ሲጋራ ማቆም የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
ሲጋራ ማቆም የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
ረዥም ዕድሜና ደስታ ያልተለየው ሕይወት መኖር የሚፈልግ ሰው ማጨስ የለበትም። ለረዥም ጊዜ ያጨሰ ሰው በትንባሆ ምክንያት የመሞት ዕድሉ ከሁለት እጅ አንድ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ዲሬክተር “ሲጋራ አጫሹን የእድሜ ልክ ሱሰኛ አድርጎ ካቆየ በኋላ በመጨረሻ ሊገድል የሚችለውን ትክክለኛ የኒኮቲን መጠን አስተካክሎ እንዲሰጥ ተደርጎ በከፍተኛ ብልሃት የሚሠራ ምርት ነው” በማለት ተናግረዋል።
ስለዚህ ማጨስ ማቆም የሚኖርብህ አንደኛው ምክንያት በጤናና በሕይወት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ ነው። ማጨስ ለሕይወት አስጊ ከሆኑ ከ25 ከሚበልጡ በሽታዎች ጋር ዝምድና እንዳለው ተደርሶበታል። ለምሳሌ ያህል ለልብ ድካም፣ አንጎል ውስጥ ለደም መፍሰስ፣ ሥር ለሰደደ ብሮንካይት፣ ለኤምፊዚማና ለተለያየ ዓይነት ካንሰር በተለይ ደግሞ ለሳንባ ካንሰር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል።
እርግጥ አንድ ሰው በእነዚህ በሽታዎች የሚያዘው ለረዥም ዓመታት ካጨሰ በኋላ ሊሆን ይችላል። እስከዚያም ቢሆን የሚያጨስ ሰው በሌሎች ዘንድ ያለው ተወዳጅነት መቀነሱ አይቀርም። ማስታወቂያዎች ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎችን ጤነኞችና ጥሩ ቁመና እንዳላቸው አድርገው ያቀርቧቸዋል። ሐቁ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ማጨስ መጥፎ የአፍ ጠረን ያመጣል፣ ጥርስ ያበልዛል፣ የጥፍር ቀለምን ይለውጣል። በወንዶች ላይ ለወሲብ ስንፈት አስተዋጽዖ ያደርጋል። ሳልና የትንፋሽ እጥረት ያስከትላል። በተጨማሪም አጫሾች አለ እድሜያቸው የፊት ቆዳ መጨማተርና ሌሎች የቆዳ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።
ማጨስ ሌሎችን እንዴት ይነካል?
መጽሐፍ ቅዱስ “ባልንጀራህን [“ጎረቤትህን፣” NW ] እንደ ነፍስህ ውደድ” ይላል። (ማቴዎስ 22:39) ማጨስ እንድታቆም ከሚያስገድዱህ ጠንካራ ምክንያቶች አንዱ ለባልንጀራህ በተለይ ደግሞ የቅርብ ባልንጀሮችህ ለሆኑት ለቤተሰብህ ያለህ ፍቅር ነው።
ማጨስ ሌሎችን ይጎዳል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ አጫሽ ሲጋራውን የትም ቦታ ቢለኩስ ማንም አይቃወመውም ነበር። አሁን ግን ሌሎች ከሚያጨሱት
ሲጋራ የሚወጣውን ጭስ መተንፈስ ያለውን ጉዳት የተገነዘቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ የሰዎች ዝንባሌ ተለውጧል። ለምሳሌ ያህል የሚያጨስ ባል ያላት አንዲት ሴት በሳንባ ካንሰር የመያዝ እድሏ የማያጨስ ባል ካላት ሴት 30 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ከሚያጨሱ ወላጆች ጋር የሚኖሩ ልጆች በሕይወታቸው የመጀመሪያ ሁለት ዓመታት በኒሞኒያ ወይም በብሮንካይት በሽታ የመያዝ እድላቸው የሚያጨስ ሰው በሌለበት ቤት ከሚኖሩት የበለጠ ነው።