አርትራይተስ—የሚያሽመደምድ በሽታ
አርትራይተስ—የሚያሽመደምድ በሽታ
“ደርሶብህ ካላየኸው በስተቀር ሕመሙ ምን ያህል ኃይለኛ እንደሆነ መገመት አትችልም። ከሕመሙ ፋታ ለማግኘት ሞቴን እመኝ ነበር።”—ሴትሱኮ፣ ጃፓን
“ሕመሙ የያዘኝ ገና ከ16 ዓመቴ ጀምሮ ስለነበር የወጣትነት ሕይወቴን መና እንዳስቀረው ይሰማኛል።”—ዳረን፣ ታላቋ ብሪታንያ
“የአልጋ ቁራኛ ሆኜ ስለነበር ከዕድሜ ላይ ሁለት ዓመት ባክኖብኛል።”—ካትያ፣ ኢጣሊያ
“ሕመሙ ከአንጓዎቼ ሲጀምር መላ ሕይወቴ ሕመም ብቻ ይሆናል።”—ጆይስ፣ ደቡብ አፍሪካ
እነዚህ አርትራይተስ በመባል በሚታወቀው በሽታ የተያዙ ሰዎች ያሰሟቸው የምሬት አስተያየቶች ናቸው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአርትራይተስ ምክንያት ካደረባቸው ሕመም፣ መሽመድመድና የቅርጽ መበላሸት ለመገላገል ሐኪሞችን ያማክራሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 42 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በአርትራይተስ የተያዙ ሲሆን ከስድስት በሽተኞች መካከል አንዱ መንቀሳቀስ እስከማይችልበት ደረጃ ይደርሳል። እንዲያውም በዚህች አገር አርትራይተስ ለአካል ጉዳተኝነት ዋነኛው ምክንያት ሆኗል። ይህ ሕመም በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጫና ‘መካከለኛ መጠን ካለው የኢኮኖሚ እድገት መቀነስ እንደማይተናነስ’ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከያ ብሔራዊ ማዕከል ገምቷል። በሕክምና ወጪና በምርታማነት መቀነስ ምክንያት የሚደርሰው ኪሣራ አሜሪካን በየዓመቱ ከ64 ቢልዮን ዶላር በላይ እንደሚያስወጣት ይገመታል። የዓለም ጤና ድርጅት በሰጠው መግለጫ መሠረት እንደ ሕንድ፣ ማሌዢያ፣ ሜክሲኮ፣ ብራዚል፣ ታይላንድ፣ ቺሊ፣ ቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፊሊፒንስና ፓኪስታን ባሉት ታዳጊ አገሮች በተደረጉ ጥናቶች “የአርትራይተስና ሌሎች የቁርጥማት በሽታዎች በእነዚህ አገሮች የሚያሳድሩት ጫና “ከበለጸጉት አገሮች አይተናነስም።”
አርትራይተስ የሚያጠቃው አረጋውያንን ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ምንም መሠረት የለውም።
እርግጥ ሰዎች በዕድሜ እየገፉ በሄዱ መጠን ይበልጥ በበሽታው ይጠቃሉ። ይሁን እንጂ በጣም ተስፋፍተው ከሚገኙ የአርትራይተስ ዓይነቶች አንዱ የሆነው ሩማቶይድ አርትራይተስ በአብዛኛው የሚያጠቃው ከ25 እስከ 50 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙትን ነው። በዩናይትድ ስቴትስ አርትራይተስ ከያዛቸው 5 ሰዎች መካከል ሦስቱ ከ65 ዓመት በታች በሆነ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው። በተመሳሳይም በታላቋ ብሪታንያ በበሽታው ከሚሠቃዩት 8 ሚልዮን ሰዎች መካከል 1.2 ሚልዮን የሚሆኑት ከ45 ዓመት በታች ናቸው። ከ14, 500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ገና ሕፃናት ናቸው።በአርትራይተስ የሚሠቃዩ ሰዎች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መጥቷል። በካናዳ በመጪው አሥር ዓመት ውስጥ በአርትራይተስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአንድ ሚልዮን ይጨምራል። በአውሮፓ የሚገኘው የአርትራይተስ ስርጭት ከአፍሪካም ሆነ ከእስያ የሚበልጥ ቢሆንም በነዚህ አህጉራትም በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መጥቷል። ከአርትራይተስ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው በሽታዎች መስፋፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የዓለም ጤና ድርጅት ከ2000-2010 ያለውን ጊዜ የአጥንትና የአንጓ አሥርተ ዓመት ሲል ሰይሟል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም የሚኖሩ ዶክተሮችና የጤና ባለሞያዎች ጥረታቸውን በማስተባበር በአጥንትና በጡንቻዎች ሕመም የሚሠቃዩ በሽተኞችን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ ይጥራሉ።
ለከፍተኛ ሥቃይ ስለሚዳርገው ስለዚህ በሽታ ምን የታወቀ ነገር አለ? በዚህ በሽታ የመያዝ አጋጣሚ ያላቸው እነማን ናቸው? አርትራይተስ የያዛቸው ሰዎች በበሽታው ምክንያት የሚደርሰውን የአካል መሽመድመድ እንዴት ሊቋቋሙ ይችላሉ? በመጪዎቹ ጊዜያትስ ፈውስ ሊገኝለት ይችል ይሆን? የሚቀጥሉት ርዕሶች በነዚህ ጥያቄዎች ላይ ያተኩራሉ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ የሥዕሎቹ ምንጮች]
ራጂ:- Used by kind permission of the Arthritis Research Campaign, United Kingdom (www.arc.org.uk)