መረጃዎችን ማዛባት
መረጃዎችን ማዛባት
“በጥሩ ዘዴና ባለመታከት የሚቀርብ ፕሮፓጋንዳ መንግሥተ ሰማያትን ሲኦል አስመስሎ ማቅረብ፣ በተቃራኒው ደግሞ በጣም አስከፊ የሆነውን ኑሮ ገነት አስመስሎ ማቅረብ ይቻላል።”— አዶልፍ ሂትለር፣ ሜይን ካምፍ
የመገናኛ መሣሪያዎች ከህትመት ወደ ቴሌፎን፣ ከዚያም ወደ ራዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት እየተራቀቁ በሄዱ መጠን የአሳማኝ መልእክቶች ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ተፋጥኗል። በመገናኛ ረገድ የተደረገው ይህ ሥር ነቀልና ፈጣን ለውጥ ሰዎች ከሁሉም አቅጣጫ በሚጎርፉ መረጃዎች እንዲጥለቀለቁ በማድረጉ የመረጃ መጨናነቅ ተፈጥሯል። ብዙ ሰዎች የሚደርሷቸውን መልእክቶች ሳይመረምሩ ወይም ሳይጠረጥሩ ፈጠን ብለው በመቀበል ይህን መጨናነቅ ለማቅለል ሞክረዋል።
በተለይ ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንዲኖር የማይፈልጉት መሠሪ ፕሮፓጋንዲስቶች ይህን አቋራጭ መንገድ ይወዱታል። ፕሮፓጋንዳ ስሜት በማነሳሳት፣ ስጋት በማሳደር፣ አሻሚ ትርጉም ባላቸው ቃላት በመጠቀምና የሎጂክ ሕጎችን በማጣመም ምክንያታዊ አስተሳሰቦችን ያዳክማል። ታሪክ እንደሚመሰክረው እንደነዚህ ያሉ ዘዴዎች በጣም ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል።
የፕሮፓጋንዳ ታሪክ
በዛሬው ጊዜ “ፕሮፓጋንዳ” የሚለው ቃል ተገቢ ያልሆኑ ዘዴዎችን የሚያመለክትና አሉታዊ አንድምታ ያለው ቃል ሆኗል። ይሁን እንጂ ለቃሉ የተሰጠው ጥንታዊ ትርጉም ከዚህ የተለየ ነበር። “ፕሮፓጋንዳ” የሚለው ቃል የመጣው ኮንግሬጋቲዊ ዲ ፐሮፓጋንዳ ፊዴ (እምነት ለማሠራጨት የተቋቋመ ጉባኤ) ለተባለው የካቶሊክ ጳጳሳት ኮሚቴ ከተሰጠው የላቲን ስያሜ ነው። ይህ በአጭሩ ፕሮፓጋንዳ እየተባለ መጠራት የጀመረው ኮሚቴ ሚስዮናውያንን እንዲቆጣጠር በፖፕ ግሪኮሪ 15ኛ የተቋቋመው በ1622 ነበር። ቀስ በቀስ ፕሮፓጋንዳ የሚለው ቃል አንድን እምነት ለማሠራጨት የሚደረገውን ማንኛውም ጥረት ለማመልከት ማገልገል ጀመረ።
ይሁን እንጂ የፕሮፓጋንዳ ፅንሰ ሐሳብ የተፈጠረው በ17ኛው መቶ ዘመን አልነበረም። ሰዎች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ርዕዮተ ዓለሞችን ለማስፋፋት ወይም ዝናቸውንና ሥልጣናቸውን ለማበልጸግ ባገኙት መሣሪያ በሙሉ ሲጠቀሙ ኖረዋል። ለምሳሌ ያህል ከግብፅ ፈርዖኖች ጀምሮ ኪነ ጥበብ ፕሮፓጋንዳዊ ዓላማዎችን ለማራመድ አገልግሏል። እነዚህ ነገሥታት ፒራሚዶቻቸውን የሠሩት ታላቅ ኃይልና ዘላለማዊነት ያላቸው መሆኑን ለማሳመን ነበር። ሮማውያን የነበራቸው የሕንጻ ጥበብም በተመሳሳይ የፖለቲካ
