በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጦርነቱ ስብከታችንን አላስቆመውም

ጦርነቱ ስብከታችንን አላስቆመውም

ጦርነቱ ስብከታችንን አላስቆመውም

ሌኦዴጋርዮ ባርላአን እንደተናገረው

በ1942 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ጃፓንና ዩናይትድ ስቴትስ ትውልድ አገሬ የሆነችውን ፊሊፒንስን ለመቆጣጠር ፍልሚያ ላይ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ከጃፓን ጋር የሚዋጉ የአገሬው ሽምቅ ተዋጊዎች ተራራ ላይ በምትገኘው በታቦናን መንደር አስረውኝ ነበር። ሰላይ ነህ በሚል ተወንጅዬ ከደበደቡኝ በኋላ ትገደላለህ ብለው ዛቱብኝ። ይህ ሁኔታ እንዴት እንዳጋጠመኝና እንዴት በሕይወት ልተርፍ እንደቻልኩ እስቲ ልንገራችሁ።

የተወለድኩት ጥር 24, 1914 በፓንጋሲናን፣ ሳን ካርሎስ ከተማ ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት አባቴ ግብርና እንዳጠና ትምህርት ቤት አስገባኝ። እሁድ እሁድ በቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እገኝ የነበረ ሲሆን ቄሱ ስለ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ወንጌሎች ይናገር ነበር። ከዚህ የተነሳ የወንጌል ዘገባዎቹን የማንበብ ፍላጎት አደረብኝ።

አንድ ቀን አትክልት ሸጬ ባገኘሁት ገንዘብ የወንጌሎቹን ቅጂ ለመግዛት ወደ ገዳም ሄድኩ። የጠየቅሁትን ሳይሆን የወንጌል ዘገባዎቹን ያልያዘ ዘ ዌይ ቱ ሄቨን የሚል ቡክሌት ሰጡኝ። ነገሩ በጣም አናደደኝ። በኋላም የወንጌሎቹን ቅጂ ለማግኘት የነበረኝን ፍላጎት ለማሳካት ወደ ማኒላ ሄድኩ። እዚያ ስደርስ የይሖዋ ምሥክር የሆነው አጎቴ ሙሉውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ሰጠኝ።

ማኒላ ውስጥ ከበርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁ ሲሆን ጥቅስ የማስታወስ ችሎታቸው በጣም አስደነቀኝ። ለነበሩኝ በርካታ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ሰጡኝ። በመጨረሻ አጎቴ ሪካርዶ ዩሶን በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በሚደረግ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ይዞኝ ሄደ። ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ስንቃረብ ሲጋራ ለኮስኩ። አጎቴ “ሲጋራህን ጣለው፤ የይሖዋ ምሥክሮች አያጨሱም” አለኝ። ወዲያው ሲጋራውን ጣልኩት፤ ከዚያ በኋላም ፈጽሞ አጭሼ አላውቅም። ወደ ቦታው ስንደርስ የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች ከሆነው ከጆሴፍ ዶስ ሳንቶስ እና ከሌሎች ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። ዛሬ በርካታ አሥርተ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም እነዚህ ግሩም ክርስቲያን ወንድሞች አሁንም ድረስ ትዝ ይሉኛል።

አምላክን የማገልገል ፍላጎት

ጥቅምት 1937 በሎስ ባንዮስ የእርሻ ኮሌጅ ትምህርቴን እየተከታተልኩ ሳለ በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት አቆምኩና መጽሐፍ ቅዱስንና አጎቴ የሰጠኝን መጽሐፍ ማንበብ ጀመርኩ። የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ኮሌጁ ግቢ መጥተው እያለ ኤልቪራ አልኢንሶድ ከምትባለው ምሥክር ጋር ያደረግሁት ውይይት ይሖዋ አምላክን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አሳደረብኝ።

