ምልክቶቹን ለይቶ ማወቅ
ምልክቶቹን ለይቶ ማወቅ
“ሐዘን የተለመደና ጤናማ የሆነ ስሜት ነው። የመንፈስ ጭንቀት ግን በሽታ ነው። ችግሩ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳቱና ማወቁ ላይ ነው።”—ዶክተር ዴቪድ ጂ ፋስለር
እንደ ሌሎቹ በሽታዎች ሁሉ የመንፈስ ጭንቀትም ግልጽ ምልክቶች አሉት። ይሁን እንጂ ምልክቶቹ በቀላሉ ተለይተው የሚታወቁ አይደሉም። ለምን? ምክንያቱም እንደ አዋቂዎች ሁሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሁሉም ወጣቶች ለማለት ይቻላል አልፎ አልፎ በሐዘን ይዋጣሉ። በትካዜና በመንፈስ ጭንቀት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? በአብዛኛው ይህን ለማወቅ የሚረዳው የችግሩ ክብደትና የሚቆይበት ጊዜ ርዝማኔ ነው።
የችግሩ ክብደት የሚለው አነጋገር ወጣቱ አሉታዊ በሆኑ ስሜቶች የሚጠቃበትን መጠን የሚያመለክት ነው። የመንፈስ ጭንቀት ለአጭር ጊዜ ከሚቆይ ሐዘን በከፋ ሁኔታ ወጣቱ የተለመደ እንቅስቃሴውን ማከናወን እንዳይችል አቅሙን ክፉኛ የሚያዳክም በስሜት ላይ የሚደርስ ሕመም ነው። ዶክተር አንድሪው ስሌቢ የበሽታውን ክብደት በዚህ መንገድ ገልጸውታል:- “እስከ አሁን ከደረሰብህ ሁሉ የከፋ ነው የምትለውን ሕመም ለማስታወስ ሞክር። የአጥንት መሰበር፣ የጥርስ ሕመም ወይም ምጥ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አሥር ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ ሕመም ይሰማሃል ሆኖም የሕመሙን መንሥዔ አታውቅም። እንዲህ ብለህ ለማሰብ ብትሞክር የመንፈስ ጭንቀት የሚያስከትለውን ሕመም ከሞላ ጎደል ልትገነዘብ ትችል ይሆናል።”
የጊዜ ርዝማኔው ደግሞ የሚያድርበት አሉታዊ ስሜት አለማቋረጥ የሚቆይበትን ጊዜ የሚያመለክት ነው። የሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ሊዮን ሲትረን እና ዶናልድ ኤች ማክኒው ጁኒየር እንዳሉት “አንድ ልጅ (በሆነ ምክንያት) ትካዜ ውስጥ ከገባ በኋላ ባለው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወይም በጣም የሚወደውን ነገር ካጣ በኋላ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ መጽናናት ወይም የተለመደውን የዕለት ተዕለት ኑሮ ማከናወን ካቃተው ለከባድ የመንፈስ ጭንቀት በእጅጉ የተጋለጠ ይሆናል።”
የተለመዱ ምልክቶች
የመንፈስ ጭንቀት በምርመራ ሊታወቅ የሚችለው በልጁ ላይ ቢያንስ ለሁለት ሳምንት በየቀኑ፣ በአብዛኛው የቀኑ ክፍል የተለያዩ ምልክቶች ከታዩበት ነው። በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ጊዜያዊ የመንፈስ ጭንቀት ሊከሰት ይችላል። ዲስታይሚያ የሚባለው ሥር የሰደደ የመንፈስ ጭንቀት በምርመራ ሊረጋገጥ የሚችለው ምልክቶቹ በመካከሉ ጋብ የሚሉበት ጊዜ ከሁለት ወር ያነሰ ሆኖ ቢያንስ ለአንድ ዓመት የሚዘልቁ ከሆነ ነው። በሁለቱም ዓይነት የመንፈስ ጭንቀቶች ላይ የሚታዩ አንዳንድ የተለመዱ ምልክቶች ምንድን ናቸው? *
በስሜትና በባሕርይ ላይ የሚታይ ድንገተኛ ለውጥ። ቀደም ሲል ገር የነበረ ልጅ በድንገት ተቀይሮ አትንኩኝ ባይ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት የያዛቸው ወጣቶች የዓመፀኝነት ባሕርይ አልፎ ተርፎም ከቤት የመኮብለል ጠባይ ይታይባቸዋል።
ራስን ከሰዎች ማግለል። የመንፈስ ጭንቀት የያዘው ወጣት ከጓደኞቹ ይርቃል። ወይም በሚያሳየው እንግዳ የሆነ ዝንባሌ ወይም ባሕርይ የተነሳ ጓደኞቹ ሊርቁት ይችላሉ።
በምንም ነገር መደሰት አለመቻል። ልጁ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ዝምተኛ ይሆናል። በጣም ይደሰትባቸው የነበሩ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች አሰልቺ ይሆኑበታል።
በአመጋገብ ልማድ ላይ የሚታይ ጉልህ ለውጥ። የምግብ ፍላጎት መጥፋት፣ አሁንም አሁንም የመብላት ፍላጎትና ከጥጋብ በላይ መብላትን የመሳሰሉ ችግሮች ብዙውን ጊዜ ከመንፈስ ጭንቀት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ (ወይም አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት የሚፈጥራቸው) ሁኔታዎች እንደሆኑ ምሁራን ያምናሉ።