ዓላማ ማለትም መንግሥትን ለማስከበር አገልግሏል። “ፕሮፓጋንዳ” የሚለው ቃል አሉታዊ ትርጉም ማስተላለፍ የጀመረው መንግሥታት በመገናኛ ብዙሐን የሚተላለፉትን የውጊያ መረጃዎች መቆጣጠር በጀመሩበት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም አዶልፍ ሂትለርና ዮሴፍ ጎበልስ የተዋጣላቸው ፕሮፓጋንዲስቶች መሆናቸውን አስመስክረዋል።ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ፕሮፓጋንዳ ለብሔራዊ መርሕ ማራመጃ ዋነኛ መሣሪያ ሆኗል። የምዕራቡም ሆነ የምሥራቁ ጎራ ሚናውን ያልለየውን ብዙሐን ከጎናቸው ለማሰለፍ ከፍተኛ ዘመቻ አካሂደዋል። እያንዳንዱ የብሔራዊ ሕይወትና ፖሊሲ ለፕሮፓጋንዳ ዓላማ አገልግሏል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጣም የተራቀቀው የፕሮፓጋንዳ ቴክኒክ በምረጡኝ ቅስቀሳዎች እንዲሁም የትንባሆ ኩባንያዎች በሚያሠራጯቸው ማስታወቂያዎች በግልጽ ይታያል። እንደ ሊቃውንትና የሕዝብ መሪዎች ተደርገው የሚታዩ ሰዎች ትንባሆ ማጨስ ጤና የሚጎዳ ሳይሆን ቁመና የሚያሳምርና ዘመናዊነት እንደሆነ በማስመሰል አቅርበዋል።
ውሸት፣ ውሸት!
ፕሮፓጋንዲስቶች በጣም ጥሩና አመቺ መሣሪያ ሆኖ ያገኙት ዓይን ያወጣ ውሸት ነው። ለምሳሌ ያህል ማርቲን ሉተር በ1543 የአውሮፓን አይሁዶች አስመልክቶ የጻፈውን ውሸት እንመልከት:- “የውኃ ጉድጓዶችን መርዘዋል፣ ሰዎችን ገድለዋል፣ ሕፃናትን አፍነዋል። . . . መርዘኞች፣ መራሮች፣ ቂመኞች፣ መሠሪ እባቦች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ በመርዛቸው የሚነድፉና የሚጎዱ የዲያብሎስ ልጆች ናቸው።” ክርስቲያን ነን ለሚሉ ሰዎች የሰጠው ማሳሰቢያ ምን ነበር? “ምኩራቦቻቸውን ወይም ትምህርት ቤቶቻቸውን አቃጥሉ። . . . ቤቶቻቸው መፍረስና መውደም አለባቸው።”
በዚያ ዘመን ላይ ጥናት ያካሄዱ አንድ የመንግሥትና የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል:- “ፀረ ሴማዊነት በመሠረቱ አይሁዳውያን ካደረጓቸው ነገሮች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ስላልነበረው ፀረ ሴማዊ የሆነ አንድ ሰው ስለ አይሁዳውያን ትክክለኛ ባሕርይ ካለው እውቀት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም።” በተጨማሪም “አይሁዳውያን የመጥፎ ነገር ሁሉ ተምሳሊት ስለሆኑ የማንኛውም ተፈጥሯዊም ሆነ ማኅበራዊ ክፋት ምንጭ ተደርገው ታይተዋል” ብለዋል።
የጅምላ አስተያየት
ሌላው ስኬት ያስገኘ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ደግሞ የጅምላ አስተያየት መስጠት ነው። የጅምላ አስተያየት የአንድን ጉዳይ ፍሬ ነገር የመሸፋፈን ባሕርይ አለው። ብዙውን ጊዜም አንድን የሰዎች ቡድን በጅምላ ለማዋረድ ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች “ጂፕሲዎች [ወይም ስደተኞች] ሌቦች ናቸው” የሚል አስተያየት ሲሰነዘር ይደመጣል። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነው?
