መፍትሔው “የግል ሃይማኖት” መፍጠር ነውን?
መፍትሔው “የግል ሃይማኖት” መፍጠር ነውን?
የታወቁ ሃይማኖቶች በብዙኃኑ ላይ የነበራቸውን ሥልጣን እያጡ በሄዱ መጠን የግላቸውን ሃይማኖት የሚፈጥሩ ሰዎች እየተበራከቱ መሄዳቸው የሚያስደንቅ አይደለም። መነሳት የሚገባው ጥያቄ ግን እንዲህ ማድረግ የአንድን ሰው መንፈሳዊ ፍላጎት ያረካልን? የሚለው ነው። መፍትሔው “የግል ሃይማኖት መፍጠር” ነውን?
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት አስቀድመን የግል ሃይማኖት ለሰው ልጆች ከተሰጡት ታላላቅ ስጦታዎች አንዱ በሆነው ‘የማስተዋል ኃይል’ ሲመዘን ሚዛን ይደፋ እንደሆነ መመልከት ይገባናል።—ሮሜ 12:1
የማስተዋል ችሎታ ያለው አእምሮ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር መቀበል ይከብደዋል። ይሁን እንጂ በስዊድን አገር በግል ሃይማኖቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ሰዎች “የተለያዩ (እንዲያውም እርስ በርሳቸው የማይጣጣሙ) የሕይወት አመለካከቶችንና ሐሳቦችን የፍልስፍናቸው ክፍል ያደርጋሉ።”
ለምሳሌ ያህል “በራሳቸው መንገድ ክርስቲያኖች” እንደሆኑ ከተናገሩት መካከል ኢየሱስ የታወቀ በታሪክ የነበረ ሰው መሆኑን የተናገሩት ከ2 በመቶ አይበልጡም። ከሞት በኋላ ሌላ አካል ለብሶ ስለመኖር ግን ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። ታዲያ የኢየሱስን አኗኗርና ትምህርቶች ወደጎን ገሸሽ እያደረጉ እንዲያውም ከክርስቶስ ትምህርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጋጩ እምነቶችን እየተቀበሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ ማለት ይቻላል? *
በተጨማሪም አእምሯችን ለመረዳት የሚያዳግቱና የተምታቱ ሐሳቦችን መቀበል ይከብደዋል። ይሁን እንጂ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ “በአምላክ ወይም መለኮታዊ በሆነ አምላክ” ያምኑ እንደሆነ ሲጠየቁ “አንድ መለኮት ወይም አምላክ መሰል ነገር ሳይኖር አይቀርም” በማለት መልሰዋል። አንድ ተጠያቂ “ከሰው በላይ የሆነ ኃይል እንደሚኖር ልመን እንጂ ያ ነገር የግድ የተወሰነ አካል ያለው አምላክ መሆን የለበትም” ብሏል። በአምላክ ከሚያምኑትም መካከል ቢሆን “በሕይወታቸው ውስጥ እምብዛም ቦታ እንደማይሰጡት” ተናግረዋል። ሪፖርቱ የግል ሃይማኖት “ግልጽ ያልሆኑና የተምታቱ እሳቤዎች፣ አመለካከቶችና ደንቦች የሰፈነበት ክልል” እንደሆነ ከገለጸ በኋላ በጣም ከተለመዱት መልሶች መካከል አንዱ የሆነውን በመጥቀስ ደምድሟል። “በአንድ ነገር አምናለሁ፣ ግን ያ ነገር ምን እንደሆነ አላውቅም።”
በካናዳ የግል ሃይማኖት ላይ የተደረገ አንድ ጥናትም ተመሳሳይ ውጤት አሳይቷል። አልበርታ ሪፖርት የተባለው መጽሔት የሚከተለውን አስተውሏል:- “ለቁጥር በሚያታክቱ በርካታ ነገሮች የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር በጣም እየበዛ እንደመጣ እንመለከታለን። ይሁን እንጂ የእነዚህ ሰዎች እምነት ምክንያታዊነት አይታይበትም። እነዚህ የግል እምነቶች ለአማኞቻቸው አኗኗር የሚሰጡት አመራር ይኖር ይሆን ብለን ለማየት በምንሞክርበት ጊዜ ምንም ነገር አናገኝም።
የሥነ ምግባር ደንብ የሚያወጣ የበላይ ባለ ሥልጣን የላቸውም። ስለዚህ ፋይዳቢሶች ናቸው።” መጽሔቱ እንደነዚህ ያሉትን እምነቶች የሚከተሉ ሰዎች “በታወቁ ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ነገሮች ስለሚቀነጫጭቡ” “የተበጣጠሰ አምላክ” አላቸው ብሏል። እንደነዚህ ባሉት የተምታቱ፣ የማያሳምኑና የተበጣጠሱ አስተሳሰቦች ላይ ሃይማኖታዊ እምነቶቻችንን፣ እንዲያውም ስለወደፊቱ ጊዜ ያለንን ተስፋ መመሥረት ምክንያታዊ ሆኖ ይታይሃል?ከሰዎች ጋር የመገናኘትና አብሮ የመሆን ፍላጎት
የሃይማኖት ተከታዮች ከጥንት ጀምሮ ለወንድማማችነት፣ ለባልንጀርነትና ለመረዳዳት ከፍተኛ ቦታ ሲሰጡ ቆይተዋል። (ሥራ 2:42, 46) የግል ሃይማኖት ግን ያው የግል ስለሆነ ይህን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችለው እንዴት ነው?
