ትምህርት ቤት የማውቀው ሰው ቢያጋጥመኝስ?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ትምህርት ቤት የማውቀው ሰው ቢያጋጥመኝስ?
“ሰኞ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ መከራ ነው። ከጓደኞቼ አንዳቸው አይተውኝ ከነበረ የሆነ ታሪክ ፈጥሬ አወራላቸዋለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ለሌበር ፓርቲው ገንዘብ ስሰበስብ እንደነበር እነግራቸዋለሁ።”—ጄምስ፣ ከእንግሊዝ
“አይተውኝ የነበሩ የትምህርት ቤት ልጆች ሁሉ ያፌዙብኝ ነበር። ተጽዕኖው በጣም ከባድ ነበር።”—ዴቦራ፣ ከብራዚል
እነዚህ ወጣቶች ጓደኞቻቸው እንዳያዩአቸው ያን ያህል የፈሩት ለምን ነበር? በአንድ ዓይነት ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ተካፍለው ስለ ነበር ይሆን? አይደለም። ከዚያ ይልቅ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ከሚሠሩት ሥራዎች ሁሉ የበለጠ ክብር ባለውና በጣም አስፈላጊ በሆነው ሥራ እየተካፈሉ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ያዘዘውን ሥራ እያከናወኑ ነበር:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19, 20
በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙ ልጆች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአምላክ ያምናሉ። ግማሽ የሚያህሉት በየሳምንቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። ብዙዎቹ ወጣቶች በመዘምራን ቡድን ውስጥ ገብተው እንደመዘመር ባሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ቢካፈሉም አብረዋቸው ለሚማሩት ልጆች ስለ አምላክ የሚናገሩት ግን ጥቂቶች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን ከቤት ወደ ቤት በሚያከናውኑት የስብከት እንቅስቃሴ በዓለም ዙሪያ የታወቁ ናቸው። በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ምሥክሮችም በዚህ ሥራ ይካፈላሉ።
አንተም ወጣት ምሥክር ከሆንክ በዚህ ሥራ እየተካፈልክ እንዳለህ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ሲባል ግን በዚህ ሥራ መካፈሉ ቀላል ሆኖ አግኝተኸዋል ማለት አይደለም። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች አንተም ከቤት ወደ ቤት በምትመሠክርበት ጊዜ ትምህርት ቤት የማውቀው ሰው ያጋጥመኝ ይሆን ብለህ ትፈራ ይሆናል። ጄኒ የተባለች አንዲት እንግሊዛዊት ወጣት “ትምህርት ቤት ከሚያውቁኝ በተለየ ሁኔታ ማለትም ረዥም ቀሚስ ለብሼና ጽሑፍ የያዘ ቦርሳ ይዤ አብረውኝ በሚማሩ ልጆች ፊት መታየቱ ከሁሉ የባሰ አሳፋሪ ነገር ነው” ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች።
አንዳንድ ወጣት ክርስቲያኖች አብረዋቸው የሚማሩ ወጣቶች እንዳያገኟቸው በጣም ከመፍራታቸው የተነሳ የሚያመልጡበትን ዘዴ እስከ መፍጠር ደርሰዋል። ሊዮን የተባለ
አንድ ወጣት እንዲህ ይላል:- “የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ካጋጠሙት ፊቱን መሸፈን እንዲችል አገልግሎት ላይ ሲሆን ኮፍያ ያለው ጃኬት የሚለብስ አንድ ወጣት ምሥክር አውቃለሁ።” ሌሎች ወጣቶች ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመስበክ ይቆጠባሉ። “ትምህርት ቤት የማውቃቸው ብዙ ልጆች በሚገኙበት በአንድ የተወሰነ መንገድ ላይ እንዳንሰብክ እጸልይ እንደነበረ አስታውሳለሁ” በማለት ሳይመን የተባለ አንድ ወጣት ተናግሯል።በስብከቱ ሥራ ላይ እያለህ የምታውቀው ሰው እንዳያጋጥምህ በትንሹም ቢሆን መፍራትህ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ይህ ፍርሃት እንዲቆጣጠርህ ከፈቀድክለት ይጎዳሃል። ኦሊሳ የተባለች አንዲት ጀርመናዊ ወጣት “ለስብከቱ ሥራ የነበረኝ መጥፎ አመለካከት በመንፈሳዊነቴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር” ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች።
