ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ሌሎች ከሚያጨሱት ትንባሆ የሚወጣውን ጭስ መተንፈስ
የካናዳው ግሎብ ኤንድ ሜይል በቅርቡ በጃፓን ተደርጎ ስለነበረ አንድ ጥናት ሲዘግብ “ሌሎች ከሚያጨሱት ትንባሆ የሚወጣውን ጭስ ለ30 ደቂቃ ያህል ብቻ መተንፈስ በአንድ የማያጨስ ጤነኛ ሰው ልብ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል” ብሏል። የኦሳካ ከተማ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አዲስ የአልትራሳውንድ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሌሎች ከሚያጨሱት ትንባሆ የሚወጣውን ጭስ መተንፈስ የልብንና የደም ቧንቧዎችን ውስጠኛ ግድግዳዎች በሚሸፍኑት ሴሎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መለካት ችለዋል። እነዚህ ሴሎች ጤነኛ በሆኑባቸው ጊዜያት በደም ቧንቧ ግድግዳዎች ላይ የቆሻሻ ቅርፊትና የደም መርጋት እንዳይከማች በመከላከል ጥሩ የደም ዝውውር እንዲኖር ያግዛሉ። ተመራማሪዎቹ “በማያጨሱ ሰዎች ልብ ውስጥ ያለው የደም ፍሰት ከሚያጨሱት በ20 ከመቶ ያህል ተሽሎ ተገኝቷል። ሌሎች ከሚያጨሱት ትንባሆ ለሚወጣ ጭስ ለ30 ደቂቃ ያህል ብቻ ከተጋለጡ በኋላ” ግን የደም ዝውውራቸው ከሚያጨሱት ጋር እኩል ሆኖ እንደተገኘ አረጋግጠዋል። ዶክተር ሪዮ ኦትሱካ የተባሉት ተመራማሪ እንዳሉት “ይህም ሌሎች ከሚያጨሱት ትንባሆ የሚወጣውን ጭስ መተንፈስ በማያጨሱ ሰዎች የልብ ደም ዝውውር ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አረጋግጧል።”
የብርሃን ብክለት የሚያሳይ አዲስ ካርታ
ሳይንስ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ “ፍኖተ ሐሊብ በጠፈር ላይ በደረሰ አንድ መዓት ምክንያት ሳይሆን በጣም እየሰፉ የሄዱት ከተሞቻችን የሚፈነጥቁት ደማቅ ብርሃን በረጨታችን ውስጥ የሚገኙትን ከዋክብት ከአብዛኞቹ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን እይታ ሰውረዋቸዋል። ይህ የሰው ሠራሽ ብርሃን ከዋክብት እንደልብ እንዳይታዩ በማድረጉ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችን በጣም አሳዝኗቸዋል” ይላል። በኢጣሊያና በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሳይንቲስቶች በዚህ የተበሳጩ ከዋክብት ተመልካቾችን ለመርዳት ሲሉ የብርሃን ብክለት የሚገኝባቸውን ቦታዎች ለይቶ የሚያመለክት አዲስ የዓለም ካርታ አውጥተዋል። ከዚህ በፊት የወጡ ካርታዎች “ከፍተኛ በሆነ ነጭ መብራት የደመቁ የአሕጉራት ክፍሎችን ብቻ የሚያሳይ ሲሆን” ከኢንተርኔት የሚገኘው ይህ አዲሱ ካርታ ግን “ከአሕጉራት ካርታ በተጨማሪ ለምሳሌ ያህል፣ ከተለያዩ የአውሮፓ ክፍሎች ከዋክብት ምን ያህል ሊታዩ እንደሚችሉ መጠቆምን የመሰሉ ዝርዝር ነገሮችን ያሳያል።”
የውቅያኖስ ወለሎችን በካርታ መሳል
በኖቫ ስኮሽያ በሚገኘው የቤድፎርድ ባሕር አጥኚዎች ማዕከል የሚሠሩ ሳይንቲስቶች ባሁኑ ጊዜ ሥራ ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የውቅያኖስ ወለሎችን ካርታ በመሳል ሥራ በግንባር ቀደምትነት እንደተሰለፉ የካናዳው ፋይናንሽያል ፖስት ዘግቧል። ይህ ቴክኖሎጂ በርካታ የብርሃን ጨረሮችን በመላክ ሳይንቲስቶች የውቅያኖስ ወለሎችን ፎቶግራፍ ለማንሳት ችለዋል። በመጨረሻ ላይ “የሩቅ መቆጣጠሪያ ያላቸው ቪዲዮ ካሜራዎች ወደ ውቅያኖስ ወለል ይላኩና ናሙናዎች ይወሰዳሉ።” ዘገባው እንደሚለው “የውቅያኖስ ወለሎችን ካርታ መሳል የሚያስገኘው ጥቅም በጣም ብዙ ነው።” በሌላው የውቅያኖስ ወለል አካባቢ ላይ ጉዳት ወይም ረብሻ ሳይደርስ በአንድ አካባቢ የሚገኝን ሀብት ማውጣት ይቻላል። የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎች የስልክ ገመዶችን ለመቅበር በጣም አመቺ የሆነውን መስመር እንዲመርጡ ይረዳቸዋል። የነዳጅ ኩባንያዎች ብዙ ምርት በሚያስገኙና ለአደጋ በማያሰጉ ቦታዎች የነዳጅ ማውጫ መሳሪያዎችን መትከል ይችላሉ። በተጨማሪም እንዲህ ያለው ካርታ በውቅያኖስ ወለሎች ተትረፍርፎ የሚገኘውን አሸዋና ጠጠር ለማውጣት ያስችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ተራሮችን ከመቆፈር ይልቅ ከውቅያኖስ ወለል ማውጣት “በወጪም ሆነ አደጋ በመቀነስ ረገድ የተሻለ” ይሆናል።
የአእምሮ በሽታን ምንነት መረዳት
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) “ከአራት ሰዎች አንዱ በሕይወት ዘመኑ ውስጥ በአእምሮ ወይም በነርቭ ቀውስ መጠቃቱ አይቀርም” ሲል ዘግቧል። ብዙዎቹ የአእምሮ በሽታዎች በሕክምና ሊድኑ የሚችሉ ቢሆኑም በበሽታው ከሚሠቃዩ ሰዎች ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት እርዳታ ለማግኘት ወደ ሐኪም ቤት አይሄዱም። የዓለም ጤና ድርጅት ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ግሮ ሃርለም ብሩንትላንድ “የአእምሮ በሽታ በግለሰቡ ጥፋት የሚመጣ አይደለም” ይላሉ። “እንዲያውም ጥፋተኛ አለ ከተባለ ጥፋተኞቹ በአእምሮ በሽታ ለሚሠቃዩ ሰዎች ትክክለኛ አያያዝ የማናደርግ ሰዎች ነን።” አስተያየታቸውን በመቀጠል “ይህ ሪፖርት ለረዥም ዘመናት ሥር ሰድዶ የቆየውን ጥርጣሬና አጉል እምነት አስወግዶ በአእምሮ ጤና መስክ አዲስ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል። በአሁኑ ጊዜ በሚታየው የጤና አዝማሚያ መሠረት “በ2020 የአእምሮ ሕመም ከልብ በሽታ ቀጥሎ የሁለተኛነቱን ደረጃ ይይዛል” ይላል የዓለም ጤና ድርጅት። ይሁን እንጂ ታማሚዎቹ ተገቢውን ሕክምና ካገኙ “የማኅበረሰቡ ክፍሎች በመሆን ፍሬያማ ኑሮ ሊኖሩ ይችላሉ።”
ወጣት ሴቶችና የአጥንት መቦርቦር
ከመጠን በላይ ምግብ በመቀነስ ምክንያት በዕድሜ በሚገፉበት ጊዜ ኦስትዮፖሮሲስ ለተባለው የአጥንት መቦርቦር በሽታ ራሳቸውን የሚያጋልጡ ወጣት ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የጃፓኑ አሳሂ ሺምቡን ጋዜጣ አስጠንቅቋል። ሸምገል ያሉ ሴቶችን የሚያጠቃው ይህ በሽታ አጥንት እንዲሳሳ ስለሚያደርግ በቀላሉ ይሰበራሉ። የሴቶች የአጥንት መዳበር ከሆርሞን መጠን ጋር የቅርብ ዝምድና አለው። ሴቶች የወር አበባ ማየት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አጥንታቸው በጣም መዳበር የሚጀምር ሲሆን በ20 