የአምድ አዘጋጅ የሆኑት ሪካርዶስ ስመሪቲስ በአንድ አገር በዚህ ዓይነቱ ግንዛቤ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ “የባዕዳን ጥላቻና ዘረኝነት ሊስፋፋ እንደቻለ” ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የዚያች አገር ተወላጆችም ሆኑ ባዕዳን ወንጀል በመፈጸም ረገድ ልዩነት እንደሌላቸው ሊረጋገጥ ችሏል። ለምሳሌ ያህል በግሪክ አገር “ከመቶ ወንጀሎች መካከል 96 የሚሆኑት የሚፈጸሙት [በግሪካውያን] በራሳቸው እንደሆነ” ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ስመሪቲስ ገልጸዋል። “የወንጀል ምክንያቶች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ናቸው እንጂ በዘር ላይ የተመኩ አይደሉም” ካሉ በኋላ “የዜና አቀራረቦችን በማጣመም የባዕዳን ጥላቻና ዘረኝነት እንዲስፋፋ ያደረጉት መገናኛ ብዙሐን ናቸው” በማለት አማርረዋል።
ስም መስጠት
አንዳንድ ሰዎች ሌሎች የእነርሱን ሐሳብ አልቀበል ሲሉ በጭብጡ ላይ ከማተኮር ይልቅ የሰዎቹን ባሕርይ በመንቀፍ የስድብ ቃል ወደመናገር ያዘነብላሉ። ለአንድ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም አስተሳሰብ አሉታዊ ትርጉም ያለው፣ በቀላሉ ሊታወስ የሚችል መጠሪያ ስም ይሰጣሉ። ስም አውጪው ያ ስያሜ ተጠብቆ እንደሚኖር ተስፋ ያደርጋል። ሰዎች ግለሰቡን ወይም አስተሳሰቡን በትክክለኛ መረጃ ሳያመዛዝኑ በተሰጠው ስም ብቻ ከተቃወሙት የስም ሰጪው ዘዴ ተሳክቷል ማለት ነው።
ለምሳሌ ያህል በቅርብ ዓመታት በአውሮፓና በሌሎች አህጉራት ሃይማኖታዊ ኑፋቄዎችን የመቃወም ዘንባሌ ተስፋፍቷል። ይህ አዝማሚያ አናሳ በሆኑ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ላይ የጥላቻ ስሜት እንዲቀሰቀስ ከማድረጉም በላይ እነዚህ ቡድኖች በጠላትነት እንዲታዩ ምክንያት ሆኗል። “ኑፋቄ” በወንጀለኝነት የሚያስፈርጅ ቃል ሆኗል። ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ማርቲን ክሪለ በ1993 “ኑፋቄ ማለት መናፍቅ ከማለት ጋር አንድ ነው። መናፍቅ ደግሞ በጀርመን አገር ዛሬም ሆነ በቀደሙት ዓመታት በእሳት ባይሆንም እንኳ . . . ስምን በማጥፋት፣ ከኅብረተሰብ በማግለልና የኢኮኖሚ አቅሙን በማውደም [እንዲጠፋ የተፈረደበት] ሰው ነው” ብለዋል።
