በተፈጥሯዊ ዘዴዎች አትክልት ማልማት
በተፈጥሯዊ ዘዴዎች አትክልት ማልማት
እስቲ ከአትክልት ቦታህ አንድ ጭብጥ አፈር ዘገን አድርገህ ተመልከት። በፀረ አረም፣ ፀረ ተባይና ፀረ ነፍሳት መድኃኒቶች የራሰ በመሆኑ ምንም ዓይነት ሕይወት ያለው ነገር የማይታይበት ነው? ወይስ ብዙ ዓይነት ትላትሎችና ጥቃቅን ነፍሳት የሚርመሰመሱበት? ሕይወት ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳት የሚርመሰመሱበት ከሆነ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ እያለማህ ነው ማለት ነው።
አትክልት በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች ማልማት ሲባል አብዛኛውን ጊዜ ከተፈጥሮ በሚገኙ ነገሮች የአፈሩን ለምነት ማሻሻል ማለት ነው። ከዓላማዎቹ አንዱ ተክሎች ተባዮችንና በሽታዎችን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ጥንካሬ የሚያስገኝ አካባቢ መፍጠር ነው። ሰው ሠራሽ ኬሚካሎችን በመጠቀም አትክልቶችን ማልማት የተለመደ በሆነባቸው አገሮች በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች የመጠቀም ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። ለምን ቢባል በርካታ ምክንያቶች አሉ።
አንደኛ ነገር በፍራፍሬዎችና በአትክልቶች ላይ የሚቀሩ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ከባድ የጤና ችግር ያስከተሉባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ “በ1985 የበጋ ወራት [በዩናይትድ ስቴትስ] በርካታ ምዕራባዊ ግዛቶችና በካናዳ የሚኖሩ ወደ 1, 000 የሚጠጉ ሰዎች ቴሚክ የተባለ ፀረ ተባይ መድኃኒት የተረጨ ከርቡሽ በመብላታቸው ተመርዘዋል” ሲል ፔስቲሳይድ አለርት የተባለው መጽሐፍ ዘግቧል።
በተጨማሪም ብዙ ሰዎች አትክልቶችን በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች ማልማት በአካባቢ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ይከላከላል ብለው ያስባሉ። አንዳንድ ተባዮች በተደጋጋሚ ከተረጩባቸው መድኃኒቶች ጋር በመላመዳቸው ሳይንቲስቶች ይበልጥ አደገኛ የሆኑ መርዞችን ለመሥራት ተገድደዋል። እነዚህ ኃይለኛ መርዞች መሬት ውስጥ ወዳለው ውኃ ሰርገው በመግባት ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውለውን ውኃ ይበክሉታል።
በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች ተክሎችን ማልማት የሚያስገኘው ሌላ ጥቅም በቆሻሻ መድፊያ ቦታዎች የሚጣለውን ቆሻሻ መጠን መቀነሱ ነው። እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ቆሻሻዎቻችን በአብዛኛው የምግብ ትርፍራፊዎችና የግቢ ጥራጊዎች ናቸው። እነዚህ ጥራጊዎች ተሰብስበው ከሚጣሉ ይልቅ በአንድ ቦታ ተጠራቅመው እንዲበሰብሱ ቢደረግ ጥሩ ማዳበሪያ ሆኖ የሚያገለግል ብስባሽ ያስገኛሉ። እንዲህ ስላለው ብስባሽ ማሰብ ለእኛ የሚያስጠላ ይሁን እንጂ ለተክሎች ግን ምርጥ ምግብ ነው!
በመጨረሻም አንዳንዶች በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች በመጠቀም አትክልት ማልማት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ፣ ፀሐይ ለመሞቅ፣ ለመቆፈርና ለመኮትኮት እንዲሁም ተክሎች ከጥቃቅን ዘሮች ተነስተው ጤናማ ተክሎች እስኪሆኑ እድገታቸውን ለመከታተል የሚያስችል አጋጣሚ የሚፈጥርላቸው በመሆኑ ይወዱታል። ታዲያ በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች በመጠቀም አትክልት ማልማት የሚወደድ ሆኖ አገኘኸው? ከሆነ እስቲ አሁን እንጀምር። በመጀመሪያ በአትክልት ቦታህ ያለውን አፈር እንመለከታለን።
ተክሎችህ የሚያድጉት እንዴት ነው?
