ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ቂጥኝ አገረሸ
ቂጥኝ ለአሥርተ ዓመታት ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል ከፈረንሳይ ምድር ጠፍቶ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት በፆታ ግንኙነት የሚተላለፈው የዚህ በሽታ አዲስ ወረርሽኝ በዋነኝነት በግብረሰዶም ፈጻሚዎች ዘንድ እንደተከሰተ ዶክተሮች የደረሱበት መሆኑን ዕለታዊው የፈረንሳይ ጋዜጣ ለ ፊጋሮ ዘግቧል። በብሪታንያና በአየርላንድም በ2000 ተመሳሳይ የቂጥኝ ወረርሽኝ እንደተከሰተ ተስተውሏል። በባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣው የቂጥኝ በሽታ ገና ሲጀምር የቆዳ ቁስልና ሽፍታ የሚያስከትል ሲሆን በጊዜው ካልታከመ በሕዋሰ ነርቮችና በሥርዓተ ልበ ወቧንቧ ላይ (cardiovascular) ጉዳት ያስከትላል። “በሕክምና ልምምዳቸው ወቅት አንድም የቂጥኝ ታማሚ አጋጥሟቸው በማያውቁት በዛሬዎቹ ዶክተሮች ዘንድ ጨርሶ የማይታወቅ በሽታ በመሆኑ” የቂጥኝ እንደገና ማገርሸት አሳሳቢ ጉዳይ ነው ሲል ለ ፊጋሮ አስተያየቱን አስፍሯል። በመሆኑም ዶክተሮች በሽታውን በትክክል ላያገኙትና ውጤታማ ሕክምና ሳይሰጥ ሊቀር ይችላል። በሽታን የሚያጠኑ ስፔሻሊስቶች እንደሚገምቱት ለቂጥኝ ማገርሸት ምክንያት የሆኑት አደገኛ ወሲባዊ ልማዶች ናቸው። ከዚህም በመነሳት ይህ ዓይነቱ ልማድ “የኤድስ ወረርሽኝ በአዲስ መልክ እንደሚፈነዳ” የሚያመላክት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።
በ2000 አዲስ የተፈጥሮ አደጋዎች ሪኮርድ
ሙኒክ ሪ የተባለው የኢንሹራንስ ኩባንያ በዓለም ዙሪያ በሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ረገድ በ2000 አዲስ ሪኮርድ መመዝገቡን ሪፖርት አድርጓል። በአጠቃላይ ከ850 በላይ አደጋዎች ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን 10, 000 ሰዎች ሞተዋል እንዲሁም ከ30 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚገመት የንብረት ውድመት ደርሷል። የተፈጥሮ አደጋዎቹ ቁጥር ይጨምር እንጂ በኢኮኖሚና በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፊተኛው ዓመት ቀንሶ ተገኝቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት አብዛኛዎቹ አደጋዎች የተከሰቱት ብዙም ነዋሪ በሌለባቸው አካባቢዎች በመሆኑ ነው ሲል የኩባንያው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታውቋል። በኢንሹራንስ ክፍያው የተሸፈነው 73 በመቶ የሚያክለው ውድመት የደረሰው በኃይለኛ ወዠብ ምክንያት ሲሆን የቀረው 23 በመቶ ደግሞ በውኃ መጥለቅለቅ ነው። ሪፖርቱ እንዳለው ከሆነ ከሕዝብ ብዛት ጭማሪና ከንብረት ዋጋ መናር አንጻር ሲታይ “በመጪዎቹ ዓመታት በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚደርሰው ኪሳራ እንደሚጨምር ይጠበቃል።”
የንቦች አቅጣጫ የመለየት ችሎታ
ንቦች ከቀፏቸው ወደ አበቦች ከዚያም ተመልሰው ወደ ቤታቸው የመብረር ችሎታ እንዳላቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከመኖሪያቸው በመሰደድ በሰሜን ህንድ ከምትገኘው ከአሳም ተነስተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በመንጋ የሚጓዙ ንቦች ከሁለት ዓመታት በኋላ ዝርያዎቻቸው ይኖሩባት ወደነበረው ዛፍ ብቻ ሳይሆን ቅርንጫፍ ጭምር ይመለሳሉ! ይህን ሁኔታ ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ሠራተኛ ንቦች የሚኖሩት ለሦስት ወይም ከዚያ ላነሱ ወራት ብቻ መሆኑ ነው። በመሆኑም ወደመኖሪያቸው ተመልሰው በሚመጡት ንቦችና ቀፎውን በሰሩት ንቦች መካከል የተወሰኑ ትውልዶች ርቀት ይኖራል። ቦታውን እንዴት መልሰው ያገኙታል የሚለው ነገር እንቆቅልሽ ነው። ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ ምናልባት ከማሽተት ሕዋሳቸው ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ሲል ሪፖርት አድርጓል። ወይም ደግሞ በሕይወት የቆየችው ንግሥቲቱ ንብ የሚበርሩበትን አቅጣጫ ለአሳሽ ንቦቹ ትጠቁማቸው ይሆናል።
የሚያሳዩ ፖስታዎች
አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ኩባንያ አንዳች ቀሪ ምልክት ሳይተው “የታሸጉ ፖስታዎች ውስጥ ያለውን ነገር ማየት የሚያስችል” የሚረጭ ፈሳሽ እንዳዘጋጀ ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት ዘግቧል። የኩባንያው ቃል አቀባይ የሆኑት ቦብ ሽላገል እንደተናገሩት ይህ ፈሳሽ ማንኛውም ዓይነት ቀለም ላለው ፖስታ የሚሠራ ሲሆን “ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ ባሕርይና መርዛማነት የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ ለአካባቢ ብክለት አያሰጋም።” ከ10 እስከ 15 ለሚያክል ደቂቃ ጥቂት ከመሽተቱ በቀር “የተጻፈበት ቀለም በፖስታው ወይም በደብዳቤው ላይ እንዲለቅ የማድረግም ሆነ ምንም ዓይነት የእርጥበት ምልክት የመተው ባሕርይ የለውም” ሲሉ ሽላገል ጨምረው ተናግረዋል። ይህ ፈሳሽ የተዘጋጀው የሕግ አስፈጻሚ አካላት በደብዳቤ መልክ የሚላኩ ቦምቦችን እንዲሁም አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሌሎች እሽጎችን ለመለየት እንዲችሉ ለመርዳት ታስቦ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ፈሳሽ የታሸጉ ደብዳቤዎችን ለማንበብም ስለሚያስችል አንድ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ባለ ሥልጣን ከግብረገብ አንጻር አጠያያቂ ነው ብለውታል።
ቋንቋና የሰው አንጎል
መስማት የሚችሉ ሰዎች አንድን ቋንቋ ሲያዳምጡና ሲናገሩ የሚጠቀሙባቸውን ሁለቱን የአንጎል ክፍሎች መስማት የተሳናቸው ሰዎችም በምልክት ቋንቋ ለመግባባት እንደሚጠቀሙባቸው ሳይንስ ኒውስ ዘግቧል። እንደ ዘገባው ከሆነ በአንጎል ላይ የተደረገው ምርመራ “እነዚህ የነርቭ ኅብረ ሕዋስ ያለባቸው አካባቢዎች የምልክት ቋንቋ በሚጠቀሙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ውስጥም ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ።” ጥናቱን የመሩትና በሞንትሪያል በሚገኘው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ላውራ-አን ፐቲቶ እንዳሉት ከሆነ ይህ ሁኔታ እነዚህ የአንጎል ክፍሎች “በቃልም ይሁን በምልክት የሚገለጹትን መሠረታዊ የቋንቋ ገጽታዎች” እንደሚቆጣጠሩ የሚጠቁም ነው። ይህም የሰው ልጅ አንጎል ቋንቋን በማስተናገድ በኩል ያለው ችሎታ ይበልጥ ጥናት ሊካሄድበት እንደሚገባ የሚጠቁም ነው። “በቃልም ይሁን በምልክት በሚገለጹ ቋንቋዎች ወቅት ምላሽ የሚሰጡት የአንጎል ክፍሎች በእጅጉ ተመሳሳይነት” እንዳላቸው ሳይንስ ኒውስ ገልጿል።
ለዝሙት አዳሪነት ሽፋን መስጠት
አንድ የጀርመን ፍርድ ቤት ዝሙት አዳሪነት በግድ የሚፈጸም የወንጀል ድርጊት እስካልሆነ ድረስ “በመሠረቱ ብልግና አይደለም” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ሳይቱንግ ዘግቧል። በበርሊን ቪልመርስዶርፍ በሚገኝ አንድ ቡና ቤት ዝሙት አዳሪዎች ከፈላጊዎቻቸው ጋር ተገናኝተው እዚያው አካባቢ ክፍል እንደሚይዙ ቢታወቅም የበርሊን አስተዳደር ችሎት ቡና ቤቱ ሥራውን እንዲቀጥል ወስኗል። ዳኞቹ ውሳኔው
