ከሚገመተው በላይ ውስብስብ የሆነ
ከሚገመተው በላይ ውስብስብ የሆነ
የኬሚካዊ ዝግመተ ለውጥ (chemical evolution) ንድፈ ሐሳብ ሕይወት ከብዙ ቢልዮን ዓመታት በፊት ድንገት በተከሰተ ኬሚካዊ አፀግብሮት አማካኝነት እንደተገኘ ይገልጻል።
ይህ ንድፈ ሐሳብ ወፎችም ሆኑ ገበሎ አስተኔዎች (reptiles) አሊያም ሌሎች ውስብስብ ፍጥረታት በቀጥታ የተገኙት ሕይወት አልባ ከሆነ ንጥረ ነገር ነው አይልም። ከዚህ ይልቅ ዋቅላሚና (algae) ነጠላ ሕዋስ ዘአካላትን የመሳሰሉት ውስብስብ ያልሆኑ ፍጥረታት የተገኙት በተከታታይ በተደረጉ ድንገተኛ ኬሚካዊ አፀግብሮቶች አማካኝነት እንደሆነ ይገልጻል።
በአሁኑ ጊዜ ስለእነዚህ ነጠላ ሕዋስ ዘአካላት ከሚታወቀው ነገር አንጻር ውስብስብ እንዳልሆኑና በድንገት ሊገኙ እንደሚችሉ አድርጎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነውን? ለምሳሌ ውስብስብ አይደሉም የሚባሉት ነጠላ ሕዋስ ዋቅላሚዎች ውስብስብ ያልሆኑት እስከ ምን ድረስ ነው? እስቲ አንዱን ዓይነት ዝርያ እንመርምር። ይህ ነጠላ ሕዋስ ዋቅላሚ በቮልቮኬልስ ክፍለ መደብ የዱናሊየላ ዝርያ የሆነው አረንጓዴ ዋቅላሚ ነው።
በዓይነታቸው ልዩ የሆኑት ነጠላ ሕዋስ ዘአካላት
የዱናሊየላ ሕዋሳት የእንቁላል ዓይነት ቅርጽ ያላቸውና በጣም ጥቃቅን ሲሆኑ ርዝማኔያቸው ወደ 10 ማይክሮን አካባቢ ይደርሳል። የአንድ ሴንቲ ሜትር ርዝማኔ እንዲኖራቸው ለማድረግ ወደ 2, 500 የሚጠጉ የዱናሊየላ ሕዋሳትን መቀጣጠል ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ሕዋስ ጫፉ ላይ ለመዋኘት የሚያስችሉት ሁለት ጭራ መሰል ልምጭቶች (flagella) አሉት። እንደ ዕፅዋት ሁሉ የዱናሊየላ ሕዋሳትም ኃይል የሚያመነጩት በብርሃን አስተጻምሮ (photosynthesis) አማካኝነት ነው። ሕዋሳቱ ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ማዕድናትና ወደ ሕዋሱ ሰርገው የሚገቡ ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ተጠቅመው ምግብ ያዘጋጃሉ። ዱናሊየላ የሚባዛው በክፋሌ ሕዋስ (cell division) ነው።
ዱናሊየላ ከፍተኛ የጨው መጠን ባለበት ውኃ ውስጥ ሳይቀር መኖር ይችላል። የዱናሊየላ ሕዋስ ከባሕር ውኃ ስምንት ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ የጨው ክምችት ባለው የሙት ባሕር ውስጥ መኖርና መራባት ከሚችሉት በጣም ጥቂት ዘአካላት መካከል አንዱ ነው። በተጨማሪም ውስብስብ አይደለም የሚባለው ይህ ነጠላ ሕዋስ ዘአካል በአካባቢው የጨው ክምችት ላይ ድንገተኛ ለውጥ ቢከሰትም ራሱን ከሁኔታው ጋር ማስማማት ይችላል።
ለምሳሌ ያህል በሲና በረሃ ጨዋማ ረግረግ ላይ የሚገኘውን የዱናሊየላ ባርዳዊል ዝርያ ተመልከት። ነጎድጓዳማ ውሽንፍር በእነዚህ ረግረጋማ ቦታዎች ላይ ያለውን ውኃ በፍጥነት ሊያቀጥነው ይችላል። ወይም ደግሞ ኃይለኛው የበረሃ ሙቀት ውኃውን ሊያተንነውና የጨዉ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። በጣም አነስተኛ የሆነው ይህ ዋቅላሚ በቂ መጠን ያለው ግሊስሮል ማመንጨትና ማከማቸት ስለሚችል እንደነዚህ ያሉትን ከባድ ለውጦች መቋቋም ይችላል። ዱናሊየላ ባርዳዊል የጨዉ ክምችት መለወጥ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እንደ አስፈላጊነቱ ራሱን ከሁኔታዎች ጋር ለማስማማት አንድም ተጨማሪ ግሊስሮል በማምረት አሊያም ያለውን በማስወገድ ግሊስሮሉን በፍጥነት የማስተጻመር ችሎታ አለው። በአንዳንድ አካባቢዎች የጨዉ ክምችት በሰዓታት ውስጥ ሊለወጥ ስለሚችል ይህ በጣም አስፈላጊ ነው።