የስብከቱ ሥራ ይህን ያህል የሚያስጨንቅህ ከሆነ መጀመሪያውኑ ለምን ትሰብካለህ? መልሱን ለማግኘት አምላክ ይህንን ኃላፊነት ለምን እንደሰጠህ እንመልከት። ከዚያም ጥረትና ቆራጥነት ታክሎበት ፍርሃትህን እንዴት ማሸነፍ እንደምትችል እናያለን።
እንድንሰብክ የተጣለብን ግዴታ
በመጀመሪያ ደረጃ፣ እምነትህን ለሌሎች ሰዎች ማካፈልህ አዲስ ወይም በአንተ የተጀመረ ነገር እንዳልሆነ ማወቅህ ሊረዳህ ይችላል። በጥንት ጊዜ የነበሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች እንደዚያ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኖኅ አንድ ግዙፍ መርከብ እንደሠራ በሰፊው ይታወቃል። (ዘፍጥረት 6:14-16) ሆኖም በ2 ጴጥሮስ 2:5 መሠረት ‘የጽድቅ ሰባኪም’ ነበር። ኖኅ እየቀረበ ስለነበረው ጥፋት ሌሎችን የማስጠንቀቅ ግዴታ እንዳለበት ተሰምቶት ነበር።—ማቴዎስ 24:37-39
ከጊዜ በኋላም አይሁዳውያን እንደ እነርሱ አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች እንዲሰብኩ ቀጥተኛ ትእዛዝ ባይሰጣቸውም እንኳ ብዙዎቹ እምነታቸውን ለሌሎች አካፍለዋል። በመሆኑም ሩት የተባለች አንዲት እንግዳ ሴት ስለ ይሖዋ ተምራለች። ሩት አይሁዳዊ ለነበረችው አማቷ አመስጋኝነቷን ስትገልጽ “ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” ብላታለች። (ሩት 1:16) ቆየት ብሎም ንጉሥ ሰሎሞን አይሁዳውያን ያልሆኑ በርካታ ሰዎች የይሖዋን ‘ታላቅ ስም’ ለመስማት እንደሚመጡና በቤተ መቅደሱ እንደሚያመልኩት አመልክቷል።—1 ነገሥት 8:41, 42
እነዚህ የጥንት የአምላክ አገልጋዮች ቀጥተኛ ትእዛዝ ሳይሰጣቸው ለሌሎች ከሰበኩ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ለመስበክ ምንኛ ሊገፋፉ ይገባቸዋል! ደግሞም እኮ እኛ “ይህ[ን] የመንግሥት ወንጌል” እንድንሰብክ ታዝዘናል። (ማቴዎስ 24:14) እኛም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን የምሥራች የመስበክ ግዴታ ተጥሎብናል። (1 ቆሮንቶስ 9:16) መዳናችን የተመካው በዚህ ላይ ነው። ሮሜ 10:9, 10 “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር . . . ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ይላል።
‘በአፍህ የምትመሰክረው’ የት ነው? መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት የራሱ ድርሻ ቢኖረውም ለሌሎች ለመስበክ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው መንገድ ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት ነው። (ሥራ 5:42፤ 20:20) ወጣት መሆንህ በዚህ ሥራ እንዳትካፈል ምክንያት ይሆንሃል? በጭራሽ። መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 148:12, 13 ላይ “ጕልማሶችና ቈነጃጅቶች፣ ሽማግሌዎችና ልጆች፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ” በማለት ይናገራል።
ለእኩዮች መመስከር ያለው ተፈታታኝ ሁኔታ
