በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መስማትና ማየት ባልችልም የተረጋጋ ሕይወት አግኝቻለሁ

መስማትና ማየት ባልችልም የተረጋጋ ሕይወት አግኝቻለሁ

መስማትና ማየት ባልችልም የተረጋጋ ሕይወት አግኝቻለሁ

ጃኒስ አዳምስ እንደተናገረችው

ከተወለድኩበት ጊዜ አንስቶ የተሟላ የመስማት ችሎታ ባይኖረኝም መስማት ከሚችሉ ሰዎች ጋር እንዴት መግባባት እንደምችል ተምሬአለሁ። ከዚያም ኮሌጅ ሳለሁ ወደፊት የማየት ችሎታዬን እንደማጣ ሲነገረኝ በጣም ተረበሽኩ። የኮሌጅ አማካሪዬ በአሳቢነት ተነሳስቶ የማየትና የመስማት ችግሬን ተቋቁሜ እንዴት መኖር እንደሚቻል የሚገልጽ ጽሑፍ ሰጠኝ። ወዲያው ዓይኔ ያረፈው መስማትም ማየትም የተሳናቸው ሰዎች በዓለማችን ላይ ከባድ ብቸኝነት እንደሚያጠቃቸው በሚናገሩት ቃላት ላይ ነበር። ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ።

የተወለድኩት ሐምሌ 11, 1954 በዲ ሞይን አይዋ፣ ዩ ኤስ ኤ ሲሆን የዴልና የፊለስ ዴን ሀርቶግ ብቸኛ ልጅ ነበርኩ። ወላጆቼ ኧሸርስ ሲንድሮም ተብሎ የሚጠራ በራሂያዊ እክል ተሸካሚ መሆናቸውን አያውቁም ነበር። ይህ እክል በሚወልዷቸው ልጆች ላይ የመስማትና ቀስ በቀስም የማየት ችግር ያስከትላል።

መጀመሪያ ላይ ወላጆቼ ምንም እክል ያለብኝ አልመሰላቸውም ነበር። ምናልባት ይህ የሆነው ዝቅተኛ የድምፅ ሞገዶችን ትንሽ ትንሽ እሰማ ስለነበረና አንዳንድ ጊዜ ለምሰማው ድምፅ ምላሽ እሰጥ ስለነበር ሊሆን ይችላል። ሆኖም አፍ መፍታት እንዳቃተኝ ሲገነዘቡ አንድ ከባድ ችግር እንዳለብኝ ገባቸው። በመጨረሻም ሦስት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ዶክተሩ ባደረገልኝ ምርመራ መስማት እንደማልችል አረጋገጠ።

ወላጆቼ ይህን ሲሰሙ በጣም ደነገጡ። ሆኖም በተቻለ መጠን ጥሩ ትምህርት እንዳገኝ ቆርጠው ነበር። የመስማት ችግር ያለባቸው በሚማሩበት በጣም ግሩም የሆነ መዋዕለ ሕፃናት አስገቡኝ። ሆኖም የመስማት ችሎታዬ እጅግ ደካማ በመሆኑ ያገኘሁት ውጤት በጣም ዝቅተኛ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ራሴን ከግድግዳ ጋር በማጋጨት ያደረብኝን የከንቱነት ስሜት አወጣ ነበር።

ልዩ ወደሆነ ትምህርት ቤት ተላክሁ

ወላጆቼ በሴይንት ሉዊ ሚዙሪ ወደሚገኘው መስማት የተሳናቸው ማዕከላዊ ተቋም (CID) ሊያስገቡኝ ወሰኑ። ምንም እንኳ ከፍተኛ ወጪ ቢጠይቅባቸውና በአምስት ዓመቴ ከእነሱ መለየቴ በጣም ቢከብዳቸውም ስኬታማና ደስተኛ ሕይወት ለመምራት ያለኝ ከሁሉ የተሻለ ተስፋ ይህ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። በዚህ ጊዜ እኔና ወላጆቼ የሐሳብ ግንኙነት የምናደርግበት መንገድ አልነበረም።