ዚ እንስቲትዩት ፎር ፕሮፓጋንዳ አናሊስስ የተባለው ድርጅት እንደሚከተለው ብሏል:- “የነቀፌታ ስሞች በዓለም ታሪክም ሆነ በግለሰብ ሕይወታችን ላይ በጣም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። የሰዎችን መልካም ስምና ዝና አውድመዋል። . . . [ለሰዎች] ወደ ወህኒ መውረድ ምክንያት ሆነዋል። ሰዎች አእምሯቸውን ስተው ለውጊያ እንዲዘምቱና አምሳዮቻቸው የሆኑ ሌሎች ሰዎችን እንዲጨፈጭፉ አድርገዋል።”
የሰዎችን ስሜት በመጠምዘዝ መጠቀም
ስሜት በጭብጦች እውነተኝነት ወይም በአንድ መከራከሪያ ነጥብ ምክንያታዊነት ላይ የሚጨምረው ወይም የሚቀንሰው ነገር ባይኖርም በማሳመን ረገድ ግን ወሳኝ የሆነ ሚና ይጫወታል። በሙያው የተካኑ አስተዋዋቂዎች ስሜት የሚማርኩ ቃላት በመሰንዘር ጥሩ ችሎታ እንዳለው ሙዚቀኛ የሰዎችን ስሜት በፈለጉበት አቅጣጫ ያስቀይሳሉ።
ፍርሃት የማመዛዘን ችሎታን የሚያጨልም ስሜት ነው። ልክ እንደ ፍርሃት ሁሉ በቅናት ስሜትም መጠቀም የሚችሉ ሰዎች አሉ። ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው የካናዳ ጋዜጣ በየካቲት 15, 1999 እትሙ ከሞስኮ የሚከተለውን ዘግቧል:- “ባለፈው ሳምንት ሦስት ልጃገረዶች በሞስኮ ራሳቸውን በገደሉ ጊዜ የሩስያ መገናኛ ብዙሐን ወዲያው ልጃገረዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች አክራሪ ተከታዮች ናቸው ብለው ነበር።” “አክራሪ” የሚለውን ቃል ልብ በል። ማንኛውም ሰው ወጣቶች ራሳቸውን እንዲገድሉ የሚገፋፋን አክራሪ የሃይማኖት ድርጅት እንደሚፈራ የታወቀ ነው። ታዲያ እነዚህ አሳዛኝ ልጃገረዶች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ናቸውን?
ለምሳሌ ያህልዘ ግሎብ እንዲህ ይላል:- “ፖሊስ ልጃገረዶቹ በምንም መንገድ [ከይሖዋ ምሥክሮች] ጋር ግንኙነት እንዳልነበራቸው ሊያረጋግጥ ቢችልም ይህ እስከሚረጋገጥበት ጊዜ ግን አንድ የሞስኮ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሺህ የሚቆጠሩ አባሎቻቸው በናዚ እንደተገደሉባቸው እየታወቀ የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ጀርመን የአዶልፍ ሂትለር ተባባሪዎች ነበሩ በማለት አዲስ ጥቃት መሰንዘር ጀምሯል።” የተሳሳተ መረጃ ለቀረበላቸውና ምናልባትም በዚህ ምክንያት ፍርሃት ላደረባቸው ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ራስን መግደል የሚያደፋፍሩ ኑፋቄዎች አለበለዚያም የናዚ ተባባሪዎች ናቸው ማለት ነው!”