ዓመት አካባቢ ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ከአርባ ዓመት ዕድሜ በኋላ ደግሞ መቀነስ ይጀምራል። “የአጥንታቸው መዳበር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ከነበረ በኋላ እንደገና እየሳሳ ቢሄድ እንኳን በቀላሉ ሊሰበር ከሚችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ይቆያል” በማለት የጃፓን ሴቶች ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ኢኩኮ ኤዛዋ ይገልጻሉ። ስለዚህ “በ20 ዓመት ዕድሜ ላይ የተቻለውን ያህል ከፍተኛ የአጥንት ጥንካሬ ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው” ይላሉ። ይሁን እንጂ ወጣት ሴቶች ስለ ኦስትዮፖሮሲስ እምብዛም ሲጨነቁ አይታይም። “በአጠቃላይ በቂ ንጥረ ምግቦችን አይወስዱም” ይላሉ ኤዛዋ። “በተለይ በቂ ካልስየም አለመውሰድና በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ በአጥንት ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጉዳት ያደርሳል።”
በመቶ ዓመት ዕድሜ ጤነኛና ደስተኛ መሆን
በዮሚዩሪ ሺምቡን ጋዜጣ ላይ በወጣው ሪፖርት መሠረት “ከ100 ዓመት በላይ ከሆናቸው ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በየቀኑ በአእምሮም ሆነ በአካል ጤነኞች እንደሆኑ ይሰማቸዋል።” የመቶ ዓመት ባለዕድሜዎች ቁጥር በጃፓን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ1, 000 የበለጠው በ1981 ሲሆን በ2000 ዓመት ላይ 13, 000 ደርሷል። በቅርቡ የጃፓን የጤናና የብርታት በጎ አድራጎት ድርጅት ከ1, 900 በሚበልጡ በባለ መቶ ዓመት የዕድሜ ባለጠጎች ላይ ጥናት አድርጓል። ይህ ጥናት እስከዛሬ ከ100 ዓመት በላይ በሆናቸው ሰዎች “የኑሮ ጣዕም” ላይ ከተደረጉት ጥናቶች ትልቁ እንደሆነ ይታሰባል። “ከወንዶቹ 43.6 በመቶ የሚሆኑትና ከሴቶቹ ደግሞ 25.8 በመቶ የሚሆኑት ‘በሕይወታቸው ዓላማ እንዳላቸው’” መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል። ከተጠቀሱት የመቶ ዓመት አረጋውያን መካከል አብዛኞቹ የሕይወት ዓላማዎቻችን ናቸው ብለው ከገለጿቸው መካከል “ቤተሰብ፣” “ረዥም ዕድሜ፣” “ጥሩ ጤና አግኝቶ ተደስቶ መኖር” ይገኙበታል። ስለዚህም ዮሚዩሪ ሺምቡን “ሕይወት ዓላማ እንዲኖረው ማድረግ ረዥም ዕድሜ ያስገኛል” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል።
በብቸኝነት መኖር
በቅርቡ በፈረንሣይ አገር በተደረገ አንድ ቆጠራ እንዳመለከተው በዚህች አገር ከ8 ሰው አንዱ የሚኖረው ብቻውን ነው። ይህ አኃዝ ከ30 ዓመት በፊት ከነበረው በእጥፍ እንደሚበልጥ ለ ሞንድ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ይህ አኃዝ ገና ተጓዳኝ ያላገኙትን ወጣቶችና አረጋውያንን ያካትታል። ከወንዶች ይልቅ ብዙ ሴቶች በብቸኝነት ይኖራሉ። “ሴቶቹ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ እያገኙ በሄዱ መጠን ብቻቸውን የመኖራቸው ዕድል