በአገልግሎት ላይ እያለህ አብሮህ የሚማር ልጅ ቢያጋጥምህ ሊያሳፍርህና ሊረብሽህ እንደሚችል እሙን ነው። ደግሞም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለግ ያለ ነገር ነው። ማፌዣና መሳለቂያ መሆን ወይም መሰደብ የሚፈልግ ማንም የለም። ታንየ የተባለች አንዲት ወጣት እንዳለችው “በትምህርት ቤት ያሉት ልጆች በጣም ክፉ ሊሆኑ ይችላሉ!” በመሆኑም አብረውኝ የሚማሩ ልጆች በደንብ ለብሼና መጽሐፍ ቅዱስ ይዤ ሲያዩኝ ምን ይሉኛል ብለህ ታስብ ይሆናል። ይባስ ብሎም ሊያሾፉብህ ይችላሉ። ፊሊፒ የተባለ ብራዚላዊ ወጣት “እኔ በምኖርበት ሕንፃ ላይ የሚኖር አብሮኝ የሚማር አንድ ልጅ ነበረ” ሲል ያስታውሳል። “‘መጽሐፍ ቅዱስህን ይዘህ ወጣህ ደግሞ! ቦርሳህ ውስጥ ያለው ምንድን ነው?’ ይለኝ ነበር።”
ይህ ዓይነቱ ፌዝ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ግማሽ ወንድሙ ዘፍጥረት 21:9) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን በደል ቀላል እንደሆነ አድርጎ አልተመለከተውም። በገላትያ 4:29 ላይ ሐዋርያው ‘ስደት’ ሲል በትክክል ገልጾታል።
የሆነው እስማኤል ከባድ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ፌዝ እንዳደረሰበት ይነግረናል። (በተመሳሳይም ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች ተከታዮቹን በጥላቻ ዓይን እንደሚመለከቷቸው ተናግሯል። እንዲህ ብሏል:- “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።”—ዮሐንስ 15:18, 19
እንግዲያው ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን በተወሰነ መጠን ስደት እንደሚደርስብህ መጠበቅ ይገባሃል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ለእኩዮችህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባትናገርም እንኳን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎችን ስለምትጠብቅና ከእነሱ ጋር መጥፎ ነገሮችን ስለማትሠራ አንዳንዶች ስደት ሊያደርሱብህ ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 4:4) ሆኖም ኢየሱስ የሚከተሉትን የሚያበረታቱ ቃላት ተናግሯል:- “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW ] ናችሁ።” (ማቴዎስ 5:11) ፌዝና ስድብ እየደረሰብህ ደስተኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? የይሖዋ አምላክን ልብ ደስ እያሰኘህ እንዳለህ ስለምታውቅ ነው! (ምሳሌ 27:11) አምላክን ማስደሰትህ ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያስገኝልሃል!—ሉቃስ 10:25-28
የሚያስደስተው በአገልግሎት ላይ እያለህ የሚያጋጥሙህ የክፍል ጓደኞችህ በሙሉ ወይም ቢያንስ አብዛኞቹ በጥላቻ ስሜት ይመለከቱሃል ማለት አይደለም። አንጀላ የተባለች አንዲት እንግሊዛዊት ወጣት እንዲህ ትለናለች:- “ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል በር ላይ ትምህርት ቤት የምታውቀው አንድ ልጅ ብታገኝ ከአንተ ይልቅ ባብዛኛው የሚረበሸው እርሱ ነው!” እንዲያውም አንዳንዶቹ ምን ልትሉ እንደሆነ ለመስማት ይጓጓሉ። ያም ሆነ ይህ ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች አብረዋቸው ለሚማሩ ልጆች በመመስከር ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። ቀጥሎ የሚወጣው የዚህ ዓምድ ርዕስ አንተም እንዲህ ማድረግ የምትችልባቸውን መንገዶች ያብራራል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ ወጣቶች በአገልግሎት ላይ እያሉ አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች እንዳያጋጥሟቸው ይፈራሉ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፌዝ በእምነትህ እንድታፍር እንዲያደርግህ አትፍቀድ