አስተማሪዎቼ ትምህርት ለማቆም እንዳሰብኩ ስነግራቸው “ማን ይደጉምሃል?” ሲሉ ጠየቁኝ። አምላክን ካገለገልኩ እሱ እንደሚረዳኝ ሙሉ እምነት ያለኝ መሆኑን ገለጽኩላቸው። ትምህርት ካቆምኩ በኋላ ወደ መጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮ ሄጄ “ሎየልቲ፣ ሪችስ እና ዌር አር ዘ ዴድ? የተባሉትን ጽሑፎች አንብቤ ጨርሻለሁ። አሁን ሙሉ ጊዜዬን ለይሖዋ አገልግሎት ማዋል እፈልጋለሁ” ስል ፈቃደኛ አገልጋይ መሆን እንደምፈልግ ገለጽኩ። በሴቡ ግዛት ካሉ ሦስት አቅኚዎች (የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መጠሪያ ነው) ጋር እንዳገለግል ተነገረኝ።

የስብከት ሥራውን ጀመርኩ

ሐምሌ 15, 1938 ሴቡ ደሴት ስደርስ ሳልቫዶር ሊዋግ ወደቡ ድረስ መጥቶ ተቀበለኝ። በሚቀጥለው ቀን ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመርኩ። ሥልጠና የሰጠኝ ሰው አልነበረም። የማደርገው ነገር ቢኖር ለቤቱ ባለቤት ስለ ሥራችን የሚያብራራ የመመሥከሪያ ካርድ መስጠት ብቻ ነበር። እንዲያውም በአካባቢው በሚነገረው በሴቡዋኖ ቋንቋ ሁለት ቃላት ብቻ ነበር የማውቀው። በአገልግሎት ያሳለፍኩትን የመጀመሪያውን ቀን የጀመርኩት በዚህ መልክ ነበር።

በአንድ ከተማ ውስጥ መስበክ ስንጀምር የምናደርገው የመጀመሪያው ነገር ወደ ማዘጋጃ ቤት መሄድ ነበር። እዚያ ስንደርስ ወንድም ሊዋግ ለከተማው ከንቲባ፣ ፓብሎ ባውቲስታ ለፖሊስ ዋና አዛዥ፣ ኮንራዶ ዳክላን ደግሞ ለዳኛው ይሰብካሉ። እኔ ደግሞ የፖስታ ቤት ኃላፊውን አነጋግራለሁ። ከዚያም ወደ አውቶቡስ መናኸሪያ፣ ወደ ፖሊሶች ሰፈር፣ ወደ ገበያ አዳራሾችና ወደ ትምህርት ቤቶች እንሄዳለን። በተጨማሪም ሰዎችን በየቤታቸው እናነጋግራለን። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳውን ኤነሚስ የተባለውን መጽሐፍ እናበረክት ነበር። አብረውኝ የሚያገለግሉት ወንድሞች ምሥክርነት የሚሰጡበትን መንገድ በመኮረጅ ቀስ በቀስ ሴቡዋኖ መናገር የቻልኩ ከመሆኑም በላይ መጻሕፍት ማበርከትም ጀመርኩ። በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ 54 ከተሞች ያሉትን የሴቡን ግዛት ባጠቃላይ አዳረስን። በዚህ ጊዜ ወንድም ሊዋግን “አሁን መጠመቅ እችላለሁ?” ስል ጠየቅሁት።

“ወንድም፣ ገና ይቀርሃል” ሲል መለሰልኝ። ቦሆል ወደሚባል ሌላ ደሴት ተዛወርንና በአንድ ወር ከግማሽ ውስጥ ሌሎች 36 ከተሞች ሸፈንን። ለመጠመቅ እንደገና ጥያቄ አቀረብኩ። “ወንድም ባርላአን፣ ገና ይቀርሃል” ተባልኩ። ቦሆልን ከዚያም የካሚጉን ደሴት ካዳረስን በኋላ ሚንዳናው ወደሚባል ትልቅ ደሴት ሄደን በካጋያን ዴ ኦሮ ሲቲ ሰበክን።

