ወፎችን በማየት የሚገኝ ደስታ
ወፎችን በማየት የሚገኝ ደስታ
ወፎች ባይኖሩ ኖሮ ዓለማችን ምን ልትመስል እንደምትችል እስቲ አስበው! የወፎችን ጫጫታና ዝማሬ መስማት፣ በቀለማት ያሸበረቀ መልካቸውን ማየትና ሲበሩ መመልከት ሕይወትን አስደሳች ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ይሁን እንጂ በቁም ነገር የምንሰማቸውና የምናያቸው ምን ያክል ነው? ሩጫና ግርግር ባለበት እንዲሁም የተሽከርካሪ ድምፅ በበዛበት አካባቢ ማለትም በከተማ የምትኖር ከሆንክ በአካባቢህ ወፎች እስከመኖራቸው እንኳ ልብ ላትል ትችላለህ። በገጠር የምትኖር እንኳን ቢሆን ወፎችን ከቁም ነገር ላትቆጥራቸው ትችላለህ። ሆኖም በአካባቢህ ያሉ ወፎችን ቀረብ ብለህ ለመመልከት ትፈልጋለህ?
ግቢህ ውስጥ በመስኮትህ አካባቢ ጥራጥሬ በተን በማድረግ ወፎችን በቅርብ መመልከት ትችላለህ። ከዚያም የሚያስፈልግህ ነገር ቢኖር አቅርቦ የሚያሳይ መነጽር ወይም ካሜራ እንዲሁም ትንሽ ትዕግሥት ብቻ ነው! የወፎቹን ዓይነት ለመለየት እንዲረዳህ ስለ ወፎች የሚያሳይ ፊልም እና ስለ ወፎች ሥዕላዊ መግለጫ ያለው መጽሐፍ አጠገብህ አድርግ። ከዚያም ወፎችን በማየትና በመስማት መደሰት ትችላለህ!