ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
የአኗኗር ዘይቤና ካንሰር
“ወደ 90, 000 ገደማ በሚጠጉ መንትያዎች ላይ የተካሄደው ጥናት እንዳመለከተው በአብዛኛው ለካንሰር የሚያጋልጥህ ተፈጥሮህ ሳይሆን የምትኖርበት ቦታ፣ የምታደርገው ነገርና በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህ ሁኔታዎች ናቸው” ሲል ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። ይህን ጥናት ያካሄደውን የምርምር ቡድን የመሩት በስዊድን የሚገኘው የካሮሊንስካ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ፖል ሊችተንሽታይን ናቸው። “ከጂኖች የበለጠ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት አካባቢያዊ ሁኔታዎች ናቸው” ብለዋል። ሳይንቲስቶች ወደ 35 በመቶ የሚጠጋው የካንሰር ሕመም የሚከሰተው ሲጋራ በማጨስ ሳቢያ እንደሆነና 30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከአመጋገብ ጋር ዝምድና እንዳለው ያምናሉ። ጂኖች የፕሮስቴት፣ የደንዳኔና የሽለላንጀት (colorectal) እንዲሁም የጡት ካንሰር በማስከተል ረገድ የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ ቢሆንም እንኳ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ውስጥ የሚገኘው የኢምፔሪያል ካንሰር ሪሰርች ፈንድ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ቲም ኪ የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል:- “ከቤተሰብህ መካከል [በካንሰር በሽታ] የተያዘ ሰው . . . ቢኖር እንኳ ትልቁን ሚና የሚጫወተው በሕይወትህ ውስጥ የምታደርገው ነገር ነው። ሲጋራ ከማጨስ መታቀብ ያለብህ ከመሆኑም በላይ በአመጋገብህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። ይህ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።”
ዓለማችን በየሳምንቱ ሁለት የእንስሳ ዝርያዎች ታጣለች
ዓለማችን በየሳምንቱ ሁለት የርቢ እንስሳት ዝርያዎች የምታጣ ሲሆን 1, 350 የሚሆኑ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል ሲል ኮሪዬሬ ዴላ ሴራ የተሰኘው የኢጣሊያ ጋዜጣ ዘግቧል። የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ተመራማሪዎች በ170 አገሮች በሚገኙና ለማዳ በተደረጉ 6, 500 አጥቢ እንስሳትና አዕዋፍ ላይ አሥር ዓመት የፈጀ ጥናት አካሂደዋል። አኒማል ጀነቲክ ሪሶርስስ ግሩፕ የተሰኘው የድርጅቱ አካል ዋና ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ኪት ሃሞንድ እንዳሉት ከሆነ “አንድ ነገር ካልተደረገ በስተቀር በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የርቢ እንስሳት ዝርያዎች ከናካቴው ይጠፋሉ።” ከወደ ሮም የተሰራጨው የሮይተርስ የዜና ዘገባ ያደጉት አገሮች እንስሳትን ወደ ሌሎች አገሮች መላካቸው ችግሩን እንዳባባሰው ይገልጻል። ከውጪ የሚገቡት እንስሳት ቀደም ሲል አገር ውስጥ ከነበሩት እንስሳት ጋር ሊዳቀሉ ስለሚችሉ የአገር ውስጥ ዝርያዎቹ ሙሉ በሙሉ ሊጠፉ ይችላሉ። “ይሁን እንጂ ችግሩ” ይላሉ ዶክተር ሃሞንድ፣ “ከውጪ አገር የሚገቡት እንስሳት በይበልጥ የሚስማማቸው ቀደም ሲል የነበሩበት አገር ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ በታዳጊ አገሮች ውስጥ ያለውን አስቸጋሪ አካባቢያዊ ሁኔታ መቋቋም ይሳናቸዋል።”
አንጎልህን አሠራው
“አንጎላችንን እስካሠራነው ድረስ እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ በሙሉ ኃይሉ መሥራት ይችላል” ሲል ቫንኩቨር ሰን የተሰኘው ጋዜጣ ገልጿል። በኦሃዮ ዩ ኤስ ኤ የሚገኘው የኬስ ዌስተርን ሪዘርቭ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ስኩል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አሚር ሶአስ “አንብብ፣ አንብብ፣ አንብብ” ሲሉ ተናግረዋል። ዕድሜህ እየገፋ ሲሄድ የአንጎልህ የመሥራት አቅም እየተዳከመ እንዳይሄድ በትርፍ ጊዜህ አእምሮን የሚያሠሩ ተግባሮች አከናውን፣ አዲስ ቋንቋ አጥና፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተማር፣ ወይም አእምሮን በሚያነቃቁ ጭውውቶች ተካፈል። “አንጎልህን የሚያሠራ ነገር ሁሉ አድርግ” ይላሉ ዶክተር ሶአስ። በተጨማሪም ቴሌቪዥን ለረጅም ሰዓት ከማየት መታቀብ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። “ቴሌቪዥን በምትመለከትበት ጊዜ አንጎልህ መሥራቱን ያቆመ ያህል ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል። ሰን የተሰኘው ጋዜጣ ጤናማ አንጎል ጤነኛ በሆኑ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች አማካኝነት የሚሰራጨውን ኦክሲጅን ማግኘት ይኖርበታል ሲል አክሎ ገልጿል። በመሆኑም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር የልብ ድካምንና የስኳር በሽታን ለመከላከል እንደሚረዳ ሁሉ አንጎልም በጥሩ ሁኔታ እንዲሠራ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የትምባሆ ሱስ በሜክሲኮ
በሜክሲኮ የትምባሆ ሱስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅርቡ ከተነደፈው ፕሮግራም ጋር በተያያዘ የጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሆሴ አንቶንዮ ጎንዛሌዝ ፈርናንዴዝ 27.7 በመቶ የሚሆኑ የሜክሲኮ ዜጎች እንደሚያጨሱ ገልጸዋል። ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው በግምት አንድ ሚልዮን የሚሆኑት አጫሾች ከ12 እስከ 17 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ነው። ሚስተር ጎንዛሌዝ በየዕለቱ ከሚሞቱት የሜክሲኮ ሰዎች መካከል ወደ 122 ገደማ የሚሆኑት ሕይወታቸው የሚያልፈው ከትምባሆ ሱስ ጋር በተያያዘ ሁኔታ እንደሆነ ይገመታል ሲሉ ተናግረዋል። “በዚህ ሱስ ሳቢያ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ፣ ለበርካታ ዓመታት በምርት ሂደት ላይ ሊያገለግል የሚችለው የሰው ኃይል በአጭር መቀጨቱን፣ . . . እና በአካባቢያችን ሆነው በሚያጨሱ ሰዎች ምክንያት በእኛም ላይ የሚደርሰውን ጉዳት” በመጥቀስ በምሬት ተናግረዋል።
ትንንሽ ልጆችና መጥፎ ሙዚቃ
የሰባትና የስምንት ዓመት ልጆች ሳይቀሩ ጸያፍ ቃላትን፣ የጾታ ብልግናን የሚያወድሱ ግጥሞችንና የኃይል ድርጊትን የሚያበረታቱ መልእክቶችን የያዘ ሙዚቃ ያዳምጣሉ ሲል ቺካጎ ትሪብዩን ዘግቧል። “ቀደም ባሉት ጊዜያት ከመዋዕለ ሕፃናት አንስቶ እስከ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድረስ ያሉ ልጆች ያዳምጡ የነበረው ‘ለልጆች ተብሎ የሚዘጋጀውን ሙዚቃ’ ነበር።” ይሁን እንጂ “በአሁኑ ጊዜ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወላጆቻቸው ወይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የሚሰሟቸውን ጣቢያዎች ከፍተው ከመስማት ወደ ኋላ አይሉም።” በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ሙዚቃ የሚቀርጹ ኩባንያዎች የኃይል ድርጊትን የሚያበረታቱ መልእክቶች ወይም የጾታ ብልግናን የሚያወድሱ ግጥሞች የያዙ ኮምፓክት ዲስኮች ልጆች እጅ እንዳይገቡ በዲስኮቹ ላይ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም እንዲህ ያሉትን ሙዚቃዎች በቀላሉ ወደ ሙዚቃ ቤቶች በመሄድ ሊያዳምጧቸው ይችላሉ። በቦስተን በሚገኘው የዊሎክ ኮሌጅ የሚሠሩትና የሕፃናት የመገናኛ ዘዴና የባሕል ስፔሽያሊስት የሆኑት ዳያን ሌቪን “ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ
ጊዜ ይበልጥ ቅጥ እያጡ ሲሄዱ እኛም ይበልጥ እየደነደንን እንሄዳለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።ለሳምባ ካንሰር የተጋለጡ የብሪታንያ ሴቶች
“በሳምባ ካንሰር የሚሞቱ የብሪታንያ ሴቶች ቁጥር በጡት ካንሰር ከሚሞቱት ሴቶች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ በልጦ የተገኘ ሲሆን በዚህም የተነሳ የሳምባ ካንሰር ሴቶችን ለሕልፈተ ሕይወት በመዳረግ ረገድ ከካንሰር በሽታዎች ሁሉ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ሊይዝ ችሏል” ይላል የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ያወጣው ዘገባ። በአሁኑ ጊዜ በበሽታው እየሞቱ ያሉት ሴቶች ከአራት አሥርተ ዓመታት በፊት፣ ሲጋራ ማጨስ ክብደት ለመቀነስ ይረዳል የሚል ማስታወቂያ ይናፈስ በነበረበት ጊዜ ማጨስ የጀመሩ ናቸው። የብሪታንያ የካንሰር ምርምር ዘመቻ ባለፉት 20 ዓመታት በጡት ካንሰር የሚሞቱ ሴቶች ቁጥር 5 በመቶ ሲቀንስ በሳምባ ካንሰር የሚሞቱት ቁጥር ግን 36 በመቶ እንደጨመረ አመልክቷል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በሳምባ ካንሰር የሚሞቱ ወንዶች ቁጥር 31 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ይህም አጫሽ የሆኑ ወንዶች ቁጥር እንደቀነሰ የሚያሳይ ነው። የካንሰር ዘመቻው ዋና ዲሬክተር የሆኑት ጎርደን መክቪ ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጡም እንኳ “ከወንዶቹ ልጆች ይበልጥ በርካታ ወጣት ልጃገረዶች ወደ አጫሾቹ ጎራ እየተቀላቀሉ ነው” ብለዋል።
የቤተሰብ መፈራረስ በብሪታንያ
በአውሮፓ ውስጥ ካሉ አገሮች መካከል ከፍተኛውን የፍቺ ቁጥር ያስመዘገበችው ብሪታንያ ስትሆን ሳይጋቡ አብረው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ የሚለያዩ ሰዎች ቁጥርም በእጅጉ ልቆ ተገኝቷል። “የቤተሰብ መፈራረስ የሚያስከትለው ኪሳራ” በሚል ርዕስ በመንግሥት የተካሄደን ጥናት መሠረት አድርጎ የወጣ አንድ ዘገባ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “ለልጆች ደህንነት መጓደል ዋነኛ መንስኤ የሚሆነው የቤተሰብ መፈራረስ፣ በተለይ ደግሞ ልጃቸውን በጋራ የሚያሳድጉት እናትና አባት መለያየት ነው።” ይህ ሁኔታ የሚያስከትለው ቀጥተኛ ችግር የብሪታንያ ግብር ከፋዮችን በየሳምንቱ በአማካይ 11 ፓውንድ [15 የአሜሪካ ዶላር] ወጪ የሚያስከትልባቸው ሲሆን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያስከትለው ኪሳራ ደግሞ ለተከፋፈሉ ቤተሰቦች መኖሪያነት የሚያገለግሉ ቤቶች ማቅረብን የሚጨምር በመሆኑ በአካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ጉዳት ይደርሳል። ዘገባው ምንም እንኳ ሥነ ምግባራዊ አመራር ለመስጠት አልሞ ባይሆንም የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “ትዳር የሰከነ ኅብረተሰብ ለመፍጠርና ልጆችን በአግባቡ ለማሳደግ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት መሆኑ በዘመናት ሂደት በሚገባ ተረጋግጧል ብለን እናምናለን።”
በውጥረት የተሞላ የምሳ ዕረፍት
“ወገብን ታጥቆ የመሥራት ባሕል ከፍ ተደርጎ በሚታይባት በብሪታንያ ምሳ በመብላት ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ሰዎች እንደ ደካማ የሚቆጠሩ በመሆኑ የሥራ ሱስ የተጠናወታቸው ሠራተኞች እዚያው የሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው ሳንድዊች በመመገብ የምሳ ዕረፍታቸውን ይሠዋሉ” ሲል የለንደኑ ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል። በቅርቡ የተካሄደው ጥናት በአሁኑ ጊዜ የአንድ ተራ ብሪታንያዊ ሰው “የምሳ ሰዓት” 36 ደቂቃ ብቻ እንደሆነ አመልክቷል። የሕክምና ጠበብት