ጥላቻ ፕሮፓጋንዲስቶች የሚጠቀሙበት ጠንካራ መሣሪያ ነው። ስውርና መጥፎ ትርጉም ያላቸው ቃላት ጥላቻ በማነሳሳት ረገድ በጣም ውጤታማ ናቸው። በአንድ የተወሰነ ዘር፣ ጎሳ ወይም ሃይማኖት ላይ ጥላቻ ሊያነሳሱ የሚችሉ ጸያፍ ቃላት እጅግ ብዙ ናቸው።
አንዳንድ ፕሮፓጋንዲስቶች በሰዎች የኩራት ስሜት ይጠቀማሉ። “አእምሮ ያለው ማንም ሰው እንደሚያውቀው . . .” ወይም “አንተን የመሰለ የተማረ ሰው ለመገንዘብ እንደሚችለው . . .” በመሳሰሉት ሐረጎች ውስጥ የአንድን ሰው የኩራት ስሜት ለመቀስቀስ የገቡ ቃላትን ማግኘት አያስቸግራቸውም። አላዋቂዎች ወይም ሞኞች ሆነን ለመታየት ስለማንፈልግ በኩራት ስሜታችን እንሸነፋለን። በዚህ ሙያ የተካኑት ሰዎች ይህን አሳምረው ያውቃሉ።
መፈክሮችና አርማዎች
መፈክሮች አንድን አቋም ወይም ግብ ለመግለጽ የሚያገለግሉ ግልጽና የማያሻማ ትርጉም የሌላቸው መግለጫዎች ናቸው። ትርጉማቸው አሻሚ በመሆኑ ከመፈክሮቹ ጋር ለመስማማት አይከብድም።
ለምሳሌ ያህል ብሔራዊ ግጭት ወይም ጦርነት በሚኖርበት ጊዜ መሪዎች “ትክክልም ይሁን ስህተት ከአገሬ ጎን እሰለፋለሁ” “አባት አገር፣ ሃይማኖት፣ ቤተሰብ” ወይም “ሞት ወይም ነፃነት” እንደሚሉት ባሉ መፈክሮች ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች ለጦርነቱ ወይም ለግጭቱ ምክንያት የሆኑትን ዋነኛ ጥያቄዎች በጥንቃቄ ይመረምራሉ? ወይስ የሚነገራቸውን ብቻ በጭፍን ይቀበላሉ?
ዊንስተን ቸርችል ስለ አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲጽፉ “እነዚህን ሰላማዊ የሆኑ አርሶ አደሮችና ሠራተኞች ለመለወጥና እርስ በርሱ የሚቦጫጨቅ ኃያል ሠራዊት ለማድረግ የሚያስፈልገው አንድ አርማ ብቻ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም አብዛኞቹ ሰዎች አድርግ የተባሉትን በጭፍን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፕሮፓጋንዲስቱ መልእክቱን ለማስተላለፍ በመሣሪያነት የሚገለገልባቸው እንደ 21 የመድፍ ተኩስ፣ ወታደራዊ ሰላምታና እንደ ባንዲራ የመሰሉ አርማዎችና ምልክቶች አሉ። የወላጆች ፍቅርም በመሣሪያነት የሚያገለግልበት ጊዜ አለ። አባት አገር፣ እናት አገር፣ እናት ቤተ ክርስቲያን የሚሉትን የመሰሉ ምሳሌያዊ ቃላት ሌሎችን ለማሳመን የሚሞክሩ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ናቸው።
ስለዚህ የረቀቀው የፕሮፓጋንዳ ጥበብ አእምሮን ሊያሽመደምድ፣ የጠራ የማሰብና የማስተዋል ችሎታን ሊያሰናክል እንዲሁም ግለሰቦች ሆ ብለው እንድን አቅጣጫ እንዲከተሉ ሊያደርግ ይችላል። ታዲያ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የረቀቀው የፕሮፓጋንዳ ጥበብ አእምሮን ሊያሽመደምድና የጠራ የማሰብ ችሎታን ሊያሰናክል ይችላል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ፕሮፓጋንዳ ማሠራጨት ነውን?
