በዱር እንስሳት ላይ ሰላይ ማቆም
በዱር እንስሳት ላይ ሰላይ ማቆም
የምታደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለማወቅና ለመከታተል እንዲቻል አነስተኛ መጠን ያለው የራዲዮ ማሠራጫ ጀርባህ ላይ እንደተገጠመልህ አድርገህ አስብ። ሚስስ ጊብሰን የሚል ስም በወጣላት አልባትሮስ የተባለች የወፍ ዝርያ ላይ የተደረገው ይህ ነበር። የተደረገላት አነስተኛ የራዲዮ ማሠራጫ ከእርሷም ሆነ ተመሳሳይ መሣሪያ ከተደረገላቸው ሌሎች እንስሳት የሚደርሳቸውን የራዲዮ መልእክት ተቀብለው ወደ ምድር በሚያሠራጩ ሳተላይቶች አማካኝነት ተመራማሪዎችን የቅርብ ክትትልና ጥናት እንዲያካሂዱ አስችሏል። በዚህ መንገድ የተገኙት መረጃዎች አስደናቂ ስለሆኑት ስለ እነዚህ አእዋፍ በጣም አስገራሚ እውቀት አስገኝተዋል። ይህ ደግሞ አእዋፉ ሞተው ከማለቃቸው በፊት ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ዘዴ ሊያስገኝ እንደሚችል ተስፋ ይደረጋል።
በቪክቶሪያ ከተማ በአውስትራሊያ የሚገኘው የላ ትሮብ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ሪፖርት መሠረት ተጓዥ አልባትሮሶች በአማካይ በቀን 300 ኪሎ ሜትር ያህል አንዳንድ ጊዜም ከ1, 000 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚጓዙ ተመራማሪዎች ሊገነዘቡ ችለዋል። እነዚህ በአየር ላይ የሚንሳፈፉ አእዋፍ ክንፋቸው ሲዘረጋ ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ 3 ሜትር ከ40 ሳንቲ ሜትር ስፋት ሲኖረው ይህን ያህል የሚረዝም ክንፍ ያለው አንድም ሌላ የወፍ ዝርያ የለም። እነዚህ አእዋፍ በዚህ ሰፊ ክንፋቸው አየሩን እየቀዘፉ በበርካታ ወራት ጊዜ ውስጥ እስከ 30, 000 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት ይጓዛሉ። በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ ተመሳሳይ ጥናት ላይሳን የተባለችው የአልባትሮስ ዝርያ አንድ ብቻዋን ለተወለደች ጫጩትዋ ምግብ ለማድረስ በሐዋይ ደሴቶች ከምትገኘው ከተርን ደሴት ተነስታ ከሆኖሉሉ ሰሜን ምዕራብ እስከምትገኘው አሉሽያን ደሴት ያለውን የ6, 000 ኪሎ ሜትር የደርሶ መልስ ርቀት አራት ጊዜ እንደተጓዘች ሊታወቅ ችሏል።
እንደነዚህ ያሉት በተራቀቀ ቴክኖሎጂ አጋዥነት የሚካሄዱ ጥናቶች የሴት ተጓዥ አልባትሮሶች ቁጥር ከወንዶቹ ይበልጥ እየተመናመነ የሄደበትንም ምክንያት ሳያሳውቅ አልቀረም። ከበረራ መስመራቸው መረዳት እንደተቻለው ለእርባታ የደረሱ ወንዶች ዓሣ የሚያጠምዱት ከአንታርክቲካ ብዙም ሳይርቁ ሲሆን ሴቶቹ ግን ቀለባቸውን የሚፈልጉት ወደ ሰሜን ርቀው በመሄድ ረዣዥም መረቦች ጥለው ዓሣ የሚያጠምዱ በርካታ ጀልባዎች በሚሰማሩባቸው የውቅያኖስ ክፍሎች ነው። ወፎቹ መረቦቹን አይተው ወደ ባሕር ተወርውረው