አስገራሚው ኤምፐረር
አስገራሚው ኤምፐረር
ከፔንግዊን ዝርያዎች በሙሉ በትልቅነቱ ግንባር ቀደሙን ስፍራ የያዘው ኤምፐረር ቁመቱ ከአንድ ሜትር በላይ ሲሆን 40 ኪሎ ግራም ይመዝናል። ሌሎቹ የፔንግዊን ዝርያዎች ኃይለኛውንና ጭጋጋማውን የአንታርክቲካ ክረምት በመሸሽ ወደ ሰሜን ሲያቀኑ ኤምፐረሮች በአንጻሩ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ አንታርክቲካ ያቀናሉ! ለምን? ወደ አንታርክቲካ የሚሄዱት ጫጩቶቻቸውን ለመፈልፈል መሆኑ የሚያስደንቅ ነው።
ሴቷ ኤምፐረር እንቁላሏን ስትጥል ወንዱ ወዲያውኑ ከበረዶው ላይ አንስቶ እግሩ ላይ ያደርገዋል። ከዚያም በታችኛው ሆዱ ላይ በሚገኘው ከረጢት መሰል የታጠፈ ቆዳ ሥር ይከትተዋል። ከዚህ በኋላ ሴቷ ምግብ ፍለጋ ወደተንጣለለው ባሕር ታቀናለች። ወንዱ ኤምፐረር እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን የአየር ጠባይ በመቋቋም ለ65 ቀናት የሰውነቱን ስብ ብቻ በመጠቀም ምንም ነገር ሳይመገብ ዕንቁላሉን እንደታቀፈ ይቆያል። እነዚህ ብልህ ወፎች በሰዓት እስከ 200 ኪሎ ሜትር በሚጓዘው በረዶ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ የሚመቱ በመሆኑ የሰውነታቸውን ሙቀት ለመጠበቅ በቡድን በቡድን ሆነው በብዛት አንድ ላይ እጅብ ብለው ይቀመጣሉ። እያንዳንዱ ወፍ በየተራ ዳር ላይ ያሉትን ወፎች በመተካት ጀርባውን ለነፋስ ሰጥቶ ይቀመጣል።
ጫጩቱ የሚፈለፈለው ልክ ሴቷ በምትመለስበት ጊዜ መሆኑ እጅግ የሚያስገርም ነው። ይሁን እንጂ በጣም ተመሳሳይ ከሆኑት በሺህ የሚቆጠሩ ኤምፐረሮች መካከል የራሷን ተጓዳኝ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? መዝሙር በማሰማት ነው። ጥንድ የሆኑት ኤምፐረሮች መጀመሪያ ላይ ሲፈላለጉ አንዳቸው ለሌላው በመዘመር የመዝሙሩን ቅላጼ በአእምሯቸው ይይዛሉ። ሴቶቹ ሲመለሱ ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ ከልባቸው ይዘምራሉ። ሰዎች ኤምፐረሮቹ በሚያሰሙት የተደበላለቀ ድምፅ ግራ ሊጋቡ ቢችሉም ኤምፐረሮቹ ግን ወዲያውኑ ጥንዶቻቸውን ለመለየት የሚችሉት በዚህ መንገድ ነው። ከዚያም ረሃብ የሞረሞረው ወንዱ ኤምፐረር ትንሽ በማንገራገር የተቀፈቀፈውን ጫጩት ከሰጠ በኋላ ውኃና ምግብ ፍለጋ ድክ ድክ እያለ 70 ኪሎ ሜትር ያህል በበረዶ ላይ ይጓዛል።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
By courtesy of John R. Peiniger