በእርግዝናቸው ወቅት የሚያጨሱ ሴቶች በጽንሱ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። በሲጋራ ጭስ ውስጥ ያለው ኒኮቲን፣ ካርቦን ሞኖክሳይድና ሌሎች አደገኛ ኬሚካሎች በእናትዬዋ ደም ውስጥ ከገቡ በኋላ ቀጥታ በማሕፀን ውስጥ ወዳለው ጽንስ ይገባሉ። በዚህም ምክንያት የማስወረድ፣ የሞተ ልጅ የመውለድና ከተወለደ በኋላ የመሞት ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል። ከዚህም በላይ በእርግዝናቸው ወቅት ያጨሱ ከነበሩት እናቶች የሚወለዱ ልጆች በጨቅላነታቸው በድንገት የመሞት ዕድላቸው ከሌሎቹ ሕፃናት በሦስት እጥፍ ይበልጣል።
ኪሳራው በጣም ከፍተኛ ነው
ማጨስ እንድታቆም የሚያደርግህ ሌላው ምክንያት ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል መሆኑ ነው። የዓለም ባንክ በማጨስ ምክንያት የሚደርሰው የሕክምና ወጪ በዓመት 200 ቢልዮን ዶላር እንደሚደርስ ገምቷል። እርግጥ በትንባሆ ምክንያት የታመሙ ሰዎች የሚደርስባቸው ሕመምና ሥቃይ በገንዘብ የሚተመን አይደለም።
ሲጋራ በአጫሹ ግለሰብ ላይ የሚያደርሰውን ቀጥተኛ ወጪ ለማስላት አስቸጋሪ አይደለም። አጫሽ ከሆንክ በቀን ለሲጋራ የምታወጣውን ገንዘብ በ365 አባዛ። በዓመት ያን የሚያክል ገንዘብ ታወጣለህ ማለት ነው። ይህንኑ አኃዝ በአሥር ብታባዛው ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ብታጨስ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስወጣህ ማየት ትችላለህ። ውጤቱ ሊያስገርምህ ይችላል። ያን በሚያክል ገንዘብ ምን ልትሠራበት እንደምትችል አስብ።
ሌላ ዓይነት ሲጋራ ማጨስ ከችግሩ ያድናልን?
የትንባሆ ኢንዱስትሪ ማጨስ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ይቀንሳል በማለት ለስላሳ ሲጋራ የሚባሉትን አነስተኛ ታርና ኒኮቲን ያላቸውን ሲጋራዎች ያስተዋውቃል። ይሁን እንጂ አነስተኛ የኒኮቲንና የታር መጠን ያላቸውን ሲጋራዎች ማጨስ የሚጀምሩ ሰዎች ከዚህ
በፊት የለመዱትን የኒኮቲን መጠን መፈለጋቸው አይቀርም። በዚህም ምክንያት እንደነዚህ ያሉትን ሲጋራዎች ማጨስ የሚጀምሩ ሰዎች የጎደለባቸውን የኒኮቲን መጠን ለማካካስ ብዙ ሲጋራዎች ያጨሳሉ ወይም በረዥሙ በመሳብ ብዙ ጭስ ወደ ሳንባቸው ያስገባሉ። ምንም ዓይነት የማካካሻ ለውጥ የማያደርጉ ቢሆኑ እንኳ ጨርሶ ቢያቆሙ ኖሮ ሊያገኙ የሚችሉትን የጤንነት ጥቅም ሳያገኙ ይቀራሉ።ፒፓዎችና ሲጋሮችስ? የትንባሆ ኢንዱስትሪ ፒፓዎችንና ሲጋሮችን የባለጠግነት ምልክት እንደሆኑ አድርጎ ሲያስተዋውቅ ቢቆይም የጭሳቸው ቀሳፊነት ከሲጋራ የሚተናነስ አይደለም። አጫሾች ከሲጋር ወይም ከፒፓ የሚወጣውን ጭስ ወደ ሳንባቸው ባይስቡም እንኳን በከንፈር፣ በአፍና በምላስ ካንሰር የመያዛቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል።