ኅብረተሰቡ ለዝሙት አዳሪነት ያለው አመለካከት መለወጡን የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል። ከ1, 002 ሰዎች የተሰባሰበው አስተያየት እንደሚያሳየው 62 በመቶ የሚያክሉት ዝሙት አዳሪነት እንደ አንድ ሥራ እውቅና ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ለሁለተኛ ጊዜ የተሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው አብዛኛዎቹ “ወሲባዊ አገልግሎቶች [ከጀርመን] ኢኮኖሚ ጋር ያላቸው ትስስር” ረጅም ጊዜ የቆየ እንደሆነ ያምናሉ።እንቅልፍና የማስታወስ ችሎታ
ስለ እንቅልፍ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ለማጥናት ብሎ እስከ እኩለ ሌሊት ከማፍጠጥ ይልቅ ጥሩ እንቅልፍ ተኝቶ ማደር “በመጪዎቹ ሳምንታት ጥሩ ለማስታወስ እንደሚረዳ” ደርሰውበታል ሲል በለንደን የሚታተመው ዚ ኢንዲፔንደንት ገልጿል። በሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት የሚሠሩት ፕሮፌሰር ሮበርት ስቲክጎልድ ካሰባሰቧቸው 24 ፈቃደኛ ሰዎች መካከል ግማሾቹ ከአንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜ በኋላ ሌሊቱን ተኝተው እንዲያድሩ ሲደረግ ሌሎቹ ግን ሌሊቱን ሙሉ እንዳይተኙ ተደረገ። ከዚያም እንቅልፍ ያጡት ከድካማቸው እንዲላቀቁ ለመርዳት ሲባል ሁለቱም ቡድኖች ለሚቀጥሉት ሁለት ሌሊቶች እንደወትሯቸው እንዲተኙ ተደረገ። ከዚያ በኋላ የማስታወስ ችሎታቸውን ለመፈተን በተደረገው ሙከራ በመጀመሪያው ዕለት የተኙት “ለፈተናው የሰጡት ምላሽ የሚያስገርምና አንድ ወጥ ሲሆን የተቀሩት ግን እንቅልፋቸውን ቢያካክሱም ምንም ዓይነት መሻሻል ሳያሳዩ ቀርተዋል።” እንቅልፍ የማስታወስ ችሎታን የሚያጠናክር በመሆኑ ይህ ግኝት በተለይ በመጀመሪያዎቹ የመኝታ ሰዓታት የሚኖረውን ከባድ እንቅልፍ ሠውቶ ለማጥናት መሞከር ብዙም ጥቅም እንደሌለው የሚያሳይ ሆኗል።
የቼርኖበል ድንገለውጥ አደጋ
“በዩክሬይን ቼርኖበል ከሚገኘው ከአገልግሎት ውጭ የሆነ የኑክሊየር ጣቢያ አቅራቢያ የሚበቅሉት ተክሎች ከሌሎች ዕፅዋት ጋር ሲነጻጸሩ ስድስት እጥፍ በራሂያዊ ጉዳት ደርሶባቸው ተገኝተዋል” ሲል በለንደን የሚታተመው ዚ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል። ከስዊዘርላንድ፣ ከብሪታንያና ከዩክሬይን የተውጣጡት ተመራማሪዎች ሁለት አንድ ዓይነት የስንዴ ዝርያዎችን፣ አንዱን በተበከለው አፈር ሌላውን ደግሞ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ባልተበከለ ተመሳሳይ የአፈር ዓይነት ላይ ተከሉ። ከዚያም ከእነዚህ ተክሎች የተገኘውን ዘር በተመሳሳይ ሁለት ቦታዎች ላይ ዘሩት። በኑክሊየር ማብለያ ጣቢያው አቅራቢያ የነበረው ዘር የሚደርስበት የኑክሌር ብናኝ አነስተኛ ቢሆንም ከፍተኛ በራሂያዊ ጉዳት ወይም ድንገለውጥ (mutation) እንደገጠመው ታይቷል። ሁኔታው ያሳሰባቸው ሳይንቲስቶቹ እንዲህ ላለው ብናኝ ለረጅም ጊዜ መጋለጥ እስካሁን ገና ያልተደረሰባቸው ሌሎች ጉዳቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። እነዚህ ግኝቶች ለቼርኖበሉ የኑክሊየር ብናኝ የሚጋለጡትን የወደፊቶቹን የአዝርዕት፣ የእንስሳትና የሰው ልጅ ትውልዶች በተመለከተ ልዩ ስጋት ፈጥረዋል።
ወንዶችና ሴቶች የሚያዳምጡበት መንገድ ይለያያል