ሲገቡ በወጥመዶቹ ይያዙና ሰምጠው ይቀራሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ለእርባታ የደረሱ ወንዶች ቁጥር ከሴቶቹ በእጥፍ በልጦ ተገኝቷል። በዚህ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች የአልባትሮስ ዝርያዎችም አሉ። እንዲያውም በአንድ ወቅት በአውስትራሊያና በኒውዚላንድ ባሕሮች በተዘረጉ መረቦች ተይዘው የሰመጡ አእዋፍ ቁጥር በዓመት እስከ 50, 000 ደርሶ ነበር። በዚህ ምክንያት የተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎች ጭራሹን እስከመጥፋት ይደርሱ ይሆናል የሚል ስጋት ተፈጥሮ ነበር። እንዲያውም የተጓዥ አልባትሮስ ዝርያ በአውስትራሊያ ሊጠፋ የተቃረበ የወፍ ዝርያ ተብሎ ነበር። እነዚህ ግኝቶች ሌላ ዓይነት ዓሣ የማጥመድ ዘዴ እንዲቀየስ ያስቻሉ ሲሆን ይህም የሚሞቱትን የተጓዥ አልባትሮሶችን ቁጥር እንዲቀንስ አድርጓል። ይሁን እንጂ ዝርያቸው በርካታ በሆኑ የመራቢያ አካባቢዎች እየቀነሱ መሄዱ አልቀረም።
በአእዋፍ ላይ አምባር ማሠር
ተመራማሪዎች አነስተኛ መጠን ያላቸው የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም በአንዳንድ የአእዋፍ ዝርያዎች ላይ ክትትል ማድረግ ቢችሉም ከፍተኛ ወጪ የማይጠይቁና በጣም ያልተራቀቁ የመከታተያ ዘዴዎች ሥራ ላይ ከዋሉ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። አንደኛው ዘዴ ከፕላስቲክ ወይም ከአነስተኛ የብረታ ብረት ዓይነቶች የተሠራ አምባር መሰል ነገር በወፎቹ እግር ላይ በጥንቃቄ ማሰር ነው።
ስሚዝሶንያን መጽሔት እንዳለው በአእዋፍ ላይ አምባር ማድረግ በማጥኛ መሣሪያነት ማገልገል የጀመረው በ1899 የዳኒሽ የትምህርት ቤት መምህር የነበረው ሃንስ ክርስትያን ሞርተንሰን ራሱ
በሠራቸው የብረት አምባሮች ላይ ስሙንና አድራሻውን ጽፎ 165 በሚያክሉ ወጣት አእዋፍ ላይ ባደረገ ጊዜ ነበር። ባሁኑ ጊዜ በአውሮፓ በአእዋፍ ላይ አምባር ማድረግ በመባል የሚታወቀው ይህ ድርጊት በመላው ዓለም ሥራ ላይ የዋለ የምርምር ዘዴ ሲሆን የአእዋፍን ስርጭትና የጉዞ ልማድ፣ ባሕርይ፣ ማኅበራዊ መዋቅር፣ ብዛት፣ አወላለድና ዕድሜ የሚመለከቱ በጣም ጠቃሚ መረጃዎች ለማሰባሰብ አስችሏል። አደን በሚፈቀድባቸው አገሮች አምባር ማሠር መንግሥታት የሚታደኑ ወፎችን ለመንከባከብ የሚያስችሉ ሕጎችንና ደንቦችን እንዲያወጡ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም አምባር ማሠር አእዋፍ በበሽታዎችና በመርዛማ ኬሚካሎች ምን ያህል እንደሚጎዱ መረጃ ያስገኛል። እንዲያውም አንዳንድ አእዋፍ እንደ ኤንሰፋላይትስ እና ላይም ዲዝዝ ባሉት የሰዎች በሽታዎች ስለሚያዙ ስለ አእዋፍ ሥነ ፍጥረትና ልማድ የሚሰበሰቡት መረጃዎች የእኛንም ጤንነት ለመጠበቅ እገዛ ሊያደርጉ ይችላሉ።አምባር ማሠር ጭካኔ ነውን?