ጭስ አልባ ትንባሆ ይሻል ይሆን? ጭስ የለሽ ትንባሆ በሁለት መንገድ ማለትም በሱረትና በሚታኘክ መልክ ይዘጋጃል። እንደ ሱረት የሚወሰደው ትንባሆ ከደቀቀ በኋላ በቆርቆሮ ወይም በኪስ መሰል ወረቀት ታሽጎ ይሸጣል። አብዛኛውን ጊዜ ተጠቃሚዎቹ በታችኛው ከንፈራቸው ወይም በጉንጫቸው ውስጥ ይይዙታል። የሚታኘከው ትንባሆ በረዥሙ ይጠቀለልና በኪስ መሰል ወረቀት ውስጥ ታሽጎ ይሸጣል። ይህ ዓይነቱ ትንባሆ የሚመጠጥ ሳይሆን የሚታኘክ ነው። ሁለቱም ቢሆኑ መጥፎ የአፍ ጠረን፣ የጥርስ መበለዝ፣ የአፍና የላንቃ ካንሰር፣ የኒኮቲን ሱስ፣ ወደ ካንሰርነት ሊለወጥ የሚችል ነጣ ያለ የአፍ ቁስል፣ የድድ መሸሽና በጥርስ አካባቢ ያሉ አጥንቶች መሸርሸር ያስከትላል። ትንባሆ መምጠጥ ወይም ማኘክ የማጨስ ጥሩ አማራጭ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ማቆም የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
የብዙ ዓመት አጫሽ ነህ እንበል። ማጨስ ስታቆም ምን ይሆናል? የመጨረሻ ሲጋራህን ካጨስክ ከ20 ደቂቃ በኋላ የደምህ ግፊት ወደ ትክክለኛው መጠን ይመለሳል። ከአንድ ሳምንት በኋላ መላ ሰውነትህ ከኒኮቲን ነፃ ይሆናል። ከአንድ ወር በኋላ ሳልህና የአፍንጫ መዘጋትህ እየቀነሰ ይሄዳል እንዲሁም ድካምህና የትንፋሽ እጥረት መሻሻል ይጀምራል። ከአምስት ዓመት በኋላ በሳንባ ካንሰር የመሞትህ ዕድል 50 በመቶ ይቀንሳል። ከ15 ዓመት በኋላ በልብ ድካም የመሞት ዕድልህ ፈጽሞ አጭሶ ከማያውቅ ሰው ጋር እኩል ይሆናል።
የምትመገበው ምግብ ይበልጥ ይጥምሃል። የአፍህ፣ 2 ቆሮንቶስ 7:1) ከእንግዲህ ብተው ምንም ዋጋ የለውም ብለህ አታስብ። ዛሬ ነገ ሳትል በፍጥነት ብታቆም የተሻለ ይሆናል።
የሰውነትህና የልብስህ ጠረን ጥሩ ይሆናል። ትንባሆ የመግዛት ችግርም ሆነ ወጪ ይቀልልሃል። ጥሩ ውጤት ላይ እንደደረስክ ስለሚሰማህ ደስ ይልሃል። ልጆች ካሉህ የአንተን ምሳሌ ስለሚመለከቱ ከማጨስ የመራቃቸው እድል ከፍተኛ ይሆናል። ረዥም እድሜ የመኖር አጋጣሚህ ይጨምራል። ከዚህ በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋን . . . ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ስለሚል ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነገር አደረግህ ማለት ነው። (ሲጋራ ማቆም በጣም አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
ሲጋራ ማቆም ከፍተኛ ፍላጎት ላላቸው እንኳን ሳይቀር አስቸጋሪ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት በትንባሆ ውስጥ የሚገኘው ኒኮቲን ከፍተኛ የሆነ ሱስ የማስያዝ ኃይል ስላለው ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው “በአእምሮ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዕፆች ሱስ በማስያዝ ኃይላቸው ሲወዳደሩ ኒኮቲን ከሄሮይንም ሆነ ከኮኬይን የበለጠ ኃይል አለው።” ኒኮቲን እንደ ሄሮይንና ኮኬይን ወዲያው አእምሮ የመሳት ወይም የመስከር ምልክት ስለማያሳይ ያለውን ኃይል አሳንሶ ለማየት ቀላል ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በሚያሳድርባቸው ደስ ደስ የመሰኘት ስሜት ምክንያት ደጋግመው ያጨሱታል። ኒኮቲን በስሜት ላይ ለውጥ የሚያስከትል መሆኑን መካድ አይቻልም። የመረበሽ ስሜት ያስወግዳል። ይሁን እንጂ ሲጋራ የሚያስወግደው ውጥረት በከፊል በኒኮቲን አምሮት ምክንያት የሚፈጠር ነው።
