በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተለያይተው የኖሩትን የኮሪያ ቤተሰቦች እንደገና ማገናኘት—አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፋች ይሆን?

ተለያይተው የኖሩትን የኮሪያ ቤተሰቦች እንደገና ማገናኘት—አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፋች ይሆን?

ተለያይተው የኖሩትን የኮሪያ ቤተሰቦች እንደገና ማገናኘት—አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፋች ይሆን?

በኮሪያ ሪፑብሊክ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ታላቅ ሰብዓዊ ድራማ ተብሎ ተጠርቷል። ትዕይንቱ 1, 300 የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችንና ከ400 የሚበልጡ የውጭ አገር ዘጋቢዎችን የሳበ ነበር። ይህ ክንውን በኮሪያ ሰሜናዊና ደቡባዊ ክፍሎች 50 ለሚያክሉ ዓመታት ተለያይተው የኖሩ ቤተሰቦችን እንደገና ለማገናኘት የተደረገው ጥረት ውጤት ነበር።

ብዙ ኮሪያውያን ለግማሽ መቶ ዓመት ከዘመዶቻቸው ጋር በደብዳቤ፣ በፋክስም ሆነ በስልክ ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። ሁለቱን አገሮች የሚከፍለው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነው ቀጣና የቤተሰብ አባላትን ለያይቷል። ቤተሰቦችን ዳግም የማገናኘቱን ተግባር እንዲሳካ ያስቻለው ምንድን ነው? *

የተለየ ስሜት የፈጠረ የማገናኘት ተግባር

ነሐሴ 15, 2000 የኮሪያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሰንደቅ ዓላማ ያለበት አውሮፕላን በኮሪያ ሪፑብሊክ ኪምፖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አረፈ። አውሮፕላኑ አንዳንድ ዘመዶቻቸው በደቡብ ኮሪያ በሕይወት መኖራቸውን በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል በኩል ማረጋገጫ ያገኙ ከሰሜን ኮሪያ የመጡ መንገደኞችን አሳፍሯል። ከዚያም አውሮፕላኑ 100 ኮሪያውያንን ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ ከደቡብ ኮሪያ አሳፍሮ ወደ ሰሜን ኮሪያ ተመልሶ በረረ። ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ያላገኘኸው ወንድም፣ እህት፣ እናት፣ አባት፣ ወንድ ወይም ሴት ልጅ ወይም ደግሞ የትዳር ጓደኛ እንዳለህ አድርገህ አስብ! ተለይተዋቸው ከኖሩ ዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት ከመጡት መካከል ብዙዎቹ በ60ዎቹና በ70ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ዘመዶቻቸውን አይተው አያውቁም!

እንደገና የተገናኙት የቤተሰብ አባላት አብረው እንዲቆዩ የታሰበው ለአራት ቀናትና ለሦስት ሌሊቶች ብቻ ሲሆን ከዚያ በኋላ ሁሉም ወደየመጡበት አገር መመለስ ይኖርባቸዋል። እንደገና የተገናኙት ብዙዎቹ የቤተሰብ አባላት ያለ ማቋረጥ ማለት ይቻላል፣ ሲያወሩ የነበረበት ምክንያት ይህ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም! የስሜት ቀውስና የአእምሮ መታወክ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በመታሰቡ ዶክተሮች፣ ነርሶችና አምቡላንሶች ዝግጁ ነበሩ። እንደተገመተውም የእነርሱ እርዳታ አስፈልጎ ነበር።

ተለያይተው ከሚኖሩ ቤተሰቦች ብዛት አንጻር ሲታይ እንዲገናኙ የተደረጉት ሰዎች ቁጥር በጣም በጣም አነስተኛ ነው። አንዳንዶች ከ60 ዓመት ዕድሜ በላይ የሚሆናቸው 690, 000 ሰዎች እንዲሁም ከ70 ዓመት ዕድሜ በላይ የሚሆናቸው 260, 000 ሰዎች ከሚወዷቸው ዘመዶቻቸው ተለያይተው መቅረታቸውን ይገምታሉ። ይሁን እንጂ ከኮሪያ ሪፑብሊክ በሰሜን ኮሪያ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት አንዳንድ ብቃቶችን አሟልተው ከተመዘገቡት 76, 000 ሰዎች መካከል የተመረጡት 100 ብቻ ነበሩ።

ከእነዚህ መካከል የ82 ዓመቱ አዛውንት ያንግ ዢን ዩል ይገኙበታል። እኚህ አዛውንት በሰሜን ኮሪያ የሚኖሩት ያንግ ዎን ዩል የተባሉት የ70 ዓመት ወንድማቸው በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ ዘመዶቻቸውን ማግኘት እንደሚፈልጉ የሚገልጽ ማስታወሻ በቀይ መስቀል አማካኝነት ደረሳቸው። የያንግ ዢን ዩል ታናሽ ወንድም በ1950 በኮሪያ ጦርነት ወቅት ደብዛቸው የጠፋው ሴኡል በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ሳሉ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ስለ እርሳቸው ምንም አልተሰማም። እነዚህ ሁለት ወንድማማቾች ከሁለት እህቶቻቸው ጋር ከአምስት አሥርተ ዓመታት መለያየት በኋላ እንደገና ተገናኝተዋል!