እማዬ በአንድ ትልቅ ሻንጣ ውስጥ ልብሶቼን ስትከት አያታለሁ። ከዚያ በመኪና ያደረግነው ጉዞ ማለቂያ ያለው አይመስልም ነበር። ወደ ተቋሙ ስንደርስ እናት የሌላቸውን ሌሎች ሴቶች ልጆች ማየቴና ‘እናትና አባት ስላለኝ መቼም እዚህ አልቀርም’ ብዬ ማሰቤ ትዝ ይለኛል። ወላጆቼ መሄጃቸው ሲደርስ በጥቂት ወራት ውስጥ ተመልሰው እንደሚመጡ ሊያስረዱኝ ሞከሩ። እንቅ አድርጌአቸው አምርሬ አለቀስኩ። ሆኖም መሄድ እንዲችሉ ሞግዚቷ ምንጭቅ አድርጋ ወሰደችኝ።

የተጣልኩ ሆኖ ተሰማኝ። በትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ቀን አዳራችን ከሌሎች ሴቶች ልጆች ጋር ሳለሁ ምንም እንኳ በወቅቱ መናገር ባልችልም የምናገር አስመስዬ ታለቅስ የነበረችን አንዲት ልጅ ለማባበል ሞከርኩ። ሞግዚቷ ከተቆጣችኝ በኋላ መገናኘት እንዳንችል በመካከላችን መከለያ አደረገች። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ግድግዳው እዚያው ቀረ። ብቸኝነቱ በጣም ከባድ ነበር።

ሁላችንም እዚህ ያለነው መስማት የተሳነን በመሆናችን ምክንያት እንደሆነ የተረዳሁት ከጊዜ በኋላ ነው። የሆነ ሆኖ ወላጆቼ እኮ ይወድዱኛል፤ መዋዕለ ሕፃናት ባልወድቅ ኖሮ ወደዚህ አይልኩኝም ነበር ስል አሰብኩ። አንድ ቀን ወደ ቤት እመለሳለሁ በሚል ተስፋ በዚህ ጊዜ በትምህርቴ የተሳካልኝ ለመሆን ቆርጬ ተነሳሁ።

በተቋሙ የሚሰጠው ትምህርት በጣም ግሩም ነበር። ምንም እንኳ በምልክት ቋንቋ መጠቀም ባይፈቀድልንም የከንፈር እንቅስቃሴን በመከታተል የሚባለውን መረዳት እንዲሁም መናገር እንድንችል በነፍስ ወከፍ ሰፊ ትምህርት ይሰጠን ነበር። በተጨማሪም በመደበኛ ትምህርት ቤት የሚሰጡትን የትምህርት ዓይነቶች በሙሉ ያስተምሩን ነበር። ምንም እንኳ በከንፈር እንቅስቃሴ ብቻ የማስተማር ዘዴ መስማት የተሳናቸው አብዛኞቹ ልጆች በቀላሉ የሚለምዱት እንዳልሆነ ባውቅም እኔ ግን ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም፤ የተሳካልኝም ሆኖ ተሰማኝ። በመስሚያ መሣሪያ እየታገዝኩ የአፍ እንቅስቃሴን በመከታተልና ሌሎች ያለ ድምፅ የሚናገሩትን እንዴት መረዳት እንደምችል ተማርኩ። ጥራት ባይኖረውም እንኳ ንግግሬ እየተሻሻለ ስለመጣ አብዛኞቹ መስማት የሚችሉ ሰዎች የምለው ይገባቸው ጀመር። ወላጆቼና ትምህርት ቤቱ ባሳየሁት እድገት ከፍተኛ እርካታ ተሰማቸው። እኔ ግን አሁንም ቢሆን ወደ ቤት ለመመለስ እጓጓ ነበር።

ክረምት በመጣ ቁጥር ለዕረፍት ወደ ቤት ስመለስ ቤት እንዲያስቀሩኝና አይዋ ውስጥ ትምህርት ቤት እንዲያስገቡኝ ወላጆቼን እለምናቸው የነበረ ቢሆንም በከተማው ፕሮግራሞቹን የሚሰጥ ትምህርት ቤት ገና አልተከፈተም ነበር። ወደ ትምህርት ቤት ከተመለስኩ በኋላ እማዬ በየቀኑ ደብዳቤ ትጽፍልኝና ከደብዳቤውም ጋር መስቲካ ትልክልኝ ነበር። መስቲካው የእናቴን ፍቅር ስለሚያስታውሰኝ በአድናቆት እመለከተው ነበር! እያንዳንዱን መስቲካ እንዲሁ አስቀምጠው የነበረ ሲሆን በተለይ በማዝንበት ወቅት ለመስቲካዎቹ ልዩ ግምት ነበረኝ።