በጨዋማ ረግረግ ላይ የሚኖረው ዱናሊየላ ባርዳዊል ለከፍተኛ የፀሐይ ሙቀት የተጋለጠ ነው። በሕዋሱ ውስጥ የሚገኘው ማቅለሚያ፣ መካች መጋረጃ ባያዘጋጅ
ኖሮ ሙቀቱ ሕዋሱን ይጎዳው ነበር። የዱናሊየላ ሕዋስ ምቹ ሁኔታ ማለትም ብዙ ናይትሮጂን ሲያገኝ መካች መጋረጃ ከሚያዘጋጀው ማቅለሚያ ወይም ክሎሮፊል የተነሣ ደማቅ አረንጓዴ ቀለም ይኖረዋል። የናይትሮጂን እጥረት ሲኖርና ሕዋሱ ለከፍተኛ የጨው፣ የሙቀትና የብርሃን መጠን ሲጋለጥ ደግሞ ብርቱካንማ ወይም ቀይ ቀለም ይኖረዋል። ለምን? እንዲህ በመሰለው አስቸጋሪ ሁኔታ ሥር በሕዋሱ ውስጥ ውስብስብ የሆነ ሕየወ ኬሚካላዊ (biochemical) ለውጥ ይካሄዳል። የክሎሮፊሉ መጠን ዝቅ ይልና በፋንታው ቤታ ካሮቲን የተባለ ሌላ አማራጭ አቅላሚ ይመረታል። ሕዋሱ ይህንን አቅላሚ የመሥራት ልዩ ችሎታ ባይኖረው ኖሮ ይሞት ነበር። በሕዋሱ ውስጥ የዋቅላሚውን ደረቅ ክብደት እስከ 10 በመቶ የሚሸፍን ከፍተኛ መጠን ያለው ቤታ ካሮቲን መኖሩ ለቀለሙ መለወጥ አስተዋጽኦ ያደርጋል።በዩናይትድ ስቴትስና በአውስትራሊያ ቤታ ካሮቲን የተባለውን ለሰው ልጅ አካል የሚጠቅም ንጥረ ነገር ለማግኘት ሲባል ዱናሊየላን በትላልቅ ኩሬዎች ውስጥ የማምረት የንግድ እንቅስቃሴ ሲካሄድ ቆይቷል። ለምሳሌ በደቡባዊና በምዕራባዊ አውስትራሊያ ውስጥ ትልልቅ የማምረቻ ቦታዎች አሉ። ቤታ ካሮቲንን ሰው ሠራሽ በሆነ መንገድ ማምረትም ይቻላል። ይሁን እንጂ ከፍተኛ የቤታ ካሮቲን ምርት ሊያስገኙ የሚችሉ፣ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁና የተራቀቁ ተቋሞች ያሏቸው ሁለት ኩባንያዎች ብቻ ናቸው። የሰው ልጆች በርካታ ዓመታት የወሰደባቸውንና ለምርምር፣ ለእድገትና ለማምረቻ ተቋሞች ግንባታ የሚሆን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የጠየቀባቸውን ነገር ዱናሊየላ በጣም በቀላሉ ይሠራዋል። ውስብስብ አይደለም የሚባለው ይህ ዋቅላሚ በዙሪያው ለሚፈጠሩት ለውጦች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ይህንን ሥራ በዓይን ለማየት በሚያስቸግር አነስተኛ ፋብሪካው ውስጥ ያከናውነዋል።
ሌላው የዱናሊየላ ልዩ ችሎታ በ1963 ለመጀመሪያ ጊዜ በተፈጥሮ በሚገኙ የሰልፈር አሲድ ምንጮችና አፈሮች ውስጥ እንደሚገኝ በታወቀው የዱናሊየላ አሲዶፊላ ዝርያ ላይ ተንጸባርቋል። እነዚህ ቦታዎች ተለይተው የሚታወቁት በከፍተኛ የሰልፈሪክ አሲድ ክምችታቸው ሲሆን የላቦራቶሪ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ የዱናሊየላ ዝርያ ከሎሚ ጭማቂ 100 ጊዜ የሚበልጥ አሲድነት ባለው የሰልፈሪክ አሲድ ውሁድ ውስጥ መኖር ይችላል። በሌላው በኩል ደግሞ ዱናሊየላ ባርዳዊል ከፍተኛ የአልካሊን ክምችት ባለው አካባቢ መኖር ይችላል። ይህም ዱናሊየላ ያለውን ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር የመላመድ ከፍተኛ ችሎታ ያሳያል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦች
ዱናሊየላ ያሉት ችሎታዎች እጅግ አስገራሚ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ የተዘረዘሩት ነጥቦች ነጠላ ሕዋስ ዘአካላት በዙሪያቸው የሚፈጠሩትን የተለያዩና አንዳንዴም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች ለመቋቋምና በሕልውና ለመቆየት በሚያደርጉት ጥረት ከሚያሳዩአቸው በርካታ አስደናቂ ችሎታዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። እነዚህ ችሎታዎች ዱናሊየላ ለእድገት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት፣ ምግብ ለመምረጥ፣ ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ላለመውሰድ፣ ቆሻሻን ለማስወገድ፣ በሽታን ለመከላከልና ለመቋቋም፣ ከአዳኞች ለማምለጥ፣ ለመራባትና እነዚህን የመሳሰሉትን ነገሮች ለማከናወን ያስችሉታል። የሰው ልጅ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ወደ 100 ትሪሊዮን የሚጠጉ ሕዋሳት ይጠቀማል!
ታዲያ ይህ ነጠላ ሕዋስ ዋቅላሚ በኦርጋኒክ ሱፕ ውስጥ ካሉ ጥቂት አሚኖ አሲዶች በአጋጣሚ የተገኘና ያልተወሳሰበ የሕይወት ጅምር ነው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይሆናልን? እነዚህ ድንቅ የተፈጥሮ ውጤቶች ድንገት የተገኙ ናቸው ማለቱስ ተገቢ ነው? ከዚህ ይልቅ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ወደ ሕልውና ያመጣው ሕይወትን በዓላማ የፈጠረው ድንቅ ንድፍ አውጪ ነው ማለቱ ምንኛ ምክንያታዊ ነው! ሕይወት ያላቸው ነገሮች ተፈጥሮ ይህን ያህል ውስብስብና እርስ በርሱ የሚደጋገፍ ሊሆን የቻለው ከዚህ በስተጀርባ ከእኛ የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነ ታላቅ ማስተዋልና ጥበብ በመኖሩ ነው።
ሃይማኖታዊም ሆነ ሳይንሳዊ ቀኖና ተጽእኖ እንዲያሳድርብን ሳንፈቅድ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናታችን የሕይወትን አመጣጥ በተመለከተ ለሚነሱት ጥያቄዎች አርኪና አጥጋቢ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል። ከፍተኛ የሳይንስ እውቀት ያካበቱ በርካታ ሰዎችን ጨምሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ያለውን ምርምር በማድረግ ሕይወታቸው እንዲበለጽግ አድርገዋል። *
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.15 አንባቢዎቻችን ሕይወት እንዴት ተገኘ ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት ? የሚለውንና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? የተባሉትን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ መጻሕፍት (እንግሊዝኛ) እንዲመረምሩ እናበረታታቸዋለን።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስተ ግራ ጥግ:- “ዱናሊየላን” ተጠቅሞ ቤታ ካሮቲንን የማምረት የንግድ እንቅስቃሴ
በስተ ግራ፦ብዙ ቤታ ካሮቲን የያዘ ብርቱካንማ የ“ዱናሊየላ” ሕዋስ በአጉሊ መነጽር ሲታይ
[ምንጭ]
© AquaCarotene Limited (www.aquacarotene.com)
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዱናሊየላ
[ምንጭ]
© F. J. Post/Visuals Unlimited
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኑክሊየስን (ኑ)፣ ክሎሮፕላስትን (ክ) እና ጎልጂን (ጎ) የሚያሳይ የኤሌክትሮን ማይክሮስኮፕ ምስል
[ምንጭ]
Image from www.cimc.cornell.edu/Pages/ dunaLTSEM.htm. Used with permission