ተመራማሪዎች ሴቶች ሲያዳምጡ የሚጠቀሙት ሁለቱንም የአንጎላቸውን ከፍል ሆኖ ሳለ ወንዶች ግን አንደኛውን የአንጎላቸውን ክፍል ብቻ እንደሚጠቀሙ ደርሰውበታል ሲል ዲስከቨሪ ኮም ኒውስ ዘግቧል። በጥናቱ ወቅት 20 ወንዶችና 20 ሴቶች በቴፕ ክር የተቀዳ መጽሐፍ እንዲያዳምጡ በማድረግ የአንጎላቸውን እንቅስቃሴ ለመመልከት ተሞክሯል። የአንጎል ምርመራው እንዳረጋገጠው ወንዶች ብዙ ጊዜ የሚያዳምጡት ከንግግርና ከማዳመጥ ጋር ተዛምዶ ያለውን የግራ የአንጎል ክፍል በመጠቀም ነው። በሌላ በኩል ግን በሴቶቹ በሁለቱም የአንጎል ክፍል እንቅስቃሴ እንዳለ ታይቷል። በኢንዲያና የሕክምና ዩኒቨርሲቲ የራዲዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ጆሴፍ ቲ ሉሪቶ እንዲህ ብለዋል:- “ያደረግነው ምርምር ቋንቋዎች በወንዶችና በሴቶች አንጎል ውስጥ የሚብላሉበት መንገድ የተለያየ መሆኑን ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት ግድ የችሎታ ልዩነት አለ ማለት አይደለም።” ዶክተር ሉሪቶ እንዳሉት ሌሎች ጥናቶች ደግሞ ሴቶች “ሁለት ውይይቶችን በአንድ ጊዜ መስማት እንደሚችሉ” ይጠቁማሉ።
ቤት አፈራሽ ሃይማኖት
ፈረንሳይ ውስጥ ሃይማኖት ተቀባይነቱን እያጣ ሄዷል። ላ ቪ በተባለው የካቶሊክ የዜና መጽሔት ድጋፍ የተካሄደው ጥናት ከደረሰባቸው መደምደሚያዎች አንዱ ይህ ነበር። ከ14 ነገሮች መካከል አንደኛ ቦታ የሚሰጡት ነገር ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ለ“መንፈሳዊ ፍላጎት” ቅድሚያ እንደሚሰጡ የገለጹት ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል 7 በመቶ የሚያክሉት ብቻ ናቸው። ከመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ የተሰጣቸው እንደ ነፃ ጊዜ፣ የሙያ ስኬት፣ የግል ነፃነት፣ ባሕላዊ ሕይወት፣ ወሲብ እና ቁሳዊ ብልጽግና ናቸው። እንደ ማኅበራዊ ሕይወት ተመራማሪዎቹ ፒየር ብሬሾን እና ዤራር ሜርሜ አባባል የተሰበሰበው አስተያየት ሃይማኖት ለግለኝነት ተጽዕኖ መሸነፉን የሚጠቁም ነው። በምን መልኩ? ሰዎች “ከእነርሱ ሕይወትና አስተሳሰብ ጋር የሚጣጣም የሚመስላቸውን ነገር በመምረጥ” የተለያዩ እምነቶችን “አንድ ላይ ያጣምራሉ” ሲሉ ብሬሾን ተናግረዋል።
ለአረጋውያን ተጓዦች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
ወደ ታዳጊ አገሮች የሚሄዱት በዕድሜ የገፉ ተጓዦች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በባክቴሪያ የተበከለ ምግብ በመብላታቸው ወይም ውኃ በመጠጣታቸው ምክንያት ብዙዎቹ ይታመማሉ ሲል ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ሄልዝ ኤንድ ኒውትሪሽን ሌተር ገልጿል። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው “የተጓዦች የተቅማጥ ሕመም” ዕድሜያቸው 60 ከዚያም በላይ በሆነ ሰዎች ላይ የከፋ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል። ሄልዝ ኤንድ ኒውትሪሽን ሌተር ትልቅና ዘመናዊ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ንጽሕናው የተጠበቀ ትልቅ ሆቴል ወይም ምግብ ቤት ውስጥ ካልሆናችሁ በቀር የሚከተለውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ ይመክራል:-
□ ለመጠጥም ይሁን ጥርሳችሁን ለመቦረሽ በቧንቧ ውኃ አትጠቀሙ። ታሽጎ የሚሸጥ፣ የፈላ ወይም መድኃኒት የተጨመረበት ውኃ ብቻ ተጠቀሙ። ከንጹሕ ውኃ የተሠራ መሆኑን እርግጠኛ እስካልሆናችሁ ድረስ የምትጠጡት ነገር ውስጥ በረዶ አትጨምሩ።
□ በደንብ ያልበሰለ ዓሣ ወይም ሥጋ አትብሉ።
□ ፓስተራይዝድ ያልሆኑ የወተት ውጤቶችን ወይም ያልበሰሉ አትክልቶችን አትመገቡ።
□ በንጹሕ ውኃ አጥባችሁ ራሳችሁ የላጣችሁት ካልሆነ በቀር ፍራፍሬ አትብሉ። ከላጣችሁት በኋላ ከመብላታችሁ በፊት እጃችሁን ታጠቡ።
□ በመንገድ ዳር የሚሸጥ ምግብ ትኩስ ቢሆንም እንኳ አትብሉ።