ወደ ቤት ብመለስም ችግሮች ተፈጠሩ

በመጨረሻ አሥር ዓመት ሲሞላኝ ወላጆቼ ወደ ቤት አመጡኝ። ከቤተሰቦቼ ጋር በመቀላቀሌ ደስታና የመረጋጋት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። በዲ ሞይን መስማት የተሳናቸው ልጆች በሚማሩበት አንድ ልዩ ትምህርት ቤት ገባሁ። የከንፈር እንቅስቃሴ በመከታተል ሰዎች የሚናገሩትን በጥሩ ሁኔታ መረዳትና ለሌሎች የሚገባ የንግግር ችሎታ አዳብሬ ስለነበር በመጨረሻ መደበኛ ትምህርት ቤት ገባሁ። ሆኖም በዚህ ጊዜ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጠሙኝ።

በፊት በነበርኩበት ተቋም (CID) ማደሪያ ውስጥ እንደ እኔ መስማት በማይችሉ ጓደኞቼ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘሁ ይሰማኝ ነበር። አሁን ግን በአንድ ጊዜ ከበርካታ ሰዎች ጋር መገናኘት ግድ ሲሆንብኝ የከንፈር እንቅስቃሴያቸውን በመከታተል ብቻ ፈጣን የሆነውን ውይይታቸውን በተሟላ መንገድ መረዳት አቃተኝ። በዚህ ምክንያት ችላ ይሉኝ ጀመር። በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ብርቱ ፍላጎት አደረብኝ!

ይህም በአሥራዎቹ እድሜ በሚገኙ ወንዶች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎት አሳደረብኝ። ከዚህ የተነሣ አጠያያቂ ሁኔታዎች ውስጥ ገባሁ። እንዲሁም ፈቃደኛ አለመሆኔን ምን ብዬ እንደምገልጽ አላውቅም ነበር። የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ተደፈርኩ። ሆኖም ለማንም አልተናገርኩም። ወላጆቼ ምንጊዜም አሳቢነትና ፍቅር ቢያሳዩኝም እንኳ የተተውኩና ደጋፊ የሌለኝ ሆኖ ተሰማኝ።

በመስሚያ መሣሪያ እየታገዝኩ በመጠኑ ሙዚቃ ማዳመጥ እችል የነበረ ቢሆንም የሙዚቃ ምርጫዬ አጠያያቂ ነበር። አደገኛ ዕፅ መጠቀምን የሚያበረታታ ሮክ ሙዚቃ አዳምጥ ነበር። በተጨማሪም የማሪዋና ቋሚ ተጠቃሚ የሆንኩ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ከሰው እየራቅሁ መጣሁ። በእነዚያ አፍላ የጉርምስና ዓመታት ያደረግኳቸውን ነገሮችና በወላጆቼም ሆነ በራሴ ላይ ያመጣሁትን መከራ ሳስብ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ጸጸት ይሰማኛል።

ሕይወቴን ለማሻሻል ያደረኩት ጥረት

በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን እውቀት የማግኘት ጥማትና የፈጠራ ችሎታን የማዳበር ፍላጎት ነበረኝ። ከማንበብ፣ ሥዕል ከመሳል፣ ከመስፋትና ጥልፍ ከመሥራት ቦዝኜ አላውቅም። ዕፅ በማሳደድ የተጠመዱ ጓደኞቼ የሚጠብቃቸው ዕጣ እንዳይደርስብኝ ስል በሕይወቴ ብዙ ነገር የማከናወን ፍላጎት ነበረኝ። በመሆኑም ለሥነ ጥበብ ያለኝን ፍላጎት ዳር ለማድረስ ቤታችን አቅራቢያ በሚገኝ መደበኛ ኮሌጅ ገባሁ። በዚህ ጊዜ ከማኅበራዊ ሕይወት መገለሉ ስላስመረረኝ የምልክት ቋንቋ ለመማር ወሰንኩ።