በአእዋፍ ላይ አምባር ማሠር ድርጊቱ በሚከናወንባቸው አገሮች የቅርብ ክትትል ይደረግበታል። አብዛኛውን ጊዜ አምባር የሚያደርጉት ፈቃድ የተሰጣቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። የአውስትራሊያ የተፈጥሮ ጥበቃ መሥሪያ ቤት እንደሚለው በአውስትራሊያ “አምባር አድራጊዎች ወፎቹን እንዴት እንደሚይዙና ከያዟቸውም በኋላ ጉዳት ሳያደርሱባቸው እንዴት አምባሩን ሊያደርጉላቸው እንደሚችሉ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ሥልጠናው አብዛኛውን ጊዜ ሁለት ዓመት የሚፈጅ ሲሆን በጣም ብዙ ልምምድ ማድረግንም ይጠይቃል።” በአውሮፓ፣ በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ሕግ አለ።
የወፎች አምባር በቅርጽ፣ በመጠን፣ በቀለምና ለመሥሪያነት በሚያገለግለው ጥሬ ዕቃ ይለያያል። ብዙዎቹ አምባሮች እንደ አልሙኒዬም ወይም ፕላስቲክ ባሉ ክብደት ከሌላቸው ዕቃዎች ይሠራሉ። ሆኖም ረዥም ዕድሜ ለሚኖሩ አእዋፋት ወይም ጨው ባለበት ባሕር ውስጥ ለሚኖሩት ዓሦች የማይዝጉ ወይም የመልቀቅ ባሕርይ የሌላቸው አምባሮች ጥቅም ላይ ይውላሉ። የመለያ ቀለማት ያሏቸው አምባሮች ወፎቹን ከርቀት ለመለየት ያስችላሉ። ከአንድ የበለጡ አምባሮችን ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም ወፎቹን በመያዝ ማንነታቸውን ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ከሚያስከትልባቸው ውጥረትና ችግር ያድናል።
ተመራማሪዎች በየትኛውም ዓይነት የአምባር ወይም ሌላ ምልክት አደራረግ ቢጠቀሙ ወፎቹን የሚያስቆጣ ወይም ባሕርያቸውን፣ ሥነ ልቦናቸውን፣ ማኅበራዊ ኑሯቸውን፣ ሥነ ምህዳራቸውንና ዕድሜያቸውን የሚጎዳ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ደማቅ ቀለም ያለው ምልክት ማድረግ አንድን ወፍ ጠላቶቹ ዓይን ውስጥ በቀላሉ እንዲገባ ወይም ተጓዳኝ የማግኘት ዕድሉ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል። አንዳንድ የአእዋፍ ዝርያዎች ኩሳቸውን እግራቸው ላይ ስለሚጥሉ አምባር መደረጉ ለኢንፌክሽን ሊያጋልጣቸው ይችላል። በቀዝቃዛ አካባቢዎች በአምባሮቹ ላይ በረዶ ሊጠራቀም ስለሚችል ይህ በተለይ በባሕር ላይ ለሚኖሩ አእዋፍ አደገኛ ሊሆን ይችላል። እነዚህ በአእዋፍ ላይ አምባር በሚደረግበት ጊዜ ጥንቃቄ ከሚደረግላቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው። ቢሆንም የጥናቱ ፕሮግራም ርህራሄ ያልጎደለው ሆኖ የተፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ ስለ አእዋፍ ሥነ ፍጥረትና ባሕርይ ምን ያህል ሳይንሳዊ እውቀት ሊኖር እንደሚገባ ያሳያሉ።
አምባር ወይም ምልክት የተደረገበት ወፍ ብታገኝስ?
