ለአደጋ የተጋለጠ ትውልድ
ለአደጋ የተጋለጠ ትውልድ
“ከሁለት ወር በፊት ደስተኛና ንቁ ነበርኩ። አሁን ግን አንድ ነገር ለመሥራት ስነሳ ወዲያው ይደክመኛል። ደስታ የራቀኝ ከመሆኑም በላይ በትንሽ በትልቁ እበሳጫለሁ። የእኔን ባሕርይ ችሎ የሚኖር ያለ አይመስለኝም። ጠባዬ እንዲህ በድንገት መቀያየር የጀመረው ለምን እንደሆነ አላውቅም።”—ፖል
“ከባድ የስሜት ሥቃይ ስላለብኝ አለቅሳለሁ። እንዲህ ዓይነት ስሜት በማይሰማኝ ጊዜ ደግሞ በድን የሆንኩ ይመስለኛል። ምንም ነገር አያስደስተኝም። ከጓደኞቼ ጋር መሆን ያስጠላኛል። ብዙ ሰዓት እተኛለሁ። ብዙ ጊዜ ጠዋት ተነስቼ ትምህርት ቤት መሄድ ስለሚያቅተኝ የትምህርት ውጤቴ አሽቆልቁሏል።”—ሜላኒ
የዚህ ችግር ተጠቂዎች ፖል እና ሜላኒ ብቻ አይደሉም። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዩናይትድ ስቴትስ ከሚኖሩት በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 8 በመቶ አካባቢ የሚሆኑት በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃዩ ሲሆን በየዓመቱም 4 በመቶ የሚሆኑት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይይዛቸዋል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት በሕክምና ምርመራ በቀላሉ ስለማይታወቅ ወይም ሙሉ በሙሉ ችላ ስለሚባል እነዚህ አኃዞች ትክክለኛውን እውነታ የሚገልጹ አይደሉም። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሥነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ዴቪድ ጂ ፋስለር “በልጆችና በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የተደረገውን ምርምር ካጠኑ በኋላ ከአራት ወጣቶች መካከል ከአንድ በላይ የሚሆኑት አሥራ ስምንት ዓመት ከመድረሳቸው በፊት የመንፈስ ጭንቀት ይገጥማቸዋል ብዬ አስባለሁ” በማለት ጽፈዋል።
የሚያስከትለው መጥፎ ውጤት
የመንፈስ ጭንቀት በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት
ያስከትላል። እንዲያውም በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የአመጋገብ ልማዳቸው እንዲዛባ፣ ከስነ ልቦና ችግር ጋር በተያያዘ ሕመም እንዲጠቁ፣ ከትምህርት ጋር ግንኙነት ያሏቸው ችግሮች እንዲገጥሟቸውና በሱስ እንዲያዙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠበብት ያምናሉ።በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ራሳቸውን የሚገድሉበት ምክንያት ከመንፈስ ጭንቀት ጋር የተያያዘ መሆኑ ሁኔታውን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ተቋም እንደሚለው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ካደረባቸው ወጣቶች መካከል 7 በመቶ የሚሆኑት ራሳቸውን ይገድላሉ። * ራሳቸውን የሚገድሉ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ ከዚያ የሚበዛ ቁጥር ያላቸው ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን የመግደል ሙከራ የሚያደርጉ በመሆናቸው ይህም አኃዝ ቢሆን የችግሩን መጠን በትክክል አይገልጥም። ካርኔጊ ካውንስል ኦን አዶለሰንት ዲቨለፕመንት የተሰኘው ተቋም እንደሚከተለው ብሎ ለመናገር በቂ ምክንያት ነበረው:- “በዛሬው ጊዜ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ያሉባቸውን ችግሮች ችላ ብሎ ማለፍ አደጋ እንደ መጋበዝ ይቆጠራል። እንዲህ ያለው ቸልተኝነት ትውልድን ለአደጋ ያጋልጣል።”
ምን ሐሳብ አለባቸው?