ከፍተኛ እንደሚሆን” ይኸው ጽሑፍ አመልክቷል። በተጨማሪም ቆጠራው ከ1990 ወዲህ በነጠላ ወላጆች የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር 22 በመቶ፣ ልጆች የሌሏቸው ባልና ሚስት ቁጥር 16 በመቶ እንደጨመረ ገልጿል። ጽሑፉ ሲደመድም “በጠቅላላው በአሁኑ ጊዜ ልጆች የሌሏቸው ባለ ትዳሮችና ብቻቸውን የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ልጆች ካሏቸው ቤተሰቦች ቁጥር በልጧል” ይላል።
ሩካቤ ሥጋ መፈጸም የጀመሩ አፍላ ወጣቶች
የብሪታንያ የቤተሰብ ጉዳይ ተቋም እንዳመለከተው “የተፋቱ ወይም ያለ ሕጋዊ ጋብቻ አብረው የሚኖሩ ወላጆች ያሏቸው” በአፍላ ጉርምስና የሚገኙ ወጣቶች “ሩካቤ ሥጋ የመፈጸም አጋጣሚያቸው በእጥፍ ይበልጣል” ይላል የለንደኑ ዘ ጋርድያን። ሩካቤ ሥጋ መፈጸም ከጀመሩ የ13 ዓመት ልጆች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት ቢያንስ አራት የወሲብ ጓደኞች ያፈራረቁ ሲሆን በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ድንግልናቸውን ባጡበት ጊዜ ሰክረው ነበር። ሪፖርቱ “ልጆችን ጥሩ አድርጎ ለማሳደግ የቤተሰብ መኖር በጣም አስፈላጊ” መሆኑን አበክሮ ገልጿል። ‘በወላጆችና በአፍላ ጎረምሳ ልጆች መካከል ያለው ግንኙነት በሚላላበት ወቅት፣ ወላጆችና ልጆች አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ በሚያንስበትና በቂ ቁጥጥር በማይኖርበት ጊዜ ችግሮች ይፈጠራሉ።’ ሪፖርቱ በማጠቃለያው “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ወላጆች ለልጆቻቸው ባሕርይ ኃላፊነት እስካልወሰዱ ድረስ የአፍላ ወጣቶች ሩካቤ ሥጋ፣ በዚያም ምክንያት የሚመጣው እርግዝናና የአባለ ዘር በሽታ ማሻቀቡን ይቀጥላል” ብሏል።
እንቅልፍ የሚጫጫናቸው አሽከርካሪዎች
ፍሊት ሜይንተናንስ ኤንድ ሴፍቲ ሪፖርት ስለ እንቅልፍ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንትና የትራፊክ ደህንነት ጠበብት አሽከርካሪዎች በጣም ደክሟቸው እንዳያሽከረክሩ እንደሚመክሩ ገልጿል። ስለ እንቅልፍ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች በየሌሊቱ ቢያንስ ስምንት ሰዓት መተኛት አስፈላጊ መሆኑን ቢያስገነዝቡም ብዙ ሰዎች የዚህን ያህል እንደማይተኙ ጥናቶች ያመለክታሉ። በተጨማሪም ከ19 እስከ 29 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አሽከርካሪዎች ከማንኛውም የዕድሜ ክልል በላይ እንቅልፍ ተጫጭኗቸው እንደሚያሽከረክሩና በሚያሸልቡበት ጊዜም ፍጥነታቸውን እንደሚጨምሩ ጥናቶች ያመለክታሉ። “መሪ ጨብጦ የማንቀላፋትን አጋጣሚ አልኮል በጣም ከፍ እንደሚያደርግ” ሪፖርቱ ይገልጻል። የአሜሪካ አውቶሞቢል ማኅበር የትራፊክ ደህንነት በጎ አድራጎት ድርጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት ዴቪድ ዊሊስ ራዲዮ መክፈት ወይም የበር መስተዋት ዝቅ ማድረግ እንደማያነቃና ከዚህ ይልቅ ጥቂት አረፍ ብሎ ማሸለብ እንደሚጠቅም ገልጸዋል። ዊሊስ “እንቅልፍ ለከበደው ብቸኛው መድኃኒት መተኛት ነው” በማለት አበክረው ገልጸዋል።