በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሜክሲኮ የሚገኙ ፒራሚዶች

በሜክሲኮ የሚገኙ ፒራሚዶች

በሜክሲኮ የሚገኙ ፒራሚዶች

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች በግብፅ ስለሚገኙት ፒራሚዶች ሰምተዋል። በአሜሪካም በተለይ ደግሞ በሜክሲኮ አርኪኦሎጂስቶች ፒራሚድ መሰል በርካታ መዋቅሮች አግኝተዋል። በግብፅ እንደሚገኙት አምሳያዎቻቸው ሁሉ የሜክሲኮ ፒራሚዶችም ብዙ መቶ ዓመታት ያስቆጠሩ ከመሆናቸውም በላይ ምሥጢራዊ ናቸው።

የግብፅ ፒራሚድ በሁለቱም ጎኑ ተመሳሳይ ቅርጽ ባለው ትልቅ የድንጋይ ንብርብር የተከደነ መቃብር ነው። ፒራሚዱ ውስጥ ያሉት መተላለፊያ መንገዶች የፒራሚዱ ዋነኛ ክፍል ወደሆነው ወደ መቃብሩ ያደርሳሉ። የሜክሲኮ ፒራሚድ ግን አናቱ ላይ ቤተ መቅደስ የተገነባበት ትልቅ የአፈር ቁልል ሲሆን ከውጭ በኩል ጫፍ ላይ የሚወጣበት ደረጃም አለው። ከጥቂቶቹ በስተቀር በአሜሪካ የሚገኙ ፒራሚዶች ለመቃብርነት የተገነቡ አይደሉም።

ቴኦቲዋካን​—⁠“የአማልክት ከተማ”

ሜክሲኮ ውስጥ ፒራሚዶች ከሚገኙባቸው በስፋት የታወቁ ስፍራዎች አንዱ ቴኦቲዋካን ነው። ከሜክሲኮ ሲቲ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 50 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኘው ቴኦቲዋካን ለስነ ሰብኣት ተመራማሪዎች (anthropologists) እና ለአርኪኦሎጂስቶች እስካሁን ድረስ ምስጢር ሆኖባቸዋል። ይህ ጥንታዊ ዋና ከተማ ከተማውን የገነቡት ሰዎች የአዝቴክ ሥልጣኔ ብቅ ከማለቱ ከ500 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ትተውት የሄዱት ቦታ ነው። ከናዋትል ቋንቋ የተገኘው ቴኦቲዋካን የሚለው ስም “የአማልክት ከተማ” ወይም “ሰዎች አማልክት የሆኑበት ቦታ” የሚል ትርጉም አለው። አዝቴኮች ከተማዋን በጎበኙበት ጊዜ ይህን ስም እንደሰጧት ይገመታል።

ናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት አዘጋጆች ከሆኑት አንዱ ጆርጅ ስቱዋርት እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ቴኦቲዋካን በምዕራባዊው ክፍለ ዓለም የመጀመሪያዋ የከተማ ማዕከል ነበረች . . . ከተማዋ በክርስትና ዘመን መጀመሪያ ላይ ተቆርቁራ ሰባት መቶ ዘመናት ገደማ ካስቆጠረች በኋላ በአፈ ታሪክ ደረጃ ብቻ የምትወሳ ሆና ቀርታለች። በ500 ዓመተ ምሕረት ገደማ ቴኦቲዋካን ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሳ በነበረበት ወቅት ከ125, 000 እስከ 200, 000 የሚደርስ የሕዝብ ብዛት እንደነበራት ይገመታል።”

መሃል ከተማው ላይ ለማለት ይቻላል፣ ታላቁ የፀሐይ ፒራሚድ ይገኛል። ፒራሚዱ የወለል ስፋቱ 220 በ225 ሜትር ገደማ ይሆናል። አምስት እርከን ያለው ከፍታው በአሁኑ ጊዜ ወደ 63 ሜትር የሚጠጋ ሲሆን አንድ ሰው ጫፉ ላይ ለመድረስ ከ240 የሚበልጡ ደረጃዎችን መውጣት አለበት። ከጥንታዊቷ ከተማ በስተ ሰሜን 40 ሜትር ከፍታ ያለው የጨረቃ ፒራሚድ ይገኛል። በአንድ ወቅት በእነዚህ ሁለት ዋና ዋና ፒራሚዶች አናት ላይ ቤተ መቅደሶች ይገኙ ነበር።

በቅርብ አሥርተ ዓመታት እነዚህን ፒራሚዶች በተመለከተ ብዙ ማወቅ ተችሏል። ይሁን እንጂ ስቱዋርት እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ስለ ከተማዋ ነዋሪዎች አመጣጥ፣ ምን ዓይነት ቋንቋ ይናገሩ እንደነበር፣ ኅብረተሰባቸው በምን መልኩ ተደራጅቶ እንደነበርና ለውድቀታቸው ምክንያት የሆነው ነገር ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ የምናውቀው ነገር የለም ማለት ይቻላል።”

ፒራሚድ የሚገኝባቸው ሌሎች ስፍራዎች

በሜክሲኮ ሲቲ እምብርት ላይ አንድ ሰው ዋነኛውን የአዝቴኮች ቤተ መቅደስ ማግኘት ይችላል። ምንም እንኳ በቦታው በግልጽ የሚታይ ፒራሚድ ባይኖርም የዋናው ቤተ መቅደስ መሠረት የነበረውን የፈራረሰ የፒራሚድ መዋቅር አሁንም ማየት ይቻላል። አርኪኦሎጂስቶች ሰዎች መሥዋዕት ሆነው ይቀርቡባቸው የነበሩ ሁለት መሠዊያዎችን አግኝተዋል።