አንዳንድ ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክሮች ጽዮናዊ ፕሮፓጋንዳ አሰራጪዎች ናቸው የሚል ክስ ሰንዝረዋል። ሌሎች ደግሞ የምሥክሮቹ አገልግሎት ኮምኒዝም ማስፋፋት ነው ብለዋል። አሁንም ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ “የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም” አስተሳሰብና ጥቅም ያስፋፋል ብለዋል። ምሥክሮቹ ሥርዓተ አልበኞች ናቸው፣ ሁከት በማስነሳት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ሕግና ሥርዓት እንዲለወጥ የማድረግ ዓላማ አላቸው የሚሉም አሉ። እነዚህ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ክሶች እውነት ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።
ሐቁ የይሖዋ ምሥክሮች አንዱንም አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸውን የሚያከናውኑት ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ሲል የሰጠውን ተልእኮ በታማኝነት መታዘዝ ነው። (ሥራ 1:8) ሥራቸው የሚያተኩረው ሙሉ በሙሉ አምላክ በመላው ምድር ላይ ሰላም ለማምጣት በሚጠቀምበት ሰማያዊ መንግሥት ምሥራች ላይ ነው።— ማቴዎስ 6:10፤ 24:14
የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ የተከታተሉ ሰዎች ይህ የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ የማንኛውንም አገር መልካም አኗኗርና ሥርዓት የሚያናጋ ተግባር እንደሚፈጽሙ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኙም።
የይሖዋ ምሥክሮች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ላበረከቷቸው ጠቃሚ ተግባራት አስተያየት የሰጡ ጋዜጠኞች፣ ዳኞችና ሌሎች ባለ ሥልጣናት ብዙ ናቸው። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። አንዲት የደቡባዊ አውሮፓ ዜና ዘጋቢ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ከተገኘች በኋላ እንዲህ ብላለች:- “ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር ያላቸው ሰዎች ናቸው። እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱና በሌሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ሕሊናቸውን አክብረው እንዲኖሩ የተማሩ ናቸው።”
ቀደም ሲል ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት ያልነበረው ሌላ ጋዜጠኛ ደግሞ “በምሳሌነት የሚጠቀስ አኗኗር አላቸው። የሥነ ምግባርና የምግባረ ሰናይ ደንቦችን አይጥሱም” ብሏል። አንድ የፖለቲካ ሳይንቲስትም በበኩሉ “ሌሎች ሰዎች ጥልቅ የሆነ ደግነት፣ ፍቅርና ጨዋነት ያሳያሉ” የሚል ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቷል።
የይሖዋ ምሥክሮች ለባለ ሥልጣኖች መገዛት ተገቢ እንደሆነ ያስተምራሉ። ሕግ አክባሪ ዜጎች እንደመሆናቸው መጠን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሃቀኝነት፣ ስለ እውነተኝነትና ስለ ንጽሕና ያወጣቸውን ደንቦች ያከብራሉ። የራሳቸው ቤተሰብ ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ይጥራሉ። ሌሎች ሰዎችም ተመሳሳይ የሆነ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ለማስተማር ይሞክራሉ። ከሰዎች ሁሉ ጋር በሰላም ይኖራሉ። ሁከት በሚያነሳሱ ረብሻዎች ወይም በፖለቲካዊ አብዮት አይካፈሉም። የይሖዋ ምሥክሮች የሁሉ የበላይ የሆነው ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ፍጹም ሰላማዊና ጻድቅ የሆነ መንግሥት በምድር ላይ እንዲመሠረት የሚያደርግበትን ጊዜ እየጠበቁ የሰብዓዊ ባለ ሥልጣኖችን ሕጎች በመታዘዝ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሆነው ለመታየት ይጥራሉ።
የምሥክሮቹ ሥራ ትምህርታዊ ገጽታም አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲያገናዝቡና ይህንንም በማድረግ ትክክለኛ የሆነ አኗኗርና ሥነ ምግባር እንዲከታተሉ ይረዳሉ። የቤተሰብ ኑሮን የሚያበለጽጉ እሴቶችን ያስፋፋሉ። ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲቋቋሙ ይረዷቸዋል። በተጨማሪም ጎጂና መጥፎ ልማድ የነበራቸው ሰዎች ልማዳቸውን የሚያሸንፉበትና ከሌሎች ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚችሉበትን ጥንካሬ እንዲያገኙ ይረዳሉ። እንዲህ ያለው ሥራ “ፕሮፓጋንዳ” ሊባል አይችልም። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዳለው ሐሳቦች በነፃ በሚንሸራሸሩበት ጊዜ ሁሉ “ፕሮፓጋንዳ ከትምህርት ይለያል።”
[ሥዕሎች]
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጅዋቸው ጽሑፎች የቤተሰብ እሴቶችንና ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋሞችን ያስፋፋሉ
[በገጽ 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ፕሮፓጋንዳ ለብዙ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑትን ጦርነትንና ማጨስን ያበረታታል