በተጨማሪም ሲጋራ ለማቆም አስቸጋሪ የሚሆነው ድርጊቱ ራሱ አመል መሆኑ ነው። አጫሾች በኒኮቲን ሱስ ከመያዛቸው በተጨማሪ በተደጋጋሚ ሲጋራ መለኮሱና ጭሱን ማቡነኑ ራሱ ሱስ ይሆንባቸዋል። ‘እጅህ ሥራ እንዳይፈታ የምታደርገው ነገር ነው።’ ‘ጊዜ ያሳልፍልሃል’ ይላሉ አንዳንዶች።
ሲጋራ ለማቆም አስቸጋሪ የሚሆንበት ሦስተኛ ምክንያት ትንባሆ ዕለት ተዕለት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ክፍል መሆኑ ነው። የትንባሆ ኢንዱስትሪ አጫሾችን መልከ ቀናዎች፣ ንቁዎች፣ ጤነኞችና አዋቂዎች እንደሆኑ የሚያሳዩ ማስታወቂያዎችን ለማሰራጨት በዓመት እስከ ስድስት ቢልዮን የሚደርስ ዶላር ወጪ ያደርጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ ፈረስ ሲጋልቡ፣ ሲዋኙ፣ ቴኒስ ሲጫወቱ ወይም በሌሎች ማራኪ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ሲካፈሉ ይታያሉ። የፊልምና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ጨዋና የተከበሩ ሰዎች ሲያጨሱ ያሳያል። የትንባሆ ሽያጭ በሕግ የተፈቀደ ከመሆኑም በላይ የትም ቦታ እንደ ልብ ይገኛል። አብዛኞቻችን በየቀኑ ከሚያጨስ ሰው ጋር መገናኘታችን አይቀርም። እነዚህ ሰዎች ከሚያሳድሩብን ተጽዕኖ ማምለጥ አንችልም።
ራስ ምታትን ለማስታገስ አስፕሪን እንደምትወስድ የማጨስ አምሮትህን የሚያጠፋልህ መድኃኒት አለመኖሩ የሚያሳዝን ነው። አንድ ሰው ይህን አስቸጋሪ የሆነውን ልማድ የማቆም ጥረት በተሳካ ሁኔታ እንዲወጣ ልባዊ የሆነ ፍላጎት ሊያድርበት ይገባል። ልክ ክብደት ለመቀነስ እንደሚደረገው ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ቆራጥነት ይጠይቃል። በዚህ ረገድ ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ የሚወድቀው በአጫሹ ላይ ነው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ገና በልጅነት ሱሰኛ መሆን
በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት ሲጋራ ከቀመሱ 4 ወጣቶች መካከል አንዱ ሱሰኛ እንደሚሆን አረጋግጠዋል። ይህ መጠን ኮኬይንና ሄሮይን ሞክረው ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው። ሙሉ ሰው ከሆኑ አጫሾች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ማጨስ መጀመራቸው የሚቆጫቸው ቢሆኑም ለማቆም የቻሉት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሲጋራ ጭስ ውስጥ ምን ነገሮች አሉ?
