ቁማር—ብዙዎችን የማረከ ልማድ
ቁማር—ብዙዎችን የማረከ ልማድ
የስኮትላንድ ተወላጅ የሆነው ጆን ሁልጊዜ የሚያልመው ሎተሪ ስለማግኘት ነው። “በየሳምንቱ ሎተሪ እገዛለሁ” ይላል። “የቲኬቱ ዋጋ በጣም ትንሽ ሲሆን ስመኝ የኖርኩትን ነገር ሁሉ የማገኝበት ተስፋ የተመካው በዚህ ቲኬት ላይ ነው።”
በጃፓን የሚኖረው ካዙሺጌ ፈረስ ግልቢያ ይወዳል። “በፈረስ ግልቢያ መወዳደሪያ ቦታ ከጓደኞቼ ጋር መወራረድ በጣም ያስደስተኛል። ብዙ ገንዘብ የማገኝበትም ጊዜ አለ” በማለት ያስታውሳል።
የአውስትራሊያ ነዋሪ የሆነችው ሊንዳ ደግሞ “የቢንጎን ያህል የምወደው ጨዋታ የለም” ትላለች። “ይህ ልማድ በሳምንት እስከ [250 ብር] የሚደርስ ወጪ የሚያስወጣኝ ቢሆንም በጨዋታው አሸናፊ መሆን በጣም ያስደስተኝ ነበር።”
ጆን፣ ካዙሺጌና ሊንዳ ቁማር ብዙም ጉዳት የማያስከትል መዝናኛ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ተመሳሳይ የሆነ አመለካከት አላቸው። በ1999 የተደረገ አንድ የሕዝብ አስተያየት ጥናት እንደሚያሳየው ከአሜሪካውያን መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ቁማርን ይደግፋሉ። በ1998 አሜሪካውያን ቁማርተኞች 50 ቢልዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ሕጋዊ ለሆኑ የቁማር ጨዋታዎች ያጠፉ ሲሆን ይህ ገንዘብ ለፊልም ቲኬቶች፣ ለሙዚቃ ቅጂዎች፣ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ለማየት፣ ፓርኮችን ለመጎብኘትና ለቪዲዮ ጨዋታዎች በጠቅላላ ካወጡት ገንዘብ ይበልጣል።
አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንዳረጋገጠው ከአውስትራሊያ ነዋሪዎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጥናቱ በተደረገበት ዓመት ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ ቁማር የተጫወቱ ሲሆን 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በየሣምንቱ ቁማር ተጫውተዋል። በዚህች አገር የሚኖሩ ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎች በአማካይ በየዓመቱ ከ3, 000 ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ለቁማር ያወጣሉ። ይህ አኃዝ አውሮፓውያን ወይም አሜሪካውያን ከሚያወጡት ገንዘብ በእጥፍ የሚበልጥ
ሲሆን አውስትራሊያውያን በቁማር ወዳድነት ከዓለም የአንደኛነትን ቦታ እንዲይዙ አድርጓቸዋል።ብዙ ጃፓናውያን ፓቺንኮ የተባለው ጨዋታ ሱስ የሆነባቸው ሲሆን በየዓመቱ በዚህ ጨዋታ በሚያደርጉት ውርርድ በብዙ ቢልዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ያጠፋሉ። በብራዚል ቢያንስ ቢያንስ በየዓመቱ 4 ቢልዮን ዶላር ለቁማር ይውላል። ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የሚውለው የሎተሪ ቲኬት ለመግዣ ነው። ይሁን እንጂ የሎተሪ ቲኬት ፍቅር የተጠናወታቸው ብራዚላውያን ብቻ አይደሉም። ፐብሊክ ጌሚንግ ኢንተርናሽናል የተባለው መጽሔት “በ102 አገሮች 306 ሎተሪዎች” እንደሚኖሩ ገምቷል። በእርግጥም ቁማር በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎችን የማረከ ልማድ ሆኗል። ይህ ልማድ ትልቅ ጥቅም አለው ብለው የሚያስቡም አሉ።
ፐብሊክ ጌሚንግ ሪሰርች ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም ተወካይ የሆኑት ሻሮን ሻርፕ በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከ1964 እስከ 1999 ባሉት ዓመታት “ከሎተሪ ሽያጭ 125 ቢልዮን ዶላር የሚያክል ገቢ ያገኘ ሲሆን ከፍተኛውን ገቢ ያገኘው ከ1993 ወዲህ ባሉት ዓመታት ነው” ብለዋል። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው ለሕዝብ ትምህርት ማስፋፊያ ፕሮግራሞች፣ ለብሔራዊ ፓርኮች ማስፋፊያና ለስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች መሥሪያ ውሏል። ከዚህም በላይ የቁማር ኢንዱስትሪ ብዙ የሥራ ዕድል አስገኝቷል። በአውስትራሊያ ብቻ 100, 000 ሰዎች ከ7, 000 በሚበልጡ የቁማር ኢንዱስትሪ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው ይሠራሉ።
በዚህ ምክንያት የቁማር ደጋፊዎች ሕጋዊ ቁማር ጥሩ መዝናኛ ከመሆኑም በላይ ሥራ ይፈጥራል፣ የታክስ ገቢ ያስገኛል፣ በኢኮኖሚ የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን ያጠናክራል ብለው ይከራከራሉ።
ስለዚህም ብዙ ሰዎች ‘ቁማር መጫወት ምን ስህተት አለው?’ ብለው ይጠይቃሉ። በሚቀጥለው ጽሑፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ የተሰጠ ሲሆን የቀረበው ማብራሪያ ለቁማር ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ያመጣ ይሆናል።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆን
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካዙሺጌ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሊንዳ