ውጭ አገር መሄድ ይኖርብኛልን?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ውጭ አገር መሄድ ይኖርብኛልን?
“ሌላ ቦታ የመኖር ፍላጎት አደረብኝ።”—ሳም
“እንዲሁ የማወቅ ጉጉት አድሮብኝ ነበር። አንድ አዲስ የሆነ ነገር ለማየት ፈለግሁ።”—ማረን
“አንድ የቅርብ ጓደኛዬ ለትንሽ ጊዜ ከቤተሰብ መለየቴ ጥሩ እንደሚሆንልኝ ነገረኝ።”—አንድሬያስ
“ጀብዱ ለመፈጸም በጣም ጓጉቼ ነበር።”—ሃገን
ውጭ አገር ለመኖር አስበህ ታውቃለህ? ምናልባትም ለተወሰነ ጊዜ? በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ውጭ አገር ይሄዳሉ። አንድሬያስ ውጭ አገር ስላሳለፈው ሕይወት ሲናገር “እንደገና ባደርገው ደስታዬን አልችለውም” ብሎ ነበር።
አንዳንድ ወጣቶች በውጭ አገር የተወሰነ ጊዜ ለማሳለፍ የሚሄዱት ገንዘብ ማግኘት ወይም የውጭ አገር ቋንቋ መማር ስለሚፈልጉ ነው። ለምሳሌ፣ በብዙ አገሮች ኦ ፔር በመባል የሚታወቅ ኘሮግራም ያለ ሲሆን ይህ ኘሮግራም ወጣት የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች የቤት ውስጥ ሥራ ሠርተው መኖሪያና ምግብ እንዲያገኙና በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ የአገሩን ቋንቋ በመማር እንዲያሳልፉ ያስችላቸዋል። በሌላው በኩል ደግሞ ለመማር ሲሉ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ወጣቶችም አሉ። ሌሎች ደግሞ ቤተሰባቸውን በቁሳዊ መንገድ ለመርዳት የሚያስችላቸውን ሥራ ለማግኘት ሲሉ ይሄዳሉ። እንዲሁም ሌሎች ትምህርት ከጨረሱ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እርግጠኞች ስላልሆኑ በውጭ አገር ጥቂት ጊዜ ለማሳለፍ ይፈልጋሉ።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች አገልግሎታቸውን ለማስፋት በማሰብ የወንጌላውያን እጥረት ወዳለባቸው ቦታዎች ሄደዋል። ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ምክንያት የሆነው ነገር ምንም ይሁን ምን በውጭ አገር መኖር ራስን በመቻል ረገድ ጠቃሚ ትምህርት ሊሰጥ የሚችል ከመሆኑም በላይ የእውቀት አድማስህን ሊያሰፋልህ ይችላል። እንዲያውም የውጭ አገር ቋንቋ አጥርቶ ለማወቅ ስለሚያስችልህ ሥራ የማግኘት አጋጣሚህ ከፍ ይላል።
ሆኖም ውጭ አገር የሄደ ሁሉ ሕይወቱ የተቃና ይሆናል ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ ለትምህርት ወደ ውጭ የሄደችው ሱዛን አንድ ዓመት ካሳለፈች በኋላ እንዲህ አለች:- “ተጀምሮ እስኪያልቅ ሁሉ ነገር የተቃና እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ። ሆኖም እንዳሰብኩት አልሆነም።” እንዲያውም አንዳንድ ወጣቶች ጉልበታቸው አላግባብ ተበዝብዟል ወይም ከባድ ችግር ውስጥ ገብተዋል። ስለዚህ ጓዝህን ጠቅልለህ ከመነሳትህ በፊት ወደ ውጭ አገር መሄድ ያለውን ጥቅምና ጉዳት ቁጭ ብለህ መመርመርህ ብልህነት ነው።