በብዙ የአትክልት ቦታዎች ያለው አፈር ሸክላማ ወይም አሸዋማ አፈር ነው። በአሸዋማ አፈር ውስጥ ያሉት የአፈር ቅንጣቶች ትላልቅ በመሆናቸው ውሃና ንጥረ ምግብ በፍጥነት እንዲሰርግ ስለሚያደርጉ ሥሮች በቂ ምግብና ውሃ እንዲያገኙ ይረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ሸክላማ አፈር በጣም ተጠጋግተው በታመቁ ጥቃቅን የአፈር ቅንጣቶች የተገነባ ስለሆነ ውሃው ወደ ታች ለመስረግ ስለማይችል ላይ ላዩን ፈስሶ ያልፋል ወይም በአንድ ቦታ ታቁሮ የተክሎቹ ሥር እንዲታፈን ያደርጋል።
የተክሎች ሥሮች ተመችቷቸው የሚያድጉት የአፈሩ ቅንጣቶች በቂ እርጥበት ይዘው ለማቆየትና እርጥበቱ በሚበዛበት ጊዜ ትርፍ የሆነውን ውኃ አሳልፈው ለመስደድ በሚችሉበት ጊዜ ነው። አትክልተኞች እንዲህ ያለውን አፈር ለም አፈር ይሉታል። እንዲህ ባለው አፈር ውስጥ አየር እንደልብ ስለሚተላለፍ የአፈሩን ለምነት የሚጨምሩ ጥቃቅን ነፍሳት ተግባራቸውን ማከናወን ይችላሉ።
አፈሩ አሸዋማም ሆነ ሸክላማ ትክክለኛውን ሚዛን የጠበቀ እንዲሆን ብዙ ብስባሽ መጨመር ያስፈልጋል። ብስባሽ ወደ አፈር በሚጨመርበት ጊዜ የአፈሩ ባሕርይ ይለወጣል።
ብስባሽ እንደ ስፖንጅ ውሃ መጥጦ የመያዝ ባሕርይ ስላለው ብዙ ውሃ ማጠጣት አስፈላጊ አይሆንም። በብስባሽ ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ባክቴሪያዎች በመበስበስ ላይ የሚገኘውን ነገር ለእጽዋት እድገት አስፈላጊ ወደሆነ ምግብነት ይለውጡታል። በተጨማሪም ብስባሽ አፈሩ በጣም ኮምጣጣ፣ በጣምም ጨዋማ እንዳይሆን ይረዳል።ረጃጅም ሥሮች ያሏቸው እንደ አልፋልፋና ማገጥ የመሰሉት ተክሎች በሚተከሉበት ጊዜ ጠንካራ አፈሮችን በማለስለስ
ለምነታቸው እንዲጨምር ያደርጋሉ። እንደ ሣርና ቅጠላ ቅጠል ያሉትን አፈር ላይ መጎዝጎዝም የአፈሩ ይዘት እንዲሻሻል ስለሚረዳ ጠቃሚነት አለው።አስደናቂ የሆነው የአፈር ትል የአትክልት ቦታህን ለምነት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። በመሬት ውስጥ እስከ 4 ሜትር ድረስ ቦርቡሮ ስለሚገባ አፈሩን ከማናፈስ በተጨማሪ የተለያዩ ማዕድናት ከውስጥ ወደ ውጭ ያወጣል፣ ውሃም ከላይ እንዳይታቆር ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ስቴፕ ባይ ስቴፕ ኦርጋኒክ ቨጅተብል ጋርደኒንግ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “በአካባቢው ከሚገኘው አፈር በናይትሮጅን፣ በፎስፎረስና በፖታሲየም አምስት እጥፍ የበለጸገ ፍግ ይጥላል።”
ጉርጦች፣ ወፎችና ትናንሽ ነፍሳት —የአትክልትህ ወዳጆች
‘ተባዮችንስ ምን ማድረግ ይቻላል? በፀረ ተባይ መድኃኒት ካልተጠቀምኩ እንዴት ላስወግዳቸው እችላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ፀረ ተባይ መድኃኒቶች የሚገድሉት የማይፈለጉ ተባዮችን ብቻ እንዳልሆነ አትዘንጋ። የአፈር ትሎችንና ፈንገሶችን የመሰሉትን ጠቃሚ ነፍሳት ጭምር ያስወግዳሉ። በተጨማሪም ጉርጦች ለአትክልት ጠቃሚ መሆናቸውን አስታውስ። አንድ ጉርጥ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ10, 000 የሚበልጡ ነፍሳት መብላት ይችላል። ጉርጦች ምግብ መራጮች አይደሉም። እንደ እንጭራሪት ያሉትን የአትክልት ጠላት የሆኑ የተለያዩ ነፍሳትንና ትላትሎችን ይበላሉ።
በተጨማሪም ወፎች ተባዮችን በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ጋርደኒንግ ዊዝአውት ፖይዝንስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው አንዲት ድንቢጥ “በግማሽ ቀን 500 ሸረሪቶችንና አባጨጓሬዎችን ለልጆቿ” እንደመገበች ተስተውሏል። ጥቂት ድንቢጦችን ወይም ትናንሽ ነፍሳትን የሚመገቡ ሌሎች ወፎችን ወደ አትክልት ቦታህ መሳብ ከፈለግህ በግልጽ ሊታይ በሚችል ቦታ ላይ ጥቂት ምግብ ወይም ለወፍ ጎጆ መስሪያ የሚያገለግል ነገር ስቀል። በጥቂት ጊዜ ውስጥ “ግብዣህ” ተቀባይነት እንዳገኘ ትመለከታለህ። ከዚህም ሌላ ለአትክልት ጠቃሚ ከሆኑ ነፍሳት ብዙዎቹ ጎጂዎቹን ነፍሳት ይመገባሉ። በአትክልት ቦታህ ጥንዚዛዎች እንዲራቡ ብታደርግ ወዲያውኑ አትክልት የሚመጥጡ ነፍሳትን ማደን ይጀምራሉ። የማርያም ፈረስ በመባል የሚታወቁትን ነፍሳትም በአትክልት ቦታ ውስጥ ማርባት ይቻላል። እነዚህ ነፍሳት በአካባቢያቸው የሚያገኟቸውን ሌሎች ነፍሳት በሙሉ ማለት ይቻላል፣ እያደኑ ይበላሉ።