በሜክሲኮ በርካታ ጎብኚዎች ፒራሚድ ለማየት ከሚሄዱባቸው ስፍራዎች አንዱ ቺቼን ኢትሳ ነው። በማያ ክልል ብዙ ጥንታዊ ፍርስራሾች ቢኖሩም እንኳ ቺቼን ኢትሳ በዩካታን ለምትገኘው የሜሪዳ ከተማ ቅርብ በመሆኗ በቀላሉ የሚደረስባት ቦታ ነች። ምንም እንኳ ፒራሚዶቹ በማያ ክልል የሚገኙ ቢሆንም በአንድ ወቅት በእነዚህ ቦታዎች ላይ የቶልቴኮች ተጽእኖ ሰፍኖ እንደነበር ያሳያሉ። አንዳንዶቹ ሕንፃዎች በግንባታው የተሰማሩ ሰዎች ያላቸውን የረቀቀ የሒሳብና የስነ ፈለክ እውቀት በተመለከተ ፍንጭ ይሰጣሉ።

በፓሌንኬ ጎብኚዎች በቺያፓስ ደን የተከበቡትን አስደናቂ የሆኑትን የማያን ሕንፃዎች ያገኛሉ። ከበርካታዎቹ ፒራሚዶችና ሕንፃዎች መካከል በግድግዳዎቻቸው ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች ያሏቸው ቤተ መንግሥትና ቤተ መቅደስ ይገኙበታል። ዘ ማያስ —⁠3000 ይርስ ኦቭ ሲቪላይዜሽን የተባለው መጽሐፍ በግድግዳዎቹ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች ያሉት ይህ ቤተ መቅደስ “በመላው ሜሶአሜሪካ በጣም ዝነኛ ከሆኑት ቤተ መቅደሶች አንዱ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት እንደሌሎቹ ፒራሚዶች ቤተ መቅደስ የተገነባበት መሠረት ብቻ ሳይሆን የመቃብር ሐውልት በመሆኑም ጭምር ነው” ሲል ገልጿል። “ከውስጥ በኩል ደግሞ እስካሁን ድረስ በማያ ክልል ከተገኙት ሁሉ በጣም ድንቅ ወደሆነው የመቃብር ቤት የሚወስድ ባለ ቅስት ጣሪያ ደረጃ አለ።” መቃብሩ በሰባተኛው መቶ ዘመን ይኖር ለነበረው ፓካል ወይም ዎክሶክ አው ለተባለ አገረ ገዢ የተገነባ ነበር።

እነዚህ በሚክሲኮ ከሚገኙት ፒራሚዶች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በመላ አገሪቱ በብዙ ቦታዎች ላይ ሌሎች ፍርስራሾችንና ፒራሚዶችን ማግኘት ይቻላል። በጓቲማላና በሆንዱራስም ግዙፍ ፒራሚዶች ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ ጥንታዊ መዋቅሮች የሜሶአሜሪካ ነዋሪዎች የአምልኮ ቦታዎቻቸውን ለመገንባት ከፍ ያለ ቦታ ይፈልጉ እንደነበር ያሳያሉ። ላስ አንቲግዋስ ኩልቱራስ ሜሂካናስ የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ቮልተር ክሪክበርግ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ደረጃ ባለው መሠረት ላይ ቤተ መቅደሶች የመገንባት ልማድ ጥንታዊ ከሆነ ከፍታን የማምለክ ልማድ የተወረሰ ነው።” አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “በእኛ አመለካከት ሰማይ እንደ ‘ቅስት ጣሪያ’ ያለ ነገር ሲሆን ሌሎች ሰዎች ግን ፀሐይ ሲነጋ የምትወጣበት ሲመሽ ደግሞ የምትወርድበት ተራራ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። በመሆኑም ቆለቆሉ (the slope) የአንድ ግዙፍ ሕንፃ ዓይነት ደረጃ አለው። በመሆኑም ይህ ‘ሐሳብ ወለድ ተራራ’ . . . ደረጃ ወዳለው ፒራሚድ የተቀየረ ሲሆን ከአፈ ታሪኮችና ሲተላለፍ ከኖረው ወግ መረዳት እንደሚቻለው በበርካታ የሜሶአሜሪካ ሰዎች ዘንድ ሰማይን የሚወክል ምልክት ተደርጎ ይታይ ጀመር።”

ይህ ሐሳብ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ከጊዜ በኋላ ባቢሎን በሚል መጠሪያ በታወቀችው ከተማ ውስጥ ስለተገነባው የባቤል ግንብ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሳያስታውሳቸው አይቀርም። በግንባታው ላይ የተሰማሩትን ሰዎች አስመልክቶ ዘፍጥረት 11:​4 እንዲህ ይላል:- “እንዲህም:- ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ . . . ስማችንን እናስጠራው አሉ።” አርኪኦሎጂስቶች ከባቢሎን ፍርስራሽ ብዙም ሳይርቅ ዚጉራቶች ተብለው የሚጠሩ የፒራሚድ መዋቅሮችን አግኝተዋል።

በባቢሎን የተጀመረው የአምልኮ ሥርዓት ወደ በርካታ የዓለም ክፍሎች በመሰራጨት ምናልባትም ሜክሲኮ ተብላ ወደምትታወቀው የዓለም ክፍል ሳይደርስ አልቀረም። በባቢሎን ያሉት ዚጉራቶችም ሆኑ በዚያ የነበረው አምልኮ በሜክሲኮ ላሉት ምሥጢራዊና አስደናቂ የሆኑ ፒራሚዶች ተምሳሌት ሆነው አገልግለዋል ቢባል ምንም የሚያስገርም አይሆንም።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴኦቲዋካን

[ምንጭ]

CNCA.-INAH.-MEX Reproducción Autorizada por el Instituto Nacional de Antropología e Historia

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓሌንኬ