ማራኪ ለመሆን ምን ማድረግ እችላለሁ?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ማራኪ ለመሆን ምን ማድረግ እችላለሁ?
“ልጃገረዶች ምን እንደሚያስቡ፣ ምን እንደሚሰማቸው ወይም ምን ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ስለማላውቅ ከእነርሱ ጋር ዘና ብዬ ማውራት ይከብደኝ ነበር።”—ታይለር
ልጃገረዶች የሚወዱት ምን ዓይነት ባህርይ ያላቸውን ወንዶች ነው? ኤምሊ የተሰኘች ወጣት “በራስ የመተማመን መንፈስ ያላቸውን ወንዶች” እንደምትወድ ተናግራለች። ሮቢን የተሰኘች በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ሌላ ወጣት ደግሞ ተጫዋች ወንዶችን አብልጣ እንደምትወድድ ተናግራለች። ወንዶችስ የሚወዱት ምን ዓይነት ሴቶችን ነው? አንድ ጥናት እንዳመለከተው ወንዶቹ ከዘረዘሯቸው መስፈርቶች መካከል ቅድሚያውን የያዘው ቁንጅና ነው። ተመሳሳይ የሆነ ፍላጎትና አመለካከት የተጠቀሰው በስድስተኛ ደረጃ ነው።
በወንድና ሴት መካከል ስላለው ግንኙነት የሚገልጹ ጽሑፎችና ጥናቶች ለወጣቶች በሚዘጋጁ መጽሔቶች ላይ አዘውትረው ይወጣሉ። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ብዙ ወጣቶች ተቃራኒ ጾታ ባላቸው እኩዮቻቸው ዘንድ ማራኪ ሆነው መታየት ስለሚፈልጉ እኩዮቻቸው ለእነርሱ ያላቸው አመለካከት ያሳስባቸዋል ወይም ያስጨንቃቸዋል። ምናልባት አንተም አልፎ አልፎ ይህ ጉዳይ ያስጨንቅህ ይሆናል። ይህ ዓይነቱ ስሜት የሚሰማህ ለማግባት ስለደረስክ ላይሆን ይችላል። ማንም ሰው ቢሆን በተፈጥሮው ማራኪ ወይም ተወዳጅ መሆን እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። ታይለር እንዲህ ብሏል:- “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስትሆን በሰዎች ዘንድ ማራኪ ሆነህ መታየት ትፈልጋለህ። በወንዶቹም ሆነ በሴቶች እኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ትፈልጋለህ።” ከዚህም በላይ አንድ ቀን እንደምታገባ ታስብ ይሆናል። በዚያ ወቅት ልታገባ ያሰብከውን ሰው ለመማረክ እንደምትፈልግ የታወቀ ነው።
ይሁንና ክርስቲያን ወጣት እንደመሆንህ መጠን ተቃራኒ ጾታን እንዴት መቅረብ እንደምትችል ብዙም የምታውቀው ነገር አይኖር ይሆናል። በዚህ ላይ ደግሞ እኩዮችህ የሚያሳድሩብህ ተጽዕኖ ለአካላዊ ቁመናህ በጣም እንድትጨነቅ ሊያደርግህ ይችላል። ውብና የፈረጠመ ሰውነት ያላቸውን ሰዎች በቴሌቪዥንና በመጽሔቶች ላይ ስትመለከት በራስ ያለመተማመንና የበታችነት ስሜት ሊያድርብህ ይችላል። በሌሎች ዘንድ ክብር ባለውና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማራኪ ሆኖ መገኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
“እንከን የለሽ” ቁመና ለማግኘት የሚደረግ ከንቱ ጥረት
ዊልያም ኤስ ፓለክ የተባሉ የሥነ ልቦና ሐኪም የመዝናኛው ዓለም በሚያሳድረው ተጽዕኖ በመገፋፋት ብዙ ወጣቶች “አመጋገባቸውን በመቆጣጠር፣ ክብደት በማንሳትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ቁመናቸውን ለማስተካከል ብዙ ሰዓት እንደሚያጠፉ” ተናግረዋል። እንዲያውም አንዳንዶች “እንከን የለሽ” ቁመና ለማግኘት ራሳቸውን እስከ ማስራብ ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ የማኅበራዊ ጉዳይ የምርምር ማዕከል እንደሚለው “በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርበውን የሴቶች ቁመና መስፈርት ሊያሟሉ የሚችሉት ከ5 በመቶ ያነሱ ሴቶች ብቻ ሲሆኑ እነዚህም ቢሆኑ መስፈርቱን የሚያሟሉት በሰውነት ክብደትና መጠን ረገድ ብቻ ነው። በጣም ቆንጆ የሚባለውን የሰውነት ቅርጽ፣ የፊት መልክ፣ ወዘተ የሚያሟሉት ግን 1 በመቶ የሚያክሉ ሴቶች ብቻ ናቸው።”
እንግዲያው “በዙሪያችሁ ያለው ዓለም በራሱ መልክ እንዳይቀርጻችሁ ተጠንቀቁ” የሚለውን በሮሜ 12:2 (የፊሊፕስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተሉ ጠቃሚ ነው። እንደዚህ ሲባል ግን ስለ መልክህ ግድየለሽ መሆን አለብህ ማለት አይደለም። በተወሰነ መጠን የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግና የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ ሰውነትህን መንከባከብህ አስፈላጊ ነው። (ሮሜ 12:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8) በቂ እረፍትና እንቅልፍ ማግኘትህ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና ማራኪ እንድትሆን ሊያደርግህ ይችላል። እንዲሁም የግል ንጽህናን መጠበቅና ለአለባበስህ ትኩረት መስጠትም አስፈላጊ ነው። ዴቪድ የተባለ እንግሊዛዊ ወጣት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በጣም ቆንጆ የሆነች አንዲት ልጅ አለች። ሆኖም መጥፎ ጠረን ስላላት ሰዎች ይርቋታል።” ስለዚህ ሰውነትህን አዘውትረህ ታጠብ። እጆችህ፣ ፀጉርህና ጥፍሮችህ ንጹህ መሆናቸውም ማራኪ እንድትሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አለባበስህ ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለብህ ቢናገርም ክርስቲያኖች ‘በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን እንዲሸልሙ’ ይመክራል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ውበት የሚጨምር ልብስ መልበስ ጥሩ ቢሆንም አለባበስህ ቅጥ ያጣ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብሃል። * ለቁመናህ ሚዛናዊ የሆነ ትኩረት መስጠትህ በራስ የመተማመን መንፈስህን ሊያሳድግልህ ይችላል። ይህን በተመለከተ ጳውሎስ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “በጣም ቆንጆ ባትሆንም እንኳ ያለህን ቁመና በተወሰነ ደረጃ ውበት ልትጨምርለት ትችላለህ።”
ውስጣዊ ባህርያት
ውበትና የሚያምር ተክለ ሰውነት ማራኪ ቢሆኑም ከጊዜ በኋላ ግን “ውበት ይረግፋል።” (ምሳሌ 31:30 አ.መ.ት ) ውበት አላፊ ከመሆኑም በላይ ማራኪ የሆኑ ውስጣዊ ባሕርያትን ሊተካ አይችልም። (ምሳሌ 11:22) እንዲሁም ‘ሰው ፊትን እግዚአብሔር ግን ልብን እንደሚያይ’ አስታውስ። (1 ሳሙኤል 16:7) ስለዚህ ስለ ሰውነትህ ቅርጽ ከልክ በላይ ከመጨነቅ ይልቅ የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጣር:- “በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።” (1 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ ኤፌሶን 4:24) እርግጥ ነው፣ ዛሬ ያሉ ብዙ ወጣቶች ለመንፈሳዊ ባሕርያት ይቅርና ለመልካም ጠባይ እንኳን እምብዛም አድናቆት የላቸውም። * ሆኖም አምላካዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች እነዚህን ባሕርያት ከፍ አድርገው ይመለከቷቸዋል እንደዚሁም ይማረኩባቸዋል።
እንግዲያው መንፈሳዊ አመለካከት ባላቸው ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ዘንድ ማራኪ ሆኖ ለመገኘት ከሁሉ የተሻለው መንገድ አንተ ራስህ መንፈሳዊ አመለካከት መያዝህ ነው። በጸሎት፣ በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት መንፈሳዊነትህን ለማሳደግ ጥረት አድርግ። (መዝሙር 1:1-3) ያም ሆኖ ልታዳብራቸው የምትችላቸው ሌሎች ጠቃሚ ችሎታዎችና ባሕርያትም አሉ። እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር ከተቃራኒ ጾታ ጋር መቀጣጠር ወይም በፍቅር መያዝ አያስፈልግህም። ከዚህ ይልቅ ከሌሎች ጋር ባለህ የዕለት ተዕለት ግንኙነት እነዚህን ባሕርያት ማዳበር ትችላለህ።
ለምሳሌ ያህል፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ስትሆን የመረበሽ ስሜት ወይም ዓይናፋርነት ይሰማሃል? ጳውሎስ የተሰኘ አንድ ወጣት እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “ከወንዶች ጋር የምግባባውን ያህል ከሴቶች ጋር መግባባት ስለማልችል አንዳንድ ጊዜ ከሴቶች ጋር ስሆን እረበሻለሁ። የሚያሳፍረኝ ነገር ማድረግ ደግሞ አልፈልግም።” ሌሎች ዘና እንዲሉ የሚያደርግ በራስ የመተማመን መንፈስ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚገኙት የተለያዩ ሰዎች ጋር በመቀራረብ ነው። በስብሰባዎች ላይ በአንተ ዕድሜ ከሚገኙ ተቃራኒ ጾታዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከልጆች፣ ከትላልቅ ሰዎችና በዕድሜ ከገፉት ጋር ጭምር ለመቀራረብ ጥረት አድርግ። (ፊልጵስዩስ 2:4) በዚህ መንገድ ከተለያዩ ሰዎች ጋር መቀራረብ መቻልህ በራስ የመተማመን መንፈስ እንድታዳብር ይረዳሃል።
ሆኖም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። ኢየሱስ ‘ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ ብሏል። (ማቴዎስ 19:19) በራስህ የምትተማመን ከሆነ ከሌሎች ጋር ስትሆን አትረበሽም። * ይሁን እንጂ ምንም እንኳን በተወሰነ መጠን በራስ የመተማመን መንፈስ ማዳበር አስፈላጊ ቢሆንም ከልክ በላይ በራስህ መተማመን የለብህም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ . . . እናገራለሁ” ብሏል።—ሮሜ 12:3
መልካም ሥነ ምግባር ማዳበርና ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት ረገድም ጠንቃቃ መሆን ይኖርብሃል። ሊድያ የተሰኘች አንዲት እንግሊዛዊ ወጣት እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “በምማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ በብዙ ልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነ አንድ ወጣት አለ። ሆኖም ባለጌና እንዳመጣለት የሚናገር በመሆኑ አንድ ጊዜ ካወቁት በኋላ ይጠሉታል።” ደግነት በተሞላበትና ሌሎችን በማይጎዳ መንገድ የሚናገርና አሳቢ የሆነ ሰው ሌሎችን ይማርካል። (ኤፌሶን 4:29, 32፤ 5:3, 4) ቲ ቤሪ ብሬዛልተን የተባሉ ዶክተር “ደስ የሚል ሥነ ምግባር ከሰዎች ጋር ነጻ ሆነን ለመነጋገር እንደሚያስችል የይለፍ ወረቀት ነው” ብለዋል። ‘መልካም ሥነ ምግባር በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ያስገኛል።’
በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ባህሎችና ሥርዓቶች አሉ። በመሆኑም የጎለመሱ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች እርስ በእርስ ባላቸው ግንኙነት አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩትን ምግባር መመልከት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ አንተ በምትኖርበት አገር አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት በር መክፈቱ የተለመደ ነውን? እንደዚያ ከሆነ አንተም ይህንን የአክብሮት መግለጫ ማሳየትህ ሰዎች መልካም ሥነ ምግባር እንዳለህ እንዲገነዘቡ ሊያደርግና ጥሩ ስም ሊያተርፍልህ ይችላል።
በመጨረሻም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተጫዋች መሆን ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለመሳቅም ጊዜ አለው” ይላል፤ ተጫዋች የሆነ ሰው ጓደኞች ለማፍራት አይቸገርም።—መክብብ 3:1, 4
ወዳጃዊ መንፈስ ማሳየት ወይስ ማሽኮርመም?
“ከተቃራኒ ጾታ ጋር በተሳካ ሁኔታ ተቀጣጥሮ መጫወት የሚቻልበትን መንገድ የሚጠቁም መመሪያ” እንደሚሰጥ የሚናገር አንድ ጽሑፍ፣ ተቃራኒ ጾታን ለመማረክ ቁልፉ ማሽኮርመም እንደሆነ ይገልጻል። አንባቢዎቹ እንዴት ማየትና ፈገግ ማለት እንዳለባቸው እንዲሁም ጥሩ ጭውውት እንዴት መክፈት እንደሚችሉ ይናገራል። እንዲህ ያለው ምክር ጳውሎስ ሴቶችን “በፍጹም ንጽሕና” እንዲይዛቸው ለጢሞቴዎስ ከሰጠው ምክር ጋር ይጋጫል።—1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2
ምንም እንኳን ማሽኮርመም አንድ ሰው ለራሱ ያለውን ግምት ከፍ ሊያደርግለት ቢችልም ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ነው። ጥሩ የሆነ ጭውውት ለማድረግ ማሽኮርመም ወይም አጉል ዓይን አፋር ለመምሰል መሞከር አያስፈልግህም። ወይም ደግሞ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በምታደርገው ጭውውት ግለሰቡ ምን እንደሚሰማው ወይም ምን እንደሚያስብ ለማወቅ የሚያሳፍሩና ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅም አይገባህም። ‘ጽድቅ የሆነውን ነገር፣ ንጹሕ የሆነውን ነገርና ፍቅር ያለበትን ነገር’ ብቻ በማውራት መንፈሳዊ አመለካከት እያዳበርክና እየጎለመስክ እንዳለህ ታሳያለህ። (ፊልጵስዩስ 4:8) ለአምላካዊ ሥርዓቶች ታዛዥ መሆንህ ተቃራኒ ጾታን የሚማርክ ብቻ ሳይሆን አምላክንም የሚያስደስት ይሆናል። *—ምሳሌ 1:7-9
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.10 በመጋቢት 1999 ንቁ! ላይ የወጣውን “ምንስ ዓይነት ልብስ ብንለብስ ምን ለውጥ አለው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.12 አንዲት ተመራማሪ እንደተናገሩት ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ እንደሚሾፍባቸው ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ወጣቶች ችሎታቸውን ለመደበቅ ይሞክራሉ።
^ አን.15 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተሰኘው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 12 ላይ በራስ የመተማመን መንፈስ ለማዳበር የሚረዱ በርካታ ተግባራዊ ሐሳቦች ይዟል።
^ አን.21 ለማግባት ካልደረስክ ከአንድ ሰው ጋር በተናጠል ከመቀራረብ ይልቅ በርከት ካሉ ወንዶችና ሴቶች ጋር በቡድን ደረጃ ብትቀራረብ የተሻለ ነው። በመጋቢት 2001 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ወላጆቼ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሬ ለመጫወት እንዳልደረስኩ ቢነግሩኝስ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በአካላዊ ውበትህ ላይ ከማተኮር ይልቅ መንፈሳዊ ባሕርያትን ለማዳበር ጣር
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተለያየ ጾታና ዕድሜ ካላቸው ሰዎች ጋር በመቀራረብ በራስ የመተማመን መንፈስ አዳብር