ቅየሳ ምንድን ነው?
ቅየሳ ምንድን ነው?
በየዓመቱ በአባይ ወንዝ ዳርቻዎች የሚገኘው መሬት በጎርፍ ከተጥለቀለቀ በኋላ ግብር ለማስከፈል የመሬቱን ድንበሮች የሚከልሉ የጥንት ባለሙያዎች ነበሩ። ግብጻውያን “ገመድ ጎታቾች” በማለት ይጠሯቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች ለዘመናችን መሬት ቀያሾች መንገድ ጠራጊዎች ሆነዋል።
በዛሬው ጊዜ ቀያሾች በአውራ ጎዳናዎችና ግንባታ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ሲሠሩ ይታያሉ። እነዚህን ባለሙያዎች ስታይ ‘ቅየሳ ምንድን ነው?’ ብለህ ሳትጠይቅ አትቀርም።
“ቅየሳ ሁለት ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች አሉት” ይላል ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ ኢላስትሬትድ። እነዚህ ሁለት የሥራ ዘርፎች የሚከተሉት ናቸው:- “(1) ያለውን ነገር ይለካል፣ የሚገኝበትን ቦታ ይመዘግብና ይህን መረጃ በመጠቀም ካርታ ወይም መግለጫ ያዘጋጃል ወይም (2) ወሰን ለማካለል ድንበሮችን ለይቶ ያመለክታል ወይም የግንባታ ሥራዎች በተዘጋጀላቸው ፕላን መሠረት እንዲከናወኑ ጥሩ አመራር ይሰጣል። ቅየሳ በመሬት ላይ፣ ከመሬት በታች ወይም ከመሬት በላይ የተቀመጡ ቦታዎችን ለይቶ ያመለክታል።”
የቅየሳ ታሪክ
የመጀመሪያው የተከለለ ቦታ የኤደን የአትክልት ቦታ እንደሆነ ግልጽ ነው። በተጨማሪም በእስራኤል ምድር መሬት የሚያካልሉና የሚያከፋፍሉ ቀያሾች እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ምሳሌ 22:28 “አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ” ይላል። ሮማውያን ደግሞ ድንበሮችን የሚቆጣጠርና የድንጋይ ምስል ያለው ቴርሚኑስ የሚባል አምላክ ነበራቸው።
የሮማ ጎዳናዎችና የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎች (ብዙዎቹ እስከ ዛሬ ድረስ ቆይተዋል) የጥንቶቹ ሮማውያን በቅየሳ ረገድ ምን ያህል ተራቅቀው እንደነበረ ይመሰክራሉ። የጥንቶቹ ቀያሾች እንደዛሬው የተራቀቁ መሣሪያዎች ሳይኖሩአቸው በጣም አስደናቂ ውጤቶች አግኝተዋል። በ200 ከዘአበ ገደማ ኤራቶስተኒስ የተባለው ግሪካዊ የስነፈለክ፣ የሂሣብና የጂኦግራፊ ሊቅ የምድር ዙሪያ ምን ያህል እንደሆነ ለማስላት ችሏል።
በ62 እዘአ የእስክንድርያው ሄሮ ወይም ሄሮን ቲኦፕትራ በተባለው መጽሐፉ የጂኦሜትሪ ሳይንስ (ጂኦሜትሪ ቃል በቃል ሲተረጎም “የመሬት ልክ” ማለት ነው) እንዴት ለቅየሳ ሥራ ሊያገለግል እንደሚችል አመልክቷል። ከ140 እስከ 160 እዘአ ባሉት ዓመታት ክላውድየስ ፕቶለሚ፣ ሂፓርከስ ያገኘውን ዘዴ በመጠቀም በዘመኑ በታወቀው ዓለም የሚገኙ 8, 000 ቦታዎችን የዘረዘረ ሲሆን እነዚህ ቦታዎች የሚገኙባቸውን የኬክሮስና የኬንትሮስ መስመሮችም ጠቅሷል።