ለመሄድ የተነሳሳህበትን ምክንያት በጥንቃቄ መርምር
ጥቅምና ጉዳቱን መመርመር ሲባል ወደ ውጭ ለመሄድ የገፋፋህን ውስጣዊ ዓላማ መመርመርንም ይጨምራል። መንፈሳዊ ፍላጎቶችን ለመከታተል ወይም የቤተሰብ ኃላፊነትን ለመወጣት ሲባል ወደ ውጭ መሄድ አንድ ነገር ነው። ሆኖም ልክ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች ብዙዎቹ ጀብዱ ለመሥራት፣ የበለጠ ነጻነት ለማግኘት ወይም ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ስለሚፈልጉ ብቻ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ይነሳሉ። ይህ በራሱ ስህተት ላይሆን ይችላል። እንዲያውም መክብብ 11:9 “በጉብዝናህ ደስ ይበልህ” በማለት ወጣቶችን ያበረታታል። ይሁን እንጂ ቁጥር 10 “ከልብህ ኀዘንን አርቅ፣ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ” በማለት ያስጠነቅቃል።
ውጭ አገር ለመሄድ የተነሳሳኸው ከወላጆች ቁጥጥር ለመሸሽ ከሆነ በራስህ ላይ ‘ችግር’ እየጋበዝክ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረውን ምሳሌ ታስታውሳለህ? ምሳሌው በራስ ወዳድነት መንፈስ ተነሳስቶ ወደ ውጭ አገር ስለሄደ አንድ ወጣት የሚናገር ሲሆን ወጣቱ ወደ ውጭ አገር የሄደው የበለጠ ነጻነት እንደሚያገኝ አስቦ እንደሆነ ከታሪኩ መረዳት ይቻላል። ብዙም ሳይቆይ መከራ ደረሰበትና ተራበ፣ ደኸየ እንዲሁም በመንፈሳዊ ታመመ።—ሉቃስ 15:11-16
ቤታቸው ካለው ችግር ለማምለጥ ሲሉ ወደ ውጭ አገር መሄድ የሚፈልጉም አሉ። ሆኖም ሃይክ በርግ የተባሉት ሴት ዋትስ አፕ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “ውጭ አገር መሄድ የፈለግከው ደስተኛ ስላልሆንክ ብቻ ከሆነና . . . ቦታ ብትቀይር ግን ሁሉ ነገር አስደሳች እንደሚሆን አስበህ ከሆነ መሄዱን እርሳው!” ሲሉ ጽፈዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ችግሮችን ከመሸሽ ይልቅ ፊት ለፊት መጋፈጡ የተሻለ ነው። አንድ ሰው ከማይፈልጋቸው ሁኔታዎች በመሸሽ ምንም ጥቅም አያገኝም።
ወደ ውጭ አገር ለመሄድ የሚገፋፉ ሌሎቹ አደገኛ ምክንያቶች ደግሞ ስስትና ፍቅረ ነዋይ ናቸው። ሀብት ለማግኘት በመገፋፋት ብዙ ወጣቶች በበለጸጉት አገሮች ስላለው ኑሮ የተጋነነና ከእውነታው የራቀ አመለካከት ያዳብራሉ። አንዳንዶች ሁሉም ምዕራባውያን ሀብታሞች እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ እውነታው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ብዙ ወጣቶች ወደ ውጭ አገር ከሄዱ በኋላ አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት በመታገል ላይ ያለች መሆኑን ሲገነዘቡ ያልጠበቁት ነገር ይሆንባቸዋል። * መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” በማለት ያስጠነቅቃል።—1 ጢሞቴዎስ 6:10
ዝግጁ ነህን?
