አባባ ጥሎን መሄዱ ያስከተለውን ሁኔታ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
አባባ ጥሎን መሄዱ ያስከተለውን ሁኔታ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
“ያለ አባት ማደግ ከባድ ነበር። ትንሽ እንኳ ትኩረት ባገኝ ደስ ይለኝ ነበር።”—ሄንሪ *
ጃን አባቷ ቤቱን ጥሎ ሲሄድ የ13 ዓመት ልጅ ነበረች። አባቷ በአልኮል ሱስ ተጠምዶ ስለነበር ጥሏቸው ከሄደም በኋላ ከልጆቹ ጋር ለመገናኘት ብዙም ጥረት አላደረገም። የሚያሳዝነው እንዲህ ያለው ሁኔታ የደረሰው በጃን ላይ ብቻ አይደለም። ብዙዎቹን ወጣቶች አባቶቻቸው ጥለዋቸው ሄደዋል።
እንዲህ ያለው ሁኔታ በአንተም ላይ ደርሶብህ ከሆነ አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተኸው ይሆናል። አልፎ አልፎ በስሜት ሥቃይና በብስጭት ትዋጥ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሐዘንና ትካዜ ይሰማህ ይሆናል። እንዲያውም ዓመፀኛ ለመሆን ትፈተን ይሆናል። ሰሎሞን የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በአንድ ወቅት እንዳለው “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል።”—መክብብ 7:7
‘የእብደት ሥራ’
ጄምስ አባቱ ቤቱን ጥሎ ከሄደ በኋላ ‘ሥራው ሁሉ የእብደት ሆኖ’ ነበር። እንዲህ ብሏል:- “ማንኛውንም ሥልጣን አላከብርም ነበር። ለእናቴም ቢሆን አክብሮት አልነበረኝም። ከሌሎች ጋር እጣላና እጨቃጨቅ ነበር። የሚቀጣኝ ሰው ስለሌለ መዋሸትና ማታ ማታ ተደብቆ መውጣት ልምድ ሆኖብኝ ነበር። እማማ ልታስቆመኝ ብትሞክርም አቃታት።” ጄምስ ዓመፀኛ መሆኑ የነበረበትን ሁኔታ አሻሽሎለት ይሆን? በፍጹም። ብዙም ሳይቆይ “አደገኛ ዕፆችን መውሰድ፣ ከትምህርት ቤት መቅረትና በፈተና መውደቅ እንደጀመረ” ተናግሯል። የጄምስ ባሕርይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይበልጥ እየተበላሸ ሄደ። “ከመደብሮች መስረቅ ጀመርኩ” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። “ከሰዎች ላይም እዘርፍ ነበር። ሁለቴ ታስሬ እስር ቤት ለተወሰነ ጊዜ ብቆይም ይህ ከመጥፎ ድርጊቴ ሊገታኝ አልቻለም።”
ጄምስ እንዲህ ዓመፀኛ የሆነበትን ምክንያት ሲጠየቅ የሚከተለውን ብሏል:- “አባቴ ቤቱን ጥሎ ስለሄደ የሚገስጸኝ አልነበረም። እናቴንም ሆነ ትንሽ ወንድሜንና እህቴን እንዲሁም ራሴን ጭምር ምን ያህል እየጎዳሁ እንደነበረ አልተገነዘብኩም። የአባባን ትኩረትና ተግሳጽ ማግኘት እፈልግ ነበር።”
ይሁን እንጂ ማመፅ መጥፎውን ሁኔታ ከማባባስ ውጭ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። (ኢዮብ 36:18, 21) ለምሳሌ ያህል፣ ጄምስ ችግር ያመጣው በራሱ ላይ ብቻ አልነበረም። እናቱም ሆነች ወንድሙና እህቱ አላስፈላጊ ለሆነ ውጥረትና ጭንቀት ተዳርገዋል። ከዚህ ሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበው ደግሞ እንዲህ ያለው የዓመፀኝነት ባሕርይ አንድን ሰው ከአምላክ ጋር ሳይቀር የሚያጣላው መሆኑ ነው። ደግሞም ወጣቶች ለእናቶቻቸው መታዘዝ እንዳለባቸው ይሖዋ ተናግሯል።—ምሳሌ 1:8፤ 30:17
የሚሰማህን የብስጭት ስሜት መቋቋም
ታዲያ ስለ አባትህ የሚሰማህን ብስጭትና ጥላቻ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ አባትህ ጥሏችሁ የሄደው በአንተ ጥፋት እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልግህ ይሆናል። ወይም አባትህ ከአሁን በኋላ አይወድህም ወይም አያስብልህም ማለትም አይደለም። አባትህ አንተን ለማነጋገር ወይም ለመጠየቅ ምንም ጥረት የማያደርግ ከሆነ በጣም ሊሰማህ እንደሚችል አይካድም። ሆኖም በዚህ ዓምድ ላይ ከዚህ ቀደም የወጣው ርዕስ እንደሚያሳየው * ቤታቸውን ጥለው የሚሄዱ ብዙ አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የማይገናኙት ልጆቻቸውን ስለማይወዷቸው ሳይሆን በጥፋተኝነትና በኃፍረት ስሜት ስለሚዋጡ ነው። ሌሎች ደግሞ ልክ እንደ ጃን አባት የአደገኛ ዕፅ ወይም የአልኮል ሱሰኞች ሆነው ይሆናል። ይህ ደግሞ በትክክል የማሰብ ችሎታቸውን ያዛባባቸዋል።
ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ወላጆችህ ፍጹማን አለመሆናቸውን አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” በማለት ይናገራል። (ሮሜ 3:23፤ 5:12) እርግጥ ይህ ሌሎችን የሚጎዳ ወይም የግድ የለሽነት ድርጊት ለመፈጸም ምክንያት አይሆንም። ይሁን እንጂ ሁላችንም ከዘር የወረስነው አለፍጽምና እንዳለብን መገንዘብህ ጎጂ የሆነውን ብስጭትና ጥላቻ እንድታስወግድ ሁኔታውን ቀላል ያደርግልህ ይሆናል።
በመክብብ 7:10 ላይ የሰፈሩት ቃላት ስለ ወላጆችህ ሊሰማህ የሚችለውን ብስጭትና ጥላቻ እንድትቋቋም ሊረዱህ ይችላሉ። ይህ ጥቅስ ባለፈ ነገር ላይ ስለማተኮር የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በል:- “ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና።” ስለዚህ በአንድ ወቅት የነበርክበትን ሁኔታ እያስታወስክ ከመተከዝ ይልቅ አሁን ያለህበትን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም መጣሩ የተሻለ ነው።
ቀዳሚ ሆኖ መገኘት
ለምሳሌ ያህል፣ ከአባትህ ጋር ለመገናኘት ቀዳሚ ሆነህ ለመገኘት ልታስብ ትችል ይሆናል። እርግጥ ትቶህ የሄደው እርሱ ስለሆነ ግንኙነት ለመፍጠርም ቀዳሚ መሆን ያለበት እርሱ ነው ብለህ ታስብ ይሆናል። ይህ ትክክል ነው። ይሁን እንጂ አባትህ ቀዳሚ ሆኖ ግንኙነታችሁ እንዲቀጥል ካላደረገና እርሱን ማግኘት አለመቻልህ የሚያሳዝንህና የሚያስከፋህ ከሆነ ራስህ ሁኔታውን ለማሻሻል መጣርህ ይጠቅምህ ይሆን? ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንድ ወዳጆቹ በበደሉት ጊዜ ምን እንዳደረገ ተመልከት። ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ሐዋርያቱ ጥለውት ሸሹ። ጴጥሮስ የመጣው ቢመጣ ኢየሱስን ጥሎት እንደማይሄድ በጉራ ተናግሮ ነበር። ሆኖም ኢየሱስን አንዴ ብቻ ሳይሆን ሦስት ጊዜ ካደው!—ማቴዎስ 26:31-35፤ ሉቃስ 22:54-62
ጴጥሮስ ድክመቶች ቢኖሩበትም ኢየሱስ እርሱን መውደዱን ቀጥሏል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለጴጥሮስ ለየት ባለ መንገድ በመታየት ከእርሱ ጋር የነበረውን ዝምድና ለማደስ ቀዳሚ ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 15:5) የሚያስገርመው ኢየሱስ “ትወደኛለህ?” ብሎ ሲጠይቀው ጴጥሮስ የሰጠው ምላሽ “አዎን ጌታ ሆይ፣ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” የሚል ነበር። ጴጥሮስ አሳፋሪ ተግባር ቢፈጽምም ለኢየሱስ የነበረው ፍቅር አልጠፋም።—ዮሐንስ 21:15
በጴጥሮስና በኢየሱስ ሁኔታ ላይ እንደታየው በአንተና በአባትህ መካከል ያለውም ሁኔታ ያን ያህል ተስፋ አስቆራጭ ላይሆን ይችላል። ምናልባትም አንተ ራስህ ቀዳሚ ሆነህ ስልክ እንደመደወል፣ ደብዳቤ እንደመጻፍ ወይም ሄዶ እንደመጠየቅ የመሳሰሉትን ነገሮች ብታደርግ አባትህ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጥ ይሆናል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ሄንሪ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ለአባባ አንድ ጊዜ ደብዳቤ ጻፍኩለት። እርሱም እንደሚኮራብኝ ገልጾ ጻፈልኝ። ደብዳቤውን መስታወት ውስጥ አስገብቼ በግድግዳዬ ላይ ለዓመታት ሰቅዬው ነበር። ይኸው እስከዛሬም ከእኔ ጋር አለ።”
በተመሳሳይም ጃን እንዲሁም ሌሎች እህቶቿና ወንድሞቿ የአልኮል ሱሰኛ አባታቸውን ለመጠየቅ ቅድሚያውን ወስደዋል። ጃን “አባታችን በጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበረም። ቢሆንም ስላየነው ደስ ብሎናል” በማለት የተሰማትን ተናግራለች። ምናልባት ቀዳሚ ሆኖ መገኘት ለአንተም ይሠራ ይሆናል። በመጀመሪያ ምንም ምላሽ ካላገኘህ ጥቂት ቆይተህ እንደገና መሞከር ትችል ይሆናል።
ጠልቶኛል የሚለው ስሜት የሚያስከትለውን ስቃይ መቋቋም
ሰሎሞን “ለመፈለግ ጊዜ አለው፣ ለማጥፋትም ጊዜ አለው” በማለት ያሳስበናል። (መክብብ 3:6) አንዳንድ ጊዜ አባትዬው ከልጆቹ ጋር ምንም ዓይነት ቅርርብ ላለመፍጠር የሚፈልግ ከሆነ አንድ ወጣት ይህንን አሳዛኝ ሐቅ ለመቀበል ይገደዳል። አባትህ እንዲህ ዓይነት ሀሳብ ካለው ምናልባት አንድ ቀን ከአንተ ጋር ቅርርብ ባለመፍጠሩ ምን ያህል እንደተጎዳ ይገነዘብ ይሆናል።
ይሁን እንጂ እርሱ አልፈለገህም ማለት ዋጋ ቢስ ነህ ማለት እንዳልሆነ እርግጠኛ ሁን። ዳዊት የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙራዊ እንዲህ ብሏል:- “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ።” (መዝሙር 27:10) አዎን፣ በአምላክ ፊት ያለህን ዋጋ አያሳጣህም።—ሉቃስ 12:6, 7
ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ ወይም ትካዜ ከተሰማህ በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ቅረብ። (መዝሙር 62:8) ምን እንደሚሰማህ በትክክል ግለጽለት። እንደሚያዳምጥህና እንደሚያጽናናህ እርግጠኛ ሁን። ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙራዊ ደግሞ “አቤቱ፣ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት” ብሏል።—መዝሙር 94:19
ከክርስቲያን ባልንጀሮች ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት መመስረትም እንደተጠላህ ሆኖ የሚሰማህን ስሜት ለመቋቋም ሊረዳህ ይችላል። ምሳሌ 17:17 “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” ይላል። እንዲህ ያሉትን እውነተኛ ወዳጆች በይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ማግኘት ትችላለህ። በተለይ ከጉባኤው ሽማግሌዎች ጋር መተዋወቅህ ሊረዳህ ይችላል። ፒተር የተባለው የጃን ታናሽ ወንድም እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል:- “በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ከጎለመሱ ሰዎች ጋር መነጋገር በጣም ይጠቅማል። አባታችሁ ጥሏችሁ ሄዶ ከሆነ ምን እንደሚሰማችሁ ግለጹላቸው።” አባትህ ቀድሞ ይሠራቸው የነበሩትን ቤት እንደመጠገን ያሉ አንዳንድ ኃላፊነቶች በመወጣት ረገድ የጉባኤ ሽማግሌዎች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች ሊሰጡህ ይችላሉ።
እናትህም የድጋፍ ምንጭ ልትሆንልህ ትችላለች። እርግጥ እርሷ ራሷ በደረሰባት የስሜት ጉዳት ምክንያት ስቃይ ላይ ልትሆን ትችላለች። ይሁን እንጂ ስሜትህን አክብሮት ባለው መንገድ ከገለጽክላት አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት የተቻላትን ያህል እንደምታደርግ ምንም ጥርጥር የለውም።
ቤተሰብህን ደግፍ!
የአባትህ አለመኖር ቤተሰባችሁን በተለያየ አቅጣጫ ይነካው ይሆናል። እናትህ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ለማሟላት ከአንድም ሁለት ቦታ ተቀጥራ መሥራት ይኖርባት ይሆናል። አንተም ሆንክ ወንድሞችህና እህቶችህ ተጨማሪ የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን ለመሸከም ትገደዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ክርስቲያናዊ ፍቅር ካዳበርክ እንዲህ የመሰሉትን ለውጦች ልትቋቋም ትችላለህ። (ቆላስይስ 3:14) ይህም አዎንታዊ አመለካከት እንድትይዝና ቅሬታህን እንድታስወግድ ሊረዳህ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-7) ፒተር “ቤተሰቤን መርዳት ላደርገው የሚገባኝ ትክክለኛ ነገር ነው። እማማንና ታላላቅ እህቶቼን እየረዳኋቸው መሆኑን ማወቄ እርካታ ይሰጠኛል” በማለት ተናግሯል።
አንድ አባት ቤቱን ጥሎ መሄዱ አሳዛኝና ስቃይ የሚያስከትል ገጠመኝ እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ በአምላክ፣ በአፍቃሪ ክርስቲያን ወዳጆችና ቤተሰቦች እርዳታ አንተና ቤተሰብህ በተሳካ መንገድ ሕይወታችሁን መምራት እንደምትችሉ እርግጠኛ ሁን። *
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።
^ አን.11 በጥር 2001 ንቁ! ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . አባባ ጥሎን የሄደው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.27 በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ስለመኖር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” በሚለው አምድ በታኅሣሥ 22, 1990 (እንግሊዝኛ) እና በመጋቢት 22, 1991 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጡትን ርዕሶች ተመልከት።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አንዳንድ ወጣቶች ከአባቶቻቸው ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ቀዳሚ ሆነዋል