አንዳንድ ጊዜ በአምባሮች ወይም በምልክቶች ላይ አድራሻ ወይም የስልክ ቁጥር ስለሚጻፍ ከምልክት አድራጊው ግለሰብ ወይም መሥሪያ ቤት ጋር መገናኘት ትችላለህ። * እንዲሁም ምልክቱ የትና መቼ እንደተገኘ፣ ምናልባትም ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችን ምልክቱን ላደረገው ሰው ማሳወቅ ትችላለህ። ለምሳሌ ዓሣ ከሆነ ባዮሎጂስቱ ዓሣው ምልክት ከተደረገለት ወዲህ ምን ያህል ርቀት በምን ያህል ፍጥነት እንደተጓዘ ማወቅ ይችላል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተመራማሪዎችና ስላገኟቸው አምባሮችና ምልክቶች ተጠንቅቀው መረጃ የሚያቀብሉ በርካታ ሰዎች ምስጋና ይድረሳቸውና ስለ ዱር እንስሳት በጣም አስደናቂ የሆኑ በርካታ መረጃዎች ሊገኙ ችለዋል። ለምሳሌ የሳንድ ፓይፐር ቤተሰብ አባል የሆነውንና ክብደቱ ከ100 እስከ 200 ግራም የሚደርሰውን ሬድ ኖት የተባለ ወፍ እንውሰድ። ባሁኑ ጊዜ ሳይንቲስቶች ሬድ ኖቶች በየዓመቱ ከካናዳ ሰሜናዊ ጫፍ ተነስተው እስከ ደቡብ አሜሪካ ታችኛ ጫፍ ከዚያም ተመልሰው ወደ መጡበት ወደ ካናዳ በጠቅላላው 30, 000 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዙ አውቀዋል!
ያረጀ ቢሆንም ገና ሙሉ ጤና ላይ በሚገኝ አንድ ሬድ ኖት ላይ የታሠረ አምባር ወፉ ይህን ጉዞ ለ15 ዓመታት እንዳደረገ አመልክቷል። አዎን፣ ይህ አነስተኛ መጠን ያለው ወፍ 400, 000 ኪሎ ሜትር የሚያክል ጉዞ ያደረገ ሲሆን ይህ ርቀት በምድርና በጨረቃ መካከል ካለው አማካይ ርቀት ይበልጣል! ስለ ተፈጥሮ በርካታ ጽሑፍ የጻፉት ስኮት ዋይደንሳው ይህችን አስደናቂ ወፍ መዳፋቸው አድርገው እየተመለከቱ “ይህን ሰፊ ዓለም ለሚያገናኙት ለእነዚህ ተጓዦች ባለኝ አክብሮትና አድናቆት ተገፋፍቼ ራሴን በመገረም ከመነቅነቅ ሌላ የማደርገው ነገር የለም” ብለዋል። በእርግጥም በጣም በርካታ ስለሆኑት የምድር ፍጥረታት ባወቅን መጠን “ሰማይንና ምድርን ባሕርንም፣ በእነርሱ ያለውንም ሁሉ” የፈጠረውን አምላክ ይበልጥ እንድናደንቅና እንድናከብር እንገፋፋለን።—መዝሙር 146:5, 6
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.13 አምባሮች ወይም ምልክቶች በጊዜ ብዛት በላያቸው የተጻፈውን ማንበብ እስከሚያስቸግር ድረስ ሊያረጁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሻጋታውን ወይም ዝገቱን የሚያስወግድ ኬሚካል በመጠቀም አብዛኛውን ጊዜ ለመለየት አስቸጋሪ ሆኖ የነበረውን ጽሑፍ ማንበብ ይቻላል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የአእዋፍ አምባር ማንበቢያ ቤተ ሙከራ በየዓመቱ በመቶ የሚቆጠሩ አምባሮችን ያነብባል።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ምልክትና ክትትል የማድረጊያ ዘዴዎች