ሌላም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ አለ:- በውጭ አገር ሊያጋጥሙህ የሚችሉትን መከራዎችና ችግሮች ለመቋቋምና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ጉልምስና አለህን? አንድ ክፍል ከሌሎች ጋር መጋራት ወይም ከአንድ ቤተሰብ ጋር መኖርና ከቤተሰቡ የዘወትር ልማድ ጋር ራስህን ማላመድ ይኖርብህ ይሆናል። ታዲያ በዚህ ረገድ አሁን ከቤተሰቦችህ ጋር ባለህ ግንኙነት ምን ያህል ተሳክቶልሃል? ወላጆችህ ለሌሎች ሰዎች የማታስብና ራስ ወዳድ እንደሆንክ ይናገራሉ? በምትበላው ምግብ ረገድ ውኃ ቀጠነ እያልክ የማማረር ዝንባሌ አለህ? በቤት ውስጥ ያለህን የሥራ ድርሻ ለመወጣት ምን ያህል ፈቃደኛ ነህ? በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ችግር ካለብህ ውጭ አገር ስትሄድ ደግሞ ምን ያህል አስቸጋሪ ሊሆኑብህ እንደሚችሉ ገምት!
ክርስቲያን ከሆንክ መንፈሳዊነትህን ጠብቀህ ለመቆየት ትችላለህ? ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግን፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በስብከቱ ሥራ የመካፈልን አስፈላጊነት ችላ እንዳትል ዘወትር የወላጆችህ ማሳሰቢያ የሚያስፈልግህ ዓይነት ሰው ነህ? ምናልባት አገርህ ብትሆን የማያጋጥሙህን ውጭ ግን ሊያጋጥሙህ የሚችሉትን ተጽዕኖዎችና ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ አለህ? ለትምህርት ውጭ አገር የሄደ አንድ ክርስቲያን ወጣት ትምህርት ቤት በሄደ በመጀመሪያው ቀን ሕገ ወጥ ዕፆች የት ሊያገኝ እንደሚችል ተነግሮታል። ቆይቶም አብራው የምትማር አንዲት ሴት ተቀጣጥሮ ለመጫወት ጥያቄ አቅርባለታለች። በትውልድ አገሩ ግን አንዲት ሴት ፍላጎቷን እንዲህ በግልጽ የመናገር ድፍረት ፈጽሞ አይኖራትም። ወደ አውሮፓ የሄደ አንድ አፍሪካዊ ወጣት ደግሞ የሚከተለውን አስተውሏል:- “በአገሬ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ሥዕሎች ባደባባይ ፈጽሞ አይታዩም። እዚህ ግን በየቦታው ታዩዋቸዋላችሁ።” አንድ ሰው ‘በእምነት የጸና’ ካልሆነ ወደ 1 ጴጥሮስ 5:9
ውጭ አገር መሄዱ በመንፈሳዊ የመስጠም አደጋ ሊያስከትልበት ይችላል።—እውነታውን ለማወቅ ሞክር!
ወደ ውጭ አገር ከመሄድህ በፊት እውነታውን ሁሉ ማወቅ ያስፈልግሃል። ሌሎች በሰጡህ መረጃ ብቻ ተማምነህ አትሂድ። ለምሳሌ፣ ለትምህርት የምትሄድ ከሆነ ምን ያህል ወጪ ይጠይቅብሃል? ብዙውን ጊዜ በሺህ የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር እንደሚጠይቅ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። በውጭ አገር የምትወስደው ትምህርት በአገርህ ተቀባይነት ያለው መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥም ይኖርብሃል። በተጨማሪም ስለምትሄድበት አገር ሕግ፣ ባህልና ልማድ የቻልከውን ያህል ብዙ መረጃ ሰብስብ። እዚያ መኖር የሚጠይቃቸው ወጪዎች ምንድን ናቸው? መክፈል የሚኖርብህስ ቀረጥ ምን ያህል ነው? ልታስብባቸው የሚገቡ በጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች አሉ? እዚያ ኖረው ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ስለ ሁኔታው መነጋገሩ ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል።