አንዳንዶች በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የመንፈስ ጭንቀት ይይዛቸዋል ብሎ ማመን ይከብዳቸዋል። ዐዋቂዎች ‘እነርሱ ልጆች አይደሉም እንዴ’ በማለት ሊያስቡ ይችላሉ። ‘ምንም ሐሳብ የለባቸውም፣ እንደ አዋቂዎች የሚያስጨንቃቸው ምንም ነገር የለም።’ አለ እንዴ? እውነታው እንደሚያሳየው ግን ወጣቶች ብዙ ዐዋቂ ሰዎች ከሚገምቱት በላይ በጣም ከባድ የሆኑ ተጽዕኖዎች ይደርሱባቸዋል። ዶክተር ዳንኤል ጎልማን እንዲህ ብለዋል:- “[20ኛው] መቶ ዘመን ከጠባበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም ላይ የተፈራረቀው እያንዳንዱ ትውልድ የኖረው ከወላጆቹ ይበልጥ ከባድ ለሆነ የመንፈስ ጭንቀት እንዲጋለጥ በሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ ነው። ይህ የመንፈስ ጭንቀት እንዲያው የሐዘን ስሜት የሚያሳድር ሳይሆን የሚያሽመደምድ ድካም፣ የመንፈስ ስብራትና ትካዜ እንዲሁም ከባድ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት የሚያስከትል ነው። እንዲህ ዓይነቱ የመንፈስ ጭንቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድሜያቸው አነስተኛ በሆኑ ልጆች ላይ መታየት ጀምሯል።”
ሆኖም ብዙ ወላጆች ‘እኛ በወጣትነታችን የመንፈስ ጭንቀት የሚባል ነገር አናውቅም። ልጃችን መጥፎ በሆኑ ስሜቶች የሚዋጠው ለምንድን ነው?’ በማለት የተቃውሞ ሐሳብ ሊሰነዝሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ዐዋቂ የሆኑ ሰዎች የእነርሱን የወጣትነት ጊዜ ከአሁኖቹ ወጣቶች ጋር ማወዳደር አይኖርባቸውም። ግለሰቦች በዙሪያቸው ያለውን ዓለም የሚመለከቱበትና ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ ይለያያል።
ከዚህም በላይ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የሚፈታተኑ ተጨማሪ ችግሮች አሉ። “የሚኖሩበት ዓለም ወላጆቻቸው ወጣት በነበሩበት ጊዜ ከነበረው ዓለም ፈጽሞ የተለየ ነው” በማለት ዶክተር ካትሊን መኮይ አንደርስታንዲንግ ዩር ቲንኤጀርስ ዲፕረሽን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ጽፈዋል። ዶክተር መኮይ ባለፉት አሥርተ ዓመታት የታዩትን ትልልቅ ለውጦች ከጠቀሱ በኋላ እንዲህ በማለት ደምድመዋል:- “በአሁኑ ጊዜ ያሉት በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ከአንድ ትውልድ በፊት ከነበረው በባሰ ሁኔታ የደህንነት ስሜት አይሰማቸውም፣ ስለ ራሳቸው ያላቸው አመለካከት ዝቅ ያለና ተስፋ የሌላቸው ናቸው።”
በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ ወጣቶች ላይ እያየለ ካለው የመንፈስ ጭንቀት አንጻር የሚቀጥሉት ርዕሶች በሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች ላይ ያተኩራሉ:-
• በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የሚደርሰው የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
• መንሥኤው ምንድን ነው?
• የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸውን በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 በድንገተኛ አደጋ እንደሞቱ ተደርጎ የሚታሰቡ ብዙዎች ራሳቸውን በራሳቸው አጥፍተው ሊሆን ስለሚችል አንዳንድ ጠበብት ትክክለኛው አኃዝ ከዚህ እንደሚበልጥ ያምናሉ።