የምሳ ሰዓት ዕረፍት ውጥረትን እንደሚቀንስ ይናገራሉ። ሆኖም አንዳንድ አሠሪዎች በምሳ ሰዓት ስብሰባ ስለሚጠሩ ሠራተኞቹ ምንም ዕረፍት አያገኙም። ዳታሞኒተር የተባለው ሪፖርቱን ያጠናቀረው የምርምር ተቋም እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ከሠራተኞቹ ብዙ በሚጠብቅና ጊዜን በጣም ውድ ዋጋ ያለው ንብረት አድርጎ በሚመለከት ኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የምሳ ሰዓት ነዳጅ ለመሙላት ቆም የሚባልበት ለዕረፍት የማያመች ጊዜ ሆኖባቸዋል።” የዳታሞኒተር ተቋም ተንታኝ የሆኑት ሴራ ኑኒ “ያለነው በዓለም አቀፉ የገበያ ውድድር ውስጥ ነው። ‘በኋላ እሠራዋለሁ’ የሚባል ነገር የለም። አሁኑኑ መሠራት አለበት” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
ማቀዝቀዣ መሣሪያ ሳይኖር ምግብን ሳይበላሽ ማቆየት
በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ማቀዝቀዣ መሣሪያ በሌለበት ሁኔታ በቀላሉ የሚበላሹ ምግቦችን ሳይበላሹ አቀዝቅዞ ማቆየት አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሚገኝ ዝናብ ብዙም በማያገኝ ደረቅ አካባቢ የተፈለሰፈ በጣም ቀላልና ርካሽ የሆነ የፈጠራ ሥራ በዚህ ረገድ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ የፈጠራ ሥራ አንድን ማሰሮ በሌላ ማሰሮ ውስጥ መክተትና በሁለቱ መካከል ያለውን ክፍተት በእርጥብ አሸዋ መሙላት የሚጠይቅ ነው። በትንሹ ማሰሮ ውስጥ ምግብ ይቀመጥና ማሰሮው በእርጥብ ጨርቅ ይሸፈናል። “ከውጪ ያለው ሞቃት አየር እርጥበቱ ወደ ማሰሮው የውጪ አካል እንዲወጣና እንዲተን ያደርገዋል” ይላል ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔት። “የውኃው ተን ሙቀቱንም ይዞት ስለሚሄድ ይህ ሂደት አሸዋውና ጨርቁ እርጥብ እስከሆኑ ድረስ ሙቀት ያለማቋረጥ ወደ ውጪ እንዲወጣ ያደርጋል።” በዚህ ዘዴ በመጠቀም ቲማቲምና ቃሪያ ሳይበላሽ ከሦስት ሳምንት በላይ እንዲቆይ ማድረግ የሚቻል ሲሆን ደበርጃንን ደግሞ ወደ አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ ማስቀመጥ ይቻላል። ይህን “ማሰሮ በማሰሮ ውስጥ” ከትቶ የመጠቀም ዘዴ የፈለሰፈው ሞሐመድ ባ አባ የተባለው ሰው አሁን ገበሬዎች ምርታቸውን የተፈለገውን ያህል መሸጥ የሚችሉ ከመሆኑም በላይ ምርቱን ለመሸጥ ሲሉ በየዕለቱ እቤት ለመቀመጥ ይገደዱ የነበሩት ሴት ልጆቻቸውም ትምህርት ቤት ለመሄድ ነፃነት ያገኛሉ ሲል ተናግሯል።
ሴቶችና የልብ በሽታ
“የልብ በሽታ በየዓመቱ ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳርጋቸው ወንዶችና ሴቶች ቁጥር ተመጣጣኝ ቢሆንም እንኳ በተለምዶ የወንዶች በሽታ እንደሆነ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል” ሲል ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። ሴቶች በልብ በሽታ በሚያዙበት ጊዜ በአብዛኛው በሽታው ተለይቶ የሚታወቀው በጣም ዘግይቶ ነው ሲል ጋዜጣው አትቷል። በሰሜን አሜሪካ የብዙዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘው ይህ የልብ በሽታ በወንዶችና በሴቶች ላይ የሚያስከትላቸው ምልክቶች የተለያዩ ናቸው። “ብዙውን ጊዜ ወንዶች ወደ አንገት፣ ጀርባና ትከሻ የሚሰራጭ ከባድ የደረት ሕመም የሚሰማቸው ሲሆን ሴቶች ደግሞ በአብዛኛው የመንጋጭላ ሕመም፣ የትንፋሽ ማጠርና የማቅለሽለሽ ስሜት ያጋጥማቸዋል” ይላል ስታር። ብዙውን ጊዜ ምልክቶቹ በሴቶች ላይ መታየት የሚጀምሩት 55 ዓመት ካለፋቸው በኋላ የኤስትሮጂን መጠን እየቀነሰ በሚሄድበት ጊዜ ነው። “ኤስትሮጂን ከሰውነታችን ውስጥ በሚሟጠጥበት ጊዜ ወዲያውኑ እኛም ከወንዶቹ እኩል ለልብ በሽታ የተጋለጥን እንሆናለን” ሲሉ በቶሮንቶ አጠቃላይ ሆስፒታል የልብ ቀዶ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ስቴፋኒ ብሪስተር ተናግረዋል።