የመኖሪያ ጉዳይም አለ። በምትሄድበት አገር የሚቀበሉህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከአንተ ቁሳዊ ጥቅም ላይጠብቁ ይችላሉ። ያም ሆኖ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች አክብሮት ከሌለው ቤተሰብ ጋር መኖር ውጥረትና ጭንቀት ሊፈጥር ይችላል። ከጓደኞች ወይም ከዘመዶች ጋር መቆየት ደግሞ ሌላው አማራጭ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እነርሱ እንድትቆይ ቢገፋፉህ እንኳ ሸክም እንዳትሆንባቸው ተጠንቀቅ። እንዲህ ያለው ሁኔታ በመካከላችሁ ባለው ዝምድና ላይ ውጥረት ሊፈጥርና ሌላው ቀርቶ ሊያበላሸው ይችላል።—ምሳሌ 25:17
ውጭ አገር እያለህ ገንዘብ ለማግኘት እቅድ ካወጣህ ዓለማዊ ባለሥልጣኖችን የመታዘዝ ክርስቲያናዊ ግዴታህን አትርሳ። (ሮሜ 13:1-7) የአገሩ ሕግ በዚያ እንድትሠራ ይፈቅድልሃል? የሚፈቅድልህ ከሆነስ በምን ሁኔታዎች ሥር? ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሠራህ ሐቀኝነት የሚጠይቅብህን ክርስቲያናዊ አቋም አደጋ ላይ ልትጥልና ራስህን የአደጋ ጊዜ ዋስትናን የመሳሰሉትን መሠረታዊ ጥበቃዎች ልታሳጣ ትችላለህ። ሕጋዊ በሆነ መንገድ በምትሠራበት ጊዜም እንኳ ጥንቃቄ ማድረግና ብልህ መሆን ያስፈልግሃል። (ምሳሌ 14:15) ይሉኝታ የሌላቸው ቀጣሪዎች ብዙውን ጊዜ የውጭ አገር ዜጎችን አላግባብ ይጠቀሙባቸዋል።
ውሳኔ ማድረግ
ስለዚህ ውጭ አገር ለመሄድ መወሰን በጥሞና ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ እንደ ቀላል ነገር ተደርጎ መታየት የለበትም። ከወላጆችህ ጋር ቁጭ ብለህ ይገኛሉ ተብሎ ተስፋ የተደረገባቸውን ጥቅሞችና ሊያጋጥሙ የሚችሉትን አደጋዎች አገናዝብ። ውጭ አገር ለመሄድ ያለህ ጉጉት የማስተዋል ችሎታህን እንዲጋርድብህ አትፍቀድለት። ለመሄድ የተነሳሳህበትን ምክንያት ስትመረምር ሐቀኛ ሁን። ወላጆችህ የሚሉህን በጥንቃቄ አዳምጥ። በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀህ ብትሄድም እንኳ ወላጆችህ ለአንተ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው መዘንጋት የለብህም። ኑሮህን መግፋት እንድትችል ምናልባት የወላጆችህ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልግህም ይሆናል።
ሁሉንም ነገሮች ግምት ውስጥ አስገብተህ ከመረመርክ በኋላ ወደ ውጭ መሄድህ ቢያንስ ለጊዜው ጥበብ እንደማይሆን ትረዳ ይሆናል። ይህ ቅር ሊያሰኝ ቢችልም አሁንም ልታደርጋቸው የምትችላቸው ሌሎች ብዙ አስደሳች ነገሮች አሉ። ለምሳሌ፣ በገዛ አገርህ ውስጥ የሚገኙትን አስደሳች ቦታዎች መጎብኘት የምትችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? ወይም ለምን አሁኑኑ አንድ የውጭ አገር ቋንቋ መማር አትጀምርም? ከጊዜ በኋላ ወደ ውጭ የመሄድ አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ውጭ አገር ለመሄድ ብትወስንስ? ወደፊት የሚወጣው እትም የውጭ አገር ቆይታህን የተሳካ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.15 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማህበር በታተመው የሚያዝያ 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ወደ ሀብታም አገር ከመዛወራችሁ በፊት ወጪውን አስቡት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ወጣቶች የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ለማስፋፋት ወደ ውጭ አገር ይሄዳሉ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውጭ አገር መሄድ ስላለው ጥቅምና ጉዳት ከወላጆችህ ጋር ተወያይ