ስለ አረጋውያን የሚባለውና እውነታው
ስለ አረጋውያን የሚባለውና እውነታው
ስለ አረጋውያን የሚባል ብዙ ነገር አለ። በዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ሥር በዕድሜ ለገፉ የጤና እንክብካቤ ለማድረግ የተቋቋመው ቡድን “ኤጂንግ—ኤክስፕሎዲንግ ዘ ሚዝስ” በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ ላይ የአንዳንዶቹን አባባሎች መሠረተ ቢስነት አጋልጧል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት።
የሚባለው :- አብዛኞቹ አረጋውያን የሚኖሩት በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ነው።
እውነታው:- እንደ እውነቱ ከሆነ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት 580 ሚልዮን የሚያክሉ አረጋውያን መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት የሚኖሩት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ሲሆን በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች ጥሩ የጤና እንክብካቤ እንዲሁም ተስማሚ የመኖሪያ አካባቢ በማግኘታቸውና የተሻሻለ የአመጋገብ እንዲሁም የንጽሕና አጠባበቅ ልማድ በማዳበራቸው ረጅም ዕድሜ ለመኖር እየታደሉ ነው።
የሚባለው:- አረጋውያን ለኀብረተሰቡ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የለም።
እውነታው:- አረጋውያን ምንም የገንዘብ ክፍያ የማያገኙባቸውን ሥራዎች በመሥራት ለማኀበረሰቡ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ለምሳሌ በዮናይትድ ስቴትስ ወደ 2 ሚልዮን የሚጠጉ ሕፃናት እንክብካቤ የሚደረግላቸው በአያቶቻቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 1.2 ሚልዮን የሚያክሉት የሚኖሩት ከአያቶቻቸው ጋር ነው። ስለዚህ አረጋውያን መጠለያ፣ ምግብና ትምህርት በማቅረብ እንዲሁም ባሕላዊ እሴቶችን ለልጅ ልጆቻቸው በማስተላለፍ የልጆቹ እናቶችና አባቶች በሥራው ዓለም እንዲቆዩ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በተመሳሳይም በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ የነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱት አረጋውያን በሚሰጡት ጠቃሚ ድጋፍ ነው። በተጨማሪም አረጋውያን ሌሎችን በመንከባከብ ረገድ ተፈላጊ ናቸው። በአንዳንድ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች 30 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች በኤድስ ቫይረስ የተጠቁ በመሆናቸው አረጋውያን በበሽታው የተያዙ ልጆቻቸውን ያስታምማሉ። በበሽታው የተጠቁት ልጆቻቸው ከሞቱ በኋላ ደግሞ ወላጅ አልባ የሆኑትን የልጅ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት እነሱ ናቸው።
የሚባለው:- አረጋውያን ከሥራው ዓለም የሚገለሉት ሥራቸውን ማከናወን ስለሚያቅታቸው ነው።
እውነታው:- ብዙውን ጊዜ ከሥራው ዓለም የሚገለሉት በትምህርት ወይም በሥልጠና ማነስ ወይም ደግሞ በኤጂዝም (ለአረጋውያን በሚሰጠው የተሳሳተ ግምት) ምክንያት እንጂ በዕድሜያቸው መግፋት ብቻ አይደለም።
የሚባለው:- አረጋውያን መሥራት አይወድዱም።
እውነታው:- አረጋውያን አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ ገበታቸው የሚገለሉት ሥራቸውን መቀጠል እየፈለጉና እየቻሉም ነው። በተለይ ሥራ አጥነት በሚስፋፋባቸው ወቅቶች በአብዛኛው አረጋውያን ቦታውን ለወጣት ሥራ ፈላጊዎች እንዲለቅቁ ይደረጋል። ይሁን እንጂ አረጋውያንን ከሥራ ገበታ ማፈናቀል ሁልጊዜ ለወጣቶች ክፍት የሥራ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል ማለት አይደለም። አንድ ወጣት ሥራ ፈላጊ አንድን አረጋዊ ተክቶ ለመሥራት የሚያስችል ልምድ አይኖረው ይሆናል። ልምድ ያካበቱ አረጋውያን የሥራውን ምርታማነት በመከታተልና የሠራተኛውን ኃይል በማደራጀት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እነዚህን እውነታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት አረጋውያንን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች አድርጎ መመልከት እንዳለበት የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) አስገንዝቧል። በዓለም የጤና ድርጅት ሥር ለአረጋውያን የጤና እንክብካቤ ለማድረግ የተቋቋመው ቡድን መሪ የሆኑት አሌክሳንደር ካላቺ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “አገሮች በዕድሜ የገፋውን የኀብረተሰብ ክፍል ልክ እንደ ችግር አድርገው ከመቁጠር ይልቅ ይህንን የኀብረተሰብ ክፍል ለችግሮች መፍትሄ እንደሚያስገኝ ኃይል አድርገው መመልከት ይኖርባቸዋል።” ይህ ደግሞ እውነት ነው።