አብረውኝ ከሚኖሩት ልጆች ጋር ተስማምቼ መኖር የምችለው እንዴት ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
አብረውኝ ከሚኖሩት ልጆች ጋር ተስማምቼ መኖር የምችለው እንዴት ነው?
“እኔ ወጥ ቤቱ ንጹህ እንዲሆን እፈልጋለሁ። አብረውኝ የሚኖሩት ልጆች ግን ሰሃኖቹ በየቦታው ቢዝረከረኩ ወይም ምድጃው ላይ የተተወ ዕቃ ቢኖር ምንም አይመስላቸውም። ወጥ ቤቱ ንጹህ ሆነ አልሆነ እነሱ ግድ አይሰጣቸውም።”—ሊን *
አብረው የሚኖሩ ሰዎች “የሚዋደዱ ጓደኛሞች አሊያም ፈጽሞ የማይስማሙ ባላጋራዎች ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ኬቨን ስኮሌሪ የተባሉ ጸሐፊ ተናግረዋል። አንተ በግልህ እንደዚህ አይሰማህ ይሆናል፤ ሆኖም ከሌላ ሰው ጋር መኖር ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። * ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት የተሰኘው መጽሔት እንደገለጸው አብረው በሚኖሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች በጣም የተለመዱ ከመሆናቸው የተነሳ ብዙ ትምህርት ቤቶች “ግጭቶችን ለማርገብ የሚረዱ ፕሮግራሞችን” እና ሴሚናሮችን በማዘጋጀት ተማሪዎቹ ተስማምተው እንዲኖሩ ለመርዳት “ከፍተኛ ጥረት” እያደረጉ ነው።
የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው ለማገልገል ሲሉ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው የሚኖሩ ወጣት ክርስቲያኖችም እንኳን ከሌላ ሰው ጋር በአንድ ቤት ውስጥ መኖር አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ደስ የሚለው ግን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግና ‘ጥበብ’ በመጠቀም አብዛኛውን ጊዜ አለመግባባቶችን መፍታት ይቻላል።—ምሳሌ 2:7 የ1980 ትርጉም
በደንብ ተዋወቁ
ራሳችሁን ችላችሁ መኖር በመጀመራችሁ የተሰማችሁ ደስታ እያለፈ ሲሄድ ሁሉ ነገር ወደ ቀድሞው ሁኔታ እንዲመለስ መመኘት ትጀምር ይሆናል። (ዘኁልቊ 11:4, 5) ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ትኖርበት በነበረው ሁኔታ ላይ ማብሰልሰልህ አሁን ካለህበት ሁኔታ ጋር እንዳትለማመድ ከማድረግ በስተቀር ምንም አይፈይድም። መክብብ 7:10 የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና።” አዎን፣ ራስህን ካለህበት ሁኔታ ጋር ለማለማመድ መሞከሩ የተሻለ ነው።
አብሮህ የሚኖረው ሰው ያለውን ባህርይ በደንብ ለማወቅ ሞክር። እውነት ነው፣ አብረው የሚኖሩ ሰዎች የቅርብ ጓደኛሞች መሆን አለባቸው ማለት አይደለም። እንዲያውም አብሮህ የሚኖረው ሰው አንተን የሚስብህ ዓይነት ባህርይ ላይኖረው ይችላል። ያም ሆኖ ከዚያ ሰው ጋር እስከኖርክ ድረስ በተቻለ መጠን ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራችሁ መጣሩ ተገቢ አይመስልህም?
ፊልጵስዩስ 2:4 “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” ሲል ይመክረናል። ውይይታችሁ የፖሊስ ጥያቄ ዓይነት እንዳይመስል ጥንቃቄ በማድረግ አብሮህ የሚኖረውን ልጅ ስለ አስተዳደጉ፣ ስለሚወድደው ነገርና ስለ ግቡ ልትጠይቀው ትችላለህ። ስለ ራስህም ንገረው። በደንብ እየተዋወቃችሁ በሄዳችሁ መጠን የዚያኑ ያህል እርስ በእርስ ትግባባላችሁ።
አልፎ አልፎ አብራችሁ አንዳንድ ነገሮች ለማከናወን እቅድ አውጡ። ሊ “አንዳንድ ጊዜ አብረውኝ ከሚኖሩት ልጆች ጋር ወጣ ብለን አንድ ላይ እንመገባለን፣ ወይም አንድ ላይ ሆነን የስዕል ኤግዚቢሽኖችን እንጎበኛለን” ትላለች። አብረው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ለጉባኤ ስብሰባዎች እንደመዘጋጀት ወይም
በወንጌላዊነቱ ሥራ እንደመካፈል ያሉ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በሕብረት በማከናወን ወዳጅነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ተጨማሪ አጋጣሚ አላቸው።ዳዊት “አብሮኝ የሚኖረው ልጅ በሕዝብ ፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ያቀርብ በነበረበት ዕለት እሱን ለማበረታታት ጉባኤው ሄጄ ነበር” ይላል። ምንም እንኳን እሱና አብሮት የሚኖረው ልጅ በስፖርትና በሙዚቃ ረገድ ምርጫቸው የተለያየ ቢሆንም ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ፍቅር በመካከላቸው የቀረበ ወዳጅነት ፈጥሯል። ዳዊት እንዲህ ይላል:- “ስለ መንፈሳዊ ነገሮች በስፋት እንወያያለን። እንዲያውም ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ማውራት ከጀመርን ጊዜውም አይበቃንም።”
ይሁንና ልትጠነቀቅበት የሚገባ አንድ ነገር አለ:- ከሌሎች ጋር ጤናማ ወዳጅነት መመሥረት እስኪሳንህ ድረስ አብሮህ የሚኖረው ልጅ ላይ ሙጭጭ ማለት የለብህም። አብሮህ የሚኖረው ልጅ በሄደበት ሁሉ ሊያስከትልህ እንደሚገባው አድርጎ እንዲያስብ ካደረግከው መፈናፈኛ እንዳሳጣኸው ሊሰማው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅራችንን ‘እንድናሰፋ’ ይመክረናል።—2 ቆሮንቶስ 6:13
ወርቃማውን ሕግ ሥራ ላይ ማዋል
እርግጥ ነው፣ የበለጠ እየተዋወቃችሁ በሄዳችሁ መጠን በባህርይ፣ በምርጫ እንዲሁም በአመለካከት ረገድ ልዩነት እንዳላችሁ ትገነዘባላችሁ። ወጣቱ ማርቆስ እንዳሳሰበው “ጉድለት እንደሚኖር መጠበቅ ይኖርባችኋል።” ግትር ወይም ራስ ወዳድ መሆን ወይም ደግሞ አብሮህ የሚኖረው ሰው አንተን ለማስደሰት ሲል የጎላ ለውጥ እንዲያደርግ መጠበቅ ውጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል።
ፌርናንዶ ከሌሎች ጋር አብሮ መኖርን በተመለከተ ያገኘውን ትምህርት ሲናገር “ራስ ወዳድ መሆን የለብህም” ብሏል። ይህ አስተያየት ታዋቂ ከሆነው ወርቃማ ሕግ ጋር የሚስማማ ነው። ሕጉ እንዲህ ይላል:- “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።” (ማቴዎስ 7:12) ለምሳሌ ያህል ፌርናንዶ በክፍላቸው ውስጥ እንዲኖር በሚፈልገው የሙቀት መጠን የተነሳ አብሮት ከሚኖረው ልጅ ጋር ሊግባባ እንዳልቻለ ተገነዘበ፤ እሱ ክፍሉ ሞቅ እንዲል ሲፈልግ አብሮት የሚኖረው ልጅ ግን ሲተኛ ቀዝቀዝ ያለ አየር እንዲኖር ይፈልጋል። ታዲያ መፍትሔ ሆኖ የተገኘው ነገር ምን ነበር? ፌርናንዶ “እኔ ብርድ ልብስ መደረብ ጀመርኩ” ይላል። አዎን፣ ማርቆስ እንደተናገረው “ግትር መሆን አያስፈልግም። አመለካከትህን ሙሉ በሙሉ መቀየር አለብህ ማለት ባይሆንም አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል።”
ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ልታደርግ የምትችልበት ሌላው መስክ ደግሞ አብሮህ የሚኖረውን ልጅ ምርጫ ማክበር ነው። ለምሳሌ ያህል የሙዚቃ ምርጫውን አትወደውም እንበል። ምናልባት እሱም ስለ አንተ ምርጫ እንደዚያ ይሰማው ይሆናል። ስለዚህ አብሮህ የሚኖረው ልጅ የሙዚቃ ምርጫ ሥነ ምግባርን የሚያበላሽ እስካልሆነ ድረስ ምርጫውን ልታከብርለት ትችላለህ። ፌርናንዶ እንዲህ ይላል:- “አብሮኝ የሚኖረው ልጅ የሙዚቃ ምርጫ እኔ የምወደው ዓይነት አይደለም። ያም ሆኖ ግን እየለመድኩት ነው።” በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው አብሮት የሚኖረው ልጅ እያጠና ከሆነ እሱን ላለመረበሽ ሙዚቃ ሲሰማ ጆሮ ላይ በሚደረግ ማዳመጫ ሊጠቀም ይችላል።
ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ከግል ንብረቶች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ግጭቶችንም ያስቀራል። ለምሳሌ ያህል፣ በማቀዝቀዣው ውስጥ የተቀመጠን የአንተ ያልሆነ ነገር የምትወስድና መልሰህ የማትተካ ከሆነ ቅሬታ ሊፈጠር ይችላል። በተመሳሳይም አብሮህ የሚኖረው ልጅ አንተ የገዛኸውን እቃ ያለ ፈቃድ ሲወስድ መቆጣት ወይም መገላመጥ ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራችሁ አያደርግም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመርዳትና ለማካፈል የተዘጋጀን’ እንድንሆን ያበረታታናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:18) አብሮህ የሚኖረው ልጅ መጠቀሚያ እንዳደረገህ ሆኖ ከተሰማህ ዝም አትበል። እርጋታና ደግነት በተሞላበት መንገድ ቅሬታህን ግለጽ።