ከአእዋፍ በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ፍጥረታት ለምርምርና ጥናት ዓላማ ምልክት ይደረግባቸዋል። ምልክት የማድረጊያ ዘዴዎቹ ዓይነት ሊገኝ በተፈለገው ሳይንሳዊ ግብና በእንስሳቱ ባሕርያትና ልማዶች ላይ የተመካ ነው። ተመራማሪዎች ከእግር አምባሮች በተጨማሪ በባንዲራዎች፣ በተንጠልጣይ ጨርቆች፣ በአርማዎች፣ በቀለሞች፣ በንቅሳት ጽሑፎች፣ በመተኮስ የሚደረግ ምልክት፣ በአንገት ላይ ማሠሪያዎች፣ በራዲዮ መከታተያ መሣሪያዎች፣ ረቂቅ በሆኑ ኮምፒውተሮችና ከማይዝግ ብረት በተሠሩ ቀስቶች (የመለያ ጽሑፍ ተደርጎባቸው) ይጠቀማሉ። በተጨማሪም ጣት፣ ጆሮ፣ ጅራት በመብሳት ወይም በመቁረጥ፣ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ዘዴዎችና መሣሪያዎች ይገለገላሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ የሲሎችን ወደ ባሕር የመጥለቅ ልማድ ለመከታተል እንደተገጠመው ምስል መቅረጫ ያለውና 15, 000 ዶላር ወጪ የጠየቀ አነስተኛ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ በጣም ውድ ሊሆኑ ይችላሉ።
ፓሲቭ ኢንተግሬትድ ትራንስፖርተር የተባለው የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሕመም እንዳይሰማው በደነዘዘ የእንስሳ ቆዳ ውስጥ ወይም አካል ውስጥ ተቀብሮ ከቆየ በኋላ ወጥቶ በልዩ መሣሪያ ሊነበብ ይችላል። ሳይንቲስቶች ብሉፊን ቱና የተባለውን የዓሣ ዘር ለማጥናት አርካይቫል ታግ ወይም ስማርት ታግ የተባለውን አነስተኛ ኮምፒውተር በዓሣው አካል ውስጥ ቀብረዋል። እነዚህ ጥቃቅን የኮምፒውተር ቅንጣቶች እስከ ዘጠኝ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ሙቀትን፣ ጥልቀትን፣ የብርሃን መጠንንና ጊዜን የሚመለከቱ መረጃዎችን ሲሰበስቡና ሲያከማቹ ቆይተዋል። እነዚህ የመከታተያ መሣሪያዎች በሚመለሱበት ጊዜ የብርሃን መጠኖችንና ጊዜን የሚመለከቱ መረጃዎችን በማመሳከር የሚገኘውን የዓሣ ጉዞ ጨምሮ በርካታ ሌሎች መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል።
በእባቦች ላይ አንዳንድ ቅርፊቶች ቀርፎ በማንሳት፣ ኤሊዎችን ድንጋያቸው ላይ ቀዳዳ በማበጀት፣ እንሽላሊቶችን ጣታቸውን ቆረጥ በማድረግ፣ አዞዎችን ጣታቸውን በመቁረጥ ወይም ጅራታቸው ላይ ያሉትን ቅርፊቶች በማንሳት ምልክት ማድረግ ይቻላል። አንዳንድ እንስሳት ተለይተው የሚታወቁባቸው የተፈጥሮ መልክ ስላላቸው ፎቶግራፍ በማስተያየት ብቻ ማንነታቸውን መለየት ይቻላል።
[ሥዕሎች]
በጥቁር ድብ ላይ የጆሮ ምልክት፣ በዳምሰል ዓሣ ላይ የስፓጌቲ ምልክት፣ በአዞዎች ላይ የጅራት ምልክት ማድረግ
የሳተላይት ማሠራጫ የተደረገለት ፔሬግኒን አሞራ
በአካሉ ውስጥ መለኪያ መሣሪያ የገባለት ባለቀስተ ደመና ዓሣ
[ምንጮች]
ድብ:- © Glenn Oliver/Visuals Unlimited; ዳምሰል ዓሣ:- Dr. James P. McVey, NOAA Sea Grant Program; አዞ:- Copyright © 2001 by Kent A. Vliet; ገጽ 2 እና ገጽ 19 ላይ ያለው አሞራ:- Photo by National Park Service; ዓሣ የያዙ ሰዎች:- © Bill Banaszewski/Visuals Unlimited
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በባለ ሹል አፉ ጭልፊት ላይ አምባር ማድረግ
[ምንጭ]
© Jane McAlonan/Visuals Unlimited