በዚህ ጊዜ ቪርሂንዮ ክሩስ ከእኛ ጋር ተቀላቀለ። በአንድ የሕዝብ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ ሲሆን አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ሲል ሥራውን አቆመ። ወደ ሌሎች ከተሞች የተጓዝን ሲሆን በመጨረሻም ላናው ሐይቅ ደረስን። እዚያ ስንደርስ መጠመቅ እችል እንደሆነ እንደገና ጥያቄ አቀረብኩ። በመጨረሻ ታኅሣሥ 28, 1938 ላይ ወደ ስድስት ወር ገደማ በአቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ ወንድም ክሩስ በሉምባታን ከተማ ላናው ሐይቅ ውስጥ አጠመቀኝ።

በአምላክ መታመን ያስገኘው ወሮታ

ከጊዜ በኋላ በኔግሮስ ኦክሲዴንታል ከሦስት አቅኚዎች ጋር ማገልገል ጀመርኩ። ሦስቱ አቅኚዎች ፉልሄንስዮ ዴ ሄሱስ፣ ኤስፔራንዛ ዴ ሄሱስ እና ናቲ ብለን የምንጠራት ናቲቪዳድ ሳንቶስ ናቸው። በዚህ ግዛት በበርካታ ከተሞች ውስጥ አብረን ሰብከናል። አንዳንድ ጊዜ የገንዘብ እጥረት ያጋጥመን ስለነበር ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን ነበረብን። አንድ ቀን ከሩዝ ጋር የምንበላው አሳ አስፈልጎን ነበር። በባሕሩ ዳርቻ አንድ ሰው አገኘሁና አሳ እንዲሸጥልኝ ጠየቅሁት። ሆኖም የነበረውን አሳ በሙሉ ወደ ገበያ ልኮ ነበር። ይሁን እንጂ ለራሱ አስቀርቶት የነበረውን አሳ ሰጠኝ። ዋጋው ስንት እንደሆነ ስጠይቀው “ግድ የለም፤ በነፃ ውሰደው” አለኝ።

ምስጋናዬን ገልጬ ተለየሁት። ሆኖም አንድ አሳ ለአራት ሰዎች እንደማይበቃ ተገንዝቤ ነበር። በአንድ ትንሽ ጅረት አጠገብ ሳልፍ ገና ከውኃ ውስጥ የወጣ አሳ ድንጋይ ላይ ተጋድሞ በማየቴ ተገረምኩ። ‘ሳይሞት አይቀርም’ ብዬ አሰብኩ። ላነሳው ጠጋ ስል ገና በሕይወት ያለ መሆኑ አስገረመኝ። እንዳያመልጠኝ አጥብቄ ያዝኩት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” ሲል የገባው ቃል ወዲያው ትዝ አለኝ።​—⁠ማቴዎስ 6:​33

በጦርነት መሀል መስበክ

የአቅኚ ቡድናችን ብዛት ዘጠኝ ሲደርስ ለሁለት ተከፈልን። የእኛ ቡድን በሴቡ እንዲያገለግል ተመደበ። ጊዜው ታኅሣሥ 1941 ሲሆን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፊሊፒንስ ውስጥ ተፋፍሞ ነበር። በቱቡራን ከተማ እያለን አንድ ፊሊፒናዊ መቶ አለቃ እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ክፍላችን መጣ። “ልጆች ተነሱ፤ ወታደሮቹ ይፈልጓችኋል” አለን። የጃፓን ሰላዮች እንደሆንን አድርገው ስለጠረጠሩን ምርመራ ሲያካሂዱብን አደሩ።

ከዚያ በኋላ በማዘጋጃ ቤቱ እስር ቤት ውስጥ አቆዩን። በሴቡ ሲቲ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይሎች የጃፓን ሰላዮች መሆን አለመሆናችንን ለማጣራት ካሉን የተለያዩ መጻሕፍት ውስጥ አንድ አንድ ቅጂ እንድንሰጣቸው ጠየቁን። በርካታ የከተማው ነዋሪዎች የጃፓን ሰላዮች ናቸው በሚል የተወነጀሉት ሰዎች ምን እንደሚመስሉ ለማየት ስለጓጉ እስር ቤት ድረስ መጥተው ያዩን ነበር። አንዳንዶች ጥያቄዎች ያቀረቡልን ሲሆን እኛም ስለ አምላክ መንግሥት መሰከርንላቸው።

