፋ መቁረጥ ሊያስከትሉ ከሚችሉ ችግሮችና ጫናዎች ነፃ አለመሆናቸውን ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና የነበራቸውን ኤልያስንና ኢዮብን ተመልከት። ኤልያስ ሕይወቱን ለማዳን ከንግሥት ኤልዛቤል ሸሽቶ ከሄደ በኋላ “ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት [ይሖዋን] ለመነ።” (1 ነገሥት 19:1-4) ጻድቁ ሰው ኢዮብ አስከፊ የሆነ በሽታንና የአሥር ልጆቹን ሞት ጨምሮ በተከታታይ አሳዛኝ ሁኔታዎች ደርሰውበታል። (ኢዮብ 1:13-19፤ 2:7, 8) ያደረበት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ‘ይህን ሥቃይ የበዛበት ሰውነት ተሸክሜ ከመኖር መሞትን እመርጣለሁ’ እንዲል አድርጎታል። (ኢዮብ 7:15 የ1980 ትርጉም) እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ያደረባቸው የጭንቀት ስሜት እጅግ አይሎባቸው እንደነበር ግልጽ ነው።
በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚያድርባቸው እርጅና በሚያስከትለው አሳዛኝ ውጤት፣ በትዳር ጓደኛ ሞት ወይም በከባድ ገንዘብ ነክ ችግሮች የተነሳ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ማቆሚያ የሌለው ውጥረት፣ አንድ አሳዛኝ ገጠመኝ የሚያስከትለው ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ችግር ወይም ቤተሰብ ነክ ችግሮች ውቅያኖስ መሀል ሆነው ላለመስጠም እየታገሉ እንዳሉና ማዕበል በተነሳ ቁጥር ዳር ለመድረስ ያላቸው ተስፋ ይበልጥ እየተመናመነ እንደሚሄድ ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋል። አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “ዋጋ ቢስ እንደሆንክና ብትሞት እንኳ ከናካቴው የሚያስታውስህ እንደማይኖር ሆኖ ይሰማሃል። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው የሚያድርበት የብቸኝነት ስሜት ከአቅሙ በላይ ይሆንበታል።”
በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሁኔታዎች የተሻለ ለውጥ በማሳየታቸው እንዲህ ዓይነቱ ከባድ ጫና ሊወገድ ይችላል። ይሁን እንጂ ሁኔታችን የማይለወጥ ቢሆንስ? መጽሐፍ ቅዱስ የተስፋ መቁረጥን ስሜት እንድንቋቋም ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳን ይችላል
ይሖዋ፣ ኤልያስና ኢዮብ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው እንዲያልፉ የመርዳት ችሎታውም ሆነ ኃይሉ ነበረው። (1 ነገሥት 19:10–12፤ ኢዮብ 42:1-6) ይህን ማወቃችን በዛሬው ጊዜ ምንኛ የሚያጽናና ነው! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” (መዝሙር 46:1፤ 55:22) የተስፋ መቁረጥ ስሜት የተቆጣጠረን መስሎ ቢታየንም እንኳ ይሖዋ በጽድቁ ቀኝ ደግፎ እንደሚያቆመን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳይያስ 41:10) ከዚህ ድጋፍ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በጸሎት አማካኝነት ‘አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችንንና አሳባችንን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል’ ሲል ይገልጻል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ከሚሰማን ጭንቀት የተነሳ ካጋጠመን ችግር መላቀቅ የምንችልበት መንገድ ላይታየን ይችላል። ይሁን እንጂ ‘በጸሎት ከጸናን’ ይሖዋ ያለብንን ችግር ለመቋቋም የሚያስችለንን ጥንካሬ በመስጠት ልባችንንና አእምሯችንን ሊጠብቅልን ይችላል።—ሮሜ 12:12፤ ኢሳይያስ 40:28-31፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ፊልጵስዩስ 4:13