ምሳሌ 11:2) አብሮህ የሚኖረው ልጅ ብቻውን መሆን የሚፈልግበት ጊዜ እንደሚኖርም አስታውስ። ወደ ክፍሉ ከመግባትህ በፊት በሩን እንደማንኳኳት ያሉ አክብሮትን የሚያሳዩ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር። አንተ አክብሮት ካሳየኸው እሱም እንዲሁ ማድረጉ አይቀርም። ዳዊት እንዲህ ይላል:- “ከሁለት አንዳችን ቤት ውስጥ ሆነን ማጥናት ከፈለግን እንችላለን። ሁለታችንም የሌላኛውን ወገን ፍላጎት በማክበር ፀጥታውን ላለመረበሽ እንሞክራለን። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ አብሮኝ የሚኖረው ልጅ እቤት ውስጥ ሆኖ ሌላ ነገር ማከናወን ከፈለገ ቤተ መጻሕፍት ሄጄ አጠናለሁ።”
አንዳችሁ የሌላኛችሁን የግል ንብረት ማክበር አለባችሁ። ፈቃድ ሳይጠይቁ የሌላውን ንብረት መውሰድ እንደ መዳፈር ይቆጠራል። (ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ከቤት ኪራዩ ላይ የራስህን ድርሻ በወቅቱ በመክፈልና በቤት ውስጥ ሥራዎች ረገድ የበኩልህን በማድረግ ኃላፊነትህን መወጣትንም ይጨምራል።
አለመግባባቶችን መፍታት
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጳውሎስና በርናባስ በተባሉ ሁለት የተከበሩ ክርስቲያኖች መካከል “የከረረ አለመግባባት” ተፈጥሮ ነበር። (ሥራ 15:39 አ.መ.ት ) በአንተና አብሮህ በሚኖረው ልጅ መካከል ተመሳሳይ ነገር ቢፈጠርስ? ምናልባትም በመካከላችሁ የባህርይ አለመጣጣም ሊኖር ይችላል። አሊያም ደግሞ አብሮህ በሚኖረው ልጅ ላይ የምታየው የሆነ ዓይነት ልማድ ሊያበሳጭህና ትዕግስትህን ሊፈታተነው ይችላል። በመካከላችሁ አለመግባባት ስለተፈጠረ ወይም የጋለ ክርክር ስለተደረገ ብቻ አብራችሁ መኖራችሁን ማቆም አለባችሁ ማለት ነው? እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስና በርናባስ አለመግባባታቸውን ማስወገድ ችለው ነበር። ምናልባት እናንተም እስከ መለያየት የሚያደርስ ከባድ እርምጃ ከመውሰዳችሁ በፊት እንደዚያ ማድረግ ትችሉ ይሆናል። ሊረዷችሁ የሚችሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።
● “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር።”—ፊልጵስዩስ 2:3
● “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።”—ኤፌሶን 4:31, 32
● “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።”—ማቴዎስ 5:23, 24፤ ኤፌሶን 4:26
የሚገኙት ጥቅሞች
አብረው የሚኖሩ ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል” የሚሉት የጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ቃላት እውነት እንደሆኑ በራሳቸው ሕይወት ላይ ባዩት ሁኔታ ማረጋገጥ ችለዋል። (መክብብ 4:9) በእርግጥም ብዙዎች ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝበዋል። ማርቆስ “ከሰዎች ጋር በተሻለ ሁኔታ ተስማምቼ መኖርንና ራስን ከሁኔታዎች ጋር ማለማመድን ተምሬያለሁ” ይላል። ረኔ እንዲህ ስትል አክላ ትናገራለች:- “ስለ ራስህ ብዙ ትማራለህ። ከዚህም በላይ አብሮህ የሚኖረው ሰው መልካም ተጽእኖ ሊያሳድርብህ ይችላል።” ሊን እንዲህ ስትል ሐቁን ተናግራለች:- “ከሌሎች ልጆች ጋር አብሬ መኖር ስጀምር በጣም ቀበጥ ልጅ ነበርኩ። አሁን ግን ግትር መሆን እንደሌለብኝ ተምሬያለሁ። አንዲት ልጅ ነገሮችን እኔ ከማስበው በተለየ መንገድ ስላከናወነች ተሳስታለች ማለት እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ።”
እውነት ነው፣ ከሌላ ሰው ጋር ተስማምቶ መኖር ጥረት ማድረግንና መሥዋዕትነት መክፈልን ይጠይቃል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ለማድረግ ከጣርክ በመካከላችሁ ሰላም የሚሰፍን ከመሆኑም በላይ ከሌላ ሰው ጋር በመኖርህ ደስተኛ መሆን ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.4 በግንቦት 2002 እትማችን ላይ የወጣውን “አብሮኝ የሚኖረው ልጅ ፀባይ ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የራስህ ያልሆኑ ነገሮችን ያለ ፈቃድ መውሰድ በመካከላችሁ ውጥረት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳችሁ የሌላኛችሁን ስሜት አክብሩ