እስር ቤት ውስጥ ለአምስት ቀናት ያህል ከቆየን በኋላ የፖሊስ ዋና አዛዡ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲፈታ ከዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠራዊት ዋና ማዕከል የቴሌግራም መልእክት ደረሰው። ይሁን እንጂ ወቅቱ የጦርነት ጊዜ ስለሆነ መስበካችንን እንድናቆም መመሪያ ሰጠን። ይህን ሥራ እንድናከናውን ተልዕኮውን የሰጠን አምላክ ስለሆነ መስበካችንን ማቆም እንደማንችል አስረዳነው። (ሥራ 5:​28, 29) በዚህ ጊዜ ዋና አዛዡ ተቆጣና “መስበካችሁን የምትቀጥሉ ከሆነ ሕዝቡ እንዲገድላችሁ አደርጋለሁ” አለን።

ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት የፖሊስ ዋና አዛዡ እኛን እንደገና ለማሳሰር ጥረት ማድረግ ጀመረ። በመጨረሻ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠራዊት ጓድ አስቆመንና ሶሪያኖ የሚባል አንድ መቶ አለቃ እህት ሳንቶስን “መስበካችሁን አታቆሙም?” ሲል ጠየቃት።

“አናቆምም” ስትል መለሰችለት።

“ረሻኝ ጓድ ፊት ብናቆማችሁስ?” ሲል ጠየቀ።

“ይህን ውሳኔያችንን አይለውጠውም” ስትል ገለጸች።

ይህን ሲሰሙ የጭነት መኪና ላይ አሳፍረው ወደ ሴቡ ከተማ ወሰዱንና ኮሎኔል ኤድመንድ ዘንድ አቀረቡን። መቶ አለቃ ሶሪያኖ “እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። የጃፓን ሰላዮች ናቸው!” በማለት ማንነታችንን ለኮሎኔሉ ነገራቸው።

ኮሎኔሉ “የይሖዋ ምሥክሮች?” ሲሉ ጠየቁ። “የይሖዋ ምሥክሮችን አሜሪካ ውስጥ አሳምሬ አውቃቸዋለሁ። ሰላዮች አይደሉም! እነሱ ገለልተኞች ናቸው።” ከዚያም ወደ እኛ ዞረው “ገለልተኞች ስለሆናችሁ ትታሰራላችሁ” አሉን። ከዚያም በአንድ መጋዘን ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ካቆዩን በኋላ ኮሎኔል ኤድመን ሊያነጋግሩን መጥተው “አሁንም የገለልተኝነት አቋማችሁን አልለወጣችሁም?” ሲሉ ጠየቁን።

“አልለወጥንም ኮሎኔል” ስንል መለስንላቸው።

“እንግዲያው አትፈቱም። ምክንያቱም ከፈታናችሁ መስበካችሁን ትቀጥላላችሁ፤ የተቀበሏችሁ ሰዎች ደግሞ ገለልተኛ መሆናቸው አይቀርም። ሁሉም ሰው ገለልተኛ ከሆነ ደግሞ ጦር ሜዳ የሚሄድ ላይኖር ነው” አሉን።

ከእስር ወጥቶ ወደ ስብከቱ ሥራ መመለስ

ከጊዜ በኋላ በሴቡ ሲቲ ወደሚገኝ እስር ቤት አዛወሩን። ሚያዝያ 10, 1942 ጃፓኖች ከተማዋን ወረሩ። ከቦምብ ድብደባ የተረፈ አካባቢ አልነበረም፤ ከባድ ቃጠሎም ተነሳ! እህት ሳንቶስ የታሰረችበት ክፍል የወህኒ ቤቱ መግቢያ አካባቢ ስለነበር የወህኒ ቤት ኃላፊው አያት። “የይሖዋ ምሥክሮች ገና አልወጡም እንዴ! በሩን ክፈቱና ልቀቋቸው!” ሲል ጮኸ። ይሖዋን ላደረገልን ጥበቃ አመሰገንነው።