“እያንዳንዱ ሰው ራሱ ቤተ ክርስቲያን” የሚሆንበት የግል ሃይማኖት በሰዎች መካከል ያለውን መከፋፈልና መለያየት ይበልጥ ሥር የሰደደና የሰፋ አያደርገውም? አልበርታ ሪፖርት “ሃይማኖት የእያንዳንዱ ሰው የግል አስተሳሰብ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ . . . በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች አገር መሆናችን ቀርቶ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ እምነቶች አገር ሆነናል” ብሏል። ስለዚህ የግል ሃይማኖት መንፈሳዊ ዝብርቅ እንደሆነ ተደርጎ መቆጠሩ የሚያስደንቅ አይደለም።
መንፈሳዊ እሴቶችስ?
ማርቲን ሎኔቦ የተባሉት ስዊድናዊ ጳጳስ ስቬንስካ ዳግብላደት የተባለው ጋዜጣ ባደረገላቸው ቃለ ምልልስ “የግል ሃይማኖት ዘመናችንን ሊያበለጽግ አይችልም። መንፈሳዊ እሴቶቹንም ለአዲሱ ዘመን የማስተላለፍ አቅም የለውም” ብለዋል። ይህ ትክክል መሆኑ የስዊድን ወላጆች ስለ ልጆች አስተዳደግ ባላቸው አመለካከት ተረጋግጧል። ስቬንስካ ዳግብላደት ዝንባሌያቸውን አጠቃልሎ ሲገልጽ “የፈለግኸውን እመን! ልጆችህም እንዲወስኑ አታስገድዳቸው። ሲያድጉ የፈለጉትን እንዲመርጡ ተዋቸው።”
ጋዜጣው ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለልጆች ማስተላለፍ የራሳቸው ያልሆነ አስተሳሰብና እምነት እንዲቀበሉ ማስገደድ እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል አምኗል። ቢሆንም ጋዜጣው “ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለልጆች ማስተላለፍ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ ለራሳቸው የሚበጃቸውን ሊወስኑ የሚችሉበት ብቸኛ መንገድ ነው” በማለት ደምድሟል። በእርግጥም ወጣቶች የሚገኙበት አሳዛኝ ሁኔታ የግል ሃይማኖት ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፉ ጠንካራ መንፈሳዊ እሴቶች ቤተሰቦችን አንድ በማድረግ ረገድ የፈየደው ነገር እንደሌለ ያሳያል።
ስለዚህ የግል ሃይማኖት ለሕይወት ጥያቄዎች አስተማማኝና ወጥ የሆኑ መልሶች ሊሰጥም ሆነ ሕዝቦችን አንድ ሊያደርግ ወይም የሰው ልጆች የሥነ ምግባር መመሪያ የማግኘት ፍላጎታቸውን ሊያሟላ የሚችል አይመስልም። ስቬንስካ ዳግብላደት ላይ የወጣው ቀደም ብለን የጠቀስነው ጽሑፍ ስለ ግል ሃይማኖት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል። “እምነት ሁሉን የሚያካትት ሲሆን ምንም የሌለው ባዶ ይሆናል። ነጻነት ገደብና ድንበር የሌለው ሲሆን ደካማ ይሆናል።”
የግል ሃይማኖት በብዙ ረገዶች የሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ሊያሟላ እንዳልቻለ ግልጽ ነው። ቀድሞውንስ ቢሆን አንድ ሰው በብፌ ገበታ ላይ እንደተቀመጠ ምግብ ከዚህም ከዚያም የቃረመው እምነት እንዴት መንፈሳዊ ፍላጎቶቹን ሊያሟላለት ይችላል? የታወቁ ሃይማኖቶችም ቢሆኑ እነዚህን ፍላጎቶች ማሟላት የተሳናቸው ይመስላል። ታዲያ ምን እናድርግ?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ኢየሱስ ሙታን ሌላ አካል ለብሰው እንደሚመጡ አላስተማረም። ከዚህ ይልቅ ሙታን ወደፊት ትንሣኤ የሚያገኙበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ከሕልውና ውጭ ሆነው እንደ እንቅልፍ ባለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ አስተምሯል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:11-14
[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሃይማኖትን የምንፈልገውን ብቻ ብድግ እንደምናደርግበት የብፌ ግብዣ ማየት ይገባናል?