ተክሎችና የተባይ ቁጥጥር
በአትክልትህ ውስጥ የሚርመሰመሱትን ተባዮች ብዛት ለመቀነስ ከፈለግህ በአንዳንድ ተክሎች መጠቀም ትችላለህ። ጥበቃ በሚያስፈልጋቸው ተክሎች አጠገብ የአትክልት ተባዮች የማይወዱትን ተክል ትከል። ለምሳሌ በብዙ ተክሎች ሥር ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ትሎች ማሪጎልድ የተባለው የአበባ ተክል በሚገኝበት አካባቢ ዝር አይሉም። ጎመን የሚያጠቁ ቢራቢሮዎች ከሮዝመሪና ከጦስኝ ስለሚሸሹ እነዚህ ተክሎች ጎመን አጠገብ ቢተከሉ ቢራቢሮዎቹ አያጠቁትም። እዚህ ላይ አንድ ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈላጊ ይሆናል። አንዳንድ ተክሎች ተባዮችን ይስባሉ።
ተክሎችን እያፈራረቁ መትከል ሌላው ተባዮችንና የአትክልት በሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥሩ ዘዴ ነው። ከዓመት ዓመት አንድ ዓይነት ተክል በአንድ ቦታ ከመትከል ይልቅ የተለያዩ ተክሎችን ማፈራረቅ ይቻላል። በዚህ መንገድ የበሽታዎችንና የተባዮችን የእድገት ሰንሰለት መበጠስ ይቻላል።
በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች ተክሎችን ማልማት ብዙ ጊዜና ትዕግሥት የሚጠይቅ በመሆኑ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች በመጠቀም የአትክልት ቦታህ አፈር ጤናማ ከሚሆንበት ደረጃ ለማድረስ በርካታ ወራት ሊጠይቅ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ልትወጣ ያልቻልከው ችግር ያጋጥምህና ኬሚካል ለመርጨት ትፈተን ይሆናል። ይሁን እንጂ ከመርጨትህ በፊት ኬሚካላዊ መርዞችን አለመጠቀም የኋላ ኋላ የሚያስገኘውን ዘለቄታዊ ጥቅም ቆም ብለህ አስብ። ትዕግሥተኛ ብትሆን ግን ብዙም ሳትቆይ ተባዮችንና በሽታዎችን የመቋቋም አቅም ያለውና በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች በቅሎ ያደገ ጥሩ የአትክልት ምርት ማግኘት ትችላለህ። የአትክልት ቦታህ አንዳች እንከን የሌለው እንደማይሆን የታወቀ ነው። ቢሆንም ደስ የምትሰኝበት ውጤት ማግኘትህ አይቀርም። ስለዚህ አትክልት መትከል የሚያስደስትህ ከሆነ በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች ለማልማት ለምን አትሞክርም?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሸክላማ አፈር
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሸዋማ አፈር
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለም አፈር
[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአትክልትህ ወዳጆች
አንድ ጉርጥ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ10, 000 የሚበልጡ ነፍሳት መብላት ይችላል
አንዲት ድንቢጥ “በግማሽ ቀን 500 ሸረሪቶችንና አባጨጓሬዎችን ለልጆቿ ” እንደመገበች ተስተውሏል
የአፈር ትል አየር ወደ አፈር ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉም በላይ የተለያዩ ማዕድናት ከመሬት ውስጥ ወደ ላይ እንዲወጡ ያደርጋል
ጥንዚዛዎች አትክልት የሚመጥጡ ነፍሳትን ይመገባሉ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብስባሽ ከአፈር ጋር ሲቀላቀል የአፈሩ ይዘት እንዲሻሻል ያደርጋል