የእምነት ጓደኞቻችንን ለማግኘት ወዲያው ወደ ተራራው አመራን። ኮምፖስቴላ የሚባል ከተማ ውስጥ አንድ የይሖዋ ምሥክር አገኘን። ቀደም ሲል ይህ ወንድም በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆኖ ያገለግል ነበር። አሁን ግን መስበኩን ለማቆምና ወደ ሴቡ ሲቲ ተዛውሮ ሸቀጣ ሸቀጥ በመነገድ ለመሥራት ወሰነ። የእኛ ውሳኔ ግን የመጣው ቢመጣ ስለ አምላክ መንግሥት መስበካችንን መቀጠል ነበር።

ከምፈርት ኦል ዛት ሞርን የተባለው ቡክሌት በርካታ ቅጂዎች የነበሩን ሲሆን ሰዎች እጅ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። ሆኖም የጃፓን ወታደሮች ካገኙን አንገታችንን እንደሚቀሉን በመንገር ብዙዎች ሊያስፈራሩን ይሞክሩ ነበር። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፀረ ጃፓን የሽምቅ ውጊያ እንቅስቃሴ ተደራጀና መስበኩን አቁሞ በንግድ ለመሰማራት ወደ ሴቡ ሲቲ የሄደው ሰው ተይዞ ታሰረ። የጃፓን ሰላይ ነህ በሚል ተወንጅሎ መገደሉን ስንሰማ በጣም አዘንን።

ሰላዮች ናችሁ ተብለን ተወነጀልን

በዚህ መሃል በተራራማዎቹ አካባቢ መስበካችንን ቀጠልን። አንድ ቀን ፍላጎት ያላት አንዲት ሴት መኖርዋን ሰማን። ሆኖም የምትኖርበት ቦታ ለመድረስ ሽምቅ ተዋጊዎች የሚቆጣጠሯቸውን በርካታ ኬላዎች ማለፍ ነበረብን። ሴትዮዋ በምትኖርበት የማንጋቦን መንደር ስንደርስ አንድ የወታደሮች ጓድ አገኘንና በቁጣ “እዚህ ምን ልትሠሩ መጣችሁ?” አለን።

“እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን። ሸክላ ማጫወቻ በመጠቀም የምናዳርሰውን መልእክት መስማት ትፈልጋላችሁ?” ስል መለስኩላቸው። መስማት እንደሚፈልጉ ሲገልጹ ዘ ቫልዩ ኦቭ ኖውሌጅ የተባለውን ሸክላ አሰማኋቸው። ከዚያ በኋላ ፈትሸውን ጥያቄዎች ከጠየቁን በኋላ በታቦናን መንደር ወደሚገኘው የሽምቅ ተዋጊዎቹ ዋና ማዕከል ወሰዱን። ወደዚህ ቦታ የተወሰደ ሁሉ ማለት ይቻላል፣ መገደሉን መስማት የተለመደ ስለነበር ይሖዋ እንዲጠብቀን ጸለይን።

በጥበቃ ሥር ተደረግን፤ ብዙ እንግልትም ደረሰብን። ይህ መጀመሪያ ላይ ወደገለጽኩት ሁኔታ ይመልሰናል። ከደበደቡኝ በኋላ መቶ አለቃው እኔ ላይ ጣቱን ቀስሮ “ሰላይ ነህ!” አለኝ። የሚደርስብን እንግልት ለተወሰነ ጊዜ ቢቀጥልም አልገደሉንም። ከዚህ ይልቅ የጉልበት ሥራ እንድንሠራ ተፈረደብን።