የ73 ዓመቱ ሊ ፖክ ዮን የ70 ዓመት ዕድሜ ካላቸው ባለቤታቸውና ከሁለት ወንዶች ልጆቻቸው ጋር እንደገና ተገናኝተዋል። እኚህ ሰው ቤተሰባቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ያዩት ልጆቹ የሁለትና የአምስት ዓመት ዕድሜ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው። ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ አንድ ቀን ብስክሌት ለመግዛት ብለው ከቤት ወጡ። ወጥተው በዚያው የቀሩ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ወዲህ ድምፃቸው አልተሰማም። ሰውነትን የሚያንቀጠቅጥ በሽታ (palsy) ያለባቸውና የስኳር ሕመምተኛ የሆኑት ባለቤታቸው እንደገና ካገኟቸው በኋላ ለአሥርተ ዓመታት በአእምሯቸው ውስጥ ሲጉላላ የኖረውን ጥያቄ ይኸውም ብስክሌቱን ገዝቶ ለመመለስ ያን ያህል ጊዜ የወሰደባቸው ለምን እንደነበረ ጠይቀዋቸዋል።

የ69 ዓመቱ ሊ ቾንግ ፒል በ1950 ከቤተሰባቸው ተለያይተው ስማቸው በጠፉ ሰዎች መዝገብ ላይ በሰፈረበት ወቅት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበሩ። በደቡብ ኮሪያ ከሚኖሩ ቾ ዎን ሆ ከተባሉ የ99 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ እናታቸው፣ ከሁለት ወንድሞቻቸውና ከሁለት እህቶቻቸው ጋር እንደገና ተገናኝተዋል። የሚያሳዝነው ግን የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት እናታቸው ሊለዩአቸው አልቻሉም።

በወቅቱ ከታዩት ከብዙዎቹ ልብ የሚነኩ ሁኔታዎች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ይህ ክንውን በአገር ውስጥና በውጭ አገር የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ ተላልፏል። ቤተሰቦች እንደገና ሲገናኙ ያዩ ተመልካቾችም በደስታ አንብተዋል! ብዙዎች ይህ ሁኔታ ለሌሎችም መንገድ ይጠርግ ይሆን የሚል ሐሳብ መጥቶባቸዋል። ያም ሆነ ይህ እነዚህ ቤተሰቦች አብረው የሚቆዩበት ጊዜ ማብቂያው ወዲያው የደረሰ ሲሆን ዳግም መለያየቱ የፈጠረው የስሜት ስቃይ ከመጀመሪያው የማይተናነስ ነበር። እነዚህ የሚዋደዱ ዘመዳሞች ወደፊት ስለ መገናኘታቸው፣ የሚገናኙም ከሆነ መቼ ሊሆን እንደሚችል የሚያውቁት ነገር የለም።

ለግማሽ መቶ ዓመት ቤተሰቦችን አለያይቶ የቆየው ሁኔታ መቋጫው ደርሶ ይሆን?

ነሐሴ 15, 1945 ኮሪያ ለ36 ዓመታት የቆየውን የጃፓን የቅኝ ግዛት ቀንበር ከላይዋ ላይ አሽቀንጥራ ጣለች። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ኮሪያ በዘመኑ ሰፍኖ በነበረው ፖለቲካ ተከፋፈለች። የአሜሪካ ኃይሎች ጃፓንን ከኮሪያ ባሕረ ሰላጤ ገፍተው በማስወጣት ደቡባዊውን ክልል በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉ ሲሆን የሶቪየት ኃይሎች ደግሞ በስተ ሰሜን የሚገኘውን ክልል ተቆጣጠሩ። ብዙም ሳይቆይ የፈነዳው ጦርነት ለችግሩ ያስገኘው መፍትሔ አልነበረም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኮሪያ ሁለት መንግሥታት ተፈጠሩ። ከ1945 አንስቶ የኮሪያ ጦርነት እስኪያበቃ ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ተለያይተዋል። በመጨረሻ ጦርነቱ በ1953 ካበቃ በኋላ በፈንጂ የታጠረው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነ ቀጣና አገሪቱን ለሁለት ከፈላት።

ለብዙ አሥርተ ዓመታት አንዳች የእርቅ ምልክት አልታየም። ይሁን እንጂ ሰኔ 13, 2000 የኮሪያ ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት ኪም ዴ ጁንግን የያዘ አንድ አውሮፕላን በፕዮንግያንግ ሱናን አውሮፕላን ማረፊያ አረፈ። የኮሪያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ርዕሰ ብሔር ኪም ጆንግ ኢል በአውሮፕላን ማረፊያው ተገኝተው አቀባበል አደረጉላቸው። ድንገተኛና ያልተጠበቀ የተስፋ ጭላንጭል መታየት ጀመረ። ሁለቱ መሪዎች ከዚያ በፊት ተገናኝተው አያውቁም። ሆኖም ላያቸው ለረጅም ጊዜ ተጠፋፍተው የኖሩ ወንድማማች ይመስሉ ነበር። ሁለቱ መሪዎች ለሦስት ቀናት ባደረጉት ስብሰባ ለግማሽ መቶ ዓመት ሰፍኖ የቆየውን ጠላትነት ለማብቃትና ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ተባብረው ለመሥራት ተስማምተዋል። ተለያይተው የኖሩትን የቤተሰብ አባላት ዳግም ለማገናኘት የተደረገው ጥረት የሁለቱ መሪዎች ውይይት ካስገኛቸው የመጀመሪያ ውጤቶች መካከል አንዱ ነበር። በቅርቡ ሌሎች እርምጃዎችም እንደሚወሰዱ ይጠበቃል።

