ጸሎት ሊረዳኝ የሚችለው እንዴት ነው?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች...
ጸሎት ሊረዳኝ የሚችለው እንዴት ነው?
“ወደ ትክክለኛው መንገድ እንድመለስ የረዳኝ ጸሎት ነው።”—ብራድ። *
ብዙ ወጣቶች ምናልባትም አንተ ከምትገምተው በላይ በተደጋጋሚ ይጸልያሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ከ13 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ወጣቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከእነዚህ ውስጥ 56 በመቶዎቹ እራት ከመብላታቸው በፊት ይጸልያሉ። በወጣቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት 62 በመቶ የሚያክሉት በየቀኑ እንደሚጸልዩ አመልክቷል።
ያም ሆኖ ጸሎት ለብዙዎቹ ወጣቶች እንዲያው ምንም ትርጉም የሌለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ወይም ልማድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ትክክለኛ እውቀት” በማለት የሚናገርለት እውቀት ያላቸው ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው። (ቆላስይስ 1:9, 10 NW ) በዚህም ምክንያት አምላክ በብዙዎቹ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የለውም። አንድ ጥናት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች አስፈላጊ ውሳኔዎች ሲያደርጉ የአምላክን እርዳታ ጠይቀው ያውቁ እንደሆነ ጠይቆ ነበር። አንዲት የ13 ዓመት ልጅ እንዲህ በማለት መልሳለች:- “በሕይወቴ ውስጥ ትክክለኛውን አቅጣጫ ለመምረጥ እንዲረዳኝ ሁልጊዜ ወደ አምላክ እጸልያለሁ።” ሆኖም እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “አሁን ይህ ነው ብዬ የማስታውሰው ውሳኔ ግን የለም።” ስለዚህ ብዙ ወጣቶች ጸሎት ኃይል እንዳለው ወይም ለእነርሱ እንደሚሠራ ሆኖ ባይሰማቸው ምንም አያስደንቅም!
የሆነ ሆኖ ልክ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ብራድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ጸሎት ያለውን ኃይል በግላቸው ቀምሰዋል። ስለዚህ አንተም ጸሎት ያለውን ኃይል መቅመስ ትችላለህ! ቀደም ሲል የወጣው ርዕስ አምላክ ጸሎታችንን እንደሚሰማ እርግጠኛ የምንሆንባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሯል። * አሁን ግን ጥያቄው ጸሎት አንተን ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው የሚል ነው? እስቲ በመጀመሪያ አምላክ ጸሎታችንን የሚመልሰው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።
አምላክ ጸሎትን የሚመልስበት መንገድ
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንዳንድ የእምነት ሰዎች ለጸሎታቸው ቀጥተኛ እንዲያውም ተአምራዊ የሆነ መልስ አግኝተዋል። ለምሳሌ ንጉሥ ሕዝቅያስ ለሞት የሚያደርስ ሕመም እንደያዘው በተገነዘበ ጊዜ አምላክ እንዲያድነው የተማጸነ ሲሆን አምላክም “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፣ እፈውስሃለሁ” የሚል መልስ ሰጥቶታል። (2 ነገሥት 20:1-6) ሌሎች ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶችና ሴቶችም እንዲሁ አምላክ በሕይወታቸው ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ተመልክተዋል።―1 ሳሙኤል 1:1-20፤ ዳንኤል 10:2-12፤ ሥራ 4:24-31፤ 10:1-7
ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም እንኳ ቢሆን መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የተለመደ አልነበረም። አምላክ አብዛኛውን ጊዜ የአገልጋዮቹን ጸሎት የመለሰው ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሳይሆን ‘የፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባቸው’ በማድረግ ነው። (ቆላስይስ 1:9, 10) አዎን፣ አምላክ ሕዝቡ ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን እውቀትና ማስተዋል በመስጠት መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። ክርስቲያኖች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በተጋፈጡበት ወቅት አምላክ ፈተናውን አስወግዶላቸዋል ማለት ባይቻልም ለመጽናት የሚያስችላቸውን “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ሰጥቷቸዋል!―2 ቆሮንቶስ 4:7 NW ፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:17