በጸሎታችን ላይ የሚያስፈልገንን ነገር በግልጽ መጥቀሳችን ጠቃሚ ነው። ምንም እንኳ ሐሳባችንን መግለጽ ሊከብደን ቢችልም ስለሚሰማን ስሜትና የችግሩ መንስዔ ነው ብለን ስላሰብነው ነገር ለይሖዋ ለመንገር ነፃነት ሊሰማን ይገባል። እያንዳንዱን ቀን በጽናት እንድናሳልፍ የሚያስችለንን ጥንካሬ እንዲሰጠን ልንማጸነው ይገባል። “[ይሖዋ] ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም” የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።—መዝሙር 145:19
ከጸሎት በተጨማሪ ራስን የማግለል ዝንባሌ ማስወገድ አለብን። (ምሳሌ 18:1) አንዳንዶች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ለሌሎች በማዋል ብርታት አግኝተዋል። (ምሳሌ 19:17፤ ሉቃስ 6:38) ካለባት የካንሰር በሽታ በተጨማሪ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ስምንት የቤተሰቦቿን አባላት በሞት ያጣችውን ማሪያ * የምትባለውን ሴት ሁኔታ ተመልከት። ማሪያ ከአልጋ ለመነሳትና የዘወትር እንቅስቃሴዋን ለማከናወን ራስዋን ማስገደድ ነበረባት። ሌሎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር በየቀኑ ለማለት ይቻላል አገልግሎት ትወጣ የነበረ ሲሆን ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ላይ ትገኝ ነበር። ወደ ቤት ከተመለሰች በኋላ ያደረባት የጭንቀት ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ ያገረሽባት ነበር። ይሁን እንጂ ማሪያ ሌሎችን መርዳት በምትችልበት መንገድ ላይ ትኩረት በማድረጓ መጽናት ችላለች።
ሆኖም መጸለይ አስቸጋሪ ቢሆንብን ወይም በራሳችን ጥረት ራሳችንን የማግለል ዝንባሌያችንን ማሸነፍ ቢያቅተንስ? በዚህ ጊዜ እርዳታ ለማግኘት መጣር አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን’ እርዳታ እንድንጠይቅ ያበረታታናል። (ያዕቆብ 5:13-16) ቀጣይ ከሆነ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ጋር የሚታገል አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “ምክንያታዊ አስተሳሰብ መያዝ እንድትችሉ አንዳንድ ጊዜ እምነት የምትጥሉበትን ሰው ማነጋገራችሁ አእምሯችሁን ሊያሳርፍና መንፈሳችሁን ሊያረጋጋ ይችላል።” (ምሳሌ 17:17) እርግጥ፣ ከባድና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የትካዜ ስሜት ሕክምና የሚያሻው ችግር መኖሩን የሚጠቁም በሚሆንበት ጊዜ ተስማሚ የሆነ የባለሙያዎች እርዳታም ሊያስፈልግ ይችላል። *—ማቴዎስ 9:12
ምንም እንኳ ቀላል መፍትሔዎች ባይኖሩም አምላክ ችግራችንን እንድንቋቋም ለመርዳት ያለውን ችሎታ አቅልለን መመልከት አይገባንም። (2 ቆሮንቶስ 4:8) በጸሎት መጽናት፣ ራስን ከማግለል መራቅ እንዲሁም ጥሩ ብቃት ያላቸውን ሰዎች እርዳታ ማግኘት ስሜታችን ዳግም እንዲረጋጋ ይረዳናል። ለሚሰማን ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት መሠረታዊ መንስዔ የሆኑትን ነገሮች አምላክ ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወግድ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጠናል። ክርስቲያኖች እነዚህ ‘የቀድሞ ነገሮች የማይታሰቡበት’ ቀን የሚመጣበትን ጊዜ በመጠባበቅ በእሱ ላይ ለመደገፍ ወስነዋል።—ኢሳይያስ 65:17፤ ራእይ 21:4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.11 ትክክለኛ ስሟ አይደለም።
^ አን.12 ንቁ! ይኼኛው የሕክምና ዓይነት የተሻለ ነው በማለት የሚሰጠው ሐሳብ የለም። ክርስቲያኖች የሚከታተሉት የትኛውም ዓይነት ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይቃረን መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የጥቅምት 15, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 25-9ን ተመልከት።