ሁለቱ መሪዎች ሰሜን ኮሪያን ከደቡብ ኮሪያ ጋር በባቡር እንደገና ለማገናኘት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በኮሪያ ደቡባዊ ክፍል 12 ኪሎ ሜትር የሚሆን የባቡር ሃዲድ፣ በሰሜናዊው ክፍል ደግሞ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር ሃዲድ የመጠገን ሥራ እስከ መስከረም 2001 ድረስ ይጠናቀቃል። ይህ የባቡር ሐዲድ ኮሪያን የሚከፍለውን ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ነጻ የሆነ ክልል አቋርጦ በማለፍ ሁለቱን ኮሪያዎች እንደገና ያገናኛቸዋል። ከጊዜ በኋላ ይህ የባቡር መስመር ቻይናን አቋርጦ ከሚያልፈው የባቡር መስመር ጋር ሲገናኝ ከኮሪያ ባሕረ ሰላጤ ተነስቶ ቻይናን በማቋረጥ እስከ አውሮፓ ድረስ የሚዘልቅ መስመር ይወጣዋል። በእውነትም ፕሬዚዳንት ኪም ዴ ጁንግ እንዳሉት “አዲስ የሐር የባቡር መንገድ” ይሆናል። ወደፊት ደግሞ ሌላኛው የባቡር መስመር ሁለቱን ኮሪያዎች የሚለየውን ክልል መሃል ለመሃል አቋርጦ በሳይቤሪያ ከሚያልፈው የሩሲያ የባቡር መስመር ጋር እንዲገናኝ ይደረጋል።

እነዚህ እርምጃዎች በእርግጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፋች መሆን አለመሆናቸው ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን ተለያይተው የኖሩ ቤተሰቦችን ለማገናኘት የተደረገው ጥረት የሚያስመሰግን እርምጃ ነው። ያም ሆኖ ግን የሰው ልጅ በአምላክ መንግሥት የሚተዳደር ዓለም አቀፋዊ አገዛዝ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 6:​9, 10) የይሖዋ ምሥክሮች ከ1912 አንስቶ ይህን መልእክት በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ለሚገኙ ሕዝቦች ሲያዳርሱ ቆይተዋል። በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ ሰሜናዊ ክፍል የሚኖረው ሕዝብ መልእክቱ የደረሰው ሲሆን ብዙዎች መልእክቱን ተቀብለዋል። ከእነዚህ ብዙዎቹ በጃፓን አገዛዝ ወቅት በጦርነት ለመካፈል ፈቃደኞች ስላልነበሩ ለእስር ተዳርገው ነበር።

እነዚህ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አልፎ ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ አንድ ላይ መሰብሰብ ጀመሩ። ብዙዎቹ የአምልኮ ነፃነት ለማግኘት ሲሉ ወደ ደቡብ ኮሪያ መጥተዋል። በሰኔ 1949 በሴኡል የመጀመሪያው ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን ዛሬ በኮሪያ ሪፑብሊክ ከ87, 000 በላይ ምሥክሮችን ያቀፈ ትልቅ ድርጅት ለመሆን በቅቷል። ከእነዚህም መካከል በሺህዎች የሚቆጠሩት በሰሜን ኮሪያ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው የመለየት እጣ የገጠማቸው ናቸው።

ምናልባት ሁኔታዎች ተለውጠው በኮሪያ ተለያይተው የሚኖሩ ቤተሰቦች እንደገና የሚገናኙበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ቤተሰቦች ተለያይተው የሚኖሩበት ሁኔታ አክትሞ በኮሪያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ያለው 22 ሚልዮን ሕዝብ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚሰማበት አጋጣሚ ይከፈት ዘንድ ምኞታችን ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በ1985ም በመንግሥት ድጋፍ የቤተሰብ አባላትን እንደገና ማገናኘት ተችሎ ነበር።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንድ ባልና ሚስት (ከላይ) እንዲሁም አንዲት እናትና ወንድ ልጃቸው (ከታች) እንደገና ሲገናኙ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቀድሞ አባቶችን አምልኮ የሚከተሉ አንድ ሰው ከመገናኘታቸው በፊት በሞቱት አባታቸው ምሥል ፊት ሲሰግዱ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያንግ ዢን ዩል (በስተ ግራ ያሉት) በሰሜን ኮሪያ ከሚኖሩ ወንድማቸው (መሃል ያሉት) ጋር ሲገናኙ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከገጽ 13-15 ያሉት ፎቶግራፎች:- The Korea Press Photojournalists Association