በታቦናን ከታሰሩት አቅኚዎች መካከል አንዱ ወንድሜ ቤርናቤ ነበር። ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት እስረኞች የሆንነው “‘ጎድ ብለስ አሜሪካ” እና “ጎድ ብለስ ፊሊፒንስ” የተባሉትን መዝሙሮች የመዘመር ግዴታ ነበረብን። የይሖዋ ምሥክሮች የሆንነው ግን “ከጌታ ጎን የቆመው ማን ነው?” የተባለውን መዝሙር እንዘምር ነበር። አንድ ቀን ተረኛ መኮንኑ ጎድ ብለስ አሜሪካ’ የሚለውን መዝሙር የማይዘምር ሰው እዛ የግራር ዛፍ ላይ በስቅላት ይቀጣል!” ሲል ጮኸ። እንዲህ ዓይነት ዛቻዎች ቢሰነዘሩም እንኳ ከመካከላችን የተገደለ ሰው አልነበረም። በመጨረሻ ወደ ሌሎች ካምፖች ተወሰድን። በኋላም ሐምሌ 1943 የተጻፈ መፈታቴን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። በዚህ ወቅት በእስር ያሳለፍኩት ጊዜ ስምንት ወር ከአሥር ቀን ደርሶ ነበር።

የዕድሜ ልክ የስብከት ሥራ

ቀደም ሲል የሰበክንላቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ለማግኘት የነበረን ፍላጎት 60 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ወደ ቶሌዶ ከተማ እንድንጓዝ አነሳሳን። በዚህ ከተማ በቋሚነት የሚደረጉ ስብሰባዎች የተጀመሩ ሲሆን ውሎ አድሮ ብዙ ሰዎች ተጠምቀዋል። በመጨረሻ ጦርነቱ በ1945 አበቃ። ከሁለት ዓመት በኋላ፣ ከተጠመቅሁ ከዘጠኝ ዓመት ገደማ በኋላ መሆኑ ነው፣ ማኒላ ውስጥ በሳንታ አና ሬስትራክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት ቻልኩ። በስብሰባው ላይ “የሕዝቦች ሁሉ ደስታ” የተባለውን የሕዝብ ንግግር ለማዳመጥ ወደ 4, 200 ሰዎች ገደማ ተገኝተው ነበር።

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ፊሊፒንስ ውስጥ ወደ 380 አካባቢ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን በ1947 ግን 2, 700 ገደማ ደርሰው ነበር! ከዚያን ጊዜ አንስቶ በይሖዋ አገልግሎት በርካታ መብቶች አግኝቻለሁ። ከ1948 እስከ 1950 በሱሪጋው ክልል በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግያለሁ። በ1951 በጦርነቱ ወቅት ከእኛ ቡድን ጋር ሆና በቆራጥነት ስትሰብክ የነበረችውን ናቲቪዳድ ሳንቶስን አገባሁ። ከተጋባን በኋላ ከ1954 እስከ 1972 በመላው ሚንዳናው በተጓዥ አገልጋይነት ሥራ ስናገለግል ቆየን።

በዕድሜ የገፉትን ወላጆቻችንን በቅርብ መርዳት እንድንችል በ1972 ልዩ አቅኚ ሆንን። ሁለታችንም በ80ዎቹ ዓመታት ውስጥ ብንሆንም እንኳ በአቅኚነት ቀጥለናል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በድምሩ ከ120 ዓመታት በላይ አሳልፈናል። ፊሊፒንስ ውስጥ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚያውጁ ሰዎች ቁጥር ከ130, 000 በላይ ደርሶ በማየታችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል! በምድር ላይ እውነተኛ ሰላምና ደስታ ለማግኘት የሚያስችለው ብቸኛው ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን ሌሎች በርካታ ሰዎች እንዲገነዘቡ የመርዳት ፍላጎት አለን።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የጃፓን ሰላዮች ናችሁ ተብለን ሌሊቱን ሙሉ ምርመራ ተካሄደብን

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1963 በቦሆል ደሴት ከጓደኞቻችን ጋር። በቀኝ በኩል አራተኛውና አምስተኛው ላይ ያለነው ባለቤቴና እኔ ነን

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከባለቤቴ ጋር

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]

ከበስተ ጀርባ ያለው ፎቶ:- U.S. Signal Corps photo