ዛሬም በተመሳሳይ ጸሎትህ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ላይመለስ ቢችልም አምላክ ቀድሞ እንዳደረገው ሁሉ ቅዱስ መንፈሱን እና የትኛውንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችልህን ጥንካሬ ሊሰጥህ ይችላል። (ገላትያ 5:22, 23) በምሳሌ ለማስረዳት፣ እስቲ ጸሎት ሊረዳህ የሚችልባቸውን አራት ዋና ዋና መንገዶች እንመልከት።
ውሳኔ በማድረግ ረገድ የሚሰጥህ እርዳታ
ካረን ከፍተኛ መንፈሳዊ ግቦች ያሉት ከሚመስል ሰው ጋር ተቀጣጥራ መጫወት ጀመረች። “የጉባኤ ሽማግሌ መሆን እንደሚፈልግ ሁልጊዜ ይነግረኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። ይህ ደግሞ ጥሩ ይመስላል። ሆኖም “አዲስ ስለጀመረው ንግድና ሊገዛልኝ ስለሚችላቸው ነገሮችም ብዙ ያወራ ነበር። በኋላ ላይ ግን የሚነግረኝን መጠራጠር ጀመርኩ።” ካረን ስለ ጉዳዩ ጸለየች። “ይሖዋ ዓይኔን እንዲከፍትልኝና ስለ እርሱ ማወቅ የሚገባኝን ነገር ሁሉ እንዳውቅ እንዲረዳኝ ለመንኩት።”
አንዳንድ ጊዜ መጸለይህ ራሱ የሚያሳስብህን ነገር ቆም ብለህ ከይሖዋ አመለካከት አንጻር እንድታጤነው ስለሚያደርግህ ጥቅም አለው። ሆኖም ካረን ተግባራዊ ምክር ማግኘትም አስፈልጓት ነበር። ተአምራዊ መልስ ታገኝ ይሆን? እስቲ ስለ ንጉሥ ዳዊት የሚናገር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ተመልከት። የሚያምነው ጓደኛው አኪጦፌል ከሃዲ የሆነውን ልጁን አቤሴሎምን እንደመከረበት በተረዳ ጊዜ ዳዊት “አቤቱ፣ የአኪጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጥ እለምንሃለሁ” ሲል ጸለየ። (2 ሳሙኤል 15:31) ሆኖም ዳዊት ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃም ወስዷል። ኩሲ ለተባለ ጓደኛው “የአኪጦፌልን ምክር ከንቱ ታደርግልኛለህ” በማለት ነገረው። (2 ሳሙኤል 15:34) በተመሳሳይም ካረን የወንድ ጓደኛዋን በቅርብ የሚያውቅ አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ሽማግሌ በማነጋገር ከጸሎቷ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወሰደች። ሽማግሌውም የወንድ ጓደኛዋ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ እድገት እንዳላደረገ በመንገር ጥርጣሬዋን አረጋገጠላት።
ካረን እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ይህ ሁኔታ ጸሎት ያለውን ኃይል እንድገነዘብ አድርጎኛል።” የሚያሳዝነው የቀድሞ ጓደኛዋ ብዙም ሳይቆይ ቁሳዊ ሃብት በማሳደድ አምላክን ማገልገሉን አቆመ። “አግብቼው ቢሆን ኖሮ” ትላለች ካረን “ወደ ስብሰባዎች የምመጣው ብቻዬን ይሆን ነበር።” ጸሎት ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድታደርግ ረድቷታል።
ስሜትህን በመቆጣጠር ረገድ የሚሰጥህ እርዳታ
መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 29:11 ላይ “ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል” በማለት ይናገራል። ችግሩ ግን ዛሬ ብዙ ሰዎች ከባድ የስሜት ውጥረት ስላለባቸው አብዛኛውን ጊዜ በቀላሉ ይገነፍላሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ አስከፊ ውጤት ያስከትላል። ወጣቱ ብራያን እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ከአንድ የሥራ ባልደረባዬ ጋር አለመግባባት ነበረኝ። አንድ ቀን ግን ጩቤ አወጣብኝ።” አንተ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር? ብራያን ጸለየ። እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ እንድረጋጋ ረዳኝ። የሥራ ባልደረባዬን ረጋ ባለ መንፈስ በማነጋገር ጩቤውን እንዳይጠቀም ማሳመን ቻልኩ። እርሱም ጩቤውን አስቀምጦ ሄደ።” ብራያን ስሜቱን መቆጣጠሩ በቁጣ ከመገንፈል ያዳነው ሲሆን ሕይወቱንም አትርፎለታል።
ጩቤ አውጥቶ የሚያስፈራራ ሰው ብዙውን ጊዜ ላያጋጥምህ ይችላል። ሆኖም በሕይወትህ ውስጥ ስሜትህን እንድትቆጣጠር የሚያስገድዱ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ጸሎት የተረጋጋ መንፈስ እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል።
ጭንቀትን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል
ባርባራ ከጥቂት ዓመታት በፊት “በአስቸጋሪ ሁኔታ ሥር ያለፈችበትን” ጊዜ በማስታወስ እንዲህ ብላለች:- “ከሥራዬ፣ ከቤተሰቤ እንዲሁም ከጓደኞቼ እርዳታ ለማግኘት ብዙ ጣርኩ። ሆኖም ሊሳካልኝ አልቻለም። ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኝ ነበር።” ባርባራ እንዲያው በደመ ነፍስ እርዳታ ለማግኘት ጸለየች። ሆኖም አንድ ችግር ነበር። “ይሖዋን ምን ብዬ እንደምጠይቀው አላውቅም። በመጨረሻ ግን የአእምሮ ሰላም እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት። በእያንዳንዱ ምሽት ስለ ምንም ነገር እንዳልጨነቅ እንዲረዳኝ እጠይቀው ነበር።”
ባርባራ ጸሎቷ የረዳት እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች:- “ከጥቂት ቀናት በኋላ ችግሮቼ ባይወገዱም ስለ እነርሱ መጨነቄንም ሆነ ማሰቤን እንዳቆምኩ ተገነዘብኩ።” መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ተስፋ ሰጥቷል:- “በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ . . . አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”―ወደ አምላክ እንድትቀርብ ሊረዳህ ይችላል
ጳውሎስ የተባለውን ወጣት ተሞክሮ ተመልከት። “ከዘመዶቼ ጋር ገና መኖር እንደጀመርኩ አንድ ምሽት ላይ በከባድ ጭንቀት ተዋጥኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቅኩት በቅርቡ ስለነበር ጓደኞቼ በሙሉ ናፍቀውኛል። አንድ ላይ ሆነን ያሳለፍናቸውን ጊዜያት ሳስብ እንባዬ መጣ።” ጳውሎስ ምን ማድረግ ይችላል? በሕይወቱ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከልቡ ጸለየ። እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ ጥንካሬና የአእምሮ ሰላም እንዲሰጠኝ ከልቤ ለመንኩት።”
ውጤቱስ ምን ሆነ? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “በሚቀጥለው ቀን ከመኝታዬ ስነሳ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የእፎይታ ስሜት ተሰማኝ። አእምሮን ከሚወጥር ጭንቀት ተላቅቄ ‘አእምሮን ሁሉ የሚያልፈውን የእግዚአብሔር ሰላም’ አገኘሁ።” ጳውሎስ አሁን ልቡ ስለተረጋጋ ነገሮችን እንደ በፊቱ በስሜታዊነት አያይም። ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ‘ጥሩ ነበሩ ያላቸው ወቅቶች’ በእርግጥ ጥሩ እንዳልነበሩ ተገነዘበ። (መክብብ 7:10) እንዲያውም በጣም የናፈቃቸው “ጓደኞቹ” በእርሱ ላይ ጥሩ ተጽእኖ የሚያሳድሩ አልነበሩም።
ከሁሉም በላይ ግን ጳውሎስ የይሖዋን እንክብካቤ በግሉ ማጣጣም ችሏል። “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” የሚሉትን የያዕቆብ 4:8ን ቃላት እውነተኝነት ተገንዝቧል። ይህ ሁኔታ በሕይወቱ ውስጥ ወሳኝ የሆነ አዲስ ምዕራፍ የመጀመር ያክል ነበር። ይሖዋን ከምንም ነገር በላይ ከፍ አድርጎ እንዲመለከተውና ሕይወቱን ለእርሱ እንዲወስን ገፋፍቶታል።
ከአምላክ ጋር ተነጋገር!
እነዚህ አዎንታዊ ተሞክሮዎች ጸሎት በእርግጥ ሊረዳህ እንደሚችል ያሳያሉ። እርግጥ ይህ እውነት የሚሆነው አምላክን የማወቅና ከእርሱ ጋር ዝምድና የመመስረት ልባዊ ፍላጎት ያለህ ከሆነ ብቻ ነው። የሚያሳዝነው ብዙ ወጣቶች እንዲህ ከማድረግ ወደ ኋላ ይላሉ። ካሪሳ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ብትሆንም እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “ከይሖዋ ጋር ያለን ልዩ ዝምድና ያለውን ድንቅ ትርጉም ሙሉ በሙሉ የተገነዘብኩት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይመስለኛል።” በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ብራድ ክርስቲያን ሆኖ ያደገ ወጣት ቢሆንም ለተወሰኑ ዓመታት እውነተኛውን አምልኮ ትቶ ነበር። “ወደ ይሖዋ ዞር ያልኩት ብዙ ነገር እንደቀረብኝ ከተገነዘብኩ በኋላ ነው። እንዲህ ካለው ዝምድና ውጪ ሕይወት ምን ያህል ቀዝቃዛና ባዶ እንደሚሆን አሁን ተገንዝቤአለሁ።”
ሆኖም ወደ አምላክ ለመቅረብ ፈተና እስኪደርስብህ ድረስ መጠበቅ አይኖርብህም። አሁኑኑ ከእርሱ ጋር አዘውትረህ መነጋገር ጀምር! (ሉቃስ 11:9-13) ‘ልብህን በፊቱ አፍስስ።’ (መዝሙር 62:8) እንዲህ ካደረግህ ብዙም ሳይቆይ ጸሎት በእርግጥ ሊረዳህ እንደሚችል ትገነዘባለህ!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.6 “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . አምላክ ጸሎቴን ይሰማልን?” የሚለውን የሐምሌ 2001 ንቁ! ተመልከት።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ጸሎት ሊረዳህ ይችላል
● ለጥሩ ውሳኔ
● በውጥረት ጊዜ ለመረጋጋት
● በጭንቀት ወቅት እፎይታ ለማግኘት
● ወደ አምላክ ለመቅረብ