በ18ኛው መቶ ዘመን የካሲኒ ቤተሰቦች በአራት ትውልዶች ዘመን ውስጥ በፈረንሳይ አገር የመጀመሪያ የሆነውን ሳይንሳዊ ቅየሳ ካካሄዱ በኋላ ላ ካርት ደ ካሲኒ የተባለውን ካርታ አውጥተዋል። ዘ ሼፕ ኦቭ ዘ ወርልድ የተባለው መጽሐፍ “በሳይንሳዊ የካርታ ሥራ ረገድ የመሪነቱን ቦታ የያዘችው ፈረንሳይ ነበረች። በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠችው ብሪታንያ ስትሆን ከዚያ በመቀጠል ደግሞ የኦስትሪያና የጀርመን ግዛቶች ይጠቀሳሉ። በቀሩት የአውሮፓ አገሮች ብሔራዊ የቅየሳ ሥራ በስፋት መካሄድ የጀመረው በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን
የመጀመሪያ አሥርተ ዓመታት ነበር” ይላል። ከአውሮፓ ባሻገር የሕንድን የካርታ ሥራ ለማጠቃለል በ1817 ታላቅ የሆነ የቅየሳ ሥራ ተካሂዷል። ይህን ሥራ ይመሩ የነበሩት ጆርጅ ኤቨረስት ሲሆኑ በርዝመቱ ከዓለም አንደኛ የሆነው ተራራ የተሰየመው በእሳቸው ስም ነው።እነዚህ የጥንት ቀያሾች ሥራቸውን ያከናውኑ የነበረበት ሁኔታ አመቺ ነው የሚባል አልነበረም። እስከ 1861 ያለው የሕንድ ቅየሳ ሥራ ታሪካዊ መዝገብ የቅየሳ ሠራተኞች በንዳድ በሽታ ይጠቁ እንደነበረ ያመለክታል። ወደ እንግሊዝ በደህና የሚመለሰው ከ70 ሠራተኞች አንዱ ብቻ እንደነበረ ይነገራል። ሌሎች ቀያሾች ደግሞ በዱር አራዊት ይጠቁ ወይም በቂ ምግብ ባለማግኘት ይጎዱ ነበር። ቢሆንም በመስክ ሥራ የመሠማራትና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በነፃነት የመሥራት አጋጣሚ ስለሚፈጥርላቸው ሥራውን ይወዱት ነበር።
ፓንዲት የሚባሉ የሕንድ ማኅበረሰብ አባሎች በኔፓልና በቲቤት ባከናወኑት አስደናቂ ሥራ ምክንያት በታሪክ ምዕራፎች ውስጥ ልዩ ቦታ ተሰጥቷቸዋል። በዘመኑ የባዕድ አገር ሰዎች ወደ እነዚህ አገሮች እንዳይገቡ የሚያግድ ውልና አዋጅ ስለነበረ እነዚህ ቀያሾች የቡድሂስት መነኮሳት መስለው ገቡ። በስውር ለሚከናወነው ሥራቸው ሲዘጋጁ እያንዳንዳቸው አንዱን ማይል ርዝመት (1.6 ኪሎ ሜትር) በ2, 000 እርምጃ እንዲሸፍኑ ሰልጥነው ነበር። እርምጃቸውን ለመቁጠርና የሄዱበትን ርቀት ለማስላት በባለ መቶ ጠጠር መቁጠሪያ ይጠቀሙ ነበር።
የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንቶች እንደነበሩት እንደ ዋሽንግተን፣ ጀፈርሰንና ሊንከን የመሰሉ ብዙ ግለሰቦች የቅየሳ ሥራ ይሠሩ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች እንደሚሉት ሊንከን በፖለቲካው መስክ የተሳካ ውጤት እንዲያገኙ በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር የቅየሳ ሥራቸው ነው። በቅየሳ ሥራ ተሰማርተው በነበሩበት ጊዜ ከአገራቸው ሰዎች ጋር በቅርብ ለመተዋወቅ ችለዋል።
የቅየሳ ሥራ በዘመናችን
በዛሬው ጊዜ በየአካባቢያችን ሲከናወን የምናየው የመሬት ቅየሳ ሥራ በሦስት ዘርፎች ይመደባል። የመጀመሪያው ሕጋዊ ቅየሳ ሲሆን ሕጋዊ ባለንብረትነትን ለመለየት የሚደረግ የቅየሳ ዘርፍ ነው። መሬት ለቤት ሥራ መሸንሸን በሚያስፈልግበት ጊዜ ወይም መንግሥት አዳዲስ አውራ ጎዳናዎች ወይም መንገዶች የሚያልፉበትን ቦታ ለማካለል በሚፈልግበት ጊዜ መሬቱን የሚያካልሉትና ሕጋዊ ካርታዎችን የሚያዘጋጁት ቀያሾች ናቸው።
