የበቀቀኖች ሕልውና አስጊ ሁኔታ ላይ ወድቋል
የበቀቀኖች ሕልውና አስጊ ሁኔታ ላይ ወድቋል
ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በዩናይትድ ስቴትስ የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ቲሞቲ ራይት “ከምድር ገጽ ሊጠፉ ከተቃረቡት አእዋፍ መካከል” በቀቀኖች ይገኛሉ ብለዋል። ለዚህ አደጋ የዳረጋቸው ደማቅ ቀለም ያለው ውብ ላባቸውና አስደናቂ የሆነው የሰዎችን ድምፅ የመቅዳት ችሎታቸው ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለማዳ ስለሆነች በቀቀን የጻፈው በአምስተኛው ምዕተ ዓመት ከዘአበ ይኖር የነበረ አንድ ግሪካዊ ሐኪም ነው። ወፊቱ አንዳንድ የግሪክኛ ቃላትንና የአገሯን የሕንድን አንዳንድ ቃላት መጥራት በመቻሏ በጣም ተደንቋል።
ዛሬ በቀቀኖች ድምፅ ለመቅዳት በመቻላቸው ምክንያት ተወዳጅነታቸው በጣም በመጨመሩ እነዚህኑ ወፎች አጥምዶ የመሸጡ ሕገወጥ ንግድ በጣም ደርቷል። ባለፉት 20 ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አዳኞች በ14 አገሮች የሚገኙ 21 የተለያዩ የበቀቀን ዝርያዎች ከሠሯቸው ጎጆዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑትን አፍርሰዋል። አራት የበቀቀን ዝርያዎች ከሠሯቸው ጎጆዎች መካከል ደግሞ 70 በመቶ የሚሆነውን አጥፍተዋል። በቀቀኖች ፈጥነው የማይራቡና በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ እንቁላል የማይፈለፍሉ በመሆናቸው እንዲሁም የመኖሪያ አካባቢያቸው እየተበላሸ በመምጣቱ የሚሸጡበት ዋጋ በጣም እያሻቀበ መጥቷል።
አንዳንድ የበቀቀን ዝርያዎች ቁጥራቸው እጅግ እየተመናመነ መምጣቱን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣታቸው ችግሩ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚጠቁም ነው። በብራዚል ሊርስ ማካው ከሚባሉት የበቀቀን ዝርያዎች በአሁኑ ጊዜ የቀሩት 200 ያህል ብቻ እንደሆኑ ይገመታል። የፖርቶ ሪኮ በቀቀኖች ሁኔታ ከዚህ የባሰ ነው። ባሁኑ ጊዜ በዱር የሚገኙት የዚህ በቀቀን ዝርያዎች ከ50 አይበልጡም። ከዱር ጨርሶ እንደጠፋ የሚነገርለት የስፒክስ ማካው ዝርያ እንደገና ሊያንሰራራ የቻለው በአብዛኛው የተጠመዱ በቀቀኖችን ለማራባት በተደረገው ጥረት ነው።
እነዚህ ውብ የሆኑ ወፎች በሕይወት እስከኖሩ ድረስ አስደናቂ ውበታቸውንና ችሎታቸውን በማየት ስለሚደሰተው ፈጣሪያቸው ይመሰክራሉ። በሰው ልጅ ስግብግብነት ምክንያት በቀቀኖች ጨርሰው ይጠፉ ይሆን? ይህ ወደፊት የሚታይ ነገር ይሆናል። ያም ሆነ ይህ አሁን ካለው ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው የእነዚህ ወፎች ሕልውና አስጊ ሁኔታ ላይ ወድቋል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕሎች]
የፖርቶ ሪኮ በቀቀኖች
ሊር ማካው የተሰኘችው በቀቀን
ስፒክስ ማካው በመባል የሚታወቁ በቀቀኖች
[ምንጮች]
Puerto Rican parrots: U.S. Geological Survey/Photo by James W. Wiley; Lear’s macaw: © Kjell B. Sandved/Visuals Unlimited; Spix’s macaws: Progenies of and courtesy of Birds International, Inc.