የዕንቅልፍ ችግር። ወጣቱ ወይ ጥቂት ሰዓት አለዚያም ረዥም ሰዓት ይተኛል። አንዳንዶች የእንቅልፍ ልማዳቸው ሊዘበራረቅና እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር አድረው ቀኑን ሙሉ ሊተኙ ይችላሉ።
ከትምህርት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮች። የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ወጣት ከአስተማሪዎቹና አብረውት ከሚማሩ ልጆች ጋር መስማማት ያቅተዋል። የትምህርት ውጤቱም ማሽቆልቆል ይጀምራል። ብዙም ሳይቆይ ትምህርት ቤት መሄድ ያስጠላዋል።
ለአደጋ የሚያጋልጥ ወይም በራስ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ድርጊት። ወጣቱ የሚያደርጋቸው ለሕይወት አደገኛ የሆኑ ድርጊቶች በሕይወት ለመኖር ፍላጎት እንደሌለው የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም የራስን አካል መቁረጥ (ሰውነትን እንደ መተልተል ያለ ድርጊት) የበሽታው ምልክት ሊሆን ይችላል።
የከንቱነት ስሜት ወይም አግባብነት የሌለው የጥፋተኝነት ስሜት። እውነታው ሌላ ሆኖ ሳለ ወጣቱ ምንም ነገር በትክክል መሥራት እንደማይችል ሆኖ ሊሰማውና ራሱን ከመጠን በላይ የሚነቅፍ ሊሆን ይችላል።
ከስነ ልቦና ጋር የተያያዙ ችግሮች። ምንም ዓይነት አካላዊ ምክንያት ሳይኖር ራስ ምታት፣ የወገብ ሕመም፣ የሆድ ቁርጠትና እንዲህ ያሉ ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች የሚፈጠሩ ከሆነ የመንፈስ ጭንቀት መኖሩን የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ።
በአእምሮ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጸነስ የመሞት ወይም ራስን የመግደል ሐሳብ። መጥፎ ነገሮችን ማሰብም ሆነ ራስን የመግደል ዛቻ የመንፈስ ጭንቀት መኖሩን ሊያመለክት ይችላል።—ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።
ባይፖላር ዲስኦርደር
ከእነዚህ ምልክቶች መካከል አንዳንዶቹ ባይፖላር ዲስኦርደር የሚባል ሌላ ግራ የሚያጋባ በሽታ መኖሩን ሊጠቁሙ ይችላሉ። ዶክተር ባርብራ ዲ ኢንገርሶል እና ዶክተር ሳም ጎልድስታይን እንዳሉት ባይፖላር ዲስኦርደር (ማኒክ ዲፕረሲቭ ዲስኦርደር ተብሎም ይታወቃል) የተባለው በሽታ “አልፎ አልፎ ከወትሮው በተለየ መንገድ የመቅበጥበጥና
ብርታት የማግኘት ሁኔታ የሚታይበት ከመንፈስ ጭንቀት ጋር የተያያዘ የጤና እክል ነው።”እንዲህ ዓይነቱ የመቅበጥበጥ ሁኔታ ሜኒያ ተብሎ ይታወቃል። ከምልክቶቹ መካከል ሐሳብን መቆጣጠር አለመቻል፣ በጣም ለፍላፊ መሆንና የእንቅልፍ ፍላጎት መቀነስ ይገኙበታል። እንዲያውም ሕመምተኛው ምንም ዓይነት የድካም ምልክት ሳይታይበት ለተወሰኑ ቀናት ሳይተኛ ሊቆይ ይችላል። ሊመጣ የሚችለውን መዘዝ ግምት ውስጥ ያላስገባ የችኩልነት ባሕርይ ሌላው የባይፖላር ዲስኦርደር በሽታ ምልክት ነው። “ብዙውን ጊዜ ሜኒያ አስተሳሰብን፣ የማመዛዘን ችሎታንና ማኅበራዊ ጠባይን ይለውጣል፣ በዚህም ሳቢያ ከባድ ችግር ሊፈጥርና ሃፍረት ላይ ሊጥል ይችላል” በማለት የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ተቋም ገልጿል። ይህ ቅብጥብጥ የሚያደርግ ሁኔታ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል? አንዳንድ ጊዜ ጥቂት ቀናት ብቻ ሊቆይ ይችላል። በሌላ ወቅት ደግሞ ሜኒያ በመንፈስ ጭንቀት ከመተካቱ በፊት ለጥቂት ወራት ሊቆይ ይችላል።
በባይፖላር ዲስኦርደር በሽታ የተያዘ ሰው ያለበት ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰዎች በዚህ በሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። የሚያስደስተው ግን በሽተኞቹ ተስፋ አላቸው። “ቶሎ ብለው ተመርምረው ጥሩ ሕክምና ካገኙ” ይላል ዘ ባይፖላር ቻይልድ የተባለው መጽሐፍ፣ “ልጆቹም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው የተረጋጋ ሕይወት መምራት ይችላሉ።”
አንድ ምልክት ብቻ በራሱ የመንፈስ ጭንቀት ወይም ባይፖላር ዲስኦርደር የተባለው በሽታ መኖሩን የሚያመለክት እንዳልሆነ ማስታወስ ይገባል። ብዙውን ጊዜ የበሽታውን መኖር የሚያመለክቱት በተወሰነ የጊዜ ርዝመት ውስጥ የሚታዩ በርካታ ምልክቶች ናቸው። ይሁንና እንዲህ ያለው ግራ የሚያጋባ በሽታ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችን የሚያጠቃው ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ አሁንም መልስ የሚያሻው ሆኖ እናገኘዋለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 እዚህ ላይ የተጠቀሱት ምልክቶች አጠቃላዩን ሁኔታ ለማሳወቅ እንጂ ሕመሙን መርምሮ ለማወቅ የሚያስችሉ መመዘኛዎች አይደሉም።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ልጃችሁ ሞትን ሲመኝ
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንደተናገረው በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉት ወጣቶች ቁጥር በካንሰር፣ በልብ በሽታ፣ በኤድስ፣ ከውልደት ጀምሮ በሚኖር ችግር፣ በጭንቅላት ውስጥ በሚከሰት የደም መፍሰስ ችግር፣ በሳምባ ምች፣ በኢንፍሉዌንዛና ሥር በሰደደ የሳንባ በሽታ ከሞቱት ወጣቶች አጠቃላይ ቁጥር በልጦ ተገኝቷል። ሌላው አስደንጋጭ እውነታ ደግሞ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ከ10 እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ነው።
ወጣቶች ራሳቸውን እንዳይገድሉ መከላከል ይቻል ይሆን? በአንዳንድ ሁኔታዎች መከላከል ይቻላል። “አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ብዙዎች ራሳቸውን ከመግደላቸው በፊት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል ወይም በቃል ፍንጭ እንዲሁም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል” በማለት ዶክተር ካትሊን መኮይ ጽፈዋል። “ልጃችሁ ራሱን የመግደል ሐሳብ እንዳለው የሚያሳይ ፍንጭ ካገኛችሁ የቅርብ ክትትል ማድረግና ምናልባትም የባለሙያ እርዳታ ለማግኘት መጣር ይኖርባችኋል።”
የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ወላጆችም ሆኑ ሌሎች ዐዋቂ ሰዎች አንድ ወጣት ሕይወቱን የማጥፋት ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ማንኛውም ፍንጭ ካገኙ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያመለክት ነው። “ራሳቸውን በገደሉ ወጣቶች ላይ ካደረግሁት ምርምር እንደተረዳሁት ወጣቱ ራሱን ከመግደሉ በፊት ይህን ድርጊት ለመፈጸም አቅዶ እንደነበር የሚያሳዩ ምልክቶች በሙሉ ችላ ተብለዋል ወይም ያን ያህል አሳሳቢ እንዳልሆኑ ተደርገው ተወስደዋል” በማለት ዶክተር አንድሪው ስሌቢ ኖ ዋን ሶው ማይ ፔይን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ጽፈዋል። “የቤተሰብ አባላትና ወዳጆች በወጣቱ ላይ የሚመለከቱት ለውጥ ክብደት ያለው መሆኑን አይገነዘቡም። ትኩረት የሚያደርጉት በችግሩ ዋነኛ መንሥኤ ላይ ሳይሆን ችግሩ ባስከተለው ውጤት ላይ በመሆኑ ግንዛቤ ውስጥ የሚገባው ነገር ‘ቤተሰብ ውስጥ ችግር መኖሩ’ ወይም ‘ዕፅ የሚወስድ መሆኑ’ ወይም ‘የምግብ ፍላጎት ማጣቱ’ ብቻ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ወጣቱ የሚሰማውን የቁጣ፣ ግራ የመጋባትና የብስጭት ስሜት ለማስወገድ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ሲደረግ ላደረበት የመንፈስ ጭንቀት ግን ምንም ዓይነት ሕክምና ሳያገኝ ይቀራል። ዋነኛው ችግር ውስጥ ውስጡን ሥቃይና ምሬት እያስከተለ ይኖራል።”
መልእክቱ ግልጽ ነው:- ራስን የማጥፋት ዝንባሌ መኖሩን የሚጠቁሙ ፍንጮች ከተመለከታችሁ አፋጣኝ እርምጃ ውሰዱ!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዓመፀኝነት ባሕርይ የመንፈስ ጭንቀት መኖሩን ሊያመለክት ይችላል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ወጣቶች ቀደም ሲል ይደሰቱባቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ያስጠሏቸዋል