ሌላው የቅየሳ ዓይነት የቶፖግራፊ ቅየሳ ይባላል። በዚህ ዓይነቱ ቅየሳ የአንድ መሬት መጠን፣ ቅርጽና ተዳፋት እንዲሁም መንገዶች፣ አጥሮች፣ ዛፎች፣ ሕንጻዎች፣ እንደ ኤሌክትሪክና ውኃ ያሉ አገልግሎት መስጫ መስመሮች ወዘተ የሚገኙበት ቦታ ተለይቶ ይከለላል። ሲቪል መሐንዲሶች፣ አርኪቴክቶችና ሌሎች ባለሞያዎች እነዚህን መረጃዎች በመጠቀም ሥራቸውን ያከናውናሉ። መረጃዎቹ ካለው ሁኔታ ጋር የሚስማማ ፕላን እንዲያዘጋጁና አንዳንድ ጊዜም እነዚህን ገጽታዎች በንድፋቸው ላይ አካትተው እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል።
ለግንባታው ፕሮጀክት የሚያስፈልገው ዲዛይን፣ ፕላንና ሌሎቹም ነገሮች ከተጠናቀቁ በኋላ በወረቀት ላይ የተነደፈው ነገር በሙሉ የት የት ቦታ ላይ መሠራት እንዳለበት ለይቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። የግንባታ ቅየሳ የሚባለው ሦስተኛ የቅየሳ ዘርፍ የሚከናወነው በዚህ ጊዜ ነው። ቀያሾቹ የግንባታ ሠራተኞቹ በፕላኑ ላይ የተመለከቱት ነገሮች በሙሉ ትክክለኛ ቦታቸውን እንዲይዙ አድርገው መሥራት ይችሉ ዘንድ ምልክት ሆነው የሚያገለግሉ ችካሎች እየተከሉ ገመዶች ይዘረጋሉ።
* ይህ ዓይነቱ ሥራ በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ይጠይቃል።
ከ19 ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት የተወሰነ የመሬት ቅየሳ የሜዳ ቅየሳ ይባላል። በጣም ሰፊ በሆነ አካባቢ ላይ የቅየሳ ሥራ በሚካሄድበት ጊዜ ግን የምድርን ገጽ ክብነት ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ዓይነቱ ቅየሳ የሚካሄደው ከኬክሮስና ከኬንትሮስ መስመሮች ጋር ተቀናጅቶ ነው።ዘመናዊው የቅየሳ ሥራ ልዩ በሆኑ ሳተላይቶችና በተራቀቁ መሣሪያዎች መገልገል ጀምሯል። ባሁኑ ጊዜ ቀያሾች በቀላሉ ሊጓጓዙ የሚችሉ መሣሪያዎችን በመጠቀም በምድር ላይ የሚገኙ የተለዩ ቦታዎችን በቀላሉ ሊያገኙ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ ሲከናወኑ የማናያቸው የቅየሳ ዓይነቶችም አሉ። በሳተላይቶች ላይ በሚገጠሙ ልዩ ካሜራዎች ፎቶግራፍ በማንሳት የአንድን መሬት አቀማመጥ አስተማማኝ በሆነ መንገድ መለካት ይቻላል። የባሕር ጠረፎችን ለይቶ ለማስቀመጥ እንዲሁም የወንዞችን፣ የሐይቆችንና የውቅያኖሶችን ጥልቀትና አቀማመጥ ለመለካት የሚያገለግል የቅየሳ ዓይነትም አለ።
ለእያንዳንዳችን ያለው አስፈላጊነት
ለምሳሌ በካሊፎርንያ ዩ ኤስ ኤ የሚገኘው ጎልደን ጌት የተባለው ድልድይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው በ1937 ነው። ያለበትን ቦታ በትክክል ለይቶ ለማወቅ በ1991 በድጋሚ የቅየሳ ሥራ ተካሂዷል። የምድር መናወጥ ቢከሰትና ድልድዩ ከነበረበት ቦታ ቢንሸራተት ድልድዩ ላይ የደረሰው ጫና ሊሰላ ስለሚችል አደጋ ከማድረሱ በፊት አስፈላጊውን ጥገና ማድረግ ይቻላል። በቨርሞንት የሚገኝ አንድ የመዝናኛ ማዕከል የበረዶ ላይ ሸርተቴ መጫወቻ ቦታው እንዲስተካከልና ከፍተኛ ደረጃ የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ሲል የቅየሳ ሥራ ባለሙያዎችን አሠማርቶ ነበር።