በሲጋራ ጭስ ውስጥ የሚገኘው ታር ከ4, 000 የሚበልጡ ኬሚካሎች አሉት። ከእነዚህ ኬሚካሎች መካከል 43ቱ ለካንሰር መንስዔ እንደሚሆኑ ታውቋል። ሳያናይድ፣ ቤንዚን፣ ሜታኖልና ችቦ ለማብራት እንደ ነዳጅ ሆኖ የሚያገለግለው አሴቲሊን ከእነዚህ መካከል የሚቆጠሩ ናቸው። በተጨማሪም በሲጋራ ጭስ ውስጥ መርዛማ የሆኑ ናይትኖጂን ኦክሳይድና ካርቦን ሞኖኦክሳይድ የሚባሉ ጋዞች ይገኛሉ። በሲጋራ ውስጥ የሚገኘው ዋነኛ ኬሚካል ኒኮቲን ሲሆን እርሱም ኃይለኛ ሱስ የማስያዝ ኃይል አለው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የምትወዱት ሰው እንዲያቆም መርዳት
የማታጨስና ማጨስ የሚያስከትለውን ጉዳት የምታውቅ ከሆንክ ጓደኞችህና የምትወዳቸው ሰዎች ማጨስ አለመተዋቸው ሊያበሳጭህ ይችላል። እንዲያቆሙ ለመርዳት ምን ልታደርግ ትችላለህ? መጨቅጨቅ፣ መለመን፣ ማስገደድና መሳደብ አብዛኛውን ጊዜ ውጤት አያስገኙም። ቁጭ አድርጎ መውቀስም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። አጫሹ ሲጋራ ማጨሱን ከማቆም ይልቅ እነዚህ ዘዴዎች የሚያስከትሉበትን የስሜት ቁስል ለማስታገስ ሲል ይበልጥ ሊያጨስ ይችላል። ስለዚህ ሲጋራ ማቆም ምን ያህል አስቸጋሪ እንዲሁም አንዳንዶች ከሌሎች የበለጠ አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ለመረዳት ሞክር።
አንድ ሰው ሲጋራ ማጨሱን እንዲያቆም ማድረግ አትችልም። ለማቆም የሚያስችለው ውስጣዊ ጥንካሬና ጽኑ እምነት ካጫሹ መምጣት አለበት። አንተ ማድረግ የሚኖርብህ ለማቆም ያለውን ፍላጎት የምታጠናክርባቸውን ፍቅራዊ መንገዶች መፈለግ ነው።
ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ተስማሚ በሆነ ጊዜ ለግለሰቡ ያለህን ፍቅር ልትገልጽለትና የማጨስ ልማዱ ወይም ልማዷ እንደሚያሳስብህ ልትናገር ትችላለህ። ለመተው የሚያደርገውን ወይም የምታደርገውን ውሳኔ በመደገፍ ከአጠገቡ ወይም ከአጠገቧ እንደምትሆን ግለጽ። እርግጥ ይህም ዘዴ ቢሆን ብዙ ጊዜ ከተደጋገመ ውጤታማነቱን ያጣል።
የምትወደው ሰው ለማቆም ከወሰነ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ማጨስ በማቆሙ ምክንያት እንደ መንፈስ ጭንቀትና እንደ ቁጠኝነት የመሰሉ ስሜቶች ሊሰሙት እንደሚችሉ አስታውስ። ራስ ምታትና እንቅልፍ ማጣትም ሊኖርበት ይችላል። እነዚህ ስሜቶች በሙሉ ጊዜያዊ እንደሆኑና ሰውነቱ ጤናማ ከሆነ አዲስ አኗኗር ጋር በመላመድ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች እንደሆኑ አስገንዝበው። ደስተኛና ብሩህ አመለካከት ይኑርህ። ማጨስ ማቆም በመጀመሩ ምን ያህል ደስ እንዳለህ ግለጽለት። የማጨስ አምሮት እየተፈታተነው ባለበት ጊዜ ወደ ማጨስ ሊመልሱት የሚችሉትን ውጥረት የሚፈጥር ሁኔታዎች በሙሉ አስወግድለት።
ተመልሶ ማጨስ ቢጀምርስ? የመደንገጥ ወይም የመቆጣት ስሜት አታሳይ። አዛኝ ሁን። ሁኔታውን ለሁለታችሁም ትምህርት የሚሰጥ ተሞክሮ እንደሆነ አድርገህ ተመልከትና ሁለተኛው ሙከራ እንዲሳካ የተቻለህን ሁሉ አድርግ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የትንባሆ ኢንዱስትሪ በየዓመቱ ለማስታወቂያ ብቻ ስድስት ቢልዮን ዶላር ያወጣል