በመጨረሻ የሴራሚክ ሥነ ጥበብ ለመማር በሮችስተር ኒው ዮርክ ወደሚገኘው መስማት የተሳናቸው የቴክኒክ ሙያ ብሔራዊ ተቋም ተዛወርኩ። ምንም እንኳ የማየት ችሎታዬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ ቢመጣና ይህን ሐቅ ለመቀበል ባልፈልግም ሕይወቴ ትክክለኛ ፈር እየያዘ እንዳለ ተሰማኝ። ሆኖም የኮሌጅ አማካሪዬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓይነ ስውር እንደምሆን በመንገር እውነታውን እንድጋፈጥ አደረገኝ።

ተቋሙ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ለማሟላት ዝግጁ ስላልነበረ ለመልቀቅ ተገደድኩ። ከዚህ በኋላ ምን ላደርግ ነው? ምንም እንኳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓይነ ስውር እንደምሆን ማወቄ ሐዘን ቢያስከትልብኝም ራሴን ችዬ የምኖርበትን መንገድ ለመፈለግና አማካሪዬ የሰጠኝ ጽሑፍ ላይ እንደሰፈረው ‘በዓለም ላይ ካሉ ከባድ የብቸኝነት ስሜት የሚያጠቃቸው ሰዎች መካከል’ ላለመሆን ቆርጬ ነበር። ብሬይል ማንበብ ለመማርና በበትር ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ለመልመድ ወደ አይዋ፣ ቤተሰቦቼ ጋር ተመለስኩ።

ወደ ዋሽንግተን ዲ ሲ ሄድኩ

በዋሽንግተን ዲ ሲ የሚገኘው ጋለዴት ዩኒቨርሲቲ መስማት ለተሳናቸው የሊበራል አርትስ ትምህርት የሚሰጥ የዓለማችን ብቸኛ ኮሌጅ ሲሆን መስማትም ሆነ ማየት ለተሳናቸው ተማሪዎች የተዘጋጀ ልዩ ትምህርት ይሰጣል። ወደዚያ ተዛውሬ በ1979 በማዕረግ ተመረቅሁ። በድጋሚ በትምህርቱ ዓለም ጥሩ ውጤት በማምጣቴ ተደሰትኩ።

ሆኖም አሁንም ቢሆን በማኅበራዊ ሕይወት ረገድ ከእኩዮቼ የተገለልኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ምንም እንኳ ዓይኔ እየደከመ ቢመጣም መስማት የተሳናቸው ሰዎች ሕብረተሰብ ክፍል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ስል አስቀድሜ የምልክት ቋንቋ ተምሬ ነበር። የምጠቀምበት የምልክት ቋንቋ መስማት የማይችሉ ሌሎች ሰዎች ከሚጠቀሙበት ጋር ተመሳሳይ ነው። ይሁን እንጂ ሐሳባቸውን ለመረዳት እጄን እጃቸው ላይ ማድረግ ስላለብኝ አንዳንድ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ነገሬ ሁሉ ግራ እንደሆነ ስለተሰማቸው ይርቁኝ ጀመር። ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የማገኝበት የሰዎች ቡድን አገኝ ይሆን ስል ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ።

እውነተኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ያደረኩት ፍለጋ

ልጅ እያለሁ ከሃይማኖት ምንም ዓይነት ማጽናኛ አግኝቼ አላውቅም። እንዲሁም በኮሌጅ የሃይማኖት ትምህርት ብከታተልም ለነበሩኝ በርካታ ጥያቄዎች መልስ አላገኘሁም። ከኮሌጅ ከተመረቅሁ በኋላ ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት ፍለጋ ቀጠልኩ። በዚህ ወቅት ከሰዎች ጋር የነበረኝ ግንኙነት አርኪ አልነበረም። በመሆኑም አምላክ መመሪያ እንዲሰጠኝ መጸለይ ጀመርኩ።

በ1981 በተኃድሶ የምክር አገልግሎት ለማስተርስ ዲግሪ ለመሥራት ተመልሼ ጋለዴት ዩኒቨርሲቲ ገባሁ። አምላክ እውነተኛውን ቤተ ክርስቲያን ማግኘት እንድችል እንዲረዳኝ መጸለዬን ቀጠልኩ። በርካታ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው ለመውሰድ ተስፋ ቢሰጡኝም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሳይሳካላቸው ቀረ። ከዚያም ከቢል ጋር ተገናኘሁ። ቢል አጥርቶ መስማት የሚችል አብሮኝ በድሕረ ምረቃ ትምህርት ቤት የሚማር ተማሪ ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔም እንደ እሱ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት እንዳለኝ ተገነዘበ። እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች በጣም አስደናቂ የሆኑ በርካታ ነገሮች እያስተማሩት እንደሆነ ነገረኝ።

ወደ አእምሮዬ የመጣው የመጀመሪያው ነገር የይሖዋ ምሥክሮች የአይሁድ መናፍቃን ናቸው የሚለው መስማት የተሳናቸው በርካታ ሰዎች ያላቸው አመለካከት ነበር። ቢል ስለ እነሱ የሚወራው ትክክል አለመሆኑን በእርግጠኝነት የነገረኝ ከመሆኑም በላይ ስለ እነሱ ማወቅ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት መሆኑን ነገረኝ። እርግጥ መሄድ አልፈለኩም ነበር። ሆኖም ምን ብዬ እንደጸለይኩ ትዝ አለኝ። አንድ ዓይነት ነገር እንድናደርግ ካስገደዱን ማምለጥ እንድንችል ከኋላ የምንቀመጥ ከሆነ ብቻ እንደምሄድ በመግለጽ እያመነታሁ ለመሄድ ተስማማሁ።

እንግድነት አልተሰማኝም

በመኪና ወደ ስብሰባው ስንሄድ በጣም ጨንቆኝ ነበር። ሁለታችንም የለበስነው ሰማያዊ ጂንስና የፍላኔል ሸሚዝ ነበር። ትንሽ አርፍደን በመድረሳችን በጣም ደስ አለኝ። ምክንያቱም ከስብሰባው በፊት ማንም ሰው አላነጋገረንም። ቢል በማየትም ሆነ በመስማት መከታተል የማልችለውን ነገር በሙሉ በዝርዝር አብራራልኝ። ምንም እንኳ የሚካሄደውን ነገር ሙሉ በሙሉ ባልረዳም ተናጋሪው በተደጋጋሚ መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀሱና በስብሰባው ላይ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ተቀምጠው በንቃት መሳተፋቸው አስደነቀኝ። ስብሰባው ካበቃ በኋላ ምንም ዓይነት አስገዳጅ ሁኔታ ካለመኖሩም በላይ በአለባበሳችንና የተለየ ዘር ያለን በመሆኑ ላይ ሳያተኩሩ ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበሉን።

መንግሥት አዳራሹ ውስጥ ያለነው ነጮች ሁለታችን ብቻ ነበርን። ምንም እንኳ በጥቁሮች ላይ ስሜታዊ ጥላቻ እንዳለኝ አስቤ ባላውቅም መጀመሪያ ላይ እዚያ መሆኔ ከበደኝ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ቃል ያለው ኃይል በዚህ ስሜት ተሸንፌ እንዳልቀር ረድቶኛል። በስብሰባዎቹ ላይ አዘውትረን መገኘት ጀመርን። ከሁሉም ይበልጥ ፈታኝ የሆነብኝ ነገር በጉባኤው ካሉት መስማት የማልችለው እኔ ብቻ መሆኔ ነበር። በመሆኑም መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚካፈሉበት ሌላ ጉባኤ እንዳለ ስንሰማ እዚያ መሰብሰብ ጀመርን። አሁንም በዚህ አዲስ ጉባኤ ካሉት ተሰብሳቢዎች መካከል ያለነው ነጮች እኛ ብቻ ነበርን። ሆኖም እንግድነት እንዳይሰማን አድርገዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንድናጠና የቀረበልንን ግብዣ ተቀበልን። በመጨረሻ ለጥያቄዎቼ መልስ ማግኘት ጀመርኩ። የሚሰጠኝ መልስ ወዲያው በግልጽ የማይገባኝ ጊዜ ነበር። ሆኖም መልሱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነበር። ተጨማሪ ምርምር በማድረግና በማሰላሰል በመጨረሻ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መረዳት ቻልኩ። በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ እንደተጠጋሁ ተሰማኝ። በዚሁ ወቅት እኔና ቢል የጠበቀ ጓደኝነት መሠረትን። ቢል እንደሚወደኝ አውቅ ነበር። ሆኖም ለጋብቻ ሲጠይቀኝ ያልጠበኩት ነገር ሆነብኝ። በደስታ ፈቃደኝነቴን ገለጽኩ። ከተጋባን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቢል የተጠመቀ ሲሆን እኔ ደግሞ ከጥቂት ወራት በኋላ የካቲት 26, 1983 ላይ ተጠመቅሁ።

ስፈልገው የነበረውን መረጋጋት አገኘሁ

ጉባኤያችን ውስጥ የነበሩት መስማት የተሳናቸው ሰዎች ሁለት ብቻ ስለነበሩና እነሱም መስማትና ማየት ከማይችል ሰው ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ስላልለመዱ መጀመሪያ ላይ ብቸኝነት ይሰማኛል የሚል ስጋት አደረብኝ። ጉባኤያችን ፍቅርና ወዳጅነት የሰፈነበት እንደሆነ መረዳት አልከበደኝም። ሆኖም መጀመሪያ ላይ ከእነሱ ጋር በቀጥታ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ አልችልም ነበር። እንዲህ መሆኑ አሳዘነኝ። ብዙ ጊዜ ተስፋ መቁረጥና ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ መንፈሳዊ ወንድሜ ወይም እህቴ የሚያሳየኝ/የምታሳየኝ ደግነት ልቤን ይነካኝና መንፈሴንም ያነቃቃል። ቢልም በአገልግሎት እንድጸናና መስማት የማይችሉ ተጨማሪ ሰዎችን ወደ ጉባኤው እንዲያመጣ ወደ ይሖዋ እንድጸልይ ያበረታታኝ ነበር።

ይበልጥ ራሴን ችዬ መንቀሳቀስ እንድችል የሰለጠነ ውሻ ለመጠቀም ወሰንኩ። ውሻው ያደረብኝን የብቸኝነት ስሜት ለማስወገድም ረድቶኛል። ቢል ሥራ ላይ ሲሆን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ለመካፈል ከሚሰበሰበው ቡድን ጋር ለመገናኘት ወደ መንግሥት አዳራሹ በእግር መሄድ ቻልኩ። ባለፉት ዓመታት አራት የሰለጠኑ ውሾች ነበሩኝ፤ እያንዳንዳቸው የቤተሰቡ አባል የሆኑ ያክል ነበር።

ምንም እንኳ የሰለጠነ ውሻ ጠቃሚ ቢሆንም ይበልጥ ከሰው ጋር መሆን እፈልግ ነበር። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ መስማት ከተሳናቸው መካከል መጽሐፍ ቅዱስ የማጥናት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ለማግኘት ያደረግነውን ጥረት ባረከልን። ማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር አድጎ ዋሽንግተን ዲ ሲ ውስጥ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ለመቋቋም በቅቷል። በመጨረሻ ከእያንዳንዱ የጉባኤው አባል ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ቻልኩ!

ቢል ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቃቱን አሟልቶ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። መስማት እንዲሁም መስማትና ማየት ለማይችሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ አግኝቻለሁ። በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ናቸው። በተጨማሪም መስማት ለተሳናቸው በመስበክ ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ መስማት የሚችሉ እህቶችን የምልክት ቋንቋ አስተምሬአቸዋለሁ።

የፈተና ጊዜ

በ1992 ወጣት እያለሁ ከተፈጸመብኝ በደል ጋር በተያያዘ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተዋጥሁ። ለተወሰኑ ዓመታት የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎችን ማከናወን አልቻልኩም። መስማት ወይም ማየት ባለመቻሌ ምክንያት ሳይሆን ካደረብኝ የስሜት ቀውስ የተነሳ ከንቱነት ተሰማኝ። አብዛኛውን ጊዜ ወደ ስብሰባ መሄድ ወይም አገልግሎት መውጣት የምችል ሆኖ አይሰማኝም ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ንጹሕ አቋም መጠበቅ እንድችል ብርታት እንዲሰጠኝ እለምነው ነበር። ከዚህ የተነሳ ከስብሰባዎች ቀርቼ አላውቅም ማለት ይቻላል። በእነዚያም ተስፋ አስቆራጭ ዓመታት በአገልግሎት አዘውታሪ ሆኜ ቀጥያለሁ።​—⁠ማቴዎስ 6:​33

በ1994 ሌላ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ እንዲቋቋም ለመርዳት በካናዳ ወደሚገኘው ቫንኩቨር ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ተዛወርን። መኖሪያ ቦታ መቀየሩ ቀላል አልነበረም። የለመድኩትን ከተማና በርካታ ውድ ጓደኞቼን ትቼ መሄድ ነበረብኝ። ምንም እንኳ ያደረብኝ የመንፈስ ጭንቀትና ውጥረት ገና ባይለቀኝም በቫንኩቨር አዲስ ጉባኤ ሲቋቋም ማየቴ ያመጣልኝ ደስታ በከፈልኳቸው መሥዋዕቶች እንዳልቆጭ አድርጎኛል። በአዲሱ ጉባኤ ውስጥ ውድ ጓደኞች በማፍራቴ ባይተዋርነት አልተሰማኝም።

ከአፍቃሪው አባታችን ያገኘነው በረከት

በ1999 እኔና ባለቤቴ እንዲሁም ሌሎች ሁለት ምሥክሮች መስማት ለተሳናቸው በሚሰጠው አገልግሎት እርዳታ ለማበርከት ለስድስት ሳምንት ወደ ሃይቲ ሄድን። እዚያ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር በኅብረት በመሥራት ለጉባኤው አባላት የምልክት ቋንቋ ከማስተማራችን በተጨማሪ እምብዛም ተሠርቶበት በማያውቀው መስማት የተሳናቸው ሰዎች የአገልግሎት ክልል አብረናቸው ሰበክን። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ፍላጎት ያላቸው 30 መስማት የተሳናቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩ! በአዲስ መንፈሳዊ ብርታት ወደ አገሬ የተመለስኩ ሲሆን ከመስከረም 1999 ጀምሮ አቅኚ ሆኜ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። ከይሖዋ፣ ከውድ ባለቤቴና ድጋፍ ከሚያደርግልኝ ጉባኤ እርዳታ ስለማገኝ አልፎ አልፎ የሚነሳብኝ የመንፈስ ጭንቀት ደስታ አላሳጣኝም።

ባለፉት ዓመታት ይሖዋ ምን ያህል ሩኅሩኅ አምላክ እንደ⁠ሆነ አይቻለሁ። (ያዕቆብ 5:​11) ሕዝቦቹን ባጠቃላይ በተለይ ደግሞ ለየት ያለ ችግር ያለባቸውን ይንከባከባል። በድርጅቱ አማካኝነት የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚረዱ ሌሎች በርካታ ጽሑፎችን በብሬይል አግኝቼአለሁ። በምልክት ቋንቋ በሚካሄዱ የአውራጃ፣ የወረዳና ልዩ ስብሰባዎች ላይ እገኛለሁ። በሁሉም ስብሰባዎች ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንድችል በእጅ ለእጅ የምልክት ቋንቋ በማስተርጎም ጉባኤው ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ይደግፈኛል። ተደራራቢ አካላዊ ችግር ቢኖርብኝም በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ተረጋግቼ መኖር ችዬአለሁ። መቀበል ብቻ ሳይሆን መስጠትም እችላለሁ። ይህ ደግሞ በጣም ደስተኛ እንድሆን ያደርገኛል።​—⁠ሥራ 20:​35

በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ የመስማትም ሆነ የማየት ችሎታዬን እንደገና የማገኝበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። እስከዚያው ድረስ ግን በዓለም ላይ ካሉ ከባድ ብቸኝነት የሚያጠቃቸው ሰዎች መካከል አልሆንኩም። ከዚህ ይልቅ በሚልዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ያሉበት ዓለም አቀፍ ቤተሰብ አግኝቻለሁ። ይህን ሁሉ ላገኝ የቻልኩት አልለቅሽም ከቶም አልተውሽም ሲል ቃል በገባልኝ በይሖዋ እርዳታ አማካኝነት ነው። አዎን፣ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝም ‘ይሖዋ ይረዳኛልና አልፈራም’ ማለት እችላለሁ።​—⁠ዕብራውያን 13:​5, 6

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእጄ አማካኝነት በምልክት ቋንቋ ሲያነጋግሩኝ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቴ ከቢል ጋር