በተጨማሪም በቻይና በሳተላይት የተገኙ መረጃዎችን በመጠቀም በመሬት የላይኛው ክፍል ላይ የሚከሰቱ ለውጦችን ለመከታተልና የምድር ነውጦች በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ነው። * ከዚህም ሌላ የምትኖርበት ቤት፣ የምትጓዝበት አውራ ጎዳና፣ የምትሠራበት ሕንጻ ወይም የምትማርበት ትምህርት ቤት በሚገነባበት ወቅት የቀያሾችን ድካም ጠይቆ ሊሆን ይችላል።
ቀያሾች የሚያከናውኑት ሥራ በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል። ከገመድ እስከ ሳተላይት የሚደርሱ የተለያዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም ውስብስብ የሆነው ይህ ያለንበት ዓለም ሥርዓት ያለው እንዲሆን ጥረት አድርገዋል። ግንባታ ማከናወናችንና ከላያችንና ከበታቻችን ያለውን ዓለም ማጥናታችን እስካልቀረ ድረስ ቀያሾች እንደሚያስፈልጉን ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ወደፊት ቀያሾች ሥራቸውን ሲያከናውኑ ካየህ እንዴት ያለ ከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሥራ እየሠሩ እንዳለ በተሻለ ሁኔታ መረዳት ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.17 ስለ ኬክሮስና ኬንትሮስ መስመሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በመጋቢት 8, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “ጠቃሚ የሆኑት የሐሳብ መስመሮች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.21 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ—መስከረም 1997 የንቁ ! እትም ላይ የወጣውን “እሳተ ገሞራ—አደጋው ያሰጋሃልን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ዝንፍ የማይሉ መሣሪያዎች
ኤሌክትሮኒክ የርቀት መለኪያ፦ ርቀቱ በሚለካበት ቦታ በተቀመጠ ልዩ መስተዋት ላይ ተንጸባርቆ ወደ መሣሪያው የሚመለስ ጨረር በመላክ ርቀቶችን ያሰላል።
ቲዮዶላይትና ቶታል ስቴሽን፦ ቲዮዶላይት (በስተግራ ያለው) የማዕዘን መጠን የሚለካ መሣሪያ ሲሆን በውስጡ ማዕዘኑን በጣም ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርጉ መስታወቶችና ማጉያ መነጽሮች አሉት። በጣም የተራቀቁ ቲዮዶላይቶች ከአንድ ሰከንድ ያነሰ መጠን ያላቸውን ማዕዘኖች ማሳየት ይችላሉ። አንድ ሰከንድ አንድ ክብ መስመር 1, 296, 000 በሚያክሉ እኩል የሆኑ ክፍልፋዮች ሲከፈል የሚገኝ ቅስት ነው። ቶታል ስቴሽን (በስተቀኝ ያለው) ማዕዘን፣ ርቀትና ሌሎች መጠኖችን የሚለካና የሚመዘግብ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ነው። መረጃዎቹ ከተሰበሰቡ በኋላ ወደ ቢሮ ይወሰዱና በኮምፒውተር አማካኝነት የተለያዩ ስሌቶችን ለመሥራትና ንድፍ ለማዘጋጀት ያገለግላሉ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀደም ባለው ዘመን ይሠራበት የነበረ የውሃ ልክ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ግብጻውያን “ገመድ ጎታቾች” ለዘመናችን ቀያሾች መንገድ ጠራጊዎች ሆነዋል
